በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብርሃም—ደፋር ሰው

አብርሃም—ደፋር ሰው

አብርሃም—ደፋር ሰው

የአብርሃም ቤተሰብና አገልጋዮቹ ወደ ከነዓን ምድር ለመጓዝ እየተዘገጃጁ ነው። (ዘፍጥረት 12:1-5) አብርሃም፣ የሚያስተዳድራቸውን እነዚህን ሁሉ ሰዎች ሲመለከት እነሱን በመንከባከብ ረገድ ያለበት ከባድ ኃላፊነት ወደ አእምሮው እንደሚመጣ ጥርጥር የለውም። በማያውቀው አገር ስለመኖር ሲያስብ የሚከተሉት ጥያቄዎች ያሳስቡት ይሆናል፦ በከነዓን ምድር ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት የሚችለው እንዴት ነው? ዑር፣ ሰፊ የግጦሽ መሬትና ለም አፈር እንዲሁም በቂ የውኃ አቅርቦት የሚገኝባት የበለጸገች ከተማ ከመሆኗ አንጻር የቤተሰብ ኃላፊነቱን ለመወጣት በዑር ቢቀመጥ ይቀልለው ይሆን? በሚሄድበት ባዕድ አገር ቢታመም ወይም ቢሞት ቤተሰቡን ማን ይንከባከባቸዋል? አብርሃም እነዚህ ነገሮች አስጨንቀውት ሊሆን ቢችልም ፍርሃት እንዲቆጣጠረው ግን አልፈቀደም። ምንም ቢመጣ ምን አምላክን ለመታዘዝ ቆርጧል፤ ይህ ደግሞ የእውነተኛ ድፍረት ምልክት ነው።

ድፍረት ምንድን ነው? ድፍረት የሚለው ቃል ብርቱ፣ ልበ ሙሉና ቆራጥ መሆንን የሚያመለክት ሲሆን በፍርሃት የመራድ ወይም የመርበትበት ተቃራኒ ነው። ይሁንና አንድ ሰው ደፋር ነው ሲባል ጨርሶ አይፈራም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላካዊ ድፍረት ያለው ሰው፣ ፍርሃት ቢሰማውም እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም።

አብርሃም ድፍረት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? አብርሃም ከሌላው ሕዝብ የተለየ ለመሆን አልፈራም። አብርሃም ያደገው ብዙ አማልክትና ጣዖታት በሚመለኩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነበር። ይሁንና ሰው ምን ይለኛል የሚል ፍርሃት፣ ትክክል እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር ከመፈጸም ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። አብርሃም “ልዑል አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ብቻ ለማምለክ በመወሰን በድፍረት ከማኅበረሰቡ የተለየ አካሄድ ተከትሏል።​—ዘፍጥረት 14:21, 22

አብርሃም ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለእውነተኛው አምላክ የሚያቀርበውን አምልኮ አስቀድሟል። ይህ የአምላክ አገልጋይ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሖዋ እንደሚያሟላለት ሙሉ በሙሉ በመተማመን በዑር የነበረውን የተደላደለ ሕይወት ትቶ በምድረ በዳ ለመኖር ፈቃደኛ ሆኗል። እርግጥ ነው፣ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በዑር የነበረውን የተመቻቸ ሕይወት መለስ ብሎ ያሰበባቸው ወቅቶች ይኖሩ ይሆናል። ይሁንና መቼም ቢሆን ለእሱና ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሖዋ እንደሚያሟላላቸው እርግጠኛ ነበር። አብርሃም ለይሖዋ ከሁሉ የላቀውን ቦታ በመስጠት ከእሱ ጋር በመጣበቁ አምላክን ለመታዘዝ ድፍረት አግኝቷል።

ምን ትምህርት እናገኛለን? በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ይሖዋን ባይታዘዙም እንኳ እኛ ይህን በማድረግ አብርሃም በድፍረት ረገድ የተወውን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን ለማምለክ የቆረጡ ሰዎች ምናልባትም አሳቢ ከሆኑ ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ተቃውሞ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዮሐንስ 15:20) ሆኖም ስለ ይሖዋ የተማርነውን ነገር ካመንንበት አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለ እምነታችን መልስ መስጠት እንችላለን።​—1 ጴጥሮስ 3:15

ከዚህም በተጨማሪ አምላክ፣ በእሱ ለሚተማመኑ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ እንደሚያሟላ በገባው ቃል ላይ እምነት ማሳደር እንችላለን። እንዲህ ያለው እምነት ሕይወታችን በቁሳዊ ነገሮች ላይ ሳይሆን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ድፍረት ይሰጠናል። (ማቴዎስ 6:33) አንድ ቤተሰብ ይህን እንዴት እንዳደረገ እስቲ እንመልከት።

ዶግ እና ቤኪ የተባሉ ባልና ሚስት፣ ሁለት ትንንሽ ወንዶች ልጆች ቢኖሯቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች የሚሰብኩ ሰዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ለመዛወር አሰቡ። በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርምር ካደረጉና አጥብቀው ከጸለዩ በኋላ ሐሳባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ወሰኑ። ዶግ “በምንሄድበት ቦታ ምን ሊያጋጥመን እንደሚችል ሳናውቅ ልጆቻችንን ይዘን ወደዚያ መዛወር ድፍረት ጠይቆብናል” ብሏል። “ይሁንና ገና ይህን እርምጃ ለመውሰድ ስናስብ አብርሃምና ሣራ በተዉት ምሳሌ ላይ ተወያይተን ነበር። በይሖዋ ላይ ምን ያህል እንደታመኑና እሱም ፈጽሞ እንዳልተዋቸው ማስታወሳችን በጣም ጠቅሞናል።”

ዶግ በሌላ አገር ስላሳለፉት ሕይወት ሲናገር “በጣም ተባርከናል” ብሏል። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “አኗኗራችን በጣም ቀላል በመሆኑ በቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ማሳለፍ ችለናል፤ አብረን እንሰብካለን፣ እናወራለን እንዲሁም ከልጆቻችን ጋር እንጫወታለን። ይህን አጋጣሚ በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን።”

እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው በሕይወቱ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ለውጥ ማድረግ ይችላል ማለት አይደለም። ያም ቢሆን ሁላችንም አምላክ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን ተማምነን ለእሱ አምልኮ ቅድሚያ በመስጠት የአብርሃምን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይህን ስናደርግ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’” ማለት እንችላለን።​—ዕብራውያን 13:5, 6

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላካዊ ድፍረት ያለው ሰው፣ ፍርሃት ቢሰማውም እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አምላክን የምትታዘዝ ውድ ሚስት

ሣራ ያገባችው ሰው ታላቅ የእምነት ምሳሌ ነው። ራሷ ሣራም ብትሆን በተለያዩ መንገዶች ግሩም አርዓያ የምትሆን ታማኝ ሴት ነበረች። አምላክን ለሚታዘዙ ሴቶች ምሳሌ እንደሆነች ተደርጋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጠቅሳለች። (ኢሳይያስ 51:1, 2፤ ዕብራውያን 11:11፤ 1 ጴጥሮስ 3:3-6) ቅዱሳን መጻሕፍት ግሩም ሴት ስለሆነችው ስለ ሣራ የሚነግሩን ነገር በአንጻራዊ ሁኔታ ትንሽ ቢሆንም እነዚህ ዘገባዎች ይህች ሴት መልካም ባሕርያት እንደነበሯት በግልጽ ያሳያሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ዑርን ለቅቀው እንዲሄዱ አምላክ እንዳዘዘው ሲነግራት መጀመሪያ ላይ ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ወዴት እንደሚሄዱና ከዑር የሚወጡት ለምን እንደሆነ ጥያቄ ተፈጥሮባት ይሆን? በቁሳዊ ረገድ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዴት እንደሚሟሉ አሳስቧት ይሆን? ወዳጅ ዘመዶቿን እንደገና የምታገኛቸው መቼ እንደሆነ ሳታውቅ ትታቸው በመሄዷ አዝና ይሆን? እንዲህ ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን ይሖዋ በታዛዥነቷ እንደሚባርካት እርግጠኛ በመሆን በፈቃደኝነት ዑርን ለቅቃ ወጥታለች።​—የሐዋርያት ሥራ 7:2, 3

ሣራ ታዛዥ የአምላክ አገልጋይ ከመሆኗም በተጨማሪ በጣም ጥሩ ሚስት ነበረች። ሣራ፣ ቤተሰባቸውን ለመምራት ከባሏ ጋር ከመፎካከር ይልቅ ለእሱ ጥልቅ አክብሮት የነበራት ሲሆን አብርሃም ቤተሰባቸውን በሚመራበት ጊዜ በፍቅር ትደግፈው ነበር። በዚህ መንገድ ግሩም የሆኑ ውስጣዊ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ራሷን አስውባለች።​—1 ጴጥሮስ 3:1-6

በዛሬው ጊዜ ያሉ ሚስቶች እንዲህ ዓይነት ባሕርያትን ማፍራታቸው ይጠቅማቸዋል? ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በትዳር ውስጥ አስደሳች ሕይወት ያሳለፈችው ጂል እንዲህ ብላለች፦ “ስሜቴን በነፃነት እንድናገርና አመለካከቴን ለባሌ ከመግለጽ ወደኋላ እንዳልል ሣራ ጥሩ ምሳሌ ሆናኛለች። በሌላ በኩል ደግሞ ባለቤቴ የቤቱ ራስ እንደመሆኑ መጠን የመጨረሻውን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት የእሱ እንደሆነ አውቃለሁ። አንድ ውሳኔ ካደረገ በኋላ ውሳኔውን ለማሳካት የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።”

ከሣራ የምናገኘው ሌላው አስፈላጊ የሆነ ትምህርት፣ እጅግ ውብ የነበረች ቢሆንም በውጫዊ ውበቷ አለመኩራቷ ነው። (ዘፍጥረት 12:10-13) በትዳር ሕይወታቸው ባጋጠሟቸው ውጣ ውረዶች ሁሉ ሣራ አብርሃምን በትሕትና ደግፋዋለች። አብርሃምና ሣራ፣ አንዳቸው ለሌላው በረከት የሆኑ ታማኝ፣ ትሑትና አፍቃሪ ባልና ሚስት እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም።