በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክህደት ጊዜያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ የምልክቱ ገጽታ!

ክህደት ጊዜያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ የምልክቱ ገጽታ!

ክህደት ጊዜያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ የምልክቱ ገጽታ!

“ታማኞች፣ ጻድቃንና ነቀፋ የሌለብን ሆነን [ተገኝተናል]።”​—1 ተሰ. 2:10

እነዚህን ዋና ዋና ነጥቦች ለይተህ ለማውጣት ሞክር፦

ደሊላ፣ አቤሴሎምና ይሁዳ ከፈጸሙት የክህደት ተግባር ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት እናገኛለን?

ዮናታንም ሆነ ጴጥሮስ ያሳዩትን የታማኝነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ለትዳር ጓደኛችንም ሆነ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

1-3. (ሀ) ዘመናችንን ለይተው ከሚያሳውቁ የምልክቱ ገጽታዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው? ምን ፍቺስ ተሰጥቶታል? (ለ) ለየትኞቹ ሦስት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

ደሊላን፣ አቤሴሎምንና የአስቆሮቱ ይሁዳን የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው? ሁሉም ታማኝነታቸውን አጓድለዋል፤ ደሊላ ይወዳት ለነበረው ለመስፍኑ ሳምሶን፣ አቤሴሎም ለአባቱ ለንጉሥ ዳዊት፣ ይሁዳ ደግሞ ለጌታው ለክርስቶስ ኢየሱስ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሦስቱም የፈጸሙት ክፉ ድርጊት በሌሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል! ይሁንና የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ማንሳታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 አንዲት ደራሲ በዛሬው ጊዜ ከተስፋፉት መጥፎ ድርጊቶች መካከል አንዱ ክህደት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ የሚጠበቅ ነገር ነው። ኢየሱስ ‘የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት’ ሲናገር “አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል” ብሏል። (ማቴ. 24:3, 10) “መክዳት” ሲባል “በማታለል ወይም ታማኝነትን በማጉደል አንድን ሰው ለሌላ አሳልፎ መስጠት ወይም በጠላት እጅ እንዲወድቅ ማድረግ” ማለት ነው። እንዲህ ያለ የእምነት ማጉደል ድርጊት መስፋፋቱ የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ መሆኑን ያረጋግጣል። ጳውሎስ በዚህ ዘመን፣ ሰዎች ‘ታማኝ እንደማይሆኑ’ እንዲሁም “ከዳተኞች” እንደሚሆኑ ጠቅሷል። (2 ጢሞ. 3:1, 2, 4) ደራሲዎችና የፊልም ጽሑፍ አዘጋጆች የክህደት ድርጊቶችን በጽሑፎቻቸውም ሆነ በፊልሞቻቸው ላይ በጣም አስደሳችና ማራኪ አድርገው ለማቅረብ ቢሞክሩም በገሃዱ ዓለም ግን ታማኝነትን ማጉደል ወይም ክህደት መከራና ሥቃይ ያስከትላል። በእርግጥም እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ዘመናችንን ለይተው የሚያሳውቁ የምልክቱ ገጽታዎች ናቸው!

3 ታማኝነታቸውን ስላጓደሉ ሰዎች ከሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ለሌሎች ታማኝ መሆናቸውን ያስመሠከሩ ሰዎች ከተዉት ምሳሌ ምን ቁም ነገር እናገኛለን? ምንጊዜም ታማኞች መሆን ያለብንስ ለማን ነው? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች

4. ደሊላ በሳምሶን ላይ የክህደት ድርጊት የፈጸመችው እንዴት ነው? ድርጊቱ ጭካኔ የተሞላበት ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

4 እስቲ በመጀመሪያ አሻጥረኛ የሆነችውን የደሊላን ሁኔታ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ሳምሶን ደሊላን እንደወደዳት ይናገራል። ሳምሶን የአምላክን ሕዝብ በመወከል ፍልስጤማውያንን የመዋጋት ፍላጎት ነበረው። ይሁንና አምስት የፍልስጤማውያን ገዥዎች ሳምሶንን ለመግደል አሴሩ፤ እነዚህ ሰዎች ደሊላ ለሳምሶን ጽኑ ፍቅር እንደሌላት ስለተረዱ ሳይሆን አይቀርም ሳምሶን ማንም የማይቋቋመው ጥንካሬ ሊኖረው የቻለበትን ሚስጥር የምትነግራቸው ከሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉቦ እንደሚሰጧት ነገሯት። የገንዘብ ፍቅር ያናወዛት ደሊላ ግብዣውን ተቀበለች፤ ይሁንና ሚስጥሩን ለማወቅ ሦስት ጊዜ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ። በመሆኑም “ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው።” በዚህም የተነሳ ‘በሕይወት መኖሩን እስከ መጥላት ደረሰ።’ በመጨረሻም፣ ፀጉሩን ተቆርጦ እንደማያውቅና ቢቆረጥ ግን ኃይሉን እንደሚያጣ ነገራት። * ደሊላም፣ ሳምሶን በጭኗ ላይ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ ፀጉሩን ከቆረጠችው በኋላ በእሱ ላይ የፈለጉትን እንዲያደርጉበት ለጠላቶቹ አሳልፋ ሰጠችው። (መሳ. 16:4, 5, 15-21) እንዴት ያለ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው! ደሊላ ስግብግብ በመሆኗ የሚወዳትን ሰው አሳልፋ ሰጥታለች።

5. (ሀ) አቤሴሎም ለዳዊት ታማኝ እንዳልሆነ ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ ስለ እሱ ምን ይጠቁማል? (ለ) አኪጦፌል ከሃዲ በመሆኑ ዳዊት ምን ተሰማው?

5 እስቲ ከዚህ በመቀጠል፣ በጣም መሠሪ የሆነውን የአቤሴሎምን ሁኔታ እንመልከት። የሥልጣን ጥም የተጠናወተው አቤሴሎም የአባቱን የንጉሥ ዳዊትን ዙፋን ለመንጠቅ ቆርጦ ተነሳ። አቤሴሎም በመጀመሪያ የውሸት ተስፋ በመስጠትና ልባዊ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን በማሳየት “የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።” ለእነሱ የሚያስብና የሚጨነቅ ሰው መስሎ ለመታየት አቅፎ ይስማቸው ነበር። (2 ሳሙ. 15:2-6) ሌላው ቀርቶ የዳዊት የቅርብ አማካሪ የሆነውን የአኪጦፌልን ልብ ማሸፈት ችሏል፤ በዚህም የተነሳ አኪጦፌል ንጉሡን በመክዳት አድማውን ተቀላቀለ። (2 ሳሙ. 15:31) ዳዊት ይህ የክህደት ድርጊት ምን ያህል እንደጎዳው በ⁠መዝሙር 3 እና 55 ላይ ገልጿል። (መዝ. 3:1-8፤ መዝሙር 55:12-14ን አንብብ።) አቤሴሎም፣ ይሖዋ የሾመውን ንጉሥ ለመገልበጥ በማሴር ለይሖዋ ሉዓላዊነት ንቀት እንዳለው አሳይቷል። (1 ዜና 28:5) በመጨረሻ አቤሴሎም የጠነሰሰው ሴራ የከሸፈ ሲሆን በይሖዋ የተቀባው ዳዊትም በንግሥናው ቀጥሏል።

6. ይሁዳ ኢየሱስን የከዳው እንዴት ነው? ይሁዳ የሚለው ስም ለየትኛው ቃል አቻ ሆኖ ያገለግላል?

6 አሁን ደግሞ ከዳተኛው አስቆሮቱ ይሁዳ በክርስቶስ ላይ ያደረገውን ነገር እንመልከት። ኢየሱስ ከ12ቱ ሐዋርያቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የፋሲካን በዓል በሚያከብርበት ዕለት ሐዋርያቱን “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። (ማቴ. 26:21) በዚያው ምሽት ትንሽ ቆየት ብሎ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሳለ ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ “እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል” በማለት ነገራቸው። ወዲያው ይሁዳ ከግብረ አበሮቹ ጋር ወደ አትክልት ስፍራው መጣ፤ ከዚያም “በቀጥታ ወደ ኢየሱስ በመሄድ ‘ረቢ! ሰላም ለአንተ ይሁን’ ብሎ ሳም አደረገው።” (ማቴ. 26:46-50፤ ሉቃስ 22:47, 52) ይሁዳ፣ ክርስቶስ በጠላቶቹ እጅ እንዲወድቅ በማድረግ ‘ጻድቁን ሰው አሳልፎ ሰጠ።’ ለመሆኑ የገንዘብ ፍቅር ያሳበደው ይሁዳ ይህን ድርጊት ለመፈጸም የተዋዋለው በምን ያህል ነበር? በ30 የብር ሳንቲሞች ነበር! (ማቴ. 27:3-5) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይሁዳ የሚለው ስም “ከሃዲ” ለሚለው ቃል አቻ በመሆን ያገለግላል፤ በተለይ ደግሞ ወዳጁን የሚከዳን ሰው ለማመልከት ይሠራበታል። *

7. (ሀ) ከአቤሴሎምና ከይሁዳ (ለ) ከደሊላ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ከእነዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? አቤሴሎምም ሆነ ይሁዳ ይሖዋ በሾማቸው ላይ የክህደት ድርጊት በመፈጸማቸው መጨረሻቸው አላማረም። (2 ሳሙ. 18:9, 14-17፤ ሥራ 1:18-20) ደሊላም ብትሆን ስሟ ሲነሳ ብዙዎች ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው አታላይና ፍቅሯ ከአንገት በላይ የሆነች ሴት መሆኗ ነው። (መዝ. 119:158) ሥልጣን የመፈለግ ወይም የስግብግብነት አዝማሚያ በጥቂቱም ቢሆን በውስጣችን ካለ የይሖዋን ሞገስ እንዳናጣ እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ቶሎ ብለን ማስወገዳችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! በእርግጥም እነዚህ ምሳሌዎች ታማኝነት የማጉደልን መጥፎ ዝንባሌ እንድናስወግድ ግሩም ትምህርት ይሰጡናል።

በታማኝነታቸው የሚታወቁ ሰዎችን ምሳሌ ተከተሉ

8, 9. (ሀ) ዮናታን ለዳዊት ታማኝ ለመሆን ቃል የገባው ለምንድን ነው? (ለ) የዮናታንን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ስለሆኑ በርካታ ሰዎችም ይናገራል። እስቲ ከእነዚህ ውስጥ ከሁለቱ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመልከት፤ የመጀመሪያው ምሳሌያችን ለዳዊት ታማኝ መሆኑን ያስመሠከረው ዮናታን ነው። የንጉሥ ሳኦል የበኩር ልጅ የሆነው ዮናታን የአባቱን ዙፋን በመውረስ የእስራኤል ገዥ የመሆን አጋጣሚ ነበረው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ዮናታንን ሳይሆን ዳዊትን ነበር። በዚህ ጊዜ ዮናታን የይሖዋን ውሳኔ አክብሯል። በመሆኑም ዳዊትን እንደተቀናቃኝ በመቁጠር በእሱ ላይ ቂም ከመያዝ ይልቅ ነፍሱ “ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቈራኘች”፤ እንዲሁም ለእሱ ታማኝ ለመሆን ቃል ገባ። ሌላው ቀርቶ ልብሱን፣ ሰይፉን፣ ቀስቱንና መታጠቂያውን በመስጠት ንጉሥ መሆን የሚገባው ዳዊት መሆኑን አሳይቷል። (1 ሳሙ. 18:1-4) ዮናታን ዳዊትን ‘ለማበረታታት’ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፤ የገዛ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ በሳኦል ፊት ለዳዊት ጥብቅና እስከ መቆም ደርሷል። ዮናታን ለዳዊት ያለውን ታማኝነት ሲገልጽ “በእስራኤል ላይ ትነግሣለህ፤ እኔም ካንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ” ብሏል። (1 ሳሙ. 20:30-34፤ 23:16, 17) በእርግጥም ዮናታን ሲሞት ዳዊት ሐዘኑንና ለእሱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ የሐዘን እንጉርጉሮ ማሰማቱ ምንም አያስገርምም።​—2 ሳሙ. 1:17, 26

9 ዮናታን ታማኝ መሆን ያለበት ለማን እንደሆነ ግራ አልተጋባም። ሉዓላዊ ለሆነው ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የተገዛ ሲሆን ዳዊትን በአምላክ እንደተሾመ አምኖ በመቀበል በሙሉ ልቡ ደግፎታል። በተመሳሳይም ዛሬ፣ በጉባኤ ውስጥ ለየት ያሉ መብቶችን ባናገኝ እንኳ በመካከላችን ግንባር ቀደም ሆነው አመራር እንዲሰጡ የተሾሙ ወንድሞችን በደስታ መደገፍ ይኖርብናል።​—1 ተሰ. 5:12, 13፤ ዕብ. 13:17, 24

10, 11. (ሀ) ጴጥሮስ፣ ለኢየሱስ ታማኝ ሆኖ የቀጠለው ለምንድን ነው? (ለ) የጴጥሮስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሳንስ ምን መሆን ይገባዋል?

10 ታማኝ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን ሌላው ሰው ደግሞ ለኢየሱስ ታማኝ መሆኑን ያሳየው ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው። በአንድ ወቅት ክርስቶስ፣ መሥዋዕት አድርጎ በሚያቀርበው ሥጋውና ደሙ ላይ እምነት ማሳደር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ ለመግለጽ ሲል ለጆሮ ከበድ የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሞ ነበር፤ በዚህ ወቅት ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ የተናገረው ነገር ሰቅጥጧቸው ትተውት ሄዱ። (ዮሐ. 6:53-60, 66) በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ወደ 12ቱ ሐዋርያት በመዞር “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠ፦ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ አንተ የአምላክ ቅዱስ እንደሆንክ አምነናል፣ እንዲሁም አውቀናል።” (ዮሐ. 6:67-69) ታዲያ ጴጥሮስ ይህን ሲናገር ኢየሱስ ወደፊት የሚያቀርበውን መሥዋዕት አስመልክቶ የተናገረውን ነገር ሙሉ በሙሉ ተረድቶ ነበር? ላይሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ጴጥሮስ ቅቡዕ ለሆነው የአምላክ ልጅ ታማኝ ለመሆን ቆርጦ ነበር።

11 ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ እንደተሳሳተና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሐሳቡን እንደሚቀይር አስቦ ይሆን? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” እንዳለው በትሕትና አምኖ ተቀብሏል። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ “ታማኝና ልባም መጋቢ” በሚያቀርብልን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ላይ፣ ለመረዳት አዳጋች የሆነ ወይም ከእኛ አመለካከት ጋር የማይጣጣም ሐሳብ ስናገኝ ምን እናደርጋለን? ትንሽ ቆይቶ ይህ ሐሳብ ከእኛ አመለካከት ጋር በሚስማማ መንገድ ይስተካከላል ብለን ከመጠበቅ ይልቅ ሐሳቡን ለመረዳት ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።​—ሉቃስ 12:42ን አንብብ።

ለትዳር ጓደኛችሁ ምንጊዜም ታማኝ ሁኑ

12, 13. ክህደት በትዳር ውስጥ መግቢያ ቀዳዳ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? አንድ ሰው በትዳር ጓደኛው ላይ ክህደት ለመፈጸም ዕድሜው ምክንያት ሊሆነው የማይችለው እንዴት ነው?

12 ድርጊቱ በምንም መልኩ ቢፈጸም ክህደት ምንጊዜም መጥፎ ተግባር ነው፤ በመሆኑም እንዲህ ያለው ድርጊት የቤተሰባችንንም ሆነ የጉባኤውን ሰላምና አንድነት እንዲያደፈርስ መፍቀድ የለብንም። ይህን በአእምሯችን በመያዝ ለትዳር ጓደኛችንም ሆነ ለአምላክ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።

13 እጅግ ጎጂ ከሆኑ የክህደት ድርጊቶች አንዱ ምንዝር ነው። ምንዝር የሚፈጽም ሰው ለትዳር ጓደኛው ያለውን ታማኝነት የሚያጓድል ከመሆኑም በላይ ትኩረቱን በሌላ ሰው ላይ ያደርጋል። ክህደት የተፈጸመበት የትዳር ጓደኛ ድንገት በብቸኝነት ስሜት ይዋጣል፤ እንዲሁም ሕይወቱ ይመሰቃቀላል። በአንድ ወቅት በጣም ይዋደዱ በነበሩ ሰዎች መካከል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊከሰት የሚችለው እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ ወደዚህ የሚመራው የመጀመሪያው እርምጃ የትዳር ጓደኛሞቹ በስሜት እየተራራቁ መምጣታቸው ነው። የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ጋብርዬላ ቱርናቱሪ ይህን ሁኔታ ሲገልጹ “ለወዳጃችን ሙሉ ልባችንን በመስጠትና ባለመስጠት መሃል የምንዋልል ከሆነ ክህደት መግቢያ ቀዳዳ ያገኛል” ብለዋል። እንዲህ ዓይነቱ ከትዳር ጓደኛ እየራቁ የመምጣት ዝንባሌ በአንዳንዶች ሌላው ቀርቶ በመካከለኛ ዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ጭምር ታይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የ50 ዓመት ሰው ለ25 ዓመት በትዳር አብራው የኖረችውን ታማኝ ሚስቱን ፈቷል፤ ይህን ያደረገው ከአንዲት የወደዳት ሴት ጋር ለመኖር ሲል ነበር። አንዳንዶች ይህ ሁኔታ በዚህ ዕድሜ ላይ የሚከሰት የተለመደ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና እንዲህ ያለውን ድርጊት በዚህ ዕድሜ ላይ ሊያጋጥም የሚችል የሕይወት ክፍል እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው፤ ይህ የተለመደ የሕይወት ክፍል ሳይሆን ክህደት ነው። *

14. (ሀ) ይሖዋ በትዳር ጓደኛ ላይ ስለሚሠራ ሸፍጥ ምን ይሰማዋል? (ለ) ኢየሱስ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆንን አስመልክቶ ምን ብሏል?

14 ይሖዋ ቅዱስ ጹሑፋዊ ምክንያት ሳይኖራቸው ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ስለሚለያዩ ሰዎች ምን ይሰማዋል? አምላካችን ‘መፋታትን የሚጠላ’ ከመሆኑም በላይ በትዳር ጓደኛቸው ላይ በደል ለሚፈጽሙና የትዳር ጓደኛቸውን ጥለው ለሚሄዱ ሰዎች ያለውን ስሜት ጠንከር ባለ አነጋገር ገልጿል። (ሚልክያስ 2:13-16ን አንብብ።) ከይሖዋ አመለካከት ጋር በሚስማማ መልኩ ኢየሱስም አንድ ሰው፣ ታማኝ የሆነው የትዳር ጓደኛው ተማርሮ እንዲሄድ አድርጎ ወይም ራሱ ትቶ ሄዶ ምንም እንዳልተፈጠረ ሆኖ መመላለስ እንደማይችል አስተምሯል።​—ማቴዎስ 19:3-6, 9ን አንብብ።

15. በጋብቻ የተሳሰሩ ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን ታማኝነት ማጠናከር የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ታዲያ ያገቡ ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን ታማኝነት እንደጠበቁ መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? የአምላክ ቃል “በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ”፤ እንዲሁም “ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ” የሚል ምክር ይሰጣል። ይህ ምክር ለባሎች ብቻ ሳይሆን ለሚስቶችም ይሠራል። (ምሳሌ 5:18፤ መክ. 9:9) በመሆኑም ባለትዳሮች ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ በአካልም ሆነ በስሜት በመቀራረብ ለትዳር አጋራቸው ‘ሙሉ ልባቸውን’ መስጠት ይኖርባቸዋል። ይህም ሲባል አንዳቸው ለሌላው ትኩረት መስጠት፣ አብረው ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም እርስ በርስ መቀራረብ አለባቸው ማለት ነው። ትዳራቸውንም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠናከር ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ አብረው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ አብረው ማገልገልና የይሖዋን በረከት ለማግኘት አብረው መጸለይ ይኖርባቸዋል።

ለይሖዋ ምንጊዜም ታማኝ ሁኑ

16, 17. (ሀ) ከጉባኤም ሆነ ከቤተሰባችን ጋር በተያያዘ ለይሖዋ ያለን ታማኝነት ሊፈተን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ከተወገደ የቤተሰባችን አባል ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናቋርጥ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ማክበራችን ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል የትኛው ምሳሌ ያሳያል?

16 አንዳንድ ክርስቲያኖች ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ምክንያት “በእምነት ጤናሞች እንዲሆኑ” ጠንከር ያለ ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል። (ቲቶ 1:13) ሌሎች ደግሞ ባሳዩት ምግባር የተነሳ ከጉባኤ ተወግደዋል። ዞሮ ዞሮ ከተግሣጹ ‘ሥልጠና ያገኙ ሰዎች’ የተሰጣቸው ምክር በመንፈሳዊ እንዲያገግሙ ረድቷቸዋል። (ዕብ. 12:11) ይሁንና የተወገደ የቤተሰብ አባል ወይም ዘመድ አሊያም የቅርብ ጓደኛ ቢኖረንስ? በዚህ ጊዜ ታማኝነታችን ፈተና ላይ ይወድቃል። እርግጥ ነው፣ ታማኝ መሆን ያለብን ለአምላክ እንጂ ለግለሰቡ አይደለም። ይሖዋ ከተወገደ ከማንኛውም ሰው ጋር ግንኙነት እንዳይኖረን የሰጠውን ትእዛዝ እንፈጽም እንደሆነና እንዳልሆነ ከላይ ሆኖ እንደሚመለከተን ማስታወስ ይኖርብናል።​—1 ቆሮንቶስ 5:11-13ን አንብብ።

17 አንድ ቤተሰብ፣ ከተወገደ የቤተሰቡ አባል ወይም ዘመዱ ጋር መገናኘት እንደሌለበት ይሖዋ የሰጠውን ትእዛዝ በማክበር ታማኝነት ማሳየቱ መልካም ውጤት እንደሚያስገኝ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ወጣት ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት ተወግዶ በቆየበት ጊዜ አባቱም ሆነ እናቱ እንዲሁም አራት ወንድሞቹ ከእሱ ጋር ‘መግጠማቸውን ትተው’ ነበር። ይህ ወጣት አንዳንድ ጊዜ የቤተሰቡ አባል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለመካፈል ጥረት ያደርግ ነበር፤ ደግነቱ ግን ሁሉም የቤተሰቡ አባል ከእሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው ጥብቅ አቋም ወሰዱ። ከቤተሰቡ ጋር ያሳልፍ የነበረው ጊዜ በተለይ ምሽት ላይ ብቻውን ሲሆን በጣም ይናፍቀው እንደነበር ውገዳው ከተነሳለት በኋላ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እንኳ ከእሱ ጋር ቢገናኙ ኖሮ በዚያ ረክቶ ሊኖር ይችል እንደነበር በግልጽ ተናግሯል። ሆኖም ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ከእሱ ጋር ለመነጋገር ምንም ዓይነት ክፍተት አልፈጠሩም፤ በመሆኑም ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንደገና እንዲያድስ ከረዱት ነገሮች አንዱ ከቤተሰቡ ጋር ለመሆን ያለው ፍላጎት ነበር። አንተም ከተወገደ የቤተሰብ አባል ወይም ዘመድ ጋር እንዳትገናኝ ይሖዋ የሰጠህን ትእዛዝ ለመጣስ በምትፈተንበት ጊዜ ይህን ተሞክሮ አስታውስ።

18. ታማኝነት ያለውን ጥቅምና ታማኝነትን ማጓደል ያለውን ጉዳት ተመልክተናል፤ ታዲያ ቁርጥ ውሳኔህ ምን መሆን ይኖርበታል?

18 የምንኖረው አታላዮችና ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። ያም ሆኖ ታማኝ በመሆን ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ክርስቲያኖች የሚከተሉት የሕይወት ጎዳና ስለ እነሱ ማንነት ይናገራል፤ ሕይወታቸውን ስንመለከት እንዲህ ብለው የተናገሩ ያህል ሆኖ ይሰማናል፦ “አማኞች በሆናችሁት በእናንተ መካከል እንዴት ታማኞች፣ ጻድቃንና ነቀፋ የሌለብን ሆነን እንደተገኘን እናንተ ምሥክሮች ናችሁ፤ አምላክም ምሥክር ነው።” (1 ተሰ. 2:10) እንግዲያው ሁላችንም ለአምላክም ሆነ አንዳችን ለሌላው ታማኞች ሆነን ለመቀጠል ከመቼው ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ለሳምሶን የጥንካሬ ምንጭ የሆነለት ፀጉሩ በራሱ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ፀጉሩ የሚወክለው ነገር ማለትም ናዝራዊ በመሆን ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ልዩ ዝምድና ነው።

^ አን.6 “የይሁዳ መሳም” የሚለው አገላለጽ “የክህደት ድርጊትን” ያመለክታል።

^ አን.13 የትዳር ጓደኛ ታማኝነቱን ሲያጓድል የሚፈጠረውን ሁኔታ ለመቋቋም የሚረዳ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሰኔ 15, 2010 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-32 ላይ የወጣውን “የትዳር ጓደኛ ሲከዳ ሁኔታውን መቋቋም” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ፣ ሌሎች ትተው ቢሄዱም እንኳ እሱ ቅቡዕ ለሆነው የአምላክ ልጅ ያለውን ታማኝነት አሳይቷል