በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ደስታን ጠብቆ መኖር ይቻላል

በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ደስታን ጠብቆ መኖር ይቻላል

በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ደስታን ጠብቆ መኖር ይቻላል

“አንቺ ሚስት፣ ባልሽን ታድኚው እንደሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ባል፣ ሚስትህን ታድን እንደሆነ ምን ታውቃለህ?”​—1 ቆሮ. 7:16

መልሶቹን ማግኘት ትችላለህ?

በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖር ክርስቲያን ሰላምን ለማስፈን ምን ማድረግ ይችላል?

አንድ ክርስቲያን የማያምነው የቤተሰቡ አባል እውነትን እንዲቀበል እንዴት ሊረዳው ይችላል?

በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ያለን የእምነት ባልንጀራቸውን ለመርዳት ሌሎች የጉባኤው አባላት ምን ማድረግ ይችላሉ?

1. አንድ ሰው የመንግሥቱን መልእክት መቀበሉ የቤተሰቡን ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው?

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ሐዋርያቱን ለአገልግሎት ሲልካቸው “‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴ. 10:1, 7) ሰዎች ይህን ምሥራች ከልብ በመነጨ አድናቆት ከተቀበሉ ሕይወታቸው ሰላምና ደስታ የሰፈነበት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ብዙዎች የመንግሥቱን ስብከት ሥራ እንደሚቃወሙ ለሐዋርያቱ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ማቴ. 10:16-23) በተለይ ደግሞ ከቤተሰብ አባላት መካከል የመንግሥቱን መልእክት የማይቀበል በሚኖርበት ጊዜ ሁኔታው ይበልጥ ከባድ ይሆናል።​—ማቴዎስ 10:34-36ን አንብብ።

2. በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ደስታ ማግኘት የሕልም እንጀራ አይሆንባቸውም የምንለው ለምንድን ነው?

2 ታዲያ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ደስታ ማግኘት የሕልም እንጀራ ይሆንባቸዋል ማለት ነው? በፍጹም! አንዳንድ ጊዜ በቤት ውስጥ የሚነሳው ተቃውሞ ከባድ ሊሆን ቢችልም ሁልጊዜ ግን እንደዚያ ይሆናል ማለት አይደለም። ደግሞም ተቃውሞው ዕድሜ ልክ ላይቀጥል ይችላል። ይህ በአብዛኛው የተመካው የቤተሰቡ አባላት ተቃዋሚ ወይም ግድ የለሽ በሚሆኑበት ወቅት አማኙ ጉዳዩን በሚይዝበት መንገድ ላይ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ አገልጋዮቹ ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ያሉበት ሁኔታ ጥሩ ባይሆንም ደስታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ በመርዳት ይባርካቸዋል። አማኝ የሆነው ወገን ይበልጥ ደስተኛ መሆን ከፈለገ (1) በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና መጫወት እንዲሁም (2) የማያምነው የቤተሰብ አባል እውነተኛውን አምልኮ እንዲቀበል ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።

በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ

3. በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖር አንድ ክርስቲያን በቤቱ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ የሚኖርበት ለምንድን ነው?

3 የጽድቅ ዘር በቤተሰብ አባላት ልብ ውስጥ ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ በቤት ውስጥ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲሰፍን ማድረግ ወሳኝ ነው። (ያዕቆብ 3:18ን አንብብ።) አንድ ክርስቲያን ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ከእሱ ጋር በአምልኮ አንድ ባይሆኑም በቤቱ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

4. ክርስቲያኖች ውስጣዊ ሰላማቸውን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

4 ክርስቲያኖች ውስጣዊ ሰላማቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይጠይቃል፤ እንዲህ ማድረጋቸው ተወዳዳሪ የሌለውን “የአምላክ ሰላም” ያስገኝላቸዋል። (ፊልጵ. 4:6, 7) በተጨማሪም ስለ ይሖዋ እውቀት በመቅሰምና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር በማዋል ደስታና ሰላም ማግኘት ይቻላል። (ኢሳ. 54:13) ከዚህም ባሻገር ሰላምና ደስታ ማግኘት ከፈለግን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ቀናተኛ መሆን ይኖርብናል። በአብዛኛው ማለት ይቻላል በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥም ሆኖ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ይቻላል። ባለቤቷ ከባድ ተቃውሞ የሚያደርስባት ኤንዛ * የተባለችን እህት እንደ ምሳሌ እንመልከት። የቤት ውስጥ ሥራዋን ከጨራረሰች በኋላ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ትካፈላለች። ኤንዛ እንዲህ ብላለች፦ “ምሥራቹን ለሌሎች ለመስበክ ጥረት በማደርግበት ጊዜ ሁሉ ጥሩ ውጤት ስለማገኝ ይሖዋ አብዝቶ እንደባረከኝ ይሰማኛል።” ይህም ለኤንዛ ሰላም፣ ደስታና እርካታ እንዳስገኘላት ምንም ጥርጥር የለውም።

5. በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ ምን ፈታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል? ምን እርዳታስ አለላቸው?

5 ከማያምኑ የቤተሰብ አባላት ጋር በሰላም ለመኖር ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጩ ነገሮችን እንድናደርግ ስለሚፈልጉ ከእነሱ ጋር በሰላም መኖር ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ትክክል ለሆነ ነገር ጥብቅ አቋም መያዛችን አንዳንድ የማያምኑ የቤተሰብ አባላትን ያበሳጫቸው ይሆናል፤ ይሁንና በአቋማችን መጽናታችን በቤት ውስጥ የኋላ ኋላ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጩ ነገሮችን ለማድረግ ፈቃደኞች መሆናችን አላስፈላጊ ከሆነ ግጭት ሊጠብቀን ይችላል። (ምሳሌ 16:7ን አንብብ።) አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ታማኝና ልባም ከሚያዘጋጃቸው ጽሑፎችና ከሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው።​—ምሳሌ 11:14

6, 7. (ሀ) አንዳንዶች፣ የቤተሰብ አባላቸው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ሲጀምር የሚቃወሙት ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ጥናት ወይም አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቡ ተቃውሞ ሲያደርስበት ምን ምላሽ መስጠት ይኖርበታል?

6 በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ በይሖዋ መታመንና የማያምኑትን የቤተሰብ አባላት ስሜት መረዳት ይጠይቃል። (ምሳሌ 16:20) አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንኳ በዚህ ረገድ አስተዋዮች መሆናቸውን ማሳየት ይችላሉ። አንዳንድ የማያምኑ ባሎች ወይም ሚስቶች የትዳር ጓደኞቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውን አይቃወሙ ይሆናል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ ለቤተሰቡ ጥሩ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎች ግን የትዳር ጓደኛቸው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቱ ጥላቻቸውን ይገልጹ ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ኤስተር፣ ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር በጣም እንደተበሳጨች ተናግራለች። “ጽሑፎቹን አውጥቼ እጥላቸው አለዚያም አቃጥላቸው ነበር” ብላለች። መጀመሪያ ላይ ባለቤቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷን ይቃወም የነበረው ሃዋርድ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ባሎች፣ ሚስቶቻቸው አንድ የሃይማኖት ቡድን ውስጥ የሚገቡት ተታለው ሊሆን ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው። በመሆኑም አንድ ባል የተፈጠረበትን ስጋት ለማስወገድ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ስለሚገባው ተቃዋሚ ሊሆን ይችላል።”

7 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የትዳር ጓደኛው ብትቃወመውም ጥናቱን መቀጠሉ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘብ መርዳት ይገባል። ብዙውን ጊዜ ለማያምነው የትዳር ጓደኛ የገርነት መንፈስና ጥልቅ አክብሮት በማሳየት ችግሮችን መፍታት ይቻላል። (1 ጴጥ. 3:15) “ባለቤቴ ስሜታዊ ሳትሆን ነገሮችን በሰከነ መንገድ ለመያዝ በመሞከሯ በጣም አመሰግናታለሁ!” በማለት ሃዋርድ ተናግሯል። ሚስቱ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ሃዋርድ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን እንዳቆም ይጫነኝ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አእምሮዬን እንዳጠቡት ተሰምቶት ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ከመከራከር ይልቅ እሱ ልክ ሊሆን እንደሚችል፣ እኔ ግን እንደዚያ ብሎ የተናገረበት ምክንያት እንዳልታየኝ ገለጽኩለት። ከፈለገ የማጠናውን መጽሐፍ ማንበብ እንደሚችል ነገርኩት። ሃዋርድ መጽሐፉን ቢያነበውም ምንም የሚያስተባብለው ነገር ማግኘት አልቻለም። ይህም ልቡን በጥልቅ ነካው።” አማኝ ያልሆኑ ሰዎች፣ የትዳር ጓደኞቻቸው በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ከቤት ሲወጡ እንደተተዉ ሊሰማቸው ወይም ስጋት ሊያድርባቸው እንደሚችል ማስታወሳችን ተገቢ ነው።

እውነተኛውን አምልኮ እንዲከተሉ እርዷቸው

8. ሐዋርያው ጳውሎስ የማያምን የትዳር ጓደኛ ላላቸው ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷል?

8 ክርስቲያኖች፣ የትዳር ጓደኞቻቸው አማኝ ስላልሆኑ ብቻ ከእነሱ ጋር ተለያይተው መኖር እንደሌለባቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ሰጥቷል። * (1 ቆሮንቶስ 7:12-16ን አንብብ።) የማያምነው የትዳር ጓደኛቸው ክርስቲያን ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ ምንጊዜም ማስታወሳቸው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥም እንኳ ደስታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ይረዳቸዋል። ከታች ያሉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የማያምነው የትዳር ጓደኛ እውነትን እንዲቀበል ለማድረግ በሚጥሩበት ጊዜ አንዳንድ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይኖርባቸዋል።

9. አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማያምኑ የቤተሰቡ አባላት ሲናገር ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል?

9 ጄሰን ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በተማረበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “ያወቅኩትን ነገር በሙሉ ለሌሎች መናገር እንዳለብኝ ተሰምቶኝ ነበር” ብሏል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተማረው ነገር እውነት መሆኑን ሲረዳ በጣም ከመደሰቱ የተነሳ ነጋ ጠባ ስለዚህ ጉዳይ ብቻ ማውራት ይፈልግ ይሆናል። ምናልባትም የማያምኑት የቤተሰቡ አባላት የመንግሥቱን መልእክት ወዲያውኑ ይቀበላሉ ብሎ መጠበቁ ምንም አያስገርምም፤ ሆኖም ምላሹ የተገላቢጦሽ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ጄሰን መጀመሪያ ላይ በስሜት ተነሳስቶ መናገሩ በሚስቱ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ? ባለቤቱ ሁኔታውን አስታውሳ ስትናገር “ሁሉንም ነገር በአንዴ እንዳዥጎደጎደብኝ ተሰማኝ” ብላለች። ባለቤቷ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ ከ18 ዓመታት በኋላ እውነትን የተቀበለች አንዲት እህት “እኔ መማር ያለብኝ ቀስ በቀስ ነበር” በማለት ተናግራለች። ለእውነት ፍላጎት የሌላት የትዳር ጓደኛ ያለችው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካለህ ባለቤቱን እንዴት አድርጎ በዘዴ ማስረዳት እንደሚችል ለማሠልጠን ቋሚ የሆነ የልምምድ ጊዜ ለምን አትመድብም? ሙሴ “ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትውረድ፤ ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤ በቡቃያ ሣር ላይ እንደ ካፊያ . . . ይውረድ” በማለት ተናግሯል። (ዘዳ. 32:2) መንፈሳዊ እውነትን እንደ ዶፍ ከማውረድ ይልቅ እንደ ካፊያ እያረሰረሰ እንዲገባ ማድረግ በአብዛኛው የተሻለ ውጤት ያስገኛል።

10-12. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ የማያምን የትዳር ጓደኛ ላላቸው ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በ⁠1 ጴጥሮስ 3:1, 2 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ልታደርግ የቻለችው እንዴት ነው?

10 ሐዋርያው ጴጥሮስ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ክርስቲያን ሚስቶች በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት በዓይናቸው ሲመለከቱ ነው።” (1 ጴጥ. 3:1, 2) አንዲት ሚስት ባለቤቷ በጥሩ መንገድ ባይዛትም እንኳ ለእሱ በመገዛትና ጥልቅ አክብሮት በማሳየት በእውነተኛው አምልኮ እንዲማረክ ማድረግ ትችላለች። በተመሳሳይም አማኝ የሆነ አንድ ባል፣ ሚስቱ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ብታደርስበትም አምላካዊ ምግባር ማሳየትና ቤተሰቡን በፍቅር ማስተዳደር ይኖርበታል።​—1 ጴጥ. 3:7-9

11 ጴጥሮስ የሰጠው ምክር ዛሬም በጣም ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። እስቲ ሰልማ ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስትጀምር ባለቤቷ ስቲቭ አልተደሰተም ነበር። “እበሳጭ፣ እቀና እንዲሁም ስጋት ያድርብኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ትኩረት እንደተነፈገኝ ይሰማኝ ነበር” በማለት ስቲቭ ተናግሯል። ሰልማ እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን ከመስማቴ በፊትም ቢሆን ከስቲቭ ጋር የምኖረው በጣም በጥንቃቄ ነበር። ምክንያቱም በቀላሉ የሚበሳጭ ሰው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ደግሞ ይህ ባሕርይው ባሰበት።” ታዲያ ሁኔታውን ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው?

12 ሰልማ አስጠኚዋ ያስተማረቻትን ነገር አትረሳውም። “አንድ ቀን በቀጠሯችን ስንገናኝ የዚያን ዕለት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደማልፈልግ ነገርኳት። ከዚያን ቀን በፊት በነበረው ምሽት ላይ በአንድ ጉዳይ ከስቲቭ ጋር በምንከራከርበት ጊዜ ላስረዳው ስሞክር መትቶኝ ነበር፤ በመሆኑም በጣም አዝኜና ከፍቶኝ ነበር። በወቅቱ ስለተከሰተው ነገርና እኔም ምን እንደተሰማኝ ለእህት ሳጫውታት 1 ቆሮንቶስ 13:4-7⁠ን እንዳነብ ነገረችኝ። ጥቅሱን በማነብበት ጊዜ ‘ስቲቭ እኮ እነዚህን የፍቅር መግለጫዎች ጨርሶ አሳይቶኝ አያውቅም’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። እህት ‘ከእነዚህ የፍቅር መግለጫዎች መካከል ምን ያህሉን ለባለቤትሽ አሳይተሻል?’ በማለት ያቀረበችልኝ ጥያቄ ሁኔታውን በተለየ መልኩ እንዳስብ አደረገኝ። ከዚያም ‘የትኛውንም አላሳየሁም፤ ምክንያቱም ከእሱ ጋር መኖር በጣም ከባድ ነው’ በማለት መለስኩላት። እህትም ረጋ ብላ ‘ሰልማ፣ ክርስቲያን ለመሆን እየጣረ ያለው ማነው? አንቺ ነሽ ወይስ ስቲቭ?’ አለችኝ። አስተሳሰቤን ማስተካከል እንዳለብኝ ስለተገነዘብኩ ለስቲቭ የበለጠ ፍቅር ማሳየት እንድችል እንዲረዳኝ ይሖዋን በጸሎት ጠየቅኩት። ቀስ በቀስ ነገሮች እየተሻሻሉ ሄዱ።” ከ17 ዓመታት በኋላ ስቲቭ እውነትን ተቀበለ።

ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

13, 14. ሌሎች የጉባኤው አባላት በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ቀስ ብሎ የሚወርድ እያንዳንዱ የዝናብ ጠብታ መሬትን በማረስረስ አትክልቶችን እንደሚያሳድግ ሁሉ በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ክርስቲያንም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ደስተኞች እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል። በብራዚል የምትኖረው ኤልቪና የተባለች አንዲት ክርስቲያን “በእውነት ውስጥ ጸንቼ እንድቆም የረዳኝ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ያሳዩኝ ፍቅር ነው” ብላለች።

14 የጉባኤው አባላት ደግነትና አሳቢነት ማሳየታቸው የማያምነው የቤተሰብ አባል ልቡ እንዲነካ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ባለቤቱ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች ከ13 ዓመት በኋላ እውነትን የተቀበለ በናይጄሪያ የሚኖር ወንድም በአንድ ወቅት የሆነውን ነገር እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “ከአንድ ወንድም ጋር እየተጓዝኩ ሳለ መንገድ ላይ መኪናው ተበላሸ። ወዲያው ወንድም በመንደሩ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጎ አገኛቸው፤ እነሱም ማደሪያ ሰጡን። ያሳዩን አሳቢነት ለረጅም ጊዜ የማውቃቸው ሆኖ እንዲሰማኝ አደረገኝ። በዚያን ወቅት፣ ባለቤቴ ሁልጊዜ ትነግረኝ የነበረውን ክርስቲያናዊ ፍቅር በገዛ ዓይኔ መመልከት ቻልኩ።” ባለቤቷ እውነትን ካወቀ ከ18 ዓመት በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነች በእንግሊዝ የምትኖር አንዲት እህት ያለፈውን አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ባለቤቴን ምግብ ሲጋብዙት እኔንም ይጠሩኝ ነበር። ከእነሱ ጋር ስሆን እንግድነት አይሰማኝም ነበር።” * በዚያው አገር የሚኖርና ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞችና እህቶች ሊጠይቁን የሚመጡበት አሊያም ቤታቸው የሚጋብዙን ጊዜ ነበር፤ በዚህ ወቅት ምን ያህል አሳቢ እንደሆኑ ማስተዋል ችያለሁ። በተለይ ታምሜ ሆስፒታል በተኛሁበት ወቅት ይህን በግልጽ ተረድቻለሁ፤ ብዙዎች መጥተው ጠይቀውኛል።” አንተስ አማኝ ላልሆነ የቤተሰብ አባል ተመሳሳይ አሳቢነት ማሳየት የምትችልባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን?

15, 16. አንድ ክርስቲያን ከቤተሰቡ አባላት አንዳንዶቹ እውነትን ለመቀበል ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ ደስታውን ጠብቆ ለመቆየት ምን ሊረዳው ይችላል?

15 እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለማያምን የትዳር ጓደኛቸው፣ ለልጆቻቸው፣ ለወላጆቻቸው ወይም ለሌሎች ዘመዶቻቸው ለዓመታት ጥሩ ምግባር ቢያሳዩም እንዲሁም በዘዴ ለመመሥከር ጥረት ቢያደርጉም እንኳ ሁሉም እውነትን ላይቀበሉ ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለእውነት ግድ የለሽ እንደሆኑ ሊቀጥሉ ወይም በተቃውሟቸው ሊገፉበት ይችላሉ። (ማቴ. 10:35-37) ያም ሆኖ ክርስቲያኖች አምላካዊ ባሕርያትን ማሳየታቸው ጥሩ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ባል እንዲህ ብሏል፦ “የሚያምነው የትዳር ጓደኛ እነዚህን ጥሩ ጥሩ ባሕርያት ማንጸባረቅ ሲጀምር በማያምነው የትዳር ጓደኛ አእምሮና ልብ ውስጥ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አታውቁም። ስለዚህ በማያምነው የትዳር ጓደኛችሁ ተስፋ አትቁረጡ።”

16 የማያምነው የቤተሰብ አባል እውነትን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ የሚያምነው ወገን ደስተኛ ሆኖ መቀጠል ይችላል። ባለቤቷ የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበል ለ21 ዓመታት ጥረት ብታደርግም እንኳ ሊሳካላት ያልቻለ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን ለማስደሰት ብሎም ለእሱ ታማኝ ለመሆንና መንፈሳዊነቴን ለማጠናከር ጥረት ማድረጌ ደስታዬን ጠብቄ እንድኖር አስችሎኛል። ራሴን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ማስጠመዴ ይኸውም የግል ጥናት ማድረጌ፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘቴ፣ በመስክ አገልግሎት መካፈሌና የጉባኤውን አባላት ለመርዳት ጥረት ማድረጌ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድቀርብና ልቤን እንድጠብቅ አስችሎኛል።”​—ምሳሌ 4:23

ተስፋ አትቁረጡ!

17, 18. በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖር አንድ ክርስቲያን ተስፋ እንዳይቆርጥ ምን ሊረዳው ይችላል?

17 በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የምትኖር ታማኝ ክርስቲያን ከሆንክ ተስፋ መቁረጥ የለብህም። ይሖዋ ‘ስለ ታላቅ ስሙ ሲል ሕዝቡን እንደማይተው’ አስታውስ። (1 ሳሙ. 12:22) እሱን የሙጥኝ እስካልክ ድረስ ምንጊዜም ከጎንህ ይሆናል። (2 ዜና መዋዕል 15:2ን አንብብ።) እንግዲያው በይሖዋ “ደስ ይበልህ።” እንዲሁም ‘መንገድህን ለአምላክ ዐደራ ስጥ፤ በእርሱም ታመን።’ (መዝ. 37:4, 5) በተጨማሪም ‘በጽናት ጸልይ’፤ በሰማይ ያለው አፍቃሪው አባትህ የሚደርስብህን ማንኛውንም መከራ እንድትቋቋም ሊረዳህ እንደሚችልም እምነት ይኑርህ።​—ሮም 12:12

18 በቤት ውስጥ ሰላም ለማስፈን በምታደርገው ጥረት ይሖዋ መንፈሱን በመስጠት እንዲያግዝህ ለምነው። (ዕብ. 12:14) አዎን በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ይቻላል፤ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ የማያምነው የቤተሰብ አባል ልቡ እንዲነካ ሊያደርግ ይችላል። “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” ብለህ የምታደርግ ከሆነ ውስጣዊ ሰላም ይኖርሃል። (1 ቆሮ. 10:31) በተጨማሪም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችህና እህቶችህ ፍቅራዊ እርዳታ እንደሚያደርጉልህ እርግጠኛ ሁን!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.8 ጳውሎስ የሰጠው ምክር ለየት ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መለያየትን የሚከለክል አይደለም። ይህ ለግለሰቦች የተተወ ከባድ ውሳኔ ነው። ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 220-221 ተመልከት።

^ አን.14 ቅዱሳን መጻሕፍት ከማያምኑ ሰዎች ጋር አብሮ መመገብን አይከለክሉም።​—1 ቆሮ. 10:27

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ ለማስረዳት አመቺ የሆነውን ጊዜ ፈልግ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለማያምን የትዳር ጓደኛ አሳቢነት አሳዩ