በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ቤተሰቡን ጠብቋል፣ ተንከባክቧል፣ ኃላፊነቱን ተወጥቷል

ቤተሰቡን ጠብቋል፣ ተንከባክቧል፣ ኃላፊነቱን ተወጥቷል

ዮሴፍ የቀረውን ጓዝ ሰብስቦ በአህያው ላይ ጫነው። ገና ጎህ ያልቀደደባትን የቤተልሔም ከተማ ዘወር ብሎ ከቃኘ በኋላ ጉዞውን ለመጀመር አህያውን ቸብ እያደረገ ሲነዳ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በዚህ ወቅት ወደ ግብፅ ስለሚያደርገው ረጅም ጉዞ እያሰበ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ቤተሰቡ በግብፅ ለአገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ ከመሆኑም ሌላ የሕዝቡ ቋንቋም ሆነ ባሕል አዲስ እንደሚሆንበት ግልጽ ነው። ይህ ትንሽ ቤተሰብ ከዚህ ሁሉ ለውጥ ጋር የሚላመደው እንዴት ይሆን?

ዮሴፍ አሳዛኙን ዜና ለውድ ባለቤቱ ለማርያም መናገር ቀላል ባይሆንለትም እንደምንም ራሱን አደፋፍሮ ነገራት። ንጉሥ ሄሮድስ ሕፃን ልጃቸውን ሊገድለው እንደሚፈልግ አምላክ በመልአኩ አማካኝነት በሕልም እንዳሳየው ገለጸላት። በአፋጣኝ መሸሽ ነበረባቸው። (ማቴዎስ 2:13, 14) ማርያም ሁኔታው በጣም ረብሿታል። ክፉና ደግ የማያውቀውን እንቦቃቅላ ልጇን ለመግደል የሚፈልግ ሰው እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ ለማርያምም ሆነ ለዮሴፍ ፈጽሞ ሊገባቸው የሚችል ነገር አይደለም። ያም ቢሆን በይሖዋ በመተማመን ለመሸሽ ተዘጋጁ።

የሚጠብቃቸውን ጉድ ያላወቁት የቤተልሔም ነዋሪዎች አገር ሰላም ብለው አንቀላፍተው እያለ ዮሴፍና ማርያም ጨለማን ተገን በማድረግ ኢየሱስን ይዘው ከከተማዋ ሹልክ ብለው ወጡ። ከዚያም ቤተሰቡ ወደ ደቡብ የሚያደርገውን ጉዞ ተያያዘው፤ ጀምበሯም በስተምሥራቅ ብቅ እያለች ነው። ዮሴፍ ጉዞውን እየቀጠለ ሲሄድ ከፊቱ የሚጠብቀው ነገር ሳያሳስበው አይቀርም። ዝቅተኛ ኑሮ ያለው አንድ አናፂ፣ ቤተሰቡን እጅግ ኃያል ከሆኑ ጠላቶች መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው? ደግሞስ የቤተሰቡን ፍላጎት ሁልጊዜ ማሟላት ይችል ይሆን? ይህን ልዩ የሆነ ልጅ ተንከባክቦ እንዲያሳድግ ይሖዋ አምላክ የሰጠውን ከባድ ኃላፊነት በታማኝነት መወጣት ይችል ይሆን? በእርግጥም ዮሴፍ እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያሳስቡት ምንም አያስገርምም። ያጋጠሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት እንደተወጣቸው አንድ በአንድ መመልከታችን በዛሬው ጊዜ ያሉ አባቶችም ሆኑ ሁላችንም ዮሴፍን በእምነቱ መምሰል የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል።

ዮሴፍ ቤተሰቡን ከአደጋ ጠብቋል

ይህ ሁሉ ከመሆኑ ከተወሰኑ ወራት በፊት፣ ዮሴፍ በሚኖርባት በናዝሬት ከተማ ከሄሊ ልጅ ጋር ተጫጭቶ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ ግን በሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነገር ተከሰተ። ዮሴፍ እስከሚያውቀው ድረስ ማርያም ንጹሕ እና ታማኝ ሴት ናት። ይሁን እንጂ ፀንሳ ተገኘች! በዚህ ጊዜ ዮሴፍ፣ እጮኛውን ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በሚስጥር ሊፈታት አሰበ። * ይሁንና አንድ መልአክ በሕልም ታይቶት ማርያም ያረገዘችው በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ ገለጸለት። መልአኩ አክሎም የሚወለደው ልጅ “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” በማለት ነገረው። በተጨማሪም “እሷን ወደ ቤት ለመውሰድ አትፍራ” በማለት ዮሴፍን አረጋጋው።​—ማቴዎስ 1:18-21

ጻድቅና ታዛዥ ሰው የነበረው ዮሴፍ መልአኩ እንደነገረው አደረገ። ዮሴፍ በዚህ ጊዜ የተቀበለው ኃላፊነት በጣም ከባድ ነበር፤ ማርያም ያረገዘችው ልጅ የእሱ ባይሆንም እንኳ ለአምላክ እጅግ ውድ የሆነውን ይህን ልጅ ተንከባክቦ እንዲያሳድግ ይጠበቅበት ነበር። ቆየት ብሎም ዮሴፍ፣ የንጉሠ ነገሥቱን አዋጅ በመታዘዝ ነፍሰ ጡር የነበረችውን ባለቤቱን ይዞ ለምዝገባ ወደ ቤተልሔም ሄደ። ልጁም እዚያው ቤተልሔም ተወለደ። *

ዮሴፍ ከቤተልሔም ወደ ናዝሬት አልተመለሰም። ከዚህ ይልቅ ከኢየሩሳሌም ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በቤተልሔም ከቤተሰቡ ጋር መኖሩን ቀጠለ። ዮሴፍና ማርያም ድሆች ነበሩ፤ ያም ቢሆን ዮሴፍ፣ ሚስቱ ማርያምና ኢየሱስ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ እንዲሁም እነሱን ከአደጋ ለመጠበቅ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ በአንዲት አነስተኛ ቤት ውስጥ መኖር ጀመሩ። ውሎ አድሮ ግን የቤተሰባቸውን ሕይወት በድንገት የሚለውጥ ነገር እንደገና አጋጠማቸው፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አንድ ዓመት ሳያልፈው አይቀርም።

አንድ ቀን የተወሰኑ ሰዎች ወደ ቤታቸው መጡ፤ እነዚህ ሰዎች ከምሥራቅ ምናልባትም ርቃ ከምትገኘው ከባቢሎን የመጡ ኮከብ ቆጣሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ወደ ዮሴፍና ማርያም ቤት የመጡት አንድ ኮከብ እየመራቸው ሲሆን ወደፊት የአይሁድ ንጉሥ የሚሆነውን ሕፃን ለማየት ፈልገው ነበር። ሰዎቹ ለቤተሰቡ ጥልቅ አክብሮት ነበራቸው።

ሆኖም እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፣ ሕፃኑን ኢየሱስን ትልቅ አደጋ ላይ ጥለውታል። እየመራ ያመጣቸው ኮከብ በመጀመሪያ የወሰዳቸው ወደ ቤተልሔም ሳይሆን ወደ ኢየሩሳሌም ነበር። እዚያም ሲደርሱ ወደፊት የአይሁድ ንጉሥ የሚሆነውን ሕፃን እየፈለጉ እንደሆነ ገለጹ፤ ክፉው ንጉሥ ሄሮድስ ይህን ሲሰማ በቅናት ድብን አለ።​—“አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . . ‘ኮከቡን’ የላከው ማን ነው?” የሚለውን በገጽ 29 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

ደግነቱ ከሄሮድስ የሚበልጥ ኃይል ያለው አካል አለ። ቀጥሎ ከተከናወኑት ሁኔታዎች ይህን በግልጽ ማየት ይቻላል። ጎብኚዎቹ በምላሹ ምንም እንዲደረግላቸው ሳይጠይቁ ለቤተሰቡ ስጦታዎችን ሰጧቸው። ዮሴፍና ማርያም እንደ “ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ” ያሉ ውድ ነገሮች በድንገት ሲያገኙ ምንኛ ተገርመው ይሆን! ኮከብ ቆጣሪዎቹ ሲፈልጉት የነበረውን ሕፃን የት እንዳገኙት ለንጉሥ ሄሮድስ ሊነግሩት አስበው ነበር። ሆኖም በዚህ ጊዜ ይሖዋ ጣልቃ ገባ። ኮከብ ቆጣሪዎቹ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በሕልም አማካኝነት አዘዛቸው።​—ማቴዎስ 2:1-12

በተጨማሪም ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከሄዱ ብዙም ሳይቆይ ዮሴፍ ከይሖዋ መልአክ ማስጠንቀቂያ ደረሰው፤ መልአኩ ዮሴፍን “ሄሮድስ ሕፃኑን ፈልጎ ሊገድለው ስላሰበ ተነስ፣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤ እኔ እስካሳውቅህም ድረስ እዚያው ቆይ” አለው። (ማቴዎስ 2:13) ስለዚህ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንዳየነው ዮሴፍ የታዘዘውን በመስማት በአፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። ከምንም ነገር በላይ የልጁን ደኅንነት በማስቀደም ቤተሰቡን ወደ ግብፅ ይዞ ሄደ። እነዚያ አረማውያን ኮከብ ቆጣሪዎች ለቤተሰቡ ውድ ስጦታዎች ስለሰጧቸው በግብፅ በእንግድነት ለመቀመጥ በቂ ንብረት አግኝተው ነበር።

ከጊዜ በኋላ የአዋልድ ተረቶችና አፈ ታሪኮች ወደ ግብፅ የተደረገውን ጉዞ አዛብተው በማቅረብ ሕፃኑ ኢየሱስ በተአምር ጉዞውን እንዳሳጠረው፣ ሽፍቶች ጉዳት እንዳያደርሱባቸው እንዳደረገ አልፎ ተርፎም የተምር ዛፎች ዘንበል እንዲሉ በማድረግ እናቱ ፍሬዎቹን እንድትለቅም እንዳስቻላት ይናገራሉ። * እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ ቤተሰቡ ወደዚያ ባዕድ አገር ያደረገው ጉዞ ረጅምና አድካሚ ነበር።

ወላጆች ከዮሴፍ ሊማሩ የሚችሉት ብዙ ነገር አለ። ዮሴፍ ቤተሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል ያላንዳች ማንገራገር ሥራውን ትቷል እንዲሁም የግል ምቾቱን መሥዋዕት አድርጓል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቤተሰቡን የመንከባከብ ቅዱስ አደራ ከይሖዋ እንደተሰጠው ተሰምቶታል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት አደገኛ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው፤ ዓለም ልጆቻቸውን ለአደጋ በሚያጋልጡ፣ በሚበክሉ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን በሚያበላሹ ተጽዕኖዎች የተሞላ ነው። ልጆቻቸውን እንዲህ ካሉ አደጋዎች ለመጠበቅ ልክ እንደ ዮሴፍ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉና ቆራጥ እርምጃ የሚወስዱ እናቶችና አባቶች ሊመሰገኑ ይገባል!

ዮሴፍ ቤተሰቡን ተንከባክቧል

ቤተሰቡ በግብፅ የነበራቸው ቆይታ ያን ያህል ረጅም የነበረ አይመስልም፤ ወደዚያ ከሄዱ ብዙም ሳይቆይ መልአኩ፣ ሄሮድስ መሞቱን ለዮሴፍ ነገረው። በመሆኑም ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ። ይሖዋ፣ ልጁን “ከግብፅ” እንደሚጠራው አስቀድሞ በትንቢት አስነግሮ ነበር። (ማቴዎስ 2:15) ዮሴፍም ይህ ትንቢት እንዲፈጸም አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ይሁንና ይህ ቤተሰብ አሁን የት ሊኖር ነው?

ዮሴፍ ጠንቃቃ ሰው ነበር። ሄሮድስን ተክቶ የነገሠው አርኬላዎስ እንደሆነ ሲሰማ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ፈራ፤ አርኬላዎስ እንደ አባቱ ጨካኝና ነፍሰ ገዳይ በመሆኑ ዮሴፍ እሱን መፍራቱ የተገባ ነበር። አምላክ በሰጠው መመሪያ መሠረት ዮሴፍ ከኢየሩሳሌምና በዚያ ሊያጋጥመው ከሚችለው አደጋ ለመራቅ በስተሰሜን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ቤተሰቡን ይዞ ሄደ። እሱና ማርያም ልጆቻቸውን ያሳደጉት በዚያ ነው።​—ማቴዎስ 2:19-23

ዮሴፍና ማርያም ቀለል ያለ ሕይወት ይመሩ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነበር ማለት ግን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ አናጺ እንደነበረ ይናገራል፤ ይህ ቃል፣ ዮሴፍ ከእንጨት ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን ያከናውን እንደነበር ያመለክታል። ይህም ዛፍ መቁረጥንና ማጓጓዝን ከዚያም እንጨቱን በማስተካከል ቤቶችን፣ ጀልባዎችን፣ አነስተኛ ድልድዮችን፣ ጋሪዎችን፣ ከእንጨት የተሠሩ ጎማዎችን፣ ቀንበሮችንና ማንኛውንም ዓይነት የእርሻ መሣሪያዎችን መሥራትን ይጨምራል። (ማቴዎስ 13:55) አናጺነት ከባድ የጉልበት ሥራ ነበር። በጥንት ዘመን የነበሩ አናጺዎች ብዙውን ጊዜ የሚሠሩት በትንሿ ቤታቸው ደጃፍ ላይ አሊያም ከቤታቸው አጠገብ ባለ ክፍል ውስጥ ነበር።

ዮሴፍ የተለያዩ መሣሪያዎችን ይጠቀም የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹ ከአባቱ የወረሳቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። ምናልባትም ስኳድራ፣ ቱንቢ፣ ጠመኔ፣ መጥረቢያ፣ መጋዝ፣ ፋስ፣ የብረት መዶሻ፣ የእንጨት መዶሻ፣ መሮዎች፣ መሰርሰሪያ (ደጋንን በማጥበቅና በማላላት የሚሠራ)፣ የተለያዩ ዓይነት ማጣበቂያዎች እንዲሁም ምስማሮች (ዋጋቸው ውድ ቢሆንም) ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል።

ትንሹ ኢየሱስ፣ አሳዳጊ አባቱ የሚሠራውን በንቃት ሲከታተል በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ዓይኖቹን በዮሴፍ ላይ ተክሎ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ሲመለከት በአባቱ የፈረጠመ ጡንቻ፣ ጠንካራ ክንዶችና በእጆቹ ቅልጥፍና እንዲሁም በብልሃት በሚያከናውነው ሥራ እንደሚደነቅ ጥርጥር የለውም። ምናልባትም ዮሴፍ፣ በደረቀ የዓሣ ቆዳ በመጠቀም ሻካራ የሆነ እንጨትን እንደ ማለስለስ ያሉ ቀላል ሥራዎች እንዴት መሥራት እንደሚቻል ለታዳጊው ልጁ ሳያሳየው አልቀረም። ከዚህም ሌላ በሚጠቀምባቸው የተለያዩ እንጨቶች ለአብነት ያህል በሾላ፣ በኦክ ወይም በወይራ መካከል ያለውን ልዩነት ለኢየሱስ አስተምሮት ሊሆን ይችላል።

በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ዮሴፍ በፈረጠሙ ክንዶቹ ዛፎችን መቁረጥ፣ ትላልቅ ግንዶችን ፈልጦ ማዘጋጀት ብሎም አንድ ላይ አገጣጥሞ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መሥራት የሚችል ጠንካራ ሰው ብቻ ሳይሆን እናቱንም ሆነ እሱንና ታናናሾቹን እቅፍ አድርጎ የሚያበረታታና የሚያጽናና ርኅሩኅ አባት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ የዮሴፍና የማርያም ቤተሰብ እያደገ የሄደ ሲሆን ከኢየሱስ ሌላ ቢያንስ ስድስት ልጆች ወለዱ። (ማቴዎስ 13:55, 56) ዮሴፍ እነዚህን ሁሉ ልጆች ተንከባክቦ ለማሳደግ ጠንክሮ መሥራት ነበረበት።

ይሁን እንጂ ዮሴፍ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝ የሚገባው ኃላፊነቱ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደሆነ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ልጆቹን ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ሕጎቹ ለማስተማር ጊዜ ይመድብ ነበር። እሱና ማርያም ልጆቻቸውን በአካባቢው ወደሚገኝ ምኩራብ አዘውትረው ይወስዷቸው ነበር፤ በዚያም ሕጉ ጮክ ተብሎ እየተነበበ ይብራራል። ከምኩራብ ሲመለሱ ኢየሱስ በርካታ ጥያቄዎችን ሳያዥጎደጉድበት አይቀርም፤ ዮሴፍም እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ የልጁን መንፈሳዊ ጥማት ለማርካት የተቻለውን ሁሉ አድርጎ መሆን አለበት። በተጨማሪም ዮሴፍ በኢየሩሳሌም ወደሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት ቤተሰቡን ይወስዳቸው ነበር። ዮሴፍና ቤተሰቡ 113 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርቀት ተጉዘው በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው የማለፍ በዓል ላይ ለመገኘትና ወደ ቤታቸው ለመመለስ ሁለት ሳምንት ሳይፈጅባቸው አይቀርም።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያደርጋሉ። እነዚህ ወላጆች ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ያላቸውን ነገር ሁሉ ለልጆቻቸው ይሰጣሉ፤ ሆኖም ቁሳዊ ነገሮችን ጨምሮ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ልጆቻቸውን በመንፈሳዊ ማሠልጠን እንደሆነ ይገነዘባሉ። ልጆቻቸውን በየሳምንቱ ወደሚደረጉትም ሆነ ወደ ትላልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመውሰድ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። እንደ ዮሴፍ ሁሉ እነዚህ ወላጆችም ለልጆቻቸው ሲሉ የሚከፍሉት ይህ መሥዋዕትነት ከሁሉ የተሻለ ውጤት እንዳለው ያውቃሉ።

“በጣም ተጨንቀን”

ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ እያለ ዮሴፍ እንደተለመደው ቤተሰቡን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዳቸው። አስደሳች በሆነው በዚህ የማለፍ በዓል ወቅት በርካታ ቤተሰቦች በጸደይ ልምላሜ የተዋቡትን ገጠራማ አካባቢዎች እያቋረጡ አንድ ላይ ይጓዛሉ። ብዙዎቹ አይሁዳውያን ከፍ ብላ ወደምትታየው ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረቡ ተወዳጅ የሆኑትን የመዓርግ (ወደ ላይ የመውጣት) መዝሙሮች ይዘምሩ ነበር። (መዝሙር 120 እስከ 134) እንዲህ ባሉት ወቅቶች ከተማዋ በመቶ ሺህዎች በሚቆጠር ሕዝብ ሳትሞላ አትቀርም። ከበዓሉ በኋላ፣ አንድ ላይ የሚጓዙት ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው የመልስ ጉዞ ማድረግ ይጀምራሉ። ዮሴፍና ማርያም፣ ትኩረታቸውን የሚሹ ብዙ ነገሮች ስለነበሩ ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስ አብሯቸው እንዳልሆነ አላስተዋሉም፤ ኢየሱስ ከሌሎች ጋር ምናልባትም ከዘመዶቻቸው ጋር እየተጓዘ መስሏቸው ነበር። ኢየሱስ አብሯቸው አለመሆኑን የተገነዘቡት ከኢየሩሳሌም የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዙ በኋላ ነበር፤ በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጡ!​—ሉቃስ 2:41-44

ዮሴፍና ማርያም በጭንቀት ተውጠው እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ ልጃቸውን እየተጣሩ ወዲያና ወዲህ ሲራወጡ ከተማዋ ምን ያህል ጭር ያለች እንደምትሆንባቸው ልትገምት ትችላለህ። ልጁ የት ገብቶ ይሆን? ለሦስት ቀናት ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም፤ በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ከይሖዋ የተቀበለውን ቅዱስ አደራ እንዳልጠበቀ ማሰብ ጀምሮ ይሆን? እነዚህ ወላጆች በስተመጨረሻም ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱ። ቤተ መቅደሱን ሲያስሱ ከቆዩ በኋላ፣ ኢየሱስን በሕጉ የተካኑ ብዙ ምሁራን በተሰበሰቡበት አንድ ክፍል ውስጥ በመካከላቸው ተቀምጦ አዩት! በዚህ ጊዜ ዮሴፍና ማርያም ምን ያህል እፎይ እንዳሉ እስቲ አስበው!​—ሉቃስ 2:45, 46

ኢየሱስ ምሁራኑን እያዳመጣቸው እንዲሁም የማወቅ ጉጉት ስለነበረው ጥያቄዎችን እየጠየቃቸው ነበር። ሰዎቹም በልጁ ማስተዋልና በመልሶቹ ተደንቀው ነበር። ማርያምና ዮሴፍ ግን በጣም ደንግጠዋል። ዘገባው ዮሴፍ የተናገረው ነገር እንዳለ አይገልጽም። ማርያም የተናገረችው ልብ የሚነካ ሐሳብ ግን የሁለቱንም ስሜት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል፤ “ልጄ፣ ምነው እንዲህ አደረግከን? እኔና አባትህ እኮ በጣም ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።​—ሉቃስ 2:47, 48

የአምላክ ቃል በዚህ አጭር ዘገባ አማካኝነት፣ ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ጫና በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንድንችል ያደርገናል። ፍጹም ልጅ ማሳደግ እንኳ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል! አደገኛ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ወላጅ መሆን ተነግሮ የማያልቅ ‘ጭንቀት’ ሊያስከትል ቢችልም ወላጆች እንዲህ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መገለጹ ያጽናናቸዋል።

ደግነቱ ኢየሱስ የቆየው በዓለም ላይ ከየትኛውም ቦታ ይበልጥ በሰማይ ወዳለው አባቱ ወደ ይሖዋ በጣም እንደቀረበ እንዲሰማው በሚያደርግ ስፍራ ሲሆን በዚያም በጉጉት እውቀት እየቀሰመ ነበር። በመሆኑም ለወላጆቹ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” በማለት ቅንነት የሚንጸባረቅበት መልስ ሰጣቸው።​—ሉቃስ 2:49

ዮሴፍ እነዚህን ቃላት ደጋግሞ ያስታውሳቸው እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ምናልባትም ኢየሱስ የተናገረውን ሲሰማ ልቡ በኩራት ተሞልቶ ሊሆን ይችላል። ደግሞስ በአደራ የተሰጠው ልጁ ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲህ እንዲሰማው ለማድረግ በትጋት ሲያስተምረው ኖሮ የለ? ኢየሱስ ገና በዚህ ለጋ ዕድሜው “አባት” የሚለው ቃል ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርበት ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲኖረው ዮሴፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ግልጽ ነው።

አንተም አባት ከሆንክ ልጆችህ አፍቃሪና ተንከባካቢ አባት ምን ዓይነት እንደሆነ እንዲያውቁ የመርዳት ትልቅ መብት እንዳለህ ትገነዘባለህ? እንዲሁም የእንጀራ ልጆች ወይም የማደጎ ልጆች ካሉህ ዮሴፍ የተወውን ምሳሌ በማስታወስ እያንዳንዱን ልጅ ልዩና ውድ እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። ልጆችህ በሰማይ ወዳለው አባታቸው፣ ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲቀርቡ እርዳቸው።

ዮሴፍ ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል

መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በኋላ ስለ ዮሴፍ የሚነግረን ብዙ ባይሆንም ስለ እሱ የምናገኘውን ሐሳብ በጥልቀት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ ለወላጆቹ “ይታዘዛቸው” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በተጨማሪም “በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ [እንደሄደ]” እናነባለን። (ሉቃስ 2:51, 52) እነዚህ ጥቅሶች ስለ ዮሴፍ ምን ይገልጹልናል? ብዙ ነገሮችን ይነግሩናል። ዮሴፍ በቤተሰቡ ውስጥ የራስነት ቦታውን ይዞ እንደቀጠለ እንረዳለን፤ እንዲህ የምንለው ፍጹም የነበረው ልጁ የዮሴፍን ሥልጣን እንደሚያከብርና ለሥልጣኑም እንደሚገዛ ስለተገለጸ ነው።

ኢየሱስ በጥበብም እያደገ እንደሄደ ጥቅሱ ይጠቁማል። በዚህ ረገድ ዮሴፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚያ ዘመን አይሁዶች፣ ጥበበኛ መሆን የሚችሉት ዘና ያለ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የሚገልጽ አንድ ጥንታዊ አባባል ነበራቸው። እንደ አናጺዎች፣ ገበሬዎችና አንጥረኞች የመሳሰሉት ባተሌ የእጅ ሞያተኞች ‘ስለ ፍትሕ እንደማያውቁና መፍረድ እንደማይችሉ’ እንዲሁም “ምሳሌዎች በሚነገሩበት ቦታ [እንደማይገኙ]” ይነገር ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ ይህ አባባል ትክክል እንዳልሆነ አጋልጧል። አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ ዝቅተኛ ኑሮ የሚመራ አናጺ የነበረ ቢሆንም ስለ ይሖዋ “ፍትሕና ፍርድ” ጥሩ አድርጎ ሲያስተምር ኢየሱስ ልጅ እያለ በተደጋጋሚ ሰምቶት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!

ኢየሱስ በአካልም እያደገ እንዲሄድ ዮሴፍ አስተዋጽኦ እንዳደረገ የሚያሳይ ማስረጃ እናገኛለን። ኢየሱስ በልጅነቱ ጥሩ እንክብካቤ በማግኘቱ ሲያድግ ጠንካራና ጤነኛ ሰው ሊሆን ችሏል። ከዚህም ሌላ ዮሴፍ ልጁን በሙያው የተካነ እንዲሆን አሠልጥኖታል። ኢየሱስ የአናጺው ልጅ ብቻ ሳይሆን “አናጺው” በመባልም ይታወቅ ነበር። (ማርቆስ 6:3) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ዮሴፍ የሰጠው ሥልጠና ውጤታማ ነበር። የቤተሰብ ራሶች፣ ልጆቻቸው ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ በማድረግ እንዲሁም ራሳቸውን ችለው ለመኖር የሚያስችላቸው ሥልጠና በመስጠት ዮሴፍን መምሰላቸው የጥበብ እርምጃ ነው።

ኢየሱስ በ30 ዓመቱ እንደተጠመቀ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በኋላ ስለ ዮሴፍ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ማስረጃው እንደሚጠቁመው ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ ማርያም መበለት ሆና ነበር። (“ዮሴፍ የሞተው መቼ ነው?” የሚለውን በገጽ 27 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ሆኖም ዮሴፍ ቤተሰቡን ከአደጋ የጠበቀ፣ የሚያስፈልጋቸውን ያሟላና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ኃላፊነቱን በታማኝነት የተወጣ ግሩም ምሳሌ የሚሆን አባት እንደነበረ የሚያሳይ አሻራ ትቶ አልፏል። ማንኛውም አባት፣ ማንኛውም የቤተሰብ ራስ አልፎ ተርፎም ማንኛውም ክርስቲያን ዮሴፍን በእምነቱ ሊመስለው ይገባል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 በዚያ ዘመን፣ የተጫጩ ሰዎች የተጋቡ ያህል ተደርገው ይታዩ ነበር።

^ አን.8 በጥቅምት 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በእምነታቸው ምሰሏቸው​—‘በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.14 ኢየሱስ የመጀመሪያውን ተአምር የፈጸመው ከተጠመቀ በኋላ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ዮሐንስ 2:1-11) ስለ አዋልድ የወንጌል ዘገባዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአዋልድ ወንጌሎች​—ስለ ኢየሱስ የተሰወሩ እውነቶችን ይዘዋል?” የሚለውን በገጽ 18 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዮሴፍ የሞተው መቼ ነው?

ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ እያለ ዮሴፍ በሕይወት እንደነበረ እናውቃለን። ብዙ አይሁዳውያን ወጣቶች የአባታቸውን ሙያ መማር የሚጀምሩት በዚህ ዕድሜ ሲሆን በ15 ዓመታቸው የአባታቸው ረዳት ይሆናሉ። ዮሴፍ የሞተው ለኢየሱስ የአናጺነት ሙያ ካስተማረው በኋላ እንደሆነ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። ኢየሱስ በ30 ዓመቱ አገልግሎቱን ሲጀምር ዮሴፍ በሕይወት ነበር? ዘገባው እንዲህ ለማለት አያስደፍርም። በዚያ ወቅት የኢየሱስ እናት እንዲሁም ወንድሞቹና እህቶቹ በሕይወት እንደነበሩ ቢጠቀስም ስለ ዮሴፍ ግን የተገለጸ ነገር የለም። እንዲያውም በአንድ ወቅት ኢየሱስ የዮሴፍ ልጅ ከመባል ይልቅ “የማርያም ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። (ማርቆስ 6:3) በተጨማሪም ማርያም፣ ባሏን ሳታማክር አንዳንድ ውሳኔዎች እንዳደረገች ተጠቅሷል። (ዮሐንስ 2:1-5) በጥንት ዘመን አንዲት ሴት ባሏ ካልሞተ በቀር እንዲህ ማድረጓ ያልተለመደ ነገር ነው። በመጨረሻም ኢየሱስ ሊሞት ሲል እናቱን እንዲንከባከባት አደራ የሰጠው ለሐዋርያው ዮሐንስ ነበር። (ዮሐንስ 19:26, 27) ዮሴፍ በሕይወት ቢኖር ኖሮ እንዲህ ማድረግ አያስፈልገውም። ከእነዚህ ነጥቦች አንጻር ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ ገና ወጣት እያለ እንደሆነ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። ኢየሱስ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን እስከተጠመቀበት ጊዜ ድረስ የአናጺነት ሥራውን ተረክቦ ቤተሰቡን እንደተንከባከበ ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ ልጁን ከአደጋ ለመጠበቅ ቆራጥና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ እርምጃ ወስዷል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ጠንክሮ ሠርቷል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ይሖዋን ለማምለክ ዘወትር ቤተሰቡን ይዞ ይሄድ ነበር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ ልጁን አናጺ እንዲሆን አሠልጥኖታል