በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ አምላክ ቅረብ

‘እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ፣ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ’

‘እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ፣ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ’

አንድ አባት ከልጁ ጋር የመኪና መንገድ በሚያቋርጥበት ጊዜ ልጁን “እጄን ያዘኝ” ይለዋል። ልጁ በትንናሽ እጆቹ ሰፊ የሆነውን የአባቱን እጅ ጥብቅ አድርጎ ከያዘ ምንም ነገር አይፈራም። አስተማማኝ ያልሆኑ ነገሮች በሞሉበት በዚህ ዓለም ውስጥ እጅህን ይዞ የሚመራህ እንዲኖር የተመኘህበት ጊዜ አለ? ከሆነ ኢሳይያስ የጻፈው ሐሳብ ሊያጽናናህ ይችላል።​—ኢሳይያስ 41:10, 13ን አንብብ።

ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ለእስራኤል ብሔር ነበር። አምላክ እነዚህን ሕዝቦች “የተወደደ ርስቴ” ብሎ ቢጠራቸውም በዙሪያቸው ያሉት ብሔራት ጠላት ሆነውባቸው ነበር። (ዘፀአት 19:5) ታዲያ እስራኤላውያን መፍራት ነበረባቸው? ይሖዋ በኢሳይያስ በመጠቀም የሚያበረታታ መልእክት ልኮላቸዋል። ይህን ሐሳብ በምንመረምርበት ጊዜ ጥቅሱ በዘመናችን ላሉ የይሖዋ አምላኪዎችም እንደሚሠራ እናስታውስ።​—ሮም 15:4

ይሖዋ “አትፍራ” ብሏል። (ቁጥር 10) ሕዝቡን እንደዚህ ያላቸው ያለ ምክንያት አይደለም። ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” በማለት ሕዝቡ መፍራት የማይኖርባቸው ለምን እንደሆነ ገልጾላቸዋል። አምላክ፣ ርቆ እንደሚገኝና ልክ ችግር ሲያጋጥማቸው ብቻ እንደሚደርስላቸው ረዳት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከጎናቸው ያለ ያህል ከእነሱ ጋር እንደሆነና ምንጊዜም ሊረዳቸው ዝግጁ እንደሆነ እንዲያውቁ ፈልጎ ነበር። ይህ የሚያጽናና ሐሳብ አይደለም?

በመቀጠልም ይሖዋ “አትደንግጥ” በማለት አምላኪዎቹን አበረታቷቸዋል። (ቁጥር 10) እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ግስ “የሚጎዳቸው ነገር እንዳይኖር በመስጋት ወዲያና ወዲህ የሚያማትሩ” ሰዎችን ያመለክታል። ይሖዋ፣ ሕዝቡ በፍርሃት አካባቢያቸውን መቃኘት የማያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “አምላክህ ነኝ” ብሏል። ከዚህ በላይ ምን የሚያጽናና ሐሳብ አለ? ይሖዋ “ልዑል” እና ‘ሁሉን የሚችል አምላክ’ ነው። (መዝሙር 91:1) ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ፣ አምላካቸው እስከሆነ ድረስ ምን የሚያስፈራቸው ነገር ይኖራል?

ታዲያ የይሖዋ አምላኪዎች ከእሱ ምን መጠበቅ ይችላሉ? ይሖዋ “በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ቁጥር 10) አክሎም “እኔ፣ . . . አምላክህ ይሖዋ፣ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ” ብሏል። (ቁጥር 13 NW) እነዚህን ጥቅሶች ስታነብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “እነዚህን ሁለት ጥቅሶች በአንድ ላይ ስናያቸው በወላጅና በልጅ መካከል ያለውን ግንኙነት ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ” ይላል። “[አባትየው] ልጁ ችግር ቢያጋጥመው ለመከላከል በማሰብ ቆሞ በመጠበቅ ብቻ አይወሰንም፤ ከዚህ ይልቅ ከልጁ ጋር አብሮ ይሆናል። ልጁ ከእሱ እንዲለይ አይፈቅድም።” እስቲ አስበው፦ ይሖዋ፣ ሕዝቡ ከእሱ እንዲለዩ አይፈቅድም፤ በሕይወታቸው በጣም ከባድ ነገር አጋጥሟቸው ሁሉ ነገር ጭልምልም እንዳለባቸው በሚሰማቸው ጊዜ እንኳ አብሯቸው ይሆናል።​—ዕብራውያን 13:5, 6

ኢሳይያስ የጻፋቸው ቃላት በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አምላኪዎችን በእጅጉ ሊያጽናኗቸው ይችላሉ። “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በተባለው በዚህ ወቅት የሕይወት ውጣ ውረድ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ የሚሰማን ጊዜ ይኖራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሁንና እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ብቻችንን መወጣት አይጠበቅብንም። ይሖዋ እጃችንን ይዞ ሊመራን ፈቃደኛ መሆኑን ነግሮናል። ልጆች በአባታቸው ተማምነው እጁን እንደሚይዙ ሁሉ እኛም ይሖዋ በትክክለኛው መንገድ እንደሚመራንና በችግራችን ጊዜ እንደሚረዳን በመተማመን ኃያል እጁን አጥብቀን መያዝ እንችላለን።​—መዝሙር 63:7, 8

በጥር ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ኢሳይያስ 24 እስከ 42