በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብርሃም—አፍቃሪ ሰው

አብርሃም—አፍቃሪ ሰው

አብርሃም—አፍቃሪ ሰው

አብርሃም የደረሰበትን ሐዘን መቋቋም በጣም ከብዶታል። ውዷ ባለቤቱ ሣራ በሞት ተለይታዋለች። ይህ አረጋዊ ሰው ባለቤቱን ሲቀብር፣ ከእሷ ጋር ያሳለፈውን አስደሳች ጊዜ የሚያስታውሱት በርካታ ትዝታዎች ወደ አእምሮው ይመጣሉ። አብርሃም ከሐዘኑ ብዛት ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። (ዘፍጥረት 23:1, 2) አብርሃም በዚህ ወቅት ማልቀሱ የሚያሳፍር ነገር ወይም የድክመት ምልክት ሳይሆን ግሩም ከሆኑት ባሕርያቱ አንዱን ይኸውም ፍቅሩን የሚያሳይ ነው።

ፍቅር ምንድን ነው? ፍቅር፣ የጠበቀ ቅርርብ ወይም ጥልቅ የመውደድ ስሜት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ፍቅር ያለው ሰው የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ቢጠይቅበትም እንኳ ለሚወዳቸው ሰዎች ያለውን ስሜት በተግባር ይገልጻል።

አብርሃም ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? አብርሃም ቤተሰቡን እንደሚወድድ አሳይቷል። አብርሃም ሥራ የሚበዛበት ሰው እንደነበር ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን የቤተሰቡን ስሜታዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ችላ ብሎ አያውቅም። አብርሃም የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን በአምልኮ ረገድ ቅድሚያውን ወስዶ ቤተሰቡን የሚመራ ሰው እንደሆነ ይሖዋ ራሱ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 18:19) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ፣ አብርሃም ለቤተሰቡ ስላለው ፍቅር ጠቅሷል። አብርሃምን ስለ ይስሐቅ ሲያናግረው “የምትወደውን አንዱን ልጅህን” ብሎታል።​—ዘፍጥረት 22:2

አብርሃም የሚወዳት ሚስቱ ሣራ ስትሞት ሐዘኑን የገለጸበት መንገድም አፍቃሪ ሰው መሆኑን የሚያሳይ ነው። አብርሃም ስቅስቅ ብሎ አልቅሷል። ብርቱና ደፋር ሰው ቢሆንም ሐዘኑን መግለጽ አላሳፈረውም። ይህ የአምላክ አገልጋይ በአንድ በኩል ጠንካራ ሰው የነበረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለስላሳ የሆኑ ባሕርያት ነበሩት።

አብርሃም አምላኩን እንደሚወድድ አሳይቷል። አኗኗሩ በሙሉ ለአምላክ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነበር። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠1 ዮሐንስ 5:3 ላይ የሚናገረው ነገር ወደ አእምሯችን ይመጣ ይሆናል፤ ጥቅሱ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው” ይላል። በዚህ ጥቅስ መሠረት አብርሃም፣ አምላክን በመውደድ ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው።

አብርሃም ይሖዋ የሰጠውን እያንዳንዱን መመሪያ ወዲያው ይታዘዝ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተደጋጋሚ ተገልጿል። (ዘፍጥረት 12:4፤ 17:22, 23፤ 21:12-14፤ 22:1-3) አብርሃም፣ የተሰጠው መመሪያ ቀላል ወይም ከባድ መሆኑ አሊያም ይሖዋ መመሪያውን የሰጠበትን ምክንያት ማወቅ አለማወቁ ለውጥ አልነበረውም። አምላኩ አንድ ነገር እንዲያደርግ ካዘዘው አብርሃም ለመታዘዝ ዝግጁ ነበር። አብርሃም እያንዳንዱን ትእዛዝ ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ለማሳየት እንደሚያስችለው አጋጣሚ አድርጎ ይመለከተው ነበር።

ምን ትምህርት እናገኛለን? ለሌሎች በተለይም ለቤተሰባችን አባላት ጥልቅ ፍቅር በማሳየት አብርሃምን መምሰል እንችላለን። መቼም ቢሆን የኑሮ ውጣ ውረድ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ለምንሰጣቸው ሰዎች ጊዜ እንዲያሳጣን አንፈልግም።

ከዚህም በተጨማሪ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ማዳበራችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለው ፍቅር በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክን ለማስደሰት ስንል በዝንባሌያችን፣ በአነጋገራችን እንዲሁም በምግባራችን ረገድ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል።​—1 ጴጥሮስ 1:14-16

የይሖዋን መመሪያዎች መታዘዝ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው። ይሁንና አብርሃምን የረዳውና “ወዳጄ” ብሎ የጠራው አምላክ እኛንም እንደሚደግፈን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳይያስ 41:8) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል እንዲሁም ጠንካሮች ያደርጋችኋል” ይላል። (1 ጴጥሮስ 5:10) አብርሃም የሚተማመንበት ወዳጁ እንዲህ ብሎ ቃል መግባቱ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወንዶች ማልቀስ የለባቸውም?

ብዙዎች ‘አዎ’ ብለው ይመልሳሉ። ምናልባትም እነዚህ ሰዎች፣ እንደ አብርሃም መንፈሰ ጠንካራ የነበሩ በርካታ ግለሰቦች የሚያሳዝን ሁኔታ ሲያጋጥማቸው እንዳለቀሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀሱን ቢያውቁ ይገረሙ ይሆናል። ከእነዚህ ታማኝ ሰዎች መካከል ዮሴፍ፣ ዳዊት፣ ሐዋርያው ጴጥሮስና የኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች ይገኙበታል፤ ሌላው ቀርቶ ኢየሱስም እንኳ አልቅሷል። (ዘፍጥረት 50:1፤ 2 ሳሙኤል 18:33፤ ሉቃስ 22:61, 62፤ ዮሐንስ 11:35፤ የሐዋርያት ሥራ 20:36-38) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ወንዶች ማልቀሳቸው የድክመት ምልክት እንደሆነ አያስተምርም።