በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተስፋችን ደስ ይበለን

በተስፋችን ደስ ይበለን

በተስፋችን ደስ ይበለን

‘ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ከረጅም ዘመናት በፊት የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጥቷል።’​—ቲቶ 1:2

ለክለሳ ያህል

አንድ ቅቡዕ ምድራዊ ሕይወቱን በታማኝነት ሲያጠናቅቅ በሰማይ ደስታ እንደሚኖር ማወቃችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

የሌሎች በጎች ተስፋ ፍጻሜ፣ ከቅቡዓኑ ተስፋ ፍጻሜ ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

ተስፋችን ሲፈጸም ለማየት ከፈለግን የትኛውን “ቅዱስ ሥነ ምግባር” መከተል እንዲሁም የትኞቹን ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮች’ መፈጸም ይኖርብናል?

1. ይሖዋ የሚሰጠን ተስፋ እንድንጸና ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

ይሖዋ ‘ተስፋ የሚሰጥ አምላክ’ ነው። ይህን ሐሳብ የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን አክሎም ይሖዋ ‘በእሱ በማመናችን የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍልን ደስታንና ሰላምን ሊሞላብን’ እንደሚችል ተናግሯል። (ሮም 15:13) ተስፋችን የተትረፈረፈ ከሆነ የሚያጋጥመንን ማንኛውም ሁኔታ መቋቋም እንችላለን፤ እንዲሁም ውስጣዊ ደስታና ሰላም ይኖረናል። ይህ ተስፋ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ክርስቲያኖችም “እንደ ነፍስ መልሕቅ እርግጠኛና ጽኑ” ሆኖላቸዋል። (ዕብ. 6:18, 19) ተስፋችንን አጥብቀን መያዛችን በሕይወታችን ውስጥ እንደ ማዕበል ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ቀስ በቀስ እንዳንወሰድ በሌላ አባባል ጥርጣሬ እንዳያድርብንና እምነታችንን እንዳናጣ ሊጠብቀን ይችላል።​—ዕብራውያን 2:1⁠ን እና 6:11ን አንብብ።

2. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች የትኞቹ ሁለት ተስፋዎች አሏቸው? “ሌሎች በጎች፣” ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለሚያገኙት ተስፋ ማወቅ የሚፈልጉት ለምንድን ነው?

2 በዚህ የመጨረሻ ዘመን የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁለት ዓይነት ተስፋ አላቸው። “ትንሽ መንጋ” የተባሉት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪ አባላት ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት በመሆን በሰማይ የማይሞት ሕይወት የማግኘት ተስፋ አላቸው። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 5:9, 10) ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ደግሞ በመሲሐዊው መንግሥት ሥር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። (ራእይ 7:9, 10፤ ዮሐ. 10:16) ሌሎች በጎች መዳናቸው የተመካው ዛሬም ጭምር በምድር ላይ የሚገኙትን የክርስቶስ ቅቡዓን ‘ወንድሞች’ በቅንዓት በመደገፋቸው ላይ መሆኑን በፍጹም መዘንጋት አይኖርባቸውም። (ማቴ. 25:34-40) ቅቡዓኑ ሽልማታቸውን ማግኘታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ሁሉ ሌሎች በጎችም ተስፋቸው መፈጸሙ አይቀርም። (ዕብራውያን 11:39, 40ን አንብብ።) እስቲ በመጀመሪያ ለቅቡዓኑ የተዘረጋላቸውን ተስፋ እንመርምር።

ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያላቸው “ሕያው ተስፋ”

3, 4. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ የተወለዱት’ እንዴት ነው? ይህ ተስፋስ ምንድን ነው?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ምርጦች” በማለት ለጠራቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሁለት ደብዳቤዎችን ጽፎላቸው ነበር። (1 ጴጥ. 1:1) ታናሹ መንጋ የሚያገኘውን ግሩም ተስፋ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ምክንያቱም እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናል፤ እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል። ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል፤ እናንተንም አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው። . . . በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው።”​—1 ጴጥ. 1:3-6

4 በሰማያዊው መንግሥት ከክርስቶስ ጋር ነገሥታት እንዲሆኑ በይሖዋ የተመረጡት ቁጥራቸው ውስን የሆነ ክርስቲያኖች የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ለመሆን ‘እንደ አዲስ ተወልደዋል።’ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል። (ራእይ 20:6) እነዚህ ክርስቲያኖች እንደ ‘አዲስ መወለዳቸው’ ጴጥሮስ ‘የማይበሰብስ፣ የማይረክስና የማይጠፋ ርስት’ በማለት የጠራውን “በሰማይ” የተጠበቀላቸውን “ሕያው ተስፋ” የማግኘት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዚህ ሕያው ተስፋ ‘እጅግ መደሰታቸው’ ምንም የሚያስገርም አይደለም! ሆኖም ተስፋቸውን ማግኘታቸው የተመካው ታማኝ በመሆናቸው ላይ ነው።

5, 6. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ጥሪያቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?

5 ጴጥሮስ በሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘መጠራታቸውንና መመረጣቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ማድረግ’ እንዳለባቸው አሳስቧቸዋል። (2 ጴጥ. 1:10) እነዚህ ክርስቲያኖች እምነትን፣ ለአምላክ ማደርን፣ ወንድማዊ መዋደድንና ፍቅርን የመሰሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ነገሮች በውስጣችሁ ቢኖሩና ቢትረፈረፉ፣ . . . ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ይጠብቋችኋል።”​—2 ጴጥሮስ 1:5-8ን አንብብ።

6 ከሞት የተነሳው ክርስቶስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በትንሿ እስያ ይገኝ በነበረው በፊላደልፊያ ጉባኤ ውስጥ ለሚያገለግሉ በመንፈስ የተወለዱ ሽማግሌዎች በላከላቸው መልእክት ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ስለ ጽናቴ የተነገረውን ቃል ስለጠበቅክ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ለመፈተን በመላው ምድር ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ። ቶሎ እመጣለሁ። ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን ምንጊዜም አጥብቀህ ያዝ።” (ራእይ 3:10, 11) አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ታማኝ ካልሆነ፣ ለተመረጡትና እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ለሚሆኑት የተገባውን ተስፋ ማለትም “የማይጠፋ የክብር አክሊል” አይቀበልም።​—1 ጴጥ. 5:4፤ ራእይ 2:10

ወደ መንግሥቱ የሚያስገባው በር

7. ይሁዳ በደብዳቤው ላይ ስለ የትኛው አስደናቂ ተስፋ ጠቅሷል?

7 የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድም የሆነው ይሁዳ “ለተጠሩት” በማለት ለጠቀሳቸው የተቀቡ የእምነት ባልንጀሮቹ በ65 ዓ.ም. ገደማ ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር። (ይሁዳ 1፤ ከ⁠ዕብራውያን 3:1 ጋር አወዳድር።) ይሁዳ መጀመሪያ ላይ ሊጽፍላቸው ያሰበው ‘ሁሉም ስለሚያገኙት’ ክብራማ የመዳን ተስፋ ማለትም ቅቡዓኑ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ ስለሚያገኙት መብት ነበር። (ይሁዳ 3) ይሁንና ይሁዳ አጣዳፊ ስለሆኑ ሌሎች ጉዳዮች መጻፍ ግድ ሆነበት፤ ያም ሆኖ በደብዳቤው መደምደሚያ ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለሚያገኙት አስደናቂ ተስፋ ከመጥቀስ ወደኋላ አላለም። እንዲህ ብሏል፦ “ከመደናቀፍ ሊጠብቃችሁና ነቀፋ የሌለባችሁ አድርጎ በታላቅ ደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችለው፣ አዳኛችን ለሆነው ብቸኛው አምላክ ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ክብር፣ ግርማ፣ ኃይልና ሥልጣን ይሁን።”​—ይሁዳ 24, 25

8. አንድ ቅቡዕ በታማኝነት ምድራዊ ሕይወቱን ሲያጠናቅቅ በሰማይ ደስታ እንደሚኖር የሚጠቁመው ምንድን ነው?

8 እርግጥ ነው፣ ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተደናቅፈው እንዳይጠፉ በግለሰብ ደረጃ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደሚያስነሳቸውና ፍጹም መንፈሳዊ ፍጥረታት አድርጎ በታላቅ ደስታ በአምላክ ፊት እንደሚያቀርባቸው ተስፋ አላቸው። አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ታማኝነቱን እንደጠበቀ ሲሞት፣ ‘መንፈሳዊ አካል ይዞ እንደሚነሳ’ እንዲሁም “የማይበሰብስ” አካል በመያዝና “በክብር” ትንሣኤ እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ነው። (1 ቆሮ. 15:42-44) “ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ” ከሆነ በመንፈስ የተወለደ አንድ የክርስቶስ ወንድም ምድራዊ ሕይወቱን በታማኝነት ሲያጠናቅቅ በሰማይ ምን ያህል ደስታ ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን። (ሉቃስ 15:7) አንድ ቅቡዕ ሽልማቱን “በታላቅ ደስታ” በሚቀበልበት ጊዜ ይሖዋና ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታቱ ከእሱ ጋር አብረው ደስ ይላቸዋል።​—1 ዮሐንስ 3:2ን አንብብ።

9. ወደ መንግሥቱ የሚያስገባው በር ለቅቡዓኑ ‘በሰፊው ተከፍቶላቸዋል’ የሚባለው እንዴት ነው? ይህ ተስፋ በምድር ላይ እያሉም ጭምር በእነሱ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድረውስ እንዴት ነው?

9 ጴጥሮስም በተመሳሳይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝ በመሆን መጠራታቸውን አስተማማኝ ካደረጉ “ወደ ጌታችንና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት የሚያስገባው በር በሰፊው [እንደሚከፈትላቸው]” ጽፎላቸዋል። (2 ጴጥ. 1:10, 11) ጴጥሮስ ቅቡዓኑ ወደ ሰማያዊ ሽልማታቸው የሚያስገባው በር ‘በሰፊው እንደሚከፈትላቸው’ ሲናገር በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ እንደሚገቡ መናገሩ ይሆናል። በተጨማሪም ‘በሰፊው ይከፈታል’ የሚለው አባባል የሕይወትን ሩጫ በከፍተኛ ተጋድሎ ያጠናቀቁ ቅቡዓን የሚያገኙት በረከት ወደር የማይገኝለት መሆኑን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ክርስቲያኖች በታማኝነት ያሳለፉትን የሕይወት ጎዳና መለስ ብለው ሲመለከቱ ልባቸው በደስታና በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል። ይህ ተስፋ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ እያሉም ‘አእምሯቸውን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ እንዲታጠቁ’ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም።​—1 ጴጥ. 1:13

ሌሎች በጎች ያላቸው “ተስፋ”

10, 11. (ሀ) ሌሎች በጎች ምን ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል? (ለ) የሌሎች በጎች ተስፋ ፍጻሜ ከክርስቶስና ‘ከአምላክ ልጆች መገለጥ’ ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በመንፈስ የተወለዱ “የአምላክ ልጆች” ‘ከክርስቶስ ጋር የመውረስ’ አስደናቂ ተስፋ እንዳላቸው ጽፏል። በመቀጠልም ይሖዋ፣ ያልተወሰነ ቁጥር ላላቸው ሌሎች በጎች ያዘጋጀውን አስደናቂ ተስፋ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “[ሰብዓዊው] ፍጥረት የአምላክን ልጆች [ይኸውም የቅቡዓኑን] መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው። ምክንያቱም ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷል፤ የተገዛው ግን በገዛ ፈቃዱ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእሱ አማካኝነት ነው፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት ማግኘት ነው።”​—ሮም 8:14-21

11 ይሖዋ ተስፋ በተደረገበት ‘ዘር’ አማካኝነት ‘ከመጀመሪያው እባብ’ ማለትም ከሰይጣን ዲያብሎስ ነፃ እንደሚያደርጋቸው ቃል በመግባት ለሰው ልጆች “ተስፋ” ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 3:15፤ ራእይ 12:9) የዚህ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ገላ. 3:16) የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የሰው ዘርን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል መሠረት ጥሏል። የዚህ ተስፋ ፍጻሜ ‘ከአምላክ ልጆች መገለጥ’ ጋር የተያያዘ ነው። ‘የዘሩ’ ሁለተኛ ክፍል የሚሆኑት ክብር የተላበሱት ቅቡዓን ናቸው፤ እነዚህ ቅቡዓን ‘የሚገለጡት’ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በመሆን የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት በሚመጡበት ጊዜ ነው። (ራእይ 2:26, 27) ይህ ከታላቁ መከራ ለሚያልፉ ሌሎች በጎች መዳን ያስገኝላቸዋል።​—ራእይ 7:9, 10, 14

12. የቅቡዓኑ መገለጥ ለሰው ዘር ምን ግሩም በረከቶች ያስገኛል?

12 ሰብዓዊው “ፍጥረት” በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በቃላት ሊገለጽ የማይችል እፎይታ ያገኛል! ክብር የተላበሱት ‘የአምላክ ልጆች’ በዚህ ወቅትም በሌላ መንገድ ይገለጣሉ፤ ይህ የሚሆነው ከክርስቶስ ጋር ካህናት በመሆን የሰው ዘር ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች እንዲያገኝ ሲያደርጉ ነው። የሰማያዊው መንግሥት ተገዥ የሆነው ሰብዓዊ “ፍጥረት” ኃጢአትና ሞት ካስከተሏቸው መጥፎ ውጤቶች ነፃ መሆን ይጀምራል። በዚህ መንገድ ታዛዥ የሆኑት የሰው ልጆች ቀስ በቀስ “ከመበስበስ ባርነት ነፃ” ይሆናሉ። በተጨማሪም እስከ ሺው ዓመት ፍጻሜ ድረስ ለይሖዋ ታማኝ ከሆኑና መጨረሻ ላይ የሚቀርበውን ፈተና ካለፉ ስማቸው “የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል” ላይ ለዘላለም ይጻፋል። በዚህ ወቅት ‘የአምላክ ልጆች የመሆን ክብራማ ነፃነት’ ያገኛሉ። (ራእይ 20:7, 8, 11, 12) በእርግጥም ይህ፣ ክብራማ የሆነ ተስፋ ነው!

ተስፋችንን ሕያው አድርገን መያዝ

13. ለተስፋችን መሠረት የሆነው ምንድን ነው? ክርስቶስ የሚገለጠው መቼ ነው?

13 ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ቅቡዓኑም ሆኑ ሌሎች በጎች ተስፋቸውን ሕያው አድርገው እንዲይዙ የሚረዷቸውን በርካታ ምክሮች ይዘዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ተስፋውን እንዲያገኙ መሠረት የሆነው ሥራቸው ሳይሆን የይሖዋ ጸጋ እንደሆነ ጴጥሮስ ጠቁሟል፤ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ።” (1 ጴጥ. 1:13 አ.መ.ት) ክርስቶስ የሚገለጠው ለታማኝ ተከታዮቹ ሽልማታቸውን ለመስጠትና አምላክ የለሽ በሆነው ዓለም ላይ የይሖዋን ፍርድ ለማስፈጸም በሚመጣበት ጊዜ ነው።​—2 ተሰሎንቄ 1:6-10ን አንብብ።

14, 15. (ሀ) ተስፋችንን ሕያው አድርገን ለመያዝ ትኩረታችን በምን ላይ ማረፍ ይኖርበታል? (ለ) ጴጥሮስ ምን ምክር ሰጥቷል?

14 ተስፋችንን ሕያው አድርገን ለመያዝ ትኩረታችንን በመጪው ‘የይሖዋ ቀን’ ላይ ማድረግ ይኖብናል፤ እንዲሁም አኗኗራችን ይህን ግምት ውስጥ እንዳስገባን የሚያሳይ መሆን አለበት። የይሖዋ ቀን ሲመጣ አሁን ያሉት “ሰማያት” ማለትም ሰብዓዊው አገዛዝ እንዲሁም “ምድር” ማለትም ክፉ የሆነው ሰብዓዊ ኅብረተሰብና “ንጥረ ነገሮቹ” ይጠፋሉ። ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! ሰማያት በእሳት ተቃጥለው የሚጠፉበትንና ንጥረ ነገሮቹም ሁሉ በኃይለኛ ሙቀት የሚቀልጡበትን የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!”​—2 ጴጥ. 3:10-12

15 አሁን ያሉት “ሰማያት” እና “ምድር” ‘በአዲስ ሰማያት [በክርስቶስ መንግሥት] እና በአዲስ ምድር [በአዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ]’ ይተካሉ። (2 ጴጥ. 3:13) በመሆኑም ጴጥሮስ ‘መጠበቅን’ ወይም ተስፋችንን ሕያው አድርገን መያዝን በተመለከተ እንዲህ የሚል ቀጥተኛ ምክር ሰጥቷል፦ “ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።”​—2 ጴጥ. 3:14

ከተስፋችን ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ

16, 17. (ሀ) “ቅዱስ ሥነ ምግባር” እና ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮች’ የተባሉት ምንድን ናቸው? (ለ) ተስፋችን የሚፈጸመው እንዴት ነው?

16 ተስፋችንን ሕያው አድርገን መያዝ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ይገባናል። እንዲሁም ለመንፈሳዊነታችን ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። “ቅዱስ ሥነ ምግባር፣” መከተል በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ ‘በአሕዛብ መካከል መልካም ምግባር ይዞ መኖርን’ ይጨምራል። (2 ጴጥ. 3:11፤ 1 ጴጥ. 2:12) እንዲሁም ‘በመካከላችን ፍቅር ሊኖር’ ይገባል። ይህ ደግሞ በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥም ሆነ በጉባኤያችን ውስጥ ያለውን አንድነት ለመጠበቅ የምንችለውን ያህል ጥረት ማድረግን ያካትታል። (ዮሐ. 13:35) ‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚያሳዩ ተግባሮች’ ሲባል ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለመጠበቅ ስንል የምናደርጋቸውን ነገሮች ያመለክታል። ይህ ደግሞ የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻልን አልፎ ተርፎም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን፣ ጥልቀት ያለው የግል ጥናት ማድረግንና የቤተሰብ አምልኮ ማከናወንን እንዲሁም ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በቅንዓት መስበክን ይጨምራል።​—ማቴ. 24:14

17 ሁላችንም ብንሆን ይሖዋ የሚቀበላቸውና ይህ ክፉ ሥርዓት ‘በሚቀልጥበት’ ወቅት የሚያድናቸው ዓይነት ሰዎች መሆን እንፈልጋለን። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከሆንን ‘ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ከረጅም ዘመናት በፊት የሰጠን የዘላለም ሕይወት ተስፋ’ ሲፈጸም እንመለከታለን።​—ቲቶ 1:2

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ተወልደዋል’

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብህ አባላት ተስፋው ሕያው ሆኖ እንዲታያቸው አድርግ