በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

አንድ ሰው ወላጆቹ በልጅነቱ ያስተማሩትን ሃይማኖት ትቶ ከሄደ በኋላ እንደገና ወደ አምላክ ቤት እንዲመለስ የገፋፋው ምንድን ነው? አንድ ወጣት ዕድሜውን ሙሉ ሲናፍቀው የኖረውን የአባት ፍቅር ያገኘው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።

“ወደ ይሖዋ መመለስ ነበረብኝ።”​—ኢሊ ከሊል

የትውልድ ዘመን፦ 1976

የትውልድ አገር፦ ቆጵሮስ

የኋላ ታሪክ፦ “አባካኝ ልጅ” የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በቆጵሮስ ቢሆንም ያደግሁት በአውስትራሊያ ነው። ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስለነበሩ ለይሖዋና ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዲያድርብኝ ለመርዳት የቻሉትን ሁሉ ጥረዋል። ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ስሆን ማመፅ ጀመርኩ። ማታ ማታ ከቤት ሹልክ ብዬ እወጣና ከእኩዮቼ ጋር ሆነን መኪኖች እንሰርቅ እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ነገሮችን እንፈጽም ነበር።

መጀመሪያ አካባቢ፣ ወላጆቼ እንዲያዝኑብኝ ስለማልፈልግ እነዚህን ነገሮች የማደርገው ተደብቄ ነበር። ይሁን እንጂ ለእነሱ የነበረኝ ፍርሃት እያደር እየጠፋ ሄደ። ለይሖዋ ፍቅር ከሌላቸው በዕድሜ በጣም ከሚበልጡኝ ሰዎች ጋር ጓደኝነት የመሠረትሁ ሲሆን እነሱም አሉታዊ ተጽዕኖ አሳደሩብኝ። በመጨረሻም ከዚህ በኋላ የእነሱን ሃይማኖት መከተል እንደማልፈልግ ለወላጆቼ ነገርኳቸው። እነሱም በትዕግሥት ሊረዱኝ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም እኔ ግን እርዳታቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበርኩም። በዚህ ጊዜ ወላጆቼ ቅስማቸው ተሰበረ።

ከቤት ከወጣሁ በኋላ ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ፤ አልፎ ተርፎም ከፍተኛ መጠን ያለው ማሪዋና ማምረትና መሸጡን ተያያዝኩት። ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ሕይወት እመራ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጭፈራ ቤቶችን በጣም አዘወትር ነበር። ከዚህም ሌላ ግልፍተኛ ሰው ሆንኩ። አንድ ሰው የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር ደስ ካላለኝ በንዴት ቱግ ብዬ አንባርቅበት ብሎም እመታው ነበር። በአጭሩ፣ አንድ ክርስቲያን ሊያደርጋቸው እንደማይገባ የተማርኳቸውን ነገሮች በሙሉ እፈጽም ጀመር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? አብሮኝ ዕፅ ከሚወስድ አንድ ሰው ጋር ወዳጆች ሆንን፤ ይህ ሰው አባቱን በሞት ያጣው በልጅነቱ ነው። ብዙውን ጊዜ እየተጫወትን በጣም እናመሽ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ስሜቱን አውጥቶ የሚናገር ሲሆን አባቱን በጣም እንደሚናፍቅ ይገልጽ ነበር። እኔም በልጅነቴ ስለ ትንሣኤ ተስፋ እየተማርኩ ስላደግሁ ስለ ኢየሱስ፣ ይኸውም ሙታንን እንዳስነሳና ወደፊትም ይህን ለማድረግ ቃል እንደገባ እነግረው ጀመር። (ዮሐንስ 5:28, 29) “አባትህን እንደገና ስታገኘው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ” እንዲሁም “ሁላችንም በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር እንችላለን” እለው ነበር። እነዚህ ሐሳቦች የጓደኛዬን ልብ ነኩት።

በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ጓደኛዬ ስለ መጨረሻው ቀን ወይም ስለ ሥላሴና ስለመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ይጠይቀኝ ነበር። እኔም የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስና ስለ መጨረሻው ቀን እውነቱን የሚያስረዱ የተለያዩ ጥቅሶችን እያወጣሁ አሳየው ነበር። (ዮሐንስ 14:28፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ለጓደኛዬ ስለ ይሖዋ ብዙ በነገርኩት መጠን እኔም ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማሰብ ጀመርኩ።

ወላጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ዘር በልቤ ውስጥ ለመዝራት ብዙ ለፍተዋል፤ በልቤ ውስጥ ተቀብረው የቆዩት እነዚህ ዘሮች ቀስ በቀስ ማደግ ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ጊዜ ጭፈራ ቤት ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር ዕፅ እየወሰድሁ እያለ በድንገት ስለ ይሖዋ ማሰብ እጀምራለሁ። ከጓደኞቼ መካከል ብዙዎቹ አምላክን እንደሚወዱ ቢናገሩም አኗኗራቸው ግን ይህን የሚያሳይ አልነበረም። እንደ እነሱ ለመሆን ስላልፈለግሁ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ወሰንኩ። ወደ ይሖዋ መመለስ ነበረብኝ።

እርግጥ ነው፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማወቅ አንድ ነገር ሲሆን ይህን በተግባር ማዋል ደግሞ ሌላ ነገር ነው። አንዳንዶቹን ለውጦች ማድረግ ቀላል ነበር፤ ለምሳሌ ዕፅ ለመተው ብዙ አልተቸገርኩም። በተጨማሪም ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥሁ፤ እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ከሚያገለግል ሰው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።

ሌሎች ለውጦችን ማድረግ ግን በጣም ከብዶኝ ነበር። በተለይ ያስቸገረኝ ንዴቴን መቆጣጠር ነው። በዚህ ረገድ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የሚሳካልኝ ቢሆንም አልፎ አልፎ ይህ ባሕርይ እንደገና ያገረሽብኛል። በዚህ ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት የምዋጥ ሲሆን ዋጋ እንደሌለኝ ይሰማኛል። በሁኔታው ተስፋ ስለቆረጥኩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናኝን ሽማግሌ አነጋገርኩት። እሱም ምንጊዜም ታጋሽና ደግ በመሆን እውነተኛ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። በአንድ ወቅት፣ ተስፋ አለመቁረጥ ያለውን ጥቅም የሚያብራራ በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ ርዕስ አስነበበኝ። * ስናደድ ልወስዳቸው ስለሚገቡ እርምጃዎችም ተወያየን። በመጠበቂያ ግንቡ ላይ ባነበብኩት ርዕስ ላይ በማሰላሰልና ወደ ይሖዋ ደጋግሜ በመጸለይ የግልፍተኝነት ባሕሪዬን እያደር መቆጣጠር ቻልኩ። በመጨረሻም ሚያዝያ 2000 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ወላጆቼ ምን ያህል በደስታ እንደፈነደቁ ቃላት ሊገልጹት አይችሉም።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ሰውነቴን በዕፅም ሆነ በፆታ ብልግና እያረከስኩት ባለመሆኔ አሁን የአእምሮ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና አለኝ። በማንኛውም ጊዜ ይኸውም ሥራ ላይ ስሆን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ እንዲሁም ስዝናና ከበፊቱ የበለጠ ደስተኛ ነኝ። ስለ ሕይወት ብሩሕ አመለካከት አለኝ።

ወላጆቼ በእኔ ተስፋ ስላልቆረጡ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። በተጨማሪም በ⁠ዮሐንስ 6:44 ላይ የሚገኙትን “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት አስባለሁ። ወደ ይሖዋ መመለስ የቻልኩት እሱ ወደ ራሱ መልሶ ስለሳበኝ መሆኑን ሳስበው ልቤ በጥልቅ ይነካል።

“የአባት ፍቅር ለማግኘት በጣም እመኝ ነበር።”​—ማርኮ አንቶኒዮ አልቫሬዝ ሶቶ

የትውልድ ዘመን፦ 1977

የትውልድ አገር፦ ቺሊ

የኋላ ታሪክ፦ የዴዝ ሜታል የሙዚቃ ቡድን አባል የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያሳደገችኝ እናቴ ስትሆን የምንኖረው በደቡብ አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ አቅራቢያ በማጄላን የባሕር ወሽመጥ ላይ በምትገኝ ፑንታ አሬናስ የምትባል ውብ ከተማ ነበር። የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ ተለያዩ፤ ይህም እንደማልፈለግ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጓል። የአባት ፍቅር ለማግኘት በጣም እመኝ ነበር።

እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስለምታጠና በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ወደሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ትወስደኝ ነበር። ይሁን እንጂ ስብሰባ መሄድ ስለሚያስጠላኝ ብዙ ጊዜ መንገድ ላይ እነጫነጭና አስቸግራት ነበር። አሥራ ሦስት ዓመት ሲሆነኝ እስከነጭራሹ ስብሰባ መሄድ አቆምኩ።

በወቅቱ የሙዚቃ ፍቅር የነበረኝ ሲሆን ተሰጥኦውም እንዳለኝ አስተዋልኩ። በመሆኑም 15 ዓመት ሲሞላኝ በቡና ቤቶች እንዲሁም በበዓላትና በግብዣዎች ላይ ሄቪ ሜታል እና ዴዝ ሜታል የሚባሉትን የሙዚቃ ስልቶች እጫወት ነበር። ጥሩ ችሎታ ካላቸው ሙዚቀኞች ጋር ጊዜ ማሳለፌም የክላሲካል ሙዚቃ ፍቅር እንዲያድርብኝ አደረገ። ስለዚህ በከተማችን በሚገኝ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቼ መማር ጀመርኩ። ሃያ ዓመት ሲሆነኝ ተጨማሪ የሙዚቃ ትምህርት ለመከታተል ወደ ዋና ከተማው ሳንቲያጎ ሄድኩ። በሄቪ ሜታልና በዴዝ ሜታል የሙዚቃ ቡድኖች ውስጥ መጫወቴንም ቀጠልኩ።

ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ከሚሰማኝ ሥር የሰደደ የባዶነት ስሜት መላቀቅ አልቻልኩም። ይህን ስሜት ለመቋቋም ስል፣ እንደ ቤተሰቦቼ አድርጌ ከምመለከታቸው የሙያ ባልደረቦቼ ጋር ዕፅ እወስድ እንዲሁም እስክሰክር ድረስ እጠጣ ነበር። የዓመፀኝነት ዝንባሌ እንደነበረኝ አለባበሴንና ፀጉሬን በመመልከት በግልጽ ማስተዋል ይቻል ነበር። ጥቁር ልብስ የምለብስና ጢሜን የማሳድግ ሲሆን ፀጉሬም ወገቤ ጋ ይደርስ ነበር።

በዓመፀኝነት ዝንባሌዬ የተነሳ በተደጋጋሚ እደባደብ እንዲሁም ከፖሊስ ጋር እጋጭ ነበር። በአንድ ወቅት ጠጥቼ እያለሁ፣ እኔንና ጓደኞቼን ያስቸግሩን በነበሩ የዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ጥቃት ሰነዘርኩ። የቡድኑ አባላት መንገጭላዬ እስኪወልቅ ድረስ ክፉኛ ደበደቡኝ።

ይሁን እንጂ ከሁሉ በላይ የጎዱኝ የቅርብ ጓደኞቼ ናቸው። አንድ ቀን፣ የሴት ጓደኛዬና በጣም የምቀርበው ጓደኛዬ ለዓመታት የዘለቀ የፍቅር ግንኙነት እንዳላቸው ደረስኩበት፤ ጓደኞቼ በሙሉ ይህን ቢያውቁም ደብቀውኝ ነበር። በዚህ ወቅት ስሜቴ በጥልቅ ተጎዳ።

ወደ ፑንታ አሬናስ ተመልሼ ሙዚቃ ማስተማር እንዲሁም ቼሎ የሚባለውን የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ጀመርኩ። ከሄቪ ሜታልና ዴዝ ሜታል የሙዚቃ ቡድኖች ጋር መጫወቴንና ሙዚቃ ማስቀረጼንም አልተውኩም። በዚህ መሃል፣ ሱዛን ከምትባል አንዲት ቆንጆ ወጣት ጋር ተዋወቅሁ፤ ከዚያም አብረን መኖር ጀመርን። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሱዛን እናቷ በሥላሴ እንደምታምንና እኔ ግን እንደማላምን አወቀች። “ታዲያ እውነቱ ምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችኝ። እኔም የሥላሴ እምነት ሐሰት መሆኑን ባውቅም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሜ ማስረጃ ማቅረብ እንደማልችል ነገርኳት። ይሁን እንጂ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉት እነማን እንደሆኑ አውቅ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች እውነቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሊያሳዩአት እንደሚችሉ ገለጽኩላት። ከዚያም ለብዙ ዓመታት አድርጌው የማላውቀውን አንድ ነገር አደረግሁ፤ ወደ አምላክ በመጸለይ እንዲረዳኝ ጠየቅሁት።

ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ ሰው አገኘሁ፤ ግለሰቡን የማውቀው ስለመሰለኝ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ጠየቅሁት። ገጽታዬ እንዳስፈራው ቢያስታውቅበትም በመንግሥት አዳራሽ ስለሚደረገው ስብሰባ ላቀርብኩለት ጥያቄ በደግነት መልስ ሰጠኝ። ይህ አጋጣሚ የጸሎቴ መልስ እንደሆነ እርግጠኛ ነበርኩ። ወደ መንግሥት አዳራሹ ሄድኩና ማንም እንዳያየኝ ከኋላ ተቀመጥሁ። ይሁን እንጂ በልጅነቴ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ የሚያውቁኝ ብዙዎች አስታወሱኝ። ሞቅ ባለ መንገድ ሲቀበሉኝና እቅፍ ሲያደርጉኝ ውስጣዊ ሰላም ተሰማኝ። ወደ ቤቴ ተመልሼ የመጣሁ ያህል ነበር። ትንሽ ልጅ ሳለሁ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ የነበረውን ሰው ሳገኘው አሁንም እንዲያስጠናኝ ጠየቅሁት።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? አንድ ቀን “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው” የሚለውን በ⁠ምሳሌ 27:11 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነበብኩ። እዚህ ግባ የማይባል ትቢያ የሆነ ሰው፣ የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪ ሊያስደስተው እንደሚችል ሳስበው ልቤ በጥልቅ ተነካ። ሕይወቴን በሙሉ ስፈልገው የቆየሁት አባት ይሖዋ እንደሆነ ተገነዘብኩ!

በሰማይ ያለውን አባቴን ለማስደሰትና ፈቃዱን ለመፈጸም ፈለግሁ፤ ይሁን እንጂ ለብዙ ዓመታት የዕፅና የአልኮል መጠጥ ባሪያ ሆኜ ኖሬያለሁ። ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 6:24 ላይ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም” በማለት የሰጠው ትምህርት የገባኝ በዚህ ጊዜ ነው። ሕይወቴን ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት አደረግኩ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” የሚለው በ⁠1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሐሳብ በጥልቅ ነካኝ። ቀደም ሲል ወደማዘወትራቸው ቦታዎች መሄዴንና ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር መዋሌን እስካልተውኩ ድረስ ከጎጂ ልማዶቼ መላቀቅ እንደማልችል ተገነዘብኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ግልጽ ነው፤ መሰናክል ከሚሆኑብኝ ነገሮች ለመላቀቅ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ነበረብኝ።​—ማቴዎስ 5:30

ለሙዚቃ ከፍተኛ ፍቅር ነበረኝ፤ በመሆኑም ካደረግኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ የከበደኝ ሄቪ ሜታል የሚባለውን ሙዚቃ መተው ነው። ይሁን እንጂ በጉባኤ ውስጥ ባሉት ጓደኞቼ እርዳታ ውሎ አድሮ ከዚህ ዓይነት ሙዚቃ ተላቀቅኩ። ከልክ በላይ መጠጣትና ዕፅ መውሰድ አቆምኩ። በተጨማሪም ፀጉሬን ተቆረጥሁ፣ ጢሜን ተላጨሁ እንዲሁም ጥቁር ልብስ ብቻ መልበሴን ተውኩ። ለሱዛን ፀጉሬን መቆረጥ እንደምፈልግ ስነግራት እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳኝ ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈለገች። “በመንግሥት አዳራሹ ምን እንደሚከናወን ለመመልከት አብሬህ እሄዳለሁ!” አለችኝ። በመንግሥት አዳራሹ ያየችውን ነገር ስለወደደችው ብዙም ሳይቆይ እሷም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ውሎ አድሮም እኔና ሱዛን ተጋባን። በ2008 ሁለታችንም ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን። አሁን ከእናቴ ጋር ይሖዋን በአንድነት ማምለክ በመቻላችን ደስተኞች ነን።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ዓለም ከሚሰጠው እውነተኛ ያልሆነ ደስታ እንዲሁም ከከዳተኛ ጓደኞች ተገላግያለሁ። አሁንም ቢሆን ሙዚቃ እወዳለሁ፤ ይሁን እንጂ በምርጫዬ ጠንቃቃ ነኝ። የቤተሰቤን አባላትና ሌሎችን፣ በተለይም ወጣቶችን ለመርዳት ተሞክሮዬን አካፍላቸዋለሁ። ይህ ዓለም የሚያቀርበው አብዛኛው ነገር ማራኪ መስሎ ሊታይ ቢችልም እንደ “ጉድፍ” መሆኑን እንዲገነዘቡ ልረዳቸው እጥራለሁ።​—ፊልጵስዩስ 3:8

ፍቅርና ሰላም በሰፈነበት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ታማኝ ጓደኞች አግኝቻለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ ይሖዋ በመቅረቤ አባት አግኝቻለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወደ ይሖዋ መመለስ የቻልኩት እሱ ወደ ራሱ መልሶ ስለሳበኝ መሆኑን ሳስበው ልቤ በጥልቅ ይነካል”