በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መናፍስታዊ ድርጊት ስህተት ነው?

መናፍስታዊ ድርጊት ስህተት ነው?

መናፍስታዊ ድርጊት ስህተት ነው?

ባርባራ * ከወጣትነቷ ጀምሮ ራእዮችን ታይ እንዲሁም ድምፆችን ትሰማ የነበረ ሲሆን በዚህ መንገድ ከሞቱ ዘመዶቿ ጋር እንደምትገናኝ ታምን ነበር። እሷና ባሏ ዮአኪም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዙ መጻሕፍትን የሚያነብቡ ከመሆኑም ሌላ የጥንቆላ ካርዶችን (ታሮት ካርድ) በማንበብም የተካኑ ነበሩ። እነዚህ ካርዶች ብዙ ገንዘብ እንደሚያገኙ አሳዩአቸው፤ እንደተባለውም በሥራቸው ብዙ ገንዘብ አተረፉ። አንድ ቀን ካርዶቹ፣ አደገኛ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንደሚመጡ ያስጠነቀቋቸው ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ ነገሯቸው።

በመናፍስታዊ ድርጊቶች ማመን ድሮ የቀረ ነገር ቢመስልም ሳይንሳዊ ማብራሪያ የሌላቸው ነገሮች የሰዎችን ቀልብ መሳባቸው በጣም የተለመደ ነው። በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች ክታቦችን ያደርጋሉ፣ በጥንቆላ ሰሌዳ (ዊጃ ቦርድ) ይጠቀማሉ እንዲሁም ስለ ዕድላቸው እንዲነግሯቸው አሊያም ራሳቸውን ከክፉ ነገር ለመጠበቅ ሲሉ መናፍስት ጠሪዎችን ያማክራሉ። ፎከስ በተሰኘው የጀርመን መጽሔት ላይ የወጣው “ላፕቶፕና ሉሲፈር” (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ “ኢንተርኔት ሰዎች ስለ ጥንቆላ ለማወቅ ያላቸው ጉጉት እንዲጨምር አድርጓል” ብሏል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች እንደሚናገር ታውቃለህ? በዚህ ርዕስ ዙሪያ የያዘውን ሐሳብ ስታውቅ ትገረም ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መናፍስታዊ ድርጊት ምን ይላል?

አምላክ ለጥንት እስራኤላውያን የሰጠው ሕግ እንዲህ ይላል፦ “ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገ[ላ]ጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።” (ዘዳግም 18:10-12) የአምላክ ሕግ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይህን ያህል አጥብቆ የሚያወግዘው ለምንድን ነው?

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ታሪክ እንደሚያመለክተው ብዙ ሰዎች ከሙታን ጋር መነጋገር እንደሚችሉና ሙታን በመናፍስታዊ ድርጊቶች አማካኝነት መረጃዎችን እንደሚያስተላልፉ ያምናሉ። እንዲህ ያለው እምነት የመነጨው ሰዎች ሲሞቱ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተሸጋግረው መኖራቸውን እንደሚቀጥሉ ከሚገልጸው በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኝ ትምህርት ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ትምህርት በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 9:5) መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ያሉ ያህል እንደሆኑና በዙሪያቸው ስለሚከናወነው ነገር አንዳች እንደማያውቁ ይገልጻል። * (ማቴዎስ 9:18, 24፤ ዮሐንስ 11:11-14) ‘ይህ ከሆነ ታዲያ አንዳንድ ሰዎች፣ እንግዳ ከሆኑ አካላት ጋር እንደተነጋገሩ ስለሚገልጹ ዘገባዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የተነጋገሩት ከማን ጋር ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

ከመናፍስት ጋር መነጋገር

የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ከመናፍስት ጋር ስለተነጋገረባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ይገልጻሉ። አንድ “ርኩስ መንፈስ” ኢየሱስን “ማን እንደሆንክ በሚገባ አውቃለሁ” እንዳለው በ⁠ማርቆስ 1:23, 24 ላይ ተዘግቧል። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ስለ አንተም በደንብ እንደሚያውቁ ጥርጥር የለውም። አንተስ ስለ እነሱ ማንነት ታውቃለህ?

አምላክ ሰዎችን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መንፈሳዊ ልጆችን ወይም መላእክትን ፈጥሮ ነበር። (ኢዮብ 38:4-7) እነዚህ መላእክት ከሰዎች የላቁ ፍጥረታት ናቸው። (ዕብራውያን 2:6, 7) ከፍተኛ ኃይልና የማስተዋል ችሎታ ያላቸው ሲሆን የተፈጠሩትም የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ነው። መዝሙራዊው “እናንተ ለቃሉ የምትታዘዙ መላእክቱ፤ ትእዛዙንም የምትፈጽሙ እናንተ ኀያላን፤ እግዚአብሔርን ባርኩ” በማለት ዘምሯል።​—መዝሙር 103:20

ከጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ መላእክት ከአምላክ ፈቃድ ውጪ ከሰዎች ጋር መነጋገር እንደጀመሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? ከሰዎች ጋር በዚህ መንገድ መጀመሪያ የተነጋገረው መንፈሳዊ ፍጡር የማታለያ ዘዴ በመጠቀም አዳምንና ሔዋንን ከአምላካቸውና ከፈጣሪያቸው እንዲርቁ አደረጋቸው። በዚህም ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ ማለትም ስም አጥፊና የአምላክ ተቃዋሚ አደረገ።​—ዘፍጥረት 3:1-6

ውሎ አድሮ ሌሎች መላእክትም በሰማይ የነበረውን “ትክክለኛ መኖሪያቸውን [ትተው]” የሰው አካል በመልበስ በምድር ላይ ከነበሩ ቆንጆ ሴቶች ጋር መኖር ጀመሩ። (ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:1, 2) እነዚያ ዓመፀኛ መላእክትና ከሴቶቹ የወለዷቸው ዲቃላ ልጆች፣ የሰው ዘሮች በሽብርና በፍርሃት እንዲዋጡ ስላደረጉ ምድር ‘በዓመፅ ተሞልታ’ ነበር። አምላክ፣ በኖኅ ዘመን በነበረው ዓመፀኛና ክፉ ትውልድ ላይ የጥፋት ውኃ እንዳመጣ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አንተም ሳታውቀው አትቀርም።​—ዘፍጥረት 6:3, 4, 11-13

የጥፋት ውኃው ሲመጣ እነዚያ መናፍስት ሥጋዊ አካላቸውን ትተው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ ተገደዱ። ይሁን እንጂ ፈጣሪ ወደ ቀድሞ “መኖሪያቸው” እንዲመለሱ አልፈቀደላቸውም። በዚህ ፈንታ ‘በድቅድቅ ጨለማ ከተዋጠ ጉድጓድ’ ጋር በሚመሳሰል የተዋረደ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ አደረገ። (2 ጴጥሮስ 2:4, 5) መጽሐፍ ቅዱስ ዓመፀኞቹን መላእክት “አጋንንት” በማለት ይጠራቸዋል። (ያዕቆብ 2:19) ከመናፍስታዊ ድርጊት በስተጀርባ ያሉት እነዚህ አጋንንት ናቸው።

አጋንንት የሚፈልጉት ምንድን ነው?

ከሰዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚጥሩት ክፉ መናፍስት ተቀዳሚ ዓላማ፣ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንዳያመልኩ ማድረግ ነው። በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚካፈሉ ብዙ ሰዎች፣ ልዩ ስጦታ ወይም ኃይል እንዳላቸው ቢገልጹም እነዚህ ነገሮች የሰው ልጆች ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት እንዳያገኙና ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ ከማዘናጋት ያለፈ ዓላማ የላቸውም።

ሁለተኛውን የአጋንንት ዓላማ ለማወቅ ደግሞ መሪያቸው የሆነው ሰይጣን ከኢየሱስ ጋር ያደረገውን ውይይት እንመልከት። ሰይጣን “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን” እንደሚሰጠው ለኢየሱስ ነግሮት ነበር። ሰይጣን በምላሹ ከኢየሱስ ምን ፈልጎ ነበር? “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” ብሎታል። አዎን፣ ሰይጣንና አጋንንቱ መመለክ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ አምላክንና እውነተኛውን አምልኮ እንዲተው የቀረበለትን ሐሳብ አጥብቆ ተቃውሟል።​—ማቴዎስ 4:8-10

በአሁኑ ጊዜ ክፉ መናፍስት፣ ከኢየሱስ ጋር እንዳደረጉት በቀጥታ ከሰዎች ጋር የሚነጋገሩት ከስንት አንዴ ነው። በዚህ ፈንታ ጉዳት የሌላቸው የሚመስሉ ነገሮችን በመጠቀም ሰዎች ሳያውቁት በወጥመዳቸው እንዲገቡ ያደርጋሉ፤ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል የክሪስታል ኳስ፣ የሻይ ቅጠል ወይም የቡና አተላ፣ የጥንቆላ ካርዶች፣ አውደ ነገሥት እና ኮከብ ቆጠራ ይገኙበታል። አንተም እንደነዚህ ባሉት ድርጊቶች እንዳትታለል ተጠንቀቅ! እነዚህ ነገሮች ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ከማይታወቀው ዓለም ጋር ለመገናኘት የሚያስችሉ ዘዴዎች አይደሉም። ክፉ መናፍስት፣ እኛን ለማታለልና ወደ ወጥመዳቸው ለማስገባት ስለ መናፍስታዊ ነገሮች ለማወቅ ባለን ጉጉት ይጠቀማሉ፤ ዓላማቸውም ይሖዋን እንዳናመልክ ማድረግ ነው። ክፉ መናፍስት በዚህ ዘዴ ዓላማቸውን ማሳካት ሲያቅታቸው ደግሞ በወጥመዳቸው ተተብትበው የተያዙትን ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚያሠቃዩአቸው ከመሆኑም በላይ ሕይወታቸውን ያመሰቃቅሉባቸዋል። አንተም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ከሆንክ ከእነሱ ተጽዕኖ ለመላቀቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ከመናፍስታዊ ድርጊቶች መላቀቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

ከሰዎች ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩ መናፍስት የአምላክ ጠላቶች እንደሆኑና ጥፋት እንደሚጠብቃቸው ፈጽሞ አትዘንጋ። (ይሁዳ 6) እነዚህ መናፍስት፣ የሞቱ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ አስመሳዮችና ውሸታሞች ናቸው። ጓደኛዬ የምትለው አንድ ሰው፣ ከአንተ ጋር ወዳጅነት የመሠረተበት ዋነኛ ዓላማ የሚጠቅምህን ነገር እንዳታደርግ እንቅፋት ለመፍጠር እንደሆነ ብታውቅ ምን ይሰማሃል? አሊያም ሰዎችን በፆታ ከሚያስነውር ግለሰብ ጋር ሳታውቀው በኢንተርኔት ወዳጅነት እንደመሠረትክ ብትገነዘብ ምን ታደርጋለህ? ከአጋንንት ጋር መቀራረብ የሚያስከትለው አደጋ ከዚህም የከፋ ነው። ከእነሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ የተቻለህን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሃል። ይህን የምታደርገው እንዴት ነው?

በጥንቷ ኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ መናፍስታዊ ድርጊት የሚያስተምሩትን ሲያውቁ ከአስማት ጋር የተያያዙ መጽሐፎቻቸውን ማስወገድ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ስለዚህም ብዙ ዋጋ የሚያወጡ ቢሆኑም እንኳ መጽሐፎቻቸውን “በሁሉ ሰው ፊት አቃጠሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 19:19, 20) በዛሬው ጊዜ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዕቃዎች መጻሕፍትን፣ ክታቦችን፣ የጥንቆላ ሰሌዳንና የመሳሰሉትን ብቻ ሳይሆን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የሚተላለፉ ነገሮችንም ያካትታሉ። ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያለው ከሚመስል ከማንኛውም ነገር ራቅ።

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱትን ባልና ሚስት እንመልከት። በጥንቆላ ካርዶቻቸው ላይ ከተመለከቱት ነገር በመነሳት አደገኛ የሆኑ ሴቶች ወደ ቤታቸው እንደሚመጡና እነዚህን ሴቶች ሊያዳምጧቸውም ሆነ ከእነሱ ምንም ነገር ሊቀበሉ እንደማይገባ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና ካኒ እና ጉድሩን የሚባሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸው መጥተው ስለ አምላክ የሚገልጽ የምሥራች እንደያዙ ሲነግሯቸው ዮአኪምና ባርባራ መልእክቱን ለማዳመጥ ወሰኑ። በውይይታቸው መሃል ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ሲነሳ ካኒና ጉድሩን ይህን ርዕስ በሚመለከት ከቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለእነዚህ ባልና ሚስት አቀረቡላቸው። ከዚያም ቋሚ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ ጀመሩ።

ብዙም ሳይቆይ ዮአኪምና ባርባራ ከአጋንንት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በሙሉ ለማቋረጥ ወሰኑ። የይሖዋ ምሥክሮቹ፣ በዚህ ውሳኔ መናፍስቱ እንደማይደሰቱ ለባልና ሚስቱ ገለጹላቸው። በእርግጥም ዮአኪምና ባርባራ አስቸጋሪ የሆነ ጊዜ ያሳለፉ ሲሆን አጋንንት አስፈሪ የሆነ ጥቃት ያደርሱባቸው ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል እያንዳንዱን ሌሊት የሚያሳልፉት በፍርሃት ነበር፤ ቤት ሲቀይሩ ግን እፎይታ አገኙ። እነዚህ ባልና ሚስት ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስባቸው በ⁠ፊልጵስዩስ 4:13 ላይ በሚገኘው “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” በሚለው ጥቅስ ላይ እምነት ነበራቸው። ይሖዋም የወሰዱትን ቁርጥ ያለ አቋም የባረከላቸው ሲሆን የኋላ ኋላ መናፍስቱ እነሱን ማስፈራራታቸውን አቆሙ። በዛሬው ጊዜ ዮአኪምና ባርባራ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በደስታ ያመልካሉ።

ቅዱሳን መጻሕፍት የይሖዋን በረከት ማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ የሚከተለውን ምክር ይሰጣሉ፦ “ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል። ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።” (ያዕቆብ 4:7, 8) አንተም ከአጋንንት ተጽዕኖ ለመላቀቅ የምትፈልግ ከሆነ ይሖዋ አምላክ አንተን የመርዳት ችሎታም ሆነ ፍላጎት አለው። ዮአኪምና ባርባራ ከመናፍስታዊ ድርጊት ነፃ ስለ መውጣታቸው ሲያስቡ “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” በሚለው በ⁠መዝሙር 121:2 (NW) ላይ በሚገኘው ሐሳብ እውነተኝነት ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.7 ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ “ሙታን የት ናቸው?” የሚለውን ምዕራፍ 6⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መናፍስታዊ ድርጊቶች፣ ሰዎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳይመሠርቱ ያግዷቸዋል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”​—ያዕቆብ 4:8