በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመላው የሰው ዘር ጥቅም የሚያስገኙ ንጉሣዊ ካህናት

ለመላው የሰው ዘር ጥቅም የሚያስገኙ ንጉሣዊ ካህናት

“እናንተ . . . ‘የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ።”​—1 ጴጥ. 2:9

1. ‘የጌታ ራት’ የመታሰቢያው በዓል ተብሎም የሚጠራው ለምንድን ነው? የዚህ በዓል ዓላማስ ምንድን ነው?

ጊዜው 33 ዓ.ም. ኒሳን 14 ምሽት ላይ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር በመሆን የአይሁዳውያንን የማለፍ በዓል ለመጨረሻ ጊዜ እያከበረ ነው። ኢየሱስ ከሃዲውን የአስቆሮቱን ይሁዳ ካሰናበተ በኋላ አንድ ሌላ በዓል አቋቋመ፤ ይህ በዓል ከጊዜ በኋላ ‘የጌታ ራት’ ተብሎ ተጠርቷል። (1 ቆሮ. 11:20) ኢየሱስ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ሁለት ጊዜ ተናግሯል። ይህ ዝግጅት የመታሰቢያው በዓል በመባልም የሚታወቅ ሲሆን በኢየሱስ ሞት ላይ ትኩረት ያደርጋል። (1 ቆሮ. 11:24, 25) የይሖዋ ምሥክሮችም ይህን ትእዛዝ በመከተል በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ የመታሰቢያውን በዓል ያከብራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ የቀን አቆጣጠር መሠረት በ2012 ኒሳን 14 የሚጀምረው ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው።

2. ኢየሱስ ቂጣውንና ወይኑን አስመልክቶ ምን ብሏል?

2 ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ፣ ኢየሱስ በዚያን ዕለት ያደረገውንና የተናገረውን ነገር እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “ቂጣ አንስቶ አመሰገነ፣ ከቆረሰውም በኋላ ሰጣቸውና ‘ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ማለት ነው። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ አላቸው። ራት ከበሉ በኋላም ጽዋውን አንስቶ ልክ እንደዚሁ አደረገ፤ እንዲህም አለ፦ ‘ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው።’” (ሉቃስ 22:19, 20) ታዲያ ሐዋርያቱ ኢየሱስ የተናገረውን ይህን ሐሳብ የተረዱት እንዴት ነበር?

3. የኢየሱስ ሐዋርያት ቂጣውና ወይኑ ምን ትርጉም እንዳለው ተረድተው ነበር?

3 ሐዋርያቱ አይሁዳውያን እንደመሆናቸው መጠን ካህናት በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ለአምላክ ስለሚያቀርቡት የእንስሳት መሥዋዕት በቂ ግንዛቤ ነበራቸው። እነዚህ መሥዋዕቶች የይሖዋን ሞገስ እንደሚያስገኙና ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ደግሞ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት እንደሚቀርቡ ያውቁ ነበር። (ዘሌ. 1:4፤ 22:17-29) በመሆኑም ኢየሱስ ለእነሱ ሲል ‘ሥጋውን እንደሚሰጥ’ እንዲሁም ‘ደሙን እንደሚያፈስ’ ሲናገር ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንደሚያቀርብ ማመልከቱ እንደሆነ ሐዋርያቱ ተረድተው መሆን አለበት። ይህ መሥዋዕት ደግሞ ከእንስሳት መሥዋዕት እጅግ የላቀ ዋጋ አለው።

4. ኢየሱስ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

4 ኢየሱስ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው” በማለት የተናገረው አባባልስ ምን ያመለክታል? ሐዋርያቱ ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን የሚናገረውን በ⁠ኤርምያስ 31:31-33 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ያውቁት ነበር። (ጥቅሱን አንብብ።) በመሆኑም ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር በኤርምያስ ላይ የተጠቀሰው አዲሱ ቃል ኪዳን መመሥረቱን እየገለጸ ነበር፤ ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ያቋቋመውን የሕጉን ቃል ኪዳን የሚተካ ነው። ታዲያ በሁለቱ ቃል ኪዳኖች መካከል ያለው ተዛማጅነት ምንድን ነው?

5. የሕጉ ቃል ኪዳን ለእስራኤላውያን ምን ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር?

5 አዎን፣ እነዚህ ቃል ኪዳኖች ዓላማቸው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ የሕጉን ቃል ኪዳን ለሕዝቡ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ።” (ዘፀ. 19:5, 6) ታዲያ እነዚህ ቃላት ለእስራኤላውያን ምን ትርጉም ነበራቸው?

ንጉሣዊ ካህናት የመሆን ተስፋ

6. የሕጉ ቃል ኪዳን የተሰጠው የትኛውን ተስፋ ለመፈጸም ነው?

6 እስራኤላውያን “ቃል ኪዳን” የሚለው ሐረግ ምን ትርጉም እንዳለው በደንብ ያውቁ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ እንዲህ ያሉ ስምምነቶችን ከቀድሞ አባቶቻቸው ከኖኅና ከአብርሃም ጋር ማድረጉን ያስታውሳሉ። (ዘፍ. 6:18፤ 9:8-17፤ 15:18፤ 17:1-9) ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን በገባበት ወቅት ከሰጠው ተስፋ አንዱ “የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” የሚለው ነው። (ዘፍ. 22:18) የሕጉ ቃል ኪዳን፣ ይሖዋ ይህን ተስፋ ወደ ፍጻሜው ለማድረስ ከተጠቀመባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በዚህ ቃል ኪዳን መሠረት የእስራኤል ብሔር ለይሖዋ ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተወደደ ርስቱ’ ሆኗል። ይሖዋ ይህን ብሔር የመረጠው ለምን ዓላማ ነው? ለእሱ “የመንግሥት ካህናት” እንዲሆኑ ነው።

7. “የመንግሥት ካህናት” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?

7 እስራኤላውያን፣ የነገሥታትና የካህናት የሥራ ድርሻ ምን እንደሆነ ያውቁ ነበር፤ ይሁንና በጥንት ዘመን በአንድ ጊዜ ንጉሥም ካህንም ሆኖ እንዲያገለግል በይሖዋ የተሾመው ብቸኛ ሰው መልከ ጼዴቅ ነው። (ዘፍ. 14:18) አሁን ግን ይሖዋ ለብሔሩ “የመንግሥት ካህናት” የማስገኘት አጋጣሚ ከፍቶላቸው። በኋላ ላይ በመንፈስ መሪነት ከተጻፉት ደብዳቤዎች መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ለብሔሩ የገባው ቃል የሚያመለክተው ብሔሩ ንጉሣዊ ካህናትን ማለትም ካህናትም ጭምር ሆነው የሚያገለግሉ ነገሥታትን የማስገኘት አጋጣሚ የተከፈተለት መሆኑን ነው።​—1 ጴጥ. 2:9

8. በአምላክ የተሾመ አንድ ካህን ምን አገልግሎቶችን ይሰጣል?

8 የንጉሥ ተግባር ሕዝቡን ማስተዳደር እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁንና የካህን ሥራ ምንድን ነው? ዕብራውያን 5:1 እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ከሰዎች መካከል የተመረጠ እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ለኃጢአት መባና መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድ የአምላክ በሆኑት ነገሮች ላይ ሰዎችን በመወከል ይሾማል።” በመሆኑም አንድ በይሖዋ የተመረጠ ካህን በሕጉ መሠረት በሚቀርቡ መሥዋዕቶች አማካኝነት ኃጢአተኛ የሆኑትን ሰዎች ወክሎ አምላክ ፊት በመቅረብ ስለ እነሱ ምልጃ ያቀርባል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ካህን ይሖዋን በመወከል መለኮታዊውን ሕግ ለሕዝቡ ያስተምራል። (ዘሌ. 10:8-11፤ ሚል. 2:7) በመሆኑም በአምላክ የተሾመ ካህን በእነዚህ ሁለት መንገዶች አማካኝነት ሕዝቡን ከአምላክ ጋር የማስታረቅ ሥራ ይሠራል።

9. (ሀ) እስራኤላውያን “የመንግሥት ካህናት” የማስገኘት ተስፋቸው እውን የሚሆነው ምን ካደረጉ ብቻ ነው? (ለ) ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር መካከል ካህናትን የመረጠው ለምንድን ነው? (ሐ) እስራኤላውያን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ሆነው “የመንግሥት ካህናት” ማስገኘት ያልቻሉት ለምንድን ነው?

9 የሕጉ ቃል ኪዳን፣ ‘ለአሕዛብ ሁሉ’ በረከት የሚያመጡ ንጉሣዊ ካህናትን የማስገኘት አጋጣሚ ለእስራኤል ብሔር ከፍቶለት ነበር። ይሁንና ይህን እጹብ ድንቅ ተስፋ መውረስ የሚችሉት ይሖዋን ‘ከታዘዙና ቃል ኪዳኑን ከጠበቁ’ ብቻ ነው። ታዲያ እስራኤላውያን ይሖዋን ‘መታዘዝ’ ይችሉ ይሆን? አዎ፣ በተወሰነ መጠን ይህን ማድረግ ይችላሉ። ሕጉን ሙሉ በሙሉ መጠበቅስ ይችላሉ? በፍጹም። (ሮም 3:19, 20) በዚህም ምክንያት ይሖዋ ሕዝቡ ባለማወቅ ለሚፈጽመው ኃጢአት የእንስሳት መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናትን ከእስራኤል ብሔር መካከል መረጠ፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ካህናት ነገሥታት ሆነው የማገልገል መብት አልተሰጣቸውም። (ዘሌ. 4:1 እስከ 6:7) ካህናቱ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ሕዝቡ ለሠራው ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ኃጢአት ጭምር ነው። (ዕብ. 5:1-3፤ 8:3) እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ቢኖራቸውም መሥዋዕቱን የሚያቀርበውን ሰው ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት አያነጹትም። በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር የሚያገለግሉት ካህናት ቅን የሆኑ እስራኤላውያንን እንኳ ከአምላክ ጋር ሙሉ በሙሉ ማስታረቅ አይችሉም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም” በማለት ሁኔታውን ገልጾታል። (ዕብ. 10:1-4) እስራኤላውያን ሕጉን ባለመጠበቃቸው ምክንያት የተረገሙ ሊሆኑ ችለዋል። (ገላ. 3:10) በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለዓለም ሁሉ ንጉሣዊ ካህናት ሆነው ማገልገል አይችሉም።

10. የሕጉ ቃል ኪዳን ያገለገለው ለምን ዓላማ ነበር?

10 ታዲያ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን “የመንግሥት ካህናት” እንደሚሆኑ የገባው ቃል ከንቱ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው? በጭራሽ! እስራኤላውያን ይሖዋን ለመታዘዝ ልባዊ ጥረት ካደረጉ የተሰጣቸውን ተስፋ የማግኘት አጋጣሚ ነበራቸው፤ ይሁን እንጂ ይህ የሚፈጸመው በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ሆነው አይደለም። ለምን? (ገላትያ 3:19-25ን አንብብ።) ይህን ለመረዳት ሕጉ የተሰጠበት ዓላማ ምን እንደሆነ በቅድሚያ ማወቅ ይኖርብናል። ሕጉ፣ ይሖዋን ለመታዘዝ ጥረት የሚያደርጉ እስራኤላውያን በሐሰት አምልኮ እንዳይበከሉ ጠብቋቸዋል። እንዲሁም ኃጢአተኛ እንደሆኑና ሊቀ ካህናታቸው ከሚያቀርበው የላቀ ሌላ መሥዋዕት እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝቧቸዋል። በተጨማሪም ሕጉ፣ ወደ ክርስቶስ ወይም ወደ መሲሑ (“የተቀባ” የሚል ትርጉም አለው) የሚመራ ሞግዚት ሆኖላቸዋል። ይሁንና መሲሑ ሲመጣ ኤርምያስ አስቀድሞ የተናገረውን አዲሱን ቃል ኪዳን ይመሠርታል። ክርስቶስን የሚቀበሉ ሁሉ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ በመታቀፍ “የመንግሥት ካህናት” የመሆን መብት ያገኛሉ። ይህ የሚሆነው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ንጉሣዊ ካህናትን የሚያስገኘው አዲሱ ቃል ኪዳን

11. ኢየሱስ ለንጉሣዊ ካህናት መሠረት የሆነው እንዴት ነው?

11 በ29 ዓ.ም. የናዝሬቱ ኢየሱስ መሲሕ ሆነ። ሠላሳ ዓመት ገደማ ሲሆነው በውኃ በመጠመቅ ይሖዋ ለእሱ ያለውን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን አቀረበ። ይሖዋም “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ” በማለት ለኢየሱስ እውቅና የሰጠው ከመሆኑ በላይ በዘይት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ቀባው። (ማቴ. 3:13-17፤ ሥራ 10:38) ኢየሱስ በዚህ መንገድ መቀባቱ በእሱ ለሚያምኑ የሰው ልጆች በሙሉ ሊቀ ካህናት ሆኖ እንደሚያገለግልና ወደፊት ደግሞ ንጉሣቸው እንደሚሆን የሚያሳይ ነው። (ዕብ. 1:8, 9፤ 5:5, 6) በዚህ መልኩ ለእውነተኛው የክህነት አገልግሎት መሠረት ሆኗል።

12. ኢየሱስ ያቀረበው መሥዋዕት ምን ነገር ማከናወን ችሏል?

12 ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች የወረሱትን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ለማስተሰረይ ምን ዓይነት መሥዋዕት ሊያቀርብ ይችላል? የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመበት ወቅት እንደጠቆመው መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወቱን ነው። (ዕብራውያን 9:11, 12ን አንብብ።) ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. በመጠመቅ ሊቀ ካህናት ሆኖ ከተሾመ በኋላ እስኪሞት ድረስ በሁሉም ረገድ የተፈተነ ለመሆንና ሥልጠና ለማግኘት ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብ. 4:15፤ 5:7-10) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ በማረግ የመሥዋዕቱን ዋጋ በይሖዋ ፊት አቅርቧል። (ዕብ. 9:24) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ በእሱ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሚያምኑ በተግባር የሚያሳዩ ሰዎችን ወክሎ ወደ ይሖዋ ልመና ማቅረብና የዘላለም ሕይወት አግኝተው አምላክን እንዲያገለግሉ መርዳት ይችላል። (ዕብ. 7:25) በተጨማሪም ኢየሱስ ያቀረበው መሥዋዕት አዲሱ ቃል ኪዳን ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ያደርጋል።​—ዕብ. 8:6፤ 9:15

13. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ እንዲታቀፉ ግብዣ የቀረበላቸው ሰዎች ምን ተስፋ ተዘርግቶላቸው ነበር?

13 በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ እንዲካተቱ ግብዣ የቀረበላቸው ሰዎችም በመንፈስ ቅዱስ መቀባት ይኖርባቸዋል። (2 ቆሮ. 1:21) ታማኝ የሆኑ አይሁዳውያን በኋላም ከአሕዛብ የመጡ ሰዎች በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ተካተዋል። (ኤፌ. 3:5, 6) ታዲያ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች ያላቸው ተስፋ ምንድን ነው? እነዚህ ቅቡዓን እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ያገኛሉ። ይሖዋ “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም” በማለት ቃል ገብቶ ነበር። (ኤር. 31:34) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኃጢአታቸው ስለተሰረዘላቸው “የመንግሥት ካህናት” ሆነው ማገልገል ይችላሉ። ጴጥሮስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን ‘ድንቅ ባሕርያት በስፋት እንድታስታውቁ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ።” (1 ጴጥ. 2:9) ጴጥሮስ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሕጉን በሰጣቸው ጊዜ የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ ይህ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ክርስቲያኖችም እንደሚሠራ ተናግሯል።​—ዘፀ. 19:5, 6

ንጉሣዊ ካህናት ለመላው የሰው ዘር ጥቅም ያስገኛሉ

14. ንጉሣዊ ካህናት የሚያገለግሉት የት ሆነው ነው?

14 በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ክርስቲያኖች የሚያገለግሉት የት ሆነው ነው? እነዚህ ክርስቲያኖች ምድር ላይ በሚኖሩበት ወቅት በቡድን ደረጃ ‘የእሱን ድንቅ ባሕርያት በስፋት በማስታወቅ’ እንዲሁም መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ይሖዋን ወክለው በካህንነት ያገለግላሉ። (ማቴ. 24:45፤ 1 ጴጥ. 2:4, 5) ሞተው ከተነሱ በኋላ ደግሞ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት በመሆን ሁለቱንም ኃላፊነታቸውን በተሟላ መልኩ ይፈጽማሉ። (ሉቃስ 22:29፤ 1 ጴጥ. 1:3-5፤ ራእይ 1:6) ሐዋርያው ዮሐንስ በሰማይ ባለው የይሖዋ ዙፋን አጠገብ በርካታ መንፈሳዊ ፍጥረታትን በራእይ መመልከቱ ይህን ያረጋግጣል። እነዚህ ፍጥረታት ‘ለበጉ’ እንዲህ የሚል “አዲስ መዝሙር” ዘምረዋል፦ “በደምህም ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ ሰዎችን ለአምላክ ዋጅተሃል፤ እንዲሁም ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንዲሆኑ አድርገሃቸዋል፤ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።” (ራእይ 5:8-10) በኋላም ዮሐንስ እነዚህን ገዥዎች አስመልክቶ “የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ” ብሏል። (ራእይ 20:6) በመሆኑም “ንጉሣዊ ካህናት” የሚባሉት፣ የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮችና ክርስቶስ በአንድነት ሆነው ሲሆን እነሱም ለመላው የሰው ልጆች ጥቅም ያስገኛሉ።

15, 16. ከሰዎች መካከል የተዋጁት ንጉሣዊ ካህናት ለምድር ሕዝቦች ምን ጥቅም ያስገኛሉ?

15 መቶ አራባ አራት ሺህዎቹ ለምድር ሕዝቦች ምን ጥቅም ያስገኛሉ? በ⁠ራእይ 21 ላይ እንደተገለጸው ንጉሣዊ ካህናቱ በሰማይ ባለች ከተማ ማለትም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም የተመሰሉ ሲሆን ‘የበጉ ሚስት’ ተብለውም ተጠርተዋል። (ራእይ 21:9) ከቁጥር 2 እስከ 4 እንዲህ ይላል፦ “ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤ እሷም ለባሏ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ነበር። በዚህ ጊዜ ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ ‘እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።’” እንዴት ያለ አስደናቂ በረከት ነው! ለእንባ፣ ለሐዘን፣ ለጩኸትና ለሥቃይ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሞት ይወገዳል። ታማኝ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ ስለሚደርሱ ከአምላክ ጋር ሙሉ በሙሉ ይታረቃሉ።

16 ራእይ 22:1, 2 እነዚህ ንጉሣዊ ካህናት ለሰው ልጆች የሚያስገኙትን ተጨማሪ በረከት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “መልአኩም ከአምላክና ከበጉ ዙፋን ወጥቶ የሚፈሰውን እንደ ክሪስታል የጠራ የሕይወት ውኃ ወንዝ አሳየኝ፤ ወንዙም [በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም] አውራ ጎዳና መካከል ቁልቁል ይፈስ ነበር። በወንዙም ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈሩ በዓመት አሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጡ የሕይወት ዛፎች ነበሩ። የዛፎቹም ቅጠሎች ብሔራትን ለመፈወስ የሚያገለግሉ ነበሩ።” “ብሔራት” ወይም ከተለያየ ዘር የተውጣጡ ሰዎች ምሳሌያዊ በሆነው በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ከአዳም ከወረሱት አለፍጽምና ነፃ በመሆን ሙሉ በሙሉ ይፈወሳሉ። በእርግጥም ‘ቀድሞ የነበሩት ነገሮች ያልፋሉ።’

ንጉሣዊ ካህናት ሥራቸውን ከፍጻሜ ያደርሳሉ

17. ንጉሣዊ ካህናት በመጨረሻ ምን ነገር ያከናውናሉ?

17 እነዚህ ንጉሣዊ ካህናት ለ1,000 ዓመት ያህል ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ ምድራዊ ተገዥዎቻቸው የሆኑትን ሰዎች ወደ ፍጽምና ደረጃ ያደርሳሉ። ከዚያም ሊቀ ካህናትና ንጉሥ የሆነው ክርስቶስ ፍጽምና የተላበሰውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ለይሖዋ ያስረክባል። (1 ቆሮንቶስ 15:22-26ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ ንጉሣዊ ካህናቱ የተሰጣቸውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ይፈጽማሉ።

18. የክርስቶስ አጋሮች የሆኑት ንጉሣዊ ካህናት ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ከፈጸሙ በኋላ ይሖዋ የሚጠቀምባቸው እንዴት ነው?

18 ታዲያ ከዚያ በኋላ ይሖዋ እነዚህን ታላቅ መብት ያገኙ የክርስቶስ አጋሮች የሚጠቀምባቸው እንዴት ነው? ራእይ 22:5 “ነገሥታት ሆነውም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይገዛሉ” በማለት ይናገራል። ለመሆኑ የሚነግሡት በማን ላይ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁንና እነዚህ ንጉሣዊ ካህናት ያገኙት ልዩ ሕይወት እንዲሁም ፍጽምና የጎደላቸውን የሰው ልጆች በመርዳት ያካበቱት ተሞክሮ የንግሥና ሥልጣናቸውን እንደያዙ ለዘላለም የይሖዋን ዓላማዎች እየፈጸሙ ለመኖር ብቁ ያደርጋቸዋል።

19. በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ ሁሉ በዚህ ዝግጅት ላይ መገኘታቸው ምን ነገር እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል?

19 ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5, 2012 የክርስቶስን ሞት ለማሰብ መሰብሰባችን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንድናስታውስ ያደርገናል። በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ካልቦካው ቂጣና ከቀዩ ወይን ይካፈላሉ፤ ይህም በአዲሱ ቃል ኪዳን እንደታቀፉ ያሳያል። የክርስቶስን መሥዋዕት የሚያመለክቱት ቂጣውና ወይኑ በአምላክ ዘላለማዊ ዓላማ ውስጥ ያገኟቸውን መብቶችና ኃላፊነቶች እንዲያስታውሱ ያደርጓቸዋል። እንግዲያው ሁላችንም ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች ጥቅም የሚያስገኙትን ንጉሣዊ ካህናት በማዘጋጀቱ ያለንን አድናቆት ለማሳየት በበዓሉ ላይ እንገኝ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሣዊ ካህናት ለሰው ልጆች ዘላለማዊ ጥቅም ያስገኛሉ