በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል አክብሮት አላቸው

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል አክብሮት አላቸው

“ቃልህ እውነት ነው።”​—ዮሐ. 17:17

1. ከራስህ ተሞክሮ በመነሳት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለዩ ናቸው እንድትል ያደረገህን አንድ ምክንያት ተናገር።

እስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ውይይት ያደረክበትን ጊዜ ለማስታወስ ሞክር። ይህን ወቅት ስታስብ ምን ነገር ትዝ ይልሃል? ብዙዎች፣ ‘ለጥያቄዎቼ በሙሉ መልስ የሰጡኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሆኑ በጣም አስገርሞኝ ነበር’ የሚል ምላሽ ይሰጡ ይሆናል። በእርግጥም፣ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ፣ ስንሞት ምን እንደምንሆንና በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ተስፋ እንዳላቸው ስናውቅ በጣም ተደስተን ነበር!

2. መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገህ እንድትመለከተው የሚያነሳሱህ አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

2 በጥናታችን ይበልጥ እየገፋን ስንሄድ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት፣ ስለ ሞትና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከመናገር ባለፈ ብዙ ቁም ነገሮችን እንደያዘ ተገንዝበናል። መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክሮችን በመያዝ ረገድ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ መሆኑን ማወቃችን ለአምላክ ቃል ከፍ ያለ ግምት እንድንሰጥ አድርጎናል። ምክሩ ጊዜ የማይሽረው ከመሆኑም በላይ ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ከልብ የሚጥሩ ሰዎች የተሳካና ደስተኛ ሕይወት መምራት ይችላሉ። (መዝሙር 1:1-3ን አንብብ።) እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም መጽሐፍ ቅዱስን የሚቀበሉት ‘እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ነው።’ (1 ተሰ. 2:13) አንዳንድ ታሪካዊ ዘገባዎችን በአጭሩ መቃኘታችን ለአምላክ ቃል እውነተኛ አክብሮት ባላቸውና በሌላቸው ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ እንዲታየን ያደርጋል።

አወዛጋቢው ጉዳይ እልባት አገኘ

3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የክርስቲያን ጉባኤ አንድነት አደጋ ላይ የጣለ ምን ነገር ተከስቶ ነበር? ጉዳዩ አጣብቂኝ እንዲሆን ያደረገውስ ምንድን ነው?

3 ካልተገረዙ አሕዛብ መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባው ቆርኔሌዎስ ሲሆን ይህ ከሆነ 13 ዓመታት አልፈዋል፤ በእነዚህ ጊዜያት በርካታ አሕዛብ ክርስትናን ተቀብለዋል። ይህም የክርስቲያን ጉባኤን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል አንድ አካራካሪ ጉዳይ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል። የክርክሩ መነሻ ‘እነዚህ ሰዎች ከመጠመቃቸው በፊት በአይሁድ ልማድ መሠረት መገረዝ ይኖርባቸዋል?’ የሚለው ጥያቄ ነው። ክርስትናን ለተቀበሉ አይሁዳውያን ይህ ጥያቄ በጣም አስቸጋሪ ነበር። የሙሴን ሕግ የሚጠብቁ አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት መመሥረት ይቅርና ቤታቸው እንኳ አይገቡም ነበር። አይሁዳውያን የሆኑ ክርስቲያኖች የቀድሞ ሃይማኖታቸውን መተዋቸው በራሱ ከባድ ስደት አስከትሎባቸዋል። አሁን ደግሞ ያልተገረዙ አሕዛብን እንደ ወዳጅ አድርገው ቢቀበሏቸው በእነሱና የሙሴን ሕግ በሚጠብቁ አይሁዶች መካከል ያለው ክፍተት ይባስ እየሰፋ ሊሄድ ነው፤ ይህ ደግሞ ክርስትናን በተቀበሉ አይሁዶች ላይ ተጨማሪ ነቀፋ እንዲደርስባቸው ያደርጋል።​—ገላ. 2:11-14

4. አከራካሪውን ጉዳይ ለመፍታት የተሰበሰቡት እነማን ናቸው? የጉዳዩን መጨረሻ ለመስማት በሚጓጉ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ምን ዓይነት ጥያቄዎች ተፈጥረው ሊሆን ይችላል?

4 በ49 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም የሚገኙትና የተገረዙ አይሁዳውያን የሆኑት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ግርዘትን አስመልክቶ የተነሳውን “ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ።” (ሥራ 15:6) በዚህ ወቅት ጥቃቅን የሆኑ ጉዳዮችን እያነሱ ናላ የሚያዞር ሃይማኖታዊ ክርክር አላደረጉም፤ ከዚህ ይልቅ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ አስደሳች ውይይት አካሂደዋል። እርግጥ ነው፣ ሁሉም በጉዳዩ ላይ የራሱን ሐሳብ ሰንዝሯል። ታዲያ የግል ምርጫ ወይም ጭፍን ጥላቻ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ይሆን? ኃላፊነት ያላቸው ሽማግሌዎች በእስራኤል ውስጥ ለክርስቲያኖች ያለው ጥላቻ ጋብ እስኪል ድረስ ውሳኔውን ለሌላ ጊዜ ያስተላልፉት ይሆን? ወይስ ሁለቱም ወገኖች የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ሲሉ በተወሰነ መጠን አቋማቸውን ያላላሉ?

5. በ49 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም የተካሄደው ስብሰባ በዛሬው ጊዜ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ከሚያደርጓቸው ስብሰባዎች የሚለየው በየትኞቹ ወሳኝ ጉዳዮች ነው?

5 በዛሬ ጊዜ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ፣ ለስምምነት ሲባል አቋምን ማላላትና የራስን አመለካከት በሌሎች ላይ መጫን የተለመዱ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር አልታየም። ያም ሆኖ በአንድ ድምፅ ውሳኔ ላይ መድረስ ችለው ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሁሉም የራሳቸው የሆነ ጠንካራ አመለካከት ቢኖራቸውም በስብሰባው ላይ የተገኙት በሙሉ ለአምላክ ቃል አክብሮት ነበራቸው፤ እንዲሁም ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት በዋነኝነት የተጠቀሙት ቅዱሳን መጻሕፍትን ነው።​—መዝሙር 119:97-101ን አንብብ።

6, 7. ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ግርዘትን አስመልክቶ የተነሳውን አከራካሪ ጉዳይ ለመፍታት ቅዱሳን መጻሕፍትን የተጠቀሙት እንዴት ነው?

6 ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጉዳዩን ለመፍታት የረዳቸው ጥቅስ አሞጽ 9:11, 12 ነበር። ይህ ጥቅስ በሐዋርያት ሥራ 15:16, 17 ላይ እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፦ “ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ዳስ ዳግመኛ እገነባለሁ፤ ፍርስራሹንም ዳግም በመገንባት እንደገና አቆመዋለሁ፤ ይህንም የማደርገው የቀሩት ሰዎች በስሜ ከተጠሩት ይኸውም ከአሕዛብ ከመጡት ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያከናውነው ይሖዋ ተናግሯል።”

7 ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ‘እንዴ፣ ይህ ጥቅስ እኮ ከአሕዛብ የመጡ አማኞች ሊገረዙ አይገባም አይልም’ የሚል የተቃውሞ ሐሳብ ይሰነዝሩ ይሆናል። ልክ ነው፣ ጥቅሱ እንደዚያ አይልም፤ ክርስቲያን የሆኑ አንዳንድ አይሁዳውያንም ጥቅሱን የተረዱት በዚህ መንገድ ነበር። እነዚህ አይሁዳውያን፣ ተገርዘው ወደ ይሁዲነት የተቀየሩትን ሰዎች የሚመለከቷቸው ‘ከአሕዛብ እንደመጡ ሰዎች’ ሳይሆን እንደ ወንድሞቻቸው ነበር። (ዘፀ. 12:48, 49) ለምሳሌ ያህል፣ በባግስተር የተዘጋጀው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አስቴር 8:17⁠ን “ከአሕዛብ መካከል ብዙዎቹ ተገርዘው አይሁዳዊ ሆኑ” በማለት ተርጉሞታል። በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው በተናገሩት መሠረት ከእስራኤል ቤት የቀሩት (አይሁዳውያንና ተገርዘው ወደ ይሁዲነት የተለወጡት አሕዛብ) “ከአሕዛብ ከመጡት ሰዎች” (ካልተገረዙት አሕዛብ) ጋር በመሆን በአምላክ ስም የሚጠሩ አንድ ሕዝብ ይሆናሉ፤ ስለዚህ ጥቅሱ የሚያስተላልፈው መልእክት ግልጽ ነበር። ከአሕዛብ የመጡ ሰዎች፣ ክርስቲያን ለመሆን የግድ መገረዝ አይኖርባቸውም።

8. አይሁዳዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ውሳኔውን ለመደገፍ ድፍረት ጠይቆባቸው ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

8 ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች በአምላክ ቃልና በመንፈሱ ተመርተው “በአንድ ልብ” ውሳኔ ላይ መድረስ ችለዋል። (ሥራ 15:25) ይህ ውሳኔ፣ አይሁዳዊ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለበለጠ ስደት እንደሚያጋልጣቸው የታወቀ ቢሆንም ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ደግፈዋል።​—ሥራ 16:4, 5

በግልጽ የሚታይ ልዩነት

9. ንጹሑ አምልኮ በሐሰተኛ ትምህርቶች እንዲበከል ካደረጉት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንዱ ምንድን ነው? በዚህም የተነሳ የትኛው የተሳሳተ ትምህርት ብቅ አለ?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የክርስትና እምነት በሐሰት ትምህርቶች እንደሚበከል አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 7ን አንብብ።) “ጤናማውን ትምህርት” ከማይታገሡት መካከል በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ይገኙበት ነበር። (2 ጢሞ. 4:3) ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩ ሽማግሌዎች “ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ” በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር። (ሥራ 20:30) ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ወዳለ የተጣመመ አስተሳሰብ ከመሯቸው ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንዱን ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፦ “የግሪክን ፍልስፍና በተወሰነ ደረጃ የተማሩ ክርስቲያኖች፣ አዋቂ መስለው ለመታየትና የተማሩ አረማውያንን [ወደ ክርስትና] ለመለወጥ ሲሉ እምነታቸውን ከግሪክ ፍልስፍና አኳያ መግለጽ እንዳለባቸው ሆኖ ተሰማቸው።” በአረማዊ ትምህርቶች ተበርዘው ከተጣመሙት መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አንዱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ጋር የተያያዘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ሲናገር የግሪክን ፍልስፍና የሚያራምዱ ሰዎች ግን እሱ ራሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው የሚል አቋም ነበራቸው።

10. ከኢየሱስ ማንነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ እልባት ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነበር?

10 ከኢየሱስ ማንነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ የሃይማኖት መሪዎች ባደረጓቸው በርካታ ስብሰባዎች ላይ ክርክር ተደርጎበታል። የሃይማኖት መሪዎቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ቦታ ቢሰጡ ኖሮ ይህ ጉዳይ በቀላሉ መፈታት ይችል ነበር፤ ይሁንና አብዛኞቹ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም። እንዲያውም ብዙዎቹ ወደ ስብሰባው ቦታ የሚመጡት የራሳቸውን ውሳኔ ካደረጉ በኋላ ነው፤ በተጨማሪም ከዚህ አቋማቸው ፍንክች ማለት አይፈልጉም። በስብሰባቸው ወቅት ቀኖናዎችንና ደንቦችን ሲያወጡ መጽሐፍ ቅዱስን ጨርሶ አይጠቀሙም ማለት ይቻላል።

11. የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተብለው የሚጠሩት የሃይማኖት መሪዎች የተናገሯቸው ነገሮች ምን ዓይነት ቦታ ተሰጥቷቸዋል? ለምንስ?

11 የሃይማኖት መሪዎቹ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት ለመመርመር ያልፈለጉት ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ቻርለስ ፍሪማን የተባሉ አንድ ምሁር ከሰጡት ሐሳብ መረዳት እንችላለን፤ እኚህ ሰው እንደተናገሩት ከሆነ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች “ኢየሱስ ብዙ ቦታዎች ላይ ከአብ እንደሚያንስ የተናገራቸውን ሐሳቦች ማስተባበል ይከብዳቸዋል።” በዚህም የተነሳ የሃይማኖት መሪዎቹ ከወንጌል ይልቅ ለሰው ወግና አስተሳሰብ ትልቅ ቦታ መስጠት ጀመሩ። እስከ አሁን ድረስ ያሉ በርካታ ቀሳውስት ከአምላክ ቃል ይልቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተብለው የሚጠሩት የሃይማኖት መሪዎች የተናገሯቸውን ነገሮች ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ይህን የተናገሩት በመንፈስ ተመርተው አይደለም። ከአንድ የሥነ መለኮት ተማሪ ጋር ስለ ሥላሴ ትምህርት ውይይት አድርገህ የምታውቅ ከሆነ ይህ እውነት መሆኑን እንዳስተዋልክ ምንም ጥርጥር የለውም።

12. የሮም ንጉሠ ነገሥት የሆነው ቆስጠንጢኖስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ምን መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሯል?

12 የጥንቶቹ የሃይማኖት መሪዎች ያደረጓቸው ጉባኤዎች ካሏቸው ጉልህ ገጽታዎች አንዱ በውይይቶቹ ላይ የሮም ነገሥታት ጣልቃ ገብነት መኖሩ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ሩበንስቲን የኒቂያ ጉባኤን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ቆስጠንጢኖስ፣ በሕልማቸው እንኳ አስበውት የማያውቁትን ክብርና ሀብት [ለጳጳሳቱ] ሰጥቷቸዋል። ይህ አዲስ ንጉሥ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን ማለት ይቻላል መልሶላቸዋል ወይም እንደገና ገንብቶላቸዋል፣ የተነጠቁትን ሥልጣንና ክብር መልሶ አጎናጽፏቸዋል። . . . ከዚህ በፊት ለአረማዊ ካህናት ይሰጡ የነበሩ መብቶችን ለክርስትና ቀሳውስት ሰጥቷል።” በዚህም የተነሳ “ቆስጠንጢኖስ በኒቂያ ጉባኤ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ችሎ ነበር፤ ምናልባትም ስብሰባውን እስከ መምራት ሳይደርስ አልቀረም።” ቻርለስ ፍሪማንም በተመሳሳይ እንዲህ ብለዋል፦ “በዚያ ጊዜ የተከናወነው ነገር ንጉሡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ኃይል ለማጠናከር ብቻ ሳይሆን በምታስተምራቸው ትምህርቶች ላይም ተጽዕኖ ለማሳደር እጁን እንዲያስገባ በር ከፍቶለታል።”​—ያዕቆብ 4:4ን አንብብ።

13. የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በግልጽ የተቀመጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ችላ እንዲሉ ያደረጋቸው ምን ይመስልሃል?

13 የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናት የኢየሱስ ክርስቶስን ትክክለኛ ማንነት ለመቀበል ቢከብዳቸውም አብዛኛው ተራው ሕዝብ ግን እንዲህ ዓይነት ችግር አልነበረበትም። እነዚህ ሰዎች እንደ ሃይማኖት መሪዎቹ ከንጉሠ ነገሥቱ በሚያገኙት ገንዘብ ኪሳቸውን የማደለብ ወይም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሹመት የማግኘት ፍላጎት ስለሌላቸው ቅዱሳን መጻሕፍት በሚሰጡት ብርሃን ታግዘው ጉዳዩን በግልጽ ለማየት ጥረት አድርገዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ይህን እንዳደረጉ በርካታ ማስረጃዎች ያሳያሉ። በዚያን ዘመን የሃይማኖት ምሁር የነበረው የኒሳው ግሪጎሪ ተራውን ሕዝብ በማስመልከት የሚከተለውን የፌዝ አስተያየት ሰጥቷል፦ “ልብስ ሻጮች፣ ገንዘብ መንዛሪዎችና ባለመደብሮች ሁሉ የሃይማኖት ምሁር ልሁን ይላሉ። ገንዘባችሁን በስንት እንደሚመነዝሩላችሁ ስትጠይቁ አንዳንድ ፈላስፎች የአብንና የወልድን ልዩነት ሊያብራሩላችሁ ይሞክራሉ። የዳቦ ዋጋ ስትጠይቁ አብ ከወልድ ይበልጣል የሚል መልስ ይሰጧችኋል። የገላ ውኃ ተሰናድቶ እንደሆነ ስትጠይቁ ወልድ ፍጡር እንደሆነ ይነግሯችኋል።” በእርግጥም አብዛኛው ተራው ሕዝብ ከሃይማኖት መሪዎቹ በተለየ መልኩ፣ አንድ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱት በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተው ነበር። ግሪጎሪና ባልደረቦቹ ተራውን ሕዝብ ቢሰሙ ኖሮ ምንኛ የተሻለ ነበር!

“ስንዴው” እና “እንክርዳዱ” አብረው ያድጋሉ

14. ከአንደኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ምንጊዜም በዚህች ምድር ላይ የተወሰኑ እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አልታጡም ብለን እንድንደመድም የሚያደርገን ምንድን ነው?

14 ኢየሱስ ስለ ስንዴውና እንክርዳዱ የተናገረው ምሳሌ ከአንደኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ምንጊዜም በዚህች ምድር ላይ የተወሰኑ እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደማይታጡ ይጠቁማል። ኢየሱስ እነዚህን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በእንክርዳድ’ መካከል ካደገ “ስንዴ” ጋር አመሳስሏቸዋል። (ማቴ. 13:30) እርግጥ ነው፣ የትኞቹ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በስንዴ ከተመሰለው የቅቡዓን ክፍል እንደሚመደቡ ማወቅ አንችልም፤ ሆኖም በድፍረት ለአምላክ ቃል ጥብቅና የቆሙና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌላቸውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ያጋለጡ አንዳንድ ሰዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደነበሩ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

15, 16. ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዳላቸው ካሳዩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ።

15 በፈረንሳይ የሊዮን ከተማ ሊቀ ጳጳሳት የሆነው አጎባርድ (779-840 ዓ.ም.) የምስል አምልኮን፣ ለቅዱሳን ተብሎ ቤተ ክርስቲያን መገንባትን እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችንና ልማዶችን ይቃወም ነበር። በተጨማሪም ከአጎባርድ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ላይ የኖረው ክላውዲየስ የተባለ ጳጳስ የቤተ ክርስቲያን ወጎችንና ለቅዱሳን የሚቀርቡ ጸሎቶችን እንዲሁም ቅዱስ ተደርገው ለሚታዩ ነገሮች ከፍ ያለ ክብር መስጠትን በጥብቅ ይቃወም ነበር። በ11ኛው መቶ ዘመን ላይ ደግሞ በፈረንሳይ የቱር ከተማ ሊቀ ዲያቆናት የሆነው በረንጋሪየስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ሥርዓተ ቁርባንን አስመልክታ የምታስተምረውን ትምህርት በመቃወሙ ተወግዞ ነበር። በተጨማሪም ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ከቤተ ክርስቲያን ወግ ይበልጣል የሚል አቋም ነበረው።

16 በ12ኛው መቶ ዘመንም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍቅር የነበራቸው ሁለት ሰዎች ተነስተው ነበር፤ እነሱም የብሪው ፒተርና የሎዛኑ ሄንሪ ናቸው። ፒተር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጨቅላ ሕፃናት ጥምቀትን፣ ሥርዓተ ቁርባንን፣ ለሙታን መጸለይንና የመስቀል አምልኮን አስመልክታ የምታስተምረው ትምህርት ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር እንደማይጣጣም ስለተገነዘበ ቅስናውን በገዛ ፈቃዱ ትቷል። በ1140 ፒተር በያዘው አቋም የተነሳ ሕይወቱን አጥቷል። መነኩሴ የነበረው ሄንሪም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚታየውን ምግባረ ብልሹነት አልፎ ተርፎም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሥርዓቶችን አጋልጧል። በዚህም የተነሳ በ1148 ተይዞ የታሰረ ሲሆን ቀሪ ሕይወቱን በሙሉ ያሳለፈው በእስር ቤት ነበር።

17. ዋልዶ እና ተከታዮቹ ምን ጠቃሚ ነገሮችን አከናውነዋል?

17 የብሪው ፒተር ቤተ ክርስቲያኒቱን ተዳፍሯል በሚል በቁሙ እንዲቃጠል በተደረገበት ወቅት አካባቢ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ቫልደስ ወይም ዋልዶ * ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማሰራጨት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ዋልዶ ከላይ እንደተጠቀሱት እንደ ፒተርና ሄንሪ ሃይማኖታዊ ማዕረግ ባይኖረውም ለአምላክ ቃል ከፍተኛ አክብሮት ነበረው፤ በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ፣ በደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይ ውስጥ በስፋት በሚነገረው ቋንቋ እንዲተረጎም ለማድረግ ሲል ያለውን ጥሪት ሁሉ እስከመስጠት ደርሷል። አንዳንድ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ በመቻላቸው በጣም ስለተደሰቱ እነሱም በበኩላቸው ያላቸውን ንብረትም ሆነ መላ ሕይወታቸውን በመስጠት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች አካፍለዋል። ሆኖም ይህ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንቅልፍ ነሳት። ከጊዜ በኋላ ዎልደንሳውያን በመባል የተጠሩት እነዚህ ቀናተኛ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች በ1184 በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተወገዙ ሲሆን የአካባቢው ጳጳስም ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርገዋቸዋል። ሆኖም ይህ እርምጃ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በሌሎች አካባቢዎች እንዲሰራጭ መንገድ ጠርጓል። ከጊዜ በኋላም በተለያዩ የአውሮፓ ግዛቶች የዋልዶ፣ የፒተርና የሄንሪ ተከታዮችን እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎችን ማየት የተለመደ ሆነ። ከዚህ በኋላ ባሉት ዘመናትም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥብቅና የቆሙ ሌሎች ግለሰቦች ተነስተዋል፤ ከእነዚህም መካከል ጆን ዊክሊፍ (1330-1384 ገደማ)፣ ዊልያም ቲንደል (1494-1536 ገደማ)፣ ሄንሪ ግሩ (1781-1862) እና ጆርጅ ስቶርዝ (1796-1879) ይገኙበታል።

‘የአምላክ ቃል አልታሰረም’

18. በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩት ቅን የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ምን ዘዴ ይጠቀሙ እንደነበር አብራራ። ይህ ዘዴ ውጤታማ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

18 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚቃወሙ ሰዎች ይህ እውነት እንዳይሰራጭ የቻሉትን ያህል ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም። ሁለተኛ 2 ጢሞቴዎስ 2:9 ‘የአምላክ ቃል አልታሰረም’ በማለት ይናገራል። በ1870 ቅን የሆኑ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እውነትን መፈለግ ጀመሩ። እነዚህ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተጠቀሙት ምን ዓይነት ዘዴ ነበር? በቅድሚያ ከመካከላቸው አንዱ ጥያቄ ይጠይቃል። ከዚያም በጥያቄው ላይ ውይይት ያደርጋሉ። በመቀጠል ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥቅሶች ይመረምራሉ፤ ጥቅሶቹ እርስ በርሳቸው የሚስማሙ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ የተነሳውን ጥያቄ አስመልክቶ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ፤ ከዚያም የደረሱበትን መደምደሚያ በጽሑፍ ያሰፍራሉ። ታዲያ በ1800ዎቹ መገባደጃ ላይ የነበሩት ታማኝ የሆኑት እነዚህ “መንፈሳዊ አያቶቻችን” በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እምነታቸው ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ጥረት ያደርጉ እንደነበር ማወቅህ አላበረታታህም?

19. ለ2012 የተመረጠው የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህ ጥቅስ መመረጡ ተገቢ የሆነውስ ለምንድን ነው?

19 ዛሬም ቢሆን ለምናምንባቸው ነገሮች መሠረት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የ2012 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን የመረጠው ኢየሱስ በሙሉ ልብ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ነው። (ዮሐ. 17:17) የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በእውነት መመላለስ ይኖርበታል፤ እንግዲያው ሁላችንም ምንጊዜም በአምላክ ቃል ለመመራት ጥረት እናድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 ቫልደስ፣ አንዳንድ ጊዜ ፒየር ቫልደስ ወይም ፒተር ዋልዶ በመባል ይጠራል። ይሁን እንጂ ትክክለኛ ስሙ ማን እንደሆነ ማረጋገጥ አልተቻለም።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የ2012 የዓመት ጥቅሳችን፦ “ቃልህ እውነት ነው።”​—ዮሐንስ 17:17

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዋልዶ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዊክሊፍ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲንደል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግሩ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስቶርዝ