በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

“ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ሳታሰልሱም ጸልዩ።”​—ማቴ. 26:41

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ጸሎታችን ነቅተን እንደምንጠብቅ ሊያሳይ የሚችለው እንዴት ነው?

በአገልግሎት ረገድ ነቅተን እንደምንጠብቅ በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?

ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ነቅተን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ ከተወው ምሳሌ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ? (ለ) ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ፍጹም የሆነው ኢየሱስ የተወውን አርዓያ መከተል ይችላሉ? በምሳሌ አስረዳ።

ምናልባት እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ በእርግጥ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይቻላል? ኢየሱስ እኮ ፍጹም ሰው ነበር! በዚያ ላይ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሌላው ቀርቶ እሱ ከኖረበት ዘመን በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ስለሚከናወኑ ነገሮች ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚችል ያሳየባቸው ወቅቶች ነበሩ! ታዲያ ኢየሱስ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልገው ነበር እንዴት ሊባል ይችላል?’ (ማቴ. 24:37-39፤ ዕብ. 4:15) ነቅቶ መጠበቅ በጣም አንገብጋቢ የሆነበትን ምክንያት ከማየታችን በፊት እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመርምር።

2 ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ፍጹም የሆነ ሰው የተወውን ምሳሌ መከተል ይችላሉ? አዎ ይችላሉ፤ ምክንያቱም አንድ ግለሰብ በሙያው በጣም ከተካነ አስተማሪ መማርም ሆነ የእሱን አርዓያ መከተል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ቀስት ውርወራ ምንም የማያውቅ ሰው በሚሠለጥንበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። መጀመሪያ ላይ ዒላማውን ሊመታ ይቅርና ቀስቱን እንኳ አስተካክሎ ማስፈንጠር አይችልም፤ በመሆኑም ቀጣይ የሆነ ሥልጠና መውሰድና ልምምድ ማድረግ ይኖርበታል። ተማሪው ችሎታውን ለማሻሻል ከፈለገ የተዋጣለት ቀስተኛ የሆነው አስተማሪው የሚያደርገውን ነገር ልብ ብሎ መመልከት ይኖርበታል። ተማሪው የአስተማሪውን አቋቋም፣ ቀስቱንና ደጋኑን የያዘበትን መንገድ እንዲሁም ፍላጻውን ለማስፈንጠር ጅማቱን እንዴት አድርጎ እንደሚወጥረው ይመለከታል። የተዋጣለት ቀስተኛ ለመሆን ከፍተኛ ጉጉት ያለው ይህ ተማሪ፣ ጅማቱን ምን ያህል መወጠር እንደሚኖርበት እንዲሁም የነፋሱን ሁኔታ እንዴት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ቀስ በቀስ እየተማረ ይሄዳል፤ በተጨማሪም በትጋት ልምምድ ማድረጉን መቀጠል ይኖርበታል። የአስተማሪውን ምሳሌ በጥንቃቄ የሚከተል ከሆነ የሚያስፈነጥራቸው ቀስቶች ይበልጥ ወደ ዒላማው እየተጠጉ ይመጣሉ። በተመሳሳይም እኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሰጠንን መመሪያ በተግባር ለማዋልና የእሱን ፍጹም ምሳሌ ለመከተል ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።

3. (ሀ) ኢየሱስ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚያስፈልገው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጉዳዮች እንመረምራለን?

3 ነቅቶ ስለመጠበቅስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ በእርግጥ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልገው ነበር? አዎ፣ ያስፈልገው ነበር። ለምሳሌ ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ ታማኝ ሐዋርያቱን “ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት አሳስቧቸው ነበር። አክሎም “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ሳታሰልሱም ጸልዩ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 26:38, 41) ኢየሱስ ምንጊዜም ነቅቶ ይጠብቅ የነበረ ቢሆንም በተለይ በእነዚያ አስጨናቂ ሰዓታት ነቅቶ መጠበቅና በተቻለ መጠን በሰማይ ከሚገኘው አባቱ ጋር መቀራረብ ፈልጎ ነበር። በተጨማሪም ተከታዮቹ ለዚያን ዕለት ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ጭምር ነቅተው መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። እስቲ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ነቅተን እንድንጠብቅ የሚፈልገው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ከዚያም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመረምራለን።

ኢየሱስ ነቅተን እንድንጠብቅ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

4. ስለወደፊቱ ጊዜ የማናውቀው ነገር መኖሩ ነቅቶ ከመጠበቅ ጋር ምን ዝምድና አለው?

4 ኢየሱስ ምንጊዜም ነቅተን እንድንጠብቅ የሚፈልግበት ምክንያት በአጭሩ፣ የማናውቀውና የምናውቀው ነገር በመኖሩ ነው። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ሲመላለስ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ሙሉ በሙሉ ያውቅ ነበር? “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” በማለት መናገሩ ሁሉንም ነገር እንደማያውቅ በትሕትና አምኖ መቀበሉን ያሳያል። (ማቴ. 24:36) “ወልድ” የተባለው ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ መቼ እንደሚሆን በትክክል አያውቅም ነበር። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ስለምንገኘው ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል? ስለወደፊቱ ጊዜ ሁሉንም ነገር እናውቃለን? እንደማናውቅ የተረጋገጠ ነው! ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት ልጁን የሚልከው መቼ እንደሆነ በትክክል አናውቅም። ይህን የምናውቅ ቢሆን ኖሮ ነቅቶ መጠበቅ ባላስፈለገን ነበር። ኢየሱስ እንደተናገረው መጨረሻው የሚመጣው ድንገትና ባልታሰበ ሰዓት በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ነቅተን መጠበቅ ያስፈልገናል።​—ማቴዎስ 24:43ን አንብብ።

5, 6. (ሀ) ስለወደፊቱ ጊዜም ሆነ ስለ አምላክ ዓላማዎች ያለን እውቀት በምን ረገድ ነቅተን እንድንጠብቅ ያደርገናል? (ለ) ሰይጣንን በተመለከተ ያለን እውቀት ይበልጥ ንቁዎች ለመሆን ያደረግነውን ውሳኔ የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?

5 በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ስለወደፊቱ ጊዜ የሚያውቃቸው ብዙ አስደናቂ ነገሮች ነበሩ፤ በዙሪያው ያሉት ሰዎች ግን ስለ እነዚህ እውነቶች ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። እርግጥ ነው፣ በእውቀት ከኢየሱስ ጋር አንወዳደርም፤ ደስ የሚለው ግን ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥትም ሆነ መንግሥቱ በቅርቡ ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ብዙ እንድናውቅ አድርጎናል። በዙሪያችን ማለትም በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በአገልግሎት ክልላችንና በሌሎች ቦታዎች የምናገኛቸው አብዛኞቹ ሰዎች ስለ እነዚህ አስደናቂ እውነቶች ምንም ግንዛቤ እንደሌላቸውና በመንፈሳዊ ሁኔታ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚገኙ ሳናስተውል አልቀረንም። በመሆኑም ነቅተን የምንጠብቅበት ሌላው ምክንያት ይህ ነው። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች ለመናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ምንጊዜም በንቃት መከታተል ይኖርብናል። እያንዳንዱን አጋጣሚ እንደ ውድ ነገር አድርገን ልንመለከተው ይገባል፤ እንግዲያው ምንም አጋጣሚ እንዲያመልጠን ማድረግ የለብንም። ምክንያቱም የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ነው!​—1 ጢሞ. 4:16

6 ኢየሱስ ምንጊዜም ነቅቶ የሚጠብቀው፣ ሌላም የሚያውቀው ነገር ስለነበረ ነው። ሰይጣን በእሱ ላይ ፈተናና ስደት ለማምጣት እንዲሁም ንጹሕ አቋሙን እንዲያላላ ለማድረግ ቆርጦ መነሳቱን ያውቅ ነበር። ይህ መሰሪ ጠላት ኢየሱስን ለመፈተን የሚያስችል “ሌላ አመቺ ጊዜ” ለማግኘት ምንጊዜም ነቅቶ ይጠባበቅ ነበር። (ሉቃስ 4:13) በመሆኑም ኢየሱስ አንድም ቀን ተዘናግቶ አያውቅም። ተቃውሞን፣ ስደትንና ማባበያን ጨምሮ ከፊቱ ለሚጠብቀው ማንኛውም ፈተና አስቀድሞ መዘጋጀት ፈልጎ ነበር። እኛስ ያለንበት ሁኔታ ተመሳሳይ አይደለም? ሰይጣን ዛሬም ድረስ፣ “የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ” በመንጎራደድ ላይ መሆኑን እናውቃለን። የአምላክ ቃል “የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፤ ንቁዎች ሆናችሁ ኑሩ” በማለት ክርስቲያኖችን የሚያሳስባቸው በዚህ ምክንያት ነው። (1 ጴጥ. 5:8) ታዲያ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በጸሎት ረገድ ነቅተን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

7, 8. ኢየሱስ ጸሎትን አስመልክቶ ምን ምክር ሰጥቷል? በዚህ ረገድስ ምን ምሳሌ ትቷል?

7 መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈሳዊ ንቁ መሆንና ጸሎት በጥብቅ የተቆራኙ ነገሮች መሆናቸውን ይገልጻል። (ቆላ. 4:2፤ 1 ጴጥ. 4:7) ኢየሱስ ተከታዮቹን ከእሱ ጋር ነቅተው እንዲጠብቁ ከነገራቸው በኋላ ብዙም ሳይቆይ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ሳታሰልሱም ጸልዩ” አላቸው። (ማቴ. 26:41) ይህን ምክር እንዲሠሩበት የፈለገው በዚያ ዕለት ለሚገጥማቸው መከራ ብቻ ነበር? በፍጹም፣ ይህ ማናችንም ብንሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ምንጊዜም ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባ ምክር ነው።

8 ኢየሱስ በጸሎት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ወደ አባቱ ሲጸልይ እንዳደረ እናስታውስ ይሆናል። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችን ለመመልከት እንሞክር። (ሉቃስ 6:12, 13ን አንብብ።) ጊዜው የጸደይ ወቅት ሲሆን ኢየሱስ የሚገኘው በዓሣ ምርቷ በምትታወቀውና በገሊላ አውራጃ ካሉት ከተሞች በአብዛኛው ለማረፊያነት በሚመርጣት በቅፍርናሆም ከተማ አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም። ምሽት ላይ ኢየሱስ በዚያ አካባቢ ከሚገኙትና የገሊላን ባሕር ቁልቁል ለመመልከት ከሚያስችሉት ተራሮች ወደ አንዱ ወጣ። ከዚያ ሆኖ ጨለማ የዋጠውን አካባቢ ሲቃኝ በቅፍርናሆምም ሆነ በአቅራቢያዋ ባሉ መንደሮች በሚገኙ ቤቶች ውስጥ የሚታዩትን ጭል ጭል የሚሉ የኩራዝ መብራቶች በርቀት ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ይሖዋን ማናገር ሲጀምር ግን ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በጸሎቱ ላይ አደረገ። በዚህ ሁኔታ ደቂቃዎች አለፉ፣ ብሎም ሰዓታት ተቆጠሩ። ጭል ጭል ሲሉ የነበሩት መብራቶች አንድ በአንድ መጥፋት ጀምረዋል፤ ጨረቃዋም ጨለማ በዋጠው ሰማይ ላይ ማዝገሟን ቀጥላለች፤ በሌላ በኩል የሌሊት አራዊቶች ምግባቸውን ፍለጋ በየቁጥቋጦው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ይሰማል፤ ሆኖም ይህ ሁሉ ኢየሱስን የረበሸው አይመስልም። ይጸልይ የነበረው ከፊቱ የተደቀነውን ከባድ ውሳኔ ይኸውም 12ቱን ሐዋርያት የመምረጡን ጉዳይ አስመልክቶ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ስለ እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር እያነሳ በአእምሮው የሚመላለሱ ነገሮችን አንድም ሳያስቀር ለአባቱ ሲነግረው በዓይነ ሕሊናችን ሊታየን ይችላል።

9. ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ስለማደሩ ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

9 ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ልክ እንደ ኢየሱስ ለረጅም ሰዓታት መጸለይ አለብን ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ “መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” በማለት መናገሩ የአቅም ገደብ እንዳለብን መገንዘቡን ይጠቁማል። (ማቴ. 26:41) ያም ቢሆን የኢየሱስን አርዓያ መከተል እንችላለን። ለምሳሌ የእኛንም ሆነ የቤተሰባችንን አሊያም የእምነት ባልንጀሮቻችንን መንፈሳዊነት ሊነካ የሚችል ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት የሰማዩን አባታችንን እናማክራለን? በጸሎታችን ላይ ስለ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንጠቅሳለን? አንድ ዓይነት አባባሎችን በዘልማድ ከመደጋገም ይልቅ የልባችንን አውጥተን ለይሖዋ እንጸልያለን? ኢየሱስ ለብቻው በመሆን የልቡን አውጥቶ ለአባቱ የሚናገርበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቅ እንደነበረም ልብ በሉ። ይህ ዓለም ውጥረት የበዛበት ከመሆኑ አንጻር ሳይታወቀን በአንዳንድ ጉዳዮች ልንጠመድና ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ልንዘነጋ እንችላለን። ለብቻችን ሆነን ከልባችን ረዘም ያለ ጸሎት ለማቅረብ በቂ ጊዜ የምንመድብ ከሆነ በመንፈሳዊ ይበልጥ ንቁ እንሆናለን። (ማቴ. 6:6, 7) በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ልባዊ ፍላጎት ካለን ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን፤ እንዲሁም ይህን ዝምድና የሚያበላሽ ምንም ነገር ላለማድረግ እንጠነቀቃለን።​—መዝ. 25:14

ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ነቅተን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

10. ኢየሱስ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ምንጊዜም በንቃት ይከታተል እንደነበር የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?

10 ኢየሱስ ይሖዋ የሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት ንቁ ነበር። አንዳንድ ሥራዎችን ሙሉ ትኩረት ሳንሰጥ ብናከናውናቸው ያን ያህል የከፋ ጉዳት አይደርስብን ይሆናል። ይሁንና አብዛኞቹ ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረትና ንቃት የሚጠይቁ ናቸው፤ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት አገልግሎት ደግሞ ከዚህ የሚመደብ ነው። ኢየሱስ ሥራውን በመወጣት ረገድ ምንጊዜም ንቁ ነበር፤ ምሥራቹን ለሰዎች ለማዳረስ አጋጣሚዎችን በንቃት ይከታተል ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ማለዳ ተነስተው ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ ቀትር ላይ ሲካር የተባለች ከተማ ደረሱ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ሄዱ። ኢየሱስ ግን በከተማዋ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ አለ፤ ይሁን እንጂ ንቁ ስለነበር ለመመሥከር የሚያስችለውን አጋጣሚ አገኘ። አንዲት ሳምራዊት ሴት ውኃ ልትቀዳ ወደ ጉድጓዱ መጣች። በዚህ ወቅት ኢየሱስ ትንሽ ቢያሸልብ ይመርጥ ነበር። ወይም ደግሞ ሴትየዋን ላለማናገር ሌሎች ምክንያቶችን ማቅረብ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ከሴትየዋ ጋር ውይይት የጀመረ ሲሆን የሰጠው ምሥክርነትም በከተማ ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች እውነትን እንዲሰሙ መንገድ ከፍቷል። (ዮሐ. 4:4-26, 39-42) እኛስ ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ ከበፊቱ ይበልጥ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን? ምናልባትም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለምናገኛቸው ሰዎች ምሥራቹን ለማካፈል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በንቃት መከታተል እንችል ይሆን?

11, 12. (ሀ) ኢየሱስ፣ ሰዎች ከሥራው ሊያዘናጉት በሞከሩ ጊዜ ምን አደረገ? (ለ) ኢየሱስ ከተሰጠው ተልእኮ ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

11 አንዳንድ ሰዎች ሆን ብለው ባይሆንም ኢየሱስን ከሥራው ሊያዘናጉት የሚችሉ ነገሮችን አድርገው ነበር። የቅፍርናሆም ሰዎች ኢየሱስ በፈጸማቸው ተአምራት በጣም ስለተደነቁ ከእነሱ ጋር እንዲቆይ ለማድረግ ሞክረው ነበር። በእርግጥ እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስገርም አይደለም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተላከው ለአንድ ከተማ ብቻ ሳይሆን “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ሁሉ እንዲሰብክ ነው። (ማቴ. 15:24) በመሆኑም ኢየሱስ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” በማለት ለእነዚህ ሰዎች ነገራቸው። (ሉቃስ 4:40-44) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ያተኮረው በአገልግሎቱ ላይ ነበር። ይህን ሥራውን ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልበት አልፈቀደም።

12 ኢየሱስ በሥራው ላይ በጣም ከማተኮሩ የተነሳ ራሱን በመጨቆን የብሕትውና ሕይወት መርቷል? ለየትኛውም ዓይነት ማኅበራዊ ሕይወት ጊዜ እስኪያጣ ድረስ በአገልግሎቱ በጣም ተጠምዶ ነበር? በጭራሽ፣ ኢየሱስ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። ራሱን ዘና የሚያደርግበትና ከወዳጆቹ ጋር ጥሩ ጊዜ የሚያሳልፍበት ወቅት ነበር። ለሰዎች ርኅራኄ ያሳይ የነበረ ከመሆኑ በላይ ለሚያስፈልጓቸው ነገሮችም ሆነ ለችግሮቻቸው ትኩረት ይሰጥ ነበር። እንዲሁም ለልጆች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል።​—ማርቆስ 10:13-16ን አንብብ።

13. ኢየሱስ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ንቁና ሚዛኑን የሚጠብቅ እንደነበር ሁሉ እኛም የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13 እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ ሚዛናዊ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ዓለም፣ ይሖዋ ከሰጠን ሥራ እንዲያዘናጋን አንፈቅድም። አንዳንድ ሰዎች ለእኛ በማሰብ አገልግሎታችንን ቀነስ እንድናደርግ ወይም ሕይወታችንን እንደሌላው ሰው እንድንመራ ይጎተጉቱን ይሆናል። ይሁን እንጂ የኢየሱስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ አገልግሎታችንን እንደ ምግብ እንቆጥረዋለን። (ዮሐ. 4:34) ይህን ሥራ መሥራታችን መንፈሳዊ ጤንነታችን እንዲጠበቅ ብሎም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። በሌላ በኩል ደግሞ ጽንፈኛ፣ ተመጻዳቂ ወይም ራሳችንን የምንጨቁን ሰዎች መሆን አንፈልግም። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ‘ደስተኛ የሆነውን አምላክ’ ሚዛናችንን ጠብቀን በደስታ ማገልገል እንፈልጋለን።​—1 ጢሞ. 1:11

ፈተና ሲያጋጥመን ነቅተን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

14. በመከራ ወቅት የትኛው ዝንባሌ እንዳያሸንፈን መዋጋት ይኖርብናል? ለምንስ?

14 እስካሁን እንደተመለከትነው ኢየሱስ ነቅቶ ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ማሳሰቢያዎችን ሰጥቷል፤ ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ አጣዳፊ መሆኑን አበክሮ የተናገረው ከባድ ፈተና ውስጥ በነበረበት ወቅት ነው። (ማርቆስ 14:37ን አንብብ።) በሕይወታችን ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የእሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። ብዙዎች ፈተና ሲያጋጥማቸው በምሳሌ መጽሐፍ ላይ ከአንዴም ሁለቴ የተጠቀሰውን በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ሐቅ ይዘነጋሉ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል።” (ምሳሌ 14:12፤ 16:25) በተለይ ከባድ ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ በራሳችን ማስተዋል የምንደገፍ ከሆነ ራሳችንንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን።

15. የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ከባድ ትግል የሚያደርግ አንድ የቤተሰብ ራስ ምን ዓይነት ፈተና ሊያጋጥመው ይችላል?

15 ለምሳሌ አንድ የቤተሰብ ራስ “የራሱ ለሆኑት” ማለትም ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገሮች ከማቅረብ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሊገባ ይችላል። (1 ጢሞ. 5:8) ምናልባትም በተደጋጋሚ ጊዜያት ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዲቀር፣ የቤተሰብ አምልኮ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዳይወጣ ወይም በአገልግሎት እንዳይካፈል ሊያግደው የሚችል ሥራ ለመያዝ ይፈተን ይሆናል። ይህ ሰው የሚታመነው በሰብዓዊ አመለካከት ብቻ ከሆነ ሥራውን መያዙ ምክንያታዊ እንዲያውም ትክክል እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ይሁንና ግለሰቡ የኋላ ኋላ በመንፈሳዊ ሁኔታ ለሕመምና ለሞት ሊዳረግ ይችላል። በ⁠ምሳሌ 3:5, 6 ላይ የሚገኘውን ምክር መከተል ምንኛ ጥበብ ነው! ሰለሞን እንዲህ ብሏል፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”

16. (ሀ) ኢየሱስ በራሱ ማስተዋል ከመደገፍ ይልቅ በይሖዋ ጥበብ እንደሚታመን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በአስቸጋሪ ጊዜያት በይሖዋ በመታመን ረገድ በርካታ የቤተሰብ ራሶች የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተሉ ያሉት እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ ፈተና ሲያጋጥመው በፍጹም በራሱ ማስተዋል አልተደገፈም። እስቲ አስቡት! በዚህች ምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው ሰው ጥያቄ ሲቀርብለት በራሱ ጥበብ ተመርኩዞ መልስ ለመስጠት አልፈለገም። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ ለሰይጣን ፈተና መልስ ሲሰጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት “ተብሎ ተጽፏል” የሚል አባባል ተጠቅሟል። (ማቴ. 4:4, 7, 10) ኢየሱስ ፈተናዎችን ለመቋቋም ይታመን የነበረው ከአባቱ በሚያገኘው ጥበብ ነው፤ በዚህ መንገድ ሰይጣን ጨርሶ የሌለውንና የማይወደውን የትሕትና ባሕርይ አንጸባርቋል። እኛስ እንዲህ እናደርጋለን? አንድ የቤተሰብ ራስ ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተል ከሆነ በተለይ ፈተና ውስጥ በሚገባበት ወቅት በአምላክ ቃል ይመራል። በዓለም ዙሪያ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤተሰብ ራሶች ይህን እያደረጉ ነው። ምንጊዜም የአምላክን መንግሥትና ንጹሑን አምልኮ ከቁሳዊ ፍላጎቶቻቸውም በላይ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። በዚህ መንገድ ለቤተሰቦቻቸው ከልብ እንደሚያስቡ ያሳያሉ። ይሖዋም፣ በገባው ቃል መሠረት የቤተሰባቸውን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያደርጉትን ጥረት ይባርክላቸዋል።​—ማቴ. 6:33

17. ነቅቶ ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንድትከተል የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

17 ኢየሱስ ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ እንደተወልን ምንም ጥያቄ የለውም። እሱ የተወው ምሳሌ ጠቃሚና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ከመሆኑም በላይ ሕይወት አድን ነው። ሰይጣን መንፈሳዊ ድብታ እንዲይዝህ፣ እምነትህ እንዲዳከም፣ አምልኮትህን በቅንዓት እንዳታካሂድና ንጹሕ አቋምህን እንድታላላ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ አስታውስ። (1 ተሰ. 5:6) ሰይጣን እንዲሳካለት አትፍቀድ! ልክ እንደ ኢየሱስ በጸሎትና በአገልግሎት ረገድ እንዲሁም ፈተናዎች ሲያጋጥሙህ ምንጊዜም ነቅተህ ጠብቅ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ሊጠፋ በተቃረበው በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንኳ ደስተኛና የተትረፈረፈ በረከት የሞላበት አርኪ ሕይወት ልትመራ ትችላለህ። በተጨማሪም ነቅተህ የምትጠብቅ ከሆነ ጌታህ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት በሚመጣበት ጊዜ ንቁ ሆነህ የአባቱን ፈቃድ እያደረክ እንድትገኝ ይረዳሃል። ይሖዋም ቢሆን ለተከተልከው የታማኝነት ጎዳና ወሮታ መክፈል መቻሉ በጣም ያስደስተዋል!​—ራእይ 16:15

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት አንዲት ሴት መሥክሯል። አንተስ በየዕለቱ ለሰዎች ለመስበክ የትኞቹን አጋጣሚዎች ትጠቀማለህ?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብህን መንፈሳዊ ፍላጎት የምታሟላ መሆንህ ነቅተህ እንደምትጠብቅ ያሳያል