በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ​—ጥያቄዎቻችንና መልሶቻቸው

ኢየሱስ ክርስቶስ​—ጥያቄዎቻችንና መልሶቻቸው

ኢየሱስ ክርስቶስ​—ጥያቄዎቻችንና መልሶቻቸው

“ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?”​—ሉቃስ 9:18

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይህን ጥያቄ የጠየቃቸው ሰዎች ስለ እሱ የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው ስለሚያውቅ ነበር። ሆኖም ሕዝቡ ስለ እሱ ማንነት ያን ያህል ግራ መጋባት አልነበረባቸውም። ኢየሱስ ራሱን ከሌሎች አግልሎ ሕቡዕ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀስ ሰው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በመንደሮችና በከተሞች በግልጽ እየተዘዋወረ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ይኖር ነበር። ሰዎች ስለ እሱ እውነቱን እንዲያውቁ ይፈልግ ስለነበር በአደባባይ ሰብኳል እንዲሁም አስተምሯል።​—ሉቃስ 8:1

ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ በጻፏቸው በአራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች በመመርመር ስለ እሱ እውነቱን ማወቅ ይቻላል። በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉት እነዚህ ዘገባዎች ስለ ኢየሱስ ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ። *​—ዮሐንስ 17:17

ጥያቄ፦ በእርግጥ ኢየሱስ የሚባል ሰው በምድር ላይ ኖሯል?

መልስ፦ አዎን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩትን ጆሴፈስንና ታሲተስን ጨምሮ ሌሎች ዓለማዊ የታሪክ ምሁራንም ኢየሱስ የሚባል ሰው እንደነበረ ጠቅሰዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ በሕይወት የነበረ ሰው እንጂ የልብ ወለድ ገጸ ባሕርይ እንዳልሆነ አሳማኝ በሆነ መንገድ ያሳያሉ። እነዚህ ዘገባዎች ክንውኖቹ ስለተፈጸሙበት ጊዜ እና ቦታ ዝርዝር መረጃ ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረበትን ዓመት ለመጠቆም በወቅቱ የነበሩ ሰባት ገዢዎችን ስም ጠቅሷል፤ እነዚህ ሰዎች በእርግጥ የነበሩ መሆናቸውን ዓለማዊ የታሪክ ምሁራንም አረጋግጠዋል።​—ሉቃስ 3:1, 2, 23

ኢየሱስ የሚባል ሰው በምድር ላይ እንደኖረ የሚያሳዩት ማስረጃዎች አሌ ሊባሉ አይችሉም። ኢየሱስ በታሪክ ውስጥ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው “አብዛኞቹ ምሁራን፣ በአንደኛው መቶ ዘመን የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚባል ሰው እንደኖረ ይቀበላሉ።”

ጥያቄ፦ ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው?

መልስ፦ አይደለም። ኢየሱስ፣ ከአምላክ ጋር እኩል እንደሆነ ፈጽሞ አስቦ አያውቅም። እንዲያውም ኢየሱስ ከይሖዋ እንደሚያንስ ብዙ ጊዜ ገልጿል። * ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ይሖዋን “አምላኬ” ያለው ሲሆን “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” በማለትም ገልጾታል። (ማቴዎስ 27:46፤ ዮሐንስ 17:3) ኢየሱስ በዚህ መንገድ ሊናገር የሚችለው የይሖዋ የበታች ከሆነ ብቻ ነው። አንድ ሠራተኛ ስለ አሠሪው ሲናገር “አለቃዬ” ወይም “ኃላፊዬ” የሚል ከሆነ በሥልጣን ከአሠሪው እንደሚያንስ እያመለከተ እንደሆነ ግልጽ ነው።

በተጨማሪም ኢየሱስ፣ እሱና ይሖዋ አንድ አካል እንዳልሆኑ ገልጿል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ስለ ራሱ በመመሥከሩ ለተቃወሙት ሰዎች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በሕጋችሁ ላይ ‘የሁለት ሰዎች ምሥክርነት እውነት ነው’ ተብሎ ተጽፏል። ስለ ራሴ የምመሠክር አንዱ እኔ ነኝ፤ የላከኝ አብም ስለ እኔ ይመሠክራል።” (ዮሐንስ 8:17, 18) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ እና ይሖዋ በአካል አንድ አይደሉም። አንድ አካል ቢሆኑ ኖሮ እሱና አባቱ እንደ ሁለት ምሥክሮች ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ? *

ጥያቄ፦ ኢየሱስ ጥሩ ነገር ሠርቶ ያለፈ ሰው ብቻ ነበር?

መልስ፦ አይደለም። ኢየሱስ እንዲሁ ጥሩ ሰው ከመሆን ባለፈ ያከናወናቸው ነገሮች አሉ። ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ረገድ የተለያዩ ወሳኝ ሚናዎችን እንደሚጫወት ያውቅ ነበር። ከእነዚህም አንዳንዶቹ ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦

‘የአምላክ አንድያ ልጅ’ (ዮሐንስ 3:18) ኢየሱስ ከየት እንደመጣ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ የተፈጠረው ሰው ሆኖ በምድር ላይ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ‘ከሰማይ እንደመጣ’ እሱ ራሱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:38) ኢየሱስ የአምላክ የመጀመሪያ ፍጥረት ሲሆን ሌሎቹ ነገሮች በሙሉ ሲፈጠሩም ከአምላክ ጋር አብሮ ሠርቷል። በአምላክ በቀጥታ የተፈጠረው እሱ ብቻ ስለሆነ ኢየሱስ የአምላክ “አንድያ ልጅ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነበር።​—ዮሐንስ 1:3, 14፤ ቆላስይስ 1:15, 16

“የሰው ልጅ” (ማቴዎስ 8:20) ኢየሱስ ራሱን “የሰው ልጅ” እያለ በተደጋጋሚ ይጠራ የነበረ ሲሆን ይህ አገላለጽ በወንጌሎች ውስጥ 80 ጊዜ ገደማ ተሠርቶበታል። እንዲህ መባሉም ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው እንደነበረ እንጂ በሰው መልክ የተገለጠ አምላክ እንዳልሆነ ያመለክታል። ታዲያ የአምላክ አንድያ ልጅ ሰው ሆኖ ሊወለድ የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የልጁን ሕይወት አይሁዳዊት ድንግል ወደነበረችው ወደ ማርያም ማህፀን በማዛወር እንድትፀንስ አደረገ። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደ።​—ማቴዎስ 1:18፤ ሉቃስ 1:35፤ ዮሐንስ 8:46

“መምህር” (ዮሐንስ 13:13) ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ‘ምሥራች የማስተማርና የመስበክ’ ተልዕኮ ከይሖዋ እንደተሰጠው በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:23፤ ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነና ይህ መንግሥት የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ በጣም ቀላል እና ግልጽ በሆነ መንገድ አስተምሯል።​—ማቴዎስ 6:9, 10

“ቃል” (ዮሐንስ 1:1) ኢየሱስ የአምላክ ቃል አቀባይ፣ ማለትም አምላክ መልእክትና መመሪያ የሚያስተላልፍበት መንገድ ሆኖ አገልግሏል። ይሖዋ ለሰዎች መልእክት ለማድረስ በኢየሱስ ተጠቅሟል።​—ዮሐንስ 7:16, 17

ጥያቄ፦ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ነበር?

መልስ፦ አዎን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ መሲሕ ወይም ክርስቶስ እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር፤ የእነዚህ ቃላት ትርጉም “የተቀባ” ማለት ነው። ይህ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ የይሖዋን ዓላማ በመፈጸም ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በአንድ ወቅት አንዲት ሳምራዊት ሴት ለኢየሱስ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ” ብላው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እያነጋገርኩሽ ያለሁት እኔ እሱ ነኝ” በማለት በግልጽ ነግሯታል።​—ዮሐንስ 4:25, 26

ታዲያ ኢየሱስ በእርግጥ መሲሕ ለመሆኑ ማስረጃ ይኖራል? ሦስት ማስረጃዎች አሉ፤ አንድን ግለሰብ ለይቶ እንደሚያሳውቅ የጣት አሻራ ሁሉ እነዚህ ማስረጃዎችም አንድ ላይ ሲታዩ መሲሑ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን ያረጋግጣሉ። እንዴት? ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች እስቲ እንመልከት።

የዘር ሐረጉ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መሲሑ ከአብርሃም የዘር ሐረግ እንዲሁም በዳዊት ቤተሰብ በኩል እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር። (ዘፍጥረት 22:18፤ መዝሙር 132:11, 12) ኢየሱስ የመጣው ከአብርሃም እና ከዳዊት የዘር ሐረግ ነው።​—ማቴዎስ 1:1-16፤ ሉቃስ 3:23-38

ፍጻሜ ያገኙ ትንቢቶች፦ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የመሲሑን ልደትና አሟሟቱን የሚመለከቱ ዝርዝር ነገሮችን ጨምሮ በምድር ላይ ስለሚያሳልፈው ሕይወት የሚገልጹ በርካታ ትንቢቶችን ይዘዋል። ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ በኢየሱስ ላይ ተፈጽመዋል። ከትንቢቶቹ መካከል በቤተልሔም እንደሚወለድ (ሚክያስ 5:2፤ ሉቃስ 2:4-11)፣ ከግብፅ ተጠርቶ እንደሚመጣ (ሆሴዕ 11:1፤ ማቴዎስ 2:15) እንዲሁም ሲገደል ከአጥንቶቹ አንዱም እንደማይሰበር (መዝሙር 34:20፤ ዮሐንስ 19:33, 36) የሚገልጹት ይገኙበታል። ኢየሱስ ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ በእሱ ላይ እንዲፈጸሙ ማድረግ የሚችልበት መንገድ አልነበረም። *

አምላክ የሰጠው ምሥክርነት፦ አምላክ፣ ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት መላእክትን በመላክ መሲሑ መወለዱን ለእረኞች እንዲያበስሩ አድርጓል። (ሉቃስ 2:10-14) ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውንም አምላክ ራሱ በኢየሱስ እንደሚደሰት በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሰማይ ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:16, 17፤ 17:1-5) ይሖዋ ታላላቅ ተአምራትን የመፈጸም ችሎታ ለኢየሱስ የሰጠው ሲሆን ይህም ኢየሱስ መሲሕ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።​—የሐዋርያት ሥራ 10:38

ጥያቄ፦ ኢየሱስ መሠቃየትና መሞት የነበረበት ለምንድን ነው?

መልስ፦ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት በመሆኑ ሥቃይ ሊደርስበት አይገባም ነበር። እንደ አንድ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በእንጨት ላይ በሚስማር እንዲቸነከርና በውርደት እንዲሞት የሚያደርግ ጥፋትም አልሠራም። ያም ሆኖ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት በደል እንደሚደርስበት ያውቅ የነበረ ሲሆን ይህንንም በፈቃደኝነት ተቀብሏል።​—ማቴዎስ 20:17-19፤ 1 ጴጥሮስ 2:21-23

ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች፣ መሲሑ የሌሎችን ኃጢአት ለማስተሰረይ ሲል መሠቃየትና መሞት እንደነበረበት ይጠቁማሉ። (ኢሳይያስ 53:5፤ ዳንኤል 9:24, 26) ኢየሱስ ራሱ “በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” እንደመጣ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት፣ የሰው ልጆችን ከኃጢአት የመዋጀት ኃይል እንዳለው የሚያምኑ ሁሉ ከኃጢአትና ከሞት የመዳንና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል። *​—ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10

ጥያቄ፦ ኢየሱስ በእርግጥ ከሞት እንደተነሳ ማመን እንችላለን?

መልስ፦ አዎን። ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳ ሙሉ እምነት ነበረው። (ማቴዎስ 16:21) ይሁን እንጂ እሱም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያለ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ከሞት እንደሚነሳ አልተናገሩም። ይህ ጨርሶ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ . . . ከሞት እስራት አላቅቆ አስነሳው” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 2:24) አምላክ መኖሩንና እሱ የሁሉ ነገሮች ፈጣሪ መሆኑን የምናምን ከሆነ ልጁን ከሞት ለማስነሳት እንደሚችል ለማመን በቂ ምክንያት አለን።​—ዕብራውያን 3:4

ታዲያ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ አለ? እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።

የዓይን ምሥክሮች፦ ኢየሱስ ከሞተ ከ22 ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የተመለከቱት ከ500 በላይ የዓይን ምሥክሮች እንደነበሩና እሱ ይህን መልእክት በጻፈበት ጊዜ አብዛኞቹ በሕይወት እንዳሉ ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 15:6) ኢየሱስ መነሳቱን እንዳዩ የተናገሩት ምሥክሮች አንድ ወይም ሁለት ቢሆኑ ኖሮ ምሥክርነታቸውን ማስተባበል ቀላል ይሆን ነበር፤ ሆኖም 500 የዓይን ምሥክሮች የሰጡትን ምሥክርነት ማን ሊክድ ይችላል?

ሊታመኑ የሚችሉ ምሥክሮች፦ የተፈጸመውን ነገር በትክክል ለማወቅ የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ የነበራቸው የኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ በድፍረት አውጀዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:29-32፤ 3:13-15) እንዲያውም በትንሣኤው ማመን የክርስትና እምነት መሠረት እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:12-19) እነዚያ ደቀ መዛሙርት በኢየሱስ ላይ የነበራቸውን እምነት ከመካድ ይልቅ መሞትን ይመርጡ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 7:51-60፤ 12:1, 2) ሐሰት መሆኑን ለሚያውቀው ነገር ለመሞት ፈቃደኛ የሚሆን ሰው ያለ ይመስልሃል?

ስለ ኢየሱስ ለሚነሱ ስድስት ዋና ዋና ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን መልሶች ተመልክተናል። እነዚህ መልሶች ኢየሱስ ማን እንደሆነ በግልጽ ለማወቅ አስችለውናል። ይሁን እንጂ መልሶቹን ማወቅ ያን ያህል አስፈላጊ ነው? በሌላ አነጋገር፣ ስለ ኢየሱስ የምታምነው ነገር ለውጥ ያመጣል?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 የመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ የሚናገሩት ነገር ከሌሎች አዋልድ መጻሕፍት እንዴት እንደሚለይ ለማወቅ በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኘውን “የአዋልድ ወንጌሎች​—ስለ ኢየሱስ የተሰወሩ እውነቶችን ይዘዋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።

^ አን.10 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከገጽ 20-22 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት​—ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.21 በኢየሱስ ላይ ከተፈጸሙት ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ገጽ 200 ላይ ይገኛሉ።

^ አን.25 የኢየሱስ ሞት ከኃጢአት የሚዋጀን እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።