በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ያለው አንድ ክርስቲያን ይህ ድርጊቱ ከጉባኤ እስከ መወገድ ሊያደርሰው ይችላል?

▪ አዎ፣ ይችላል። በመጽሔቶች፣ በፊልሞች፣ በቪዲዮዎችና በኢንተርኔት ላይ ከሚወጡ የብልግና ጽሑፎችም ሆነ ምስሎች መራቅ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።

የብልግና ምስሎች በዓለም ዙሪያ እንደ አሸን ፈልተዋል ማለት ይቻላል። ኢንተርኔት ደግሞ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በቀላሉ እንዲገኙ እያደረገ ነው፤ በተጨማሪም በዚህ ክፉ ደዌ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ወጣቶችና አዋቂዎች ሳያስቡት የብልግና ምስሎች የሚታዩባቸውን ድረ ገጾች ተመልክተዋል። ሌሎች ደግሞ ማንም ሳያያቸው የብልግና ጽሑፎችንና ምስሎችን በቤታቸው አሊያም በቢሯቸው ሆነው ሊያነቡ ወይም ሊመለከቱ እንደሚችሉ ማወቃቸው ድፍረት ስለሰጣቸው ሆን ብለው ወደ እነዚህ ድረ ገጾች ገብተዋል። ታዲያ ክርስቲያኖች ይህን ጉዳይ በቁም ነገር ሊያስቡበት የሚገባው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ “የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል” በማለት የሰጠው ማስጠንቀቂያ ዋነኛው ምክንያት ምን እንደሆነ ይጠቁመናል። (ማቴ. 5:28) እርግጥ ነው፣ በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል የሚፈጸመው የፆታ ግንኙነት ተገቢ ከመሆኑም በላይ ደስታ እንደሚያስገኝ አይካድም። (ምሳሌ 5:15-19፤ 1 ቆሮ. 7:2-5) ይሁን እንጂ የብልግና ምስሎች የሚዘጋጁት ይህን ክቡር ዓላማ ለማስተጋባት አይደለም። እንዲያውም እነዚህ ምስሎች ኢየሱስ ያስጠነቀቀው ዓይነት መጥፎ ሐሳብ በውስጣችን እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉ የፆታ ብልግናዎች ሲፈጸሙ ያሳያሉ። የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ማየትም ሆነ ማንበብ የሚከተለውን መለኮታዊ መመሪያ በቀጥታ እንደሚቃረን ግልጽ ነው፦ “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።”​—ቆላ. 3:5

አንድ ክርስቲያን ለአንድ ወይም ለሁለት ጊዜ ያህል ብቻ የብልግና ምስሎችን ቢመለከትስ? የዚህ ክርስቲያን ሁኔታ መዝሙራዊው አሳፍ በአንድ ወቅት ከነበረበት አደገኛ ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ግን እግሬ ሊሰናከል፣ አዳልጦኝም ልወድቅ ጥቂት ቀረኝ።” አንድ ክርስቲያን፣ የወንዶችን ወይም የሴቶችን እርቃን አሊያም አንድ ወንድና ሴት ዝሙት ሲፈጽሙ የሚያሳይ የብልግና ምስል እየተመለከተ ንጹሕ ሕሊናም ሆነ ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዴት ሊኖረው ይችላል? አሳፍም ቢሆን በወቅቱ ከአምላክ ጋር ሰላም አልነበረውም፤ በመሆኑም “ቀኑን ሙሉ ተቀሠፍሁ፤ ጠዋት ጠዋትም ተቀጣሁ” ብሏል።​—መዝ. 73:2, 14

እንዲህ ያለ ችግር ውስጥ የገባ አንድ ክርስቲያን መንቃትና መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አምኖ መቀበል ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን እርዳታ ከጉባኤ ማግኘት እንደሚቻል ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ እርምጃ ቢወስድ እንኳ መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ፤ ይህን ስታደርጉ እያንዳንዳችሁ . . . ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (ገላ. 6:1) አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች ‘ለታመመው ሰው ፈውስና የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኝለትን የእምነት ጸሎት’ ማቅረብን ጨምሮ የሚያስፈልገውን ማንኛውም እርዳታ ሊሰጡት ይችላሉ። (ያዕ. 5:13-15) መጥፎ ከሆነው የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ለመላቀቅ የሚያስችላቸውን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ሁሉ ልክ እንደ አሳፍ ወደ አምላክ መቅረብ የተሻለ እንደሆነ ተገንዝበዋል።​—መዝ. 73:28

ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሠሩት ርኩሰት፣ ዝሙትና ብልግና” * ንስሐ ያልገቡ አንዳንድ ሰዎች መኖራቸውን ተናግሯል። (2 ቆሮ. 12:21) ፕሮፌሰር ማርቪን ቪንሰንት እዚህ ላይ “ርኩሰት” ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል አስመልክተው ሲጽፉ “አስነዋሪ የሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸም መቆሸሽን ያመለክታል” ብለዋል። አንዳንድ የብልግና ምስሎች እርቃንን ወይም አንድ ወንድና ሴት የፆታ ግንኙነት ሲፈጽሙ ከማሳየት ባለፈ ዘግናኝ ድርጊቶችን የያዙ መሆናቸው በጣም ያሳዝናል። ግብረ ሰዶማዊነትን (በተመሳሳይ ፆታዎች መካከል የሚፈጸም ወሲብን)፣ ከእንስሳት ጋር ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን እንዲሁም ሕፃናትን ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግን፣ በቡድን ሆኖ አስገድዶ መድፈርን፣ ሴቶችን ማሠቃየትን፣ ግለሰቡን አስሮ የፆታ ግንኙነት መፈጸምን ብሎም ሰውን በማሠቃየት መደሰትን የመሳሰሉ ድርጊቶችን የሚያሳዩ አስነዋሪና አስጸያፊ የብልግና ምስሎች አሉ። በጳውሎስ ዘመን የሚኖሩ ‘አእምሯቸው የጨለመባቸው’ አንዳንድ ሰዎች “የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ለብልግና አሳልፈው ሰጥተው” ነበር።​—ኤፌ. 4:18, 19

ጳውሎስ “ርኩሰት” የሚለውን ቃል በ⁠ገላትያ 5:19 ላይም ጠቅሶታል። አንድ የብሪታንያ ምሁር ይህ ቃል “እዚህ ላይ የተሠራበት ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ የፆታ ምኞቶችን በሙሉ ለማመልከት ሊሆን ይችላል” ብለዋል። ከላይ የተጠቀሱት ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርዱ አስጸያፊ የሆኑ የብልግና ምስሎች “ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ የፆታ ምኞቶች” እና አስነዋሪ ተግባሮች መሆናቸውን የሚክድ ክርስቲያን ሊኖር ይችላል? ጳውሎስ በ⁠ገላትያ 5:19-21 ላይ ያለውን ሐሳብ ሲደመድም “እንዲህ ያሉ” ርኩሰቶችን “የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” ብሏል። በመሆኑም አንድ ሰው ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርዱ አስጸያፊ የሆኑ የብልግና ምስሎችን የመመልከት ሥር የሰደደ ልማድ ካለውና ምናልባትም በዚህ ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ከቆየ እንዲሁም ንስሐ ለመግባትና ይህን ድርጊቱን ለመተው ፈቃደኛ ካልሆነ የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንደሆነ መቀጠል አይችልም። የጉባኤው ንጽሕናና መንፈስ ተጠብቆ እንዲቆይ ግለሰቡ መወገድ ይኖርበታል።​—1 ቆሮ. 5:5, 11

አስጸያፊ የሆኑ የብልግና ምስሎችን የማየት ልማድ የተጠናወታቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ወደ ሽማግሌዎች በመሄድ የተሰጣቸውን መንፈሳዊ እርዳታ ተቀብለው ለውጥ ማድረጋቸውን ማወቁ የሚያበረታታ ነው። ኢየሱስ በጥንቷ ሰርዴስ ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ሊሞቱ የተቃረቡትን የቀሩትን ነገሮችም አጠናክር። ስለዚህ የተቀበልከውንና የሰማኸውን ምንጊዜም አትርሳ፤ እንዲሁም ዘወትር ጠብቀው፤ ንስሐም ግባ። ካልነቃህ ግን . . . በየትኛው ሰዓት ከተፍ እንደምልብህም ፈጽሞ አታውቅም።” (ራእይ 3:2, 3) በእርግጥም ንስሐ መግባትና ከእሳት ውስጥ የመውጣት ያህል ቢሆንም ከዚህ ልማድ መላቀቅ ይቻላል።​—ይሁዳ 22, 23

ይሁን እንጂ እያንዳንዳችን እንዲህ ወዳለ አደገኛ ሁኔታ ድርሽ ላለማለት ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን ምንኛ የተሻለ ነው! አዎ፣ ከማንኛውም ዓይነት የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ‘በርኩሰት፣ በዝሙትና በብልግና’ መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት የሐምሌ 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-31 ተመልከት።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ችግር ውስጥ የገባ አንድ ክርስቲያን መንቃትና መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አምኖ መቀበል ይኖርበታል