በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ መግባት አለባቸው?

ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ መግባት አለባቸው?

ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ መግባት አለባቸው?

በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ አይገቡም። ለምን? የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ስለሚፈልጉ ነው። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ክፍል [አይደለሁም]” ብሏል። ተከታዮቹን አስመልክቶ ደግሞ “የዓለም ክፍል [አይደላችሁም]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14) ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ መግባት የሌለባቸው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት።

1. የሰው ልጆች አቅም ውስንነት፦ የሰው ልጆች ራሳቸውን ለማስተዳደር አቅሙም ሆነ መብቱ እንደሌላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ነቢዩ ኤርምያስ የሰው ልጅ “[አካሄዱን] በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል” ጽፏል።​—ኤርምያስ 10:23

ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፦ የሰው ልጆች ያለምንም እገዛ በራሳችን መብረር እንድንችል ተደርገን አልተፈጠርንም፤ በተመሳሳይም ስንፈጠር ራሳችንን በተሳካ ሁኔታ የማስተዳደር ችሎታ አልተሰጠንም። ዴቪድ ፍረምኪን የተባሉ የታሪክ ምሁር መንግሥታት ስላለባቸው የአቅም ገደብ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “መንግሥታት የተዋቀሩት በሰዎች ነው፤ በመሆኑም ስህተት የሚሠሩ ከመሆኑም ሌላ ወደፊት ምን እንደሚገጥማቸው ማወቅ አይቻልም። ኃይል ቢኖራቸውም አቅማቸው ውስን ነው።” (ዘ ኩዌስችን ኦቭ ገቨርንመንት) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሰው ልጆች እንዳንታመን የሚያስጠነቅቀን መሆኑ ምንም አያስገርምም!​—መዝሙር 146:3

2. ክፉ የሆኑ መንፈሳዊ ኃይሎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ፦ ኢየሱስ የዓለም ገዥ እንዲሆን ሰይጣን ግብዣ ባቀረበለት ወቅት ዲያብሎስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ የመስጠት ሥልጣን ያለው መሆኑን ኢየሱስ አላስተባበለም። እንዲያውም በሌላ ወቅት ኢየሱስ፣ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣንን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” ብሎታል። (ዮሐንስ 14:30፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) ጳውሎስ ለእምነት ባልደረቦቹ ሲጽፍ “ትግል የምንገጥመው . . . ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዢዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው” ብሏል። (ኤፌሶን 6:12) አብዛኛው የሰው ዘር ባያስተውለውም ይህን ዓለም የሚገዙት ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ናቸው። ታዲያ ይህን ማወቃችን ለፖለቲካ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ሊያደርገን ይገባል?

እስቲ የሚከተለውን ንጽጽር እንመልከት፦ ኃይለኛ የባሕር ማዕበል ትናንሽ ጀልባዎችን እየገፋ ወደፈለገበት አቅጣጫ እንደሚወስዳቸው ሁሉ ኃያል የሆኑ ክፉ መናፍስትም ሰብዓዊውን የፖለቲካ ሥርዓት ወደፈለጉት አቅጣጫ ይመሩታል። ጀልባዎቹን የሚቀዝፉት ሰዎች ኃይለኛ የሆነውን ማዕበል አቅጣጫ ማስቀየር እንደማይችሉ ሁሉ ፖለቲከኞችም ኃያል የሆኑት ክፉ መናፍስት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መቋቋም አይችሉም። እነዚህ ኃያላን መናፍስት የሰውን ዘር መልሶ ሊስተካከል በማይችል መልኩ ለመበከልና በምድር ላይ ወዮታ ለማምጣት ቆርጠው ተነስተዋል። (ራእይ 12:12) በመሆኑም እውነተኛ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ከሰይጣንም ሆነ ከአጋንንቱ የበለጠ ኃይል ያለው አካል ብቻ ነው። ይህ አካል ደግሞ ከይሖዋ አምላክ (ያህዌ) ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። *​—ዘፀአት 6:3፤ መዝሙር 83:18፤ ኤርምያስ 10:7, 10

3. እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚደግፉት የአምላክን መንግሥት ብቻ ነው፦ አምላክ መላውን ምድር የሚገዛ መስተዳድር እሱ በወሰነው ጊዜ በሰማይ እንደሚያቋቁም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያውቁ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መስተዳደር የአምላክ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ሲሆን ንጉሡም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 11:15) ይህ መንግሥት በመላው የሰው ዘር ሕይወት ላይ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ኢየሱስ የስብከቱ ዋነኛ ጭብጥ ያደረገው “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” ነበር። (ሉቃስ 4:43) ከዚህም ሌላ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። ለምን? ምክንያቱም በዚህ መንግሥት አገዛዝ ሥር የአምላክ ፈቃድ በሰማይም በምድርም ላይ ይፈጸማል።​—ማቴዎስ 6:9, 10

ታዲያ በዚህ ወቅት ሰብዓዊ መንግሥታት ምን ይገጥማቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ እንደሚጠፉ ይናገራል። (ራእይ 16:14፤ 19:19-21) አንድ ሰው የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊውን የፖለቲካ ሥርዓት ጠራርጎ እንደሚያጠፋው የሚያምን ከሆነ ይህን የፖለቲካ ሥርዓት እንደማይደግፍ የታወቀ ነው። ደግሞም ጥፋት የማይቀርላቸውን እነዚህን ሰብዓዊ መንግሥታት መደገፍ አምላክን መቃወም ይሆንበታል።

ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ አይገቡም ሲባል የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ምንም ተሳትፎ አያደርጉም ማለት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ምሥክሮች ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ከመጣር ይልቅ የአምላክን መንግሥት በሙሉ ልባቸው ይደግፋሉ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የአምላክ ስም ይሖዋ (ያህዌ) እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።