በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሌሎች መጻሕፍት ይለያል?

ከሌሎች መጻሕፍት ይለያል?

ከሌሎች መጻሕፍት ይለያል?

“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማል፤ ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”​—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

አንዳንድ ሰዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። አንተስ? መጽሐፍ ቅዱስን የምትመለከተው እንዴት ነው?

• ግሩም እንደሆነ የሥነ ጽሑፍ ሥራ

• እንደ ማንኛውም ቅዱስ መጽሐፍ

• ግብረ ገብ እንደሚያስተምር የተረት መጽሐፍ

• እንደ አምላክ ቃል

ከዚህ ጋር በተያያዘ ‘ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለህ አመለካከት ለውጥ ያመጣል?’ የሚል ጥያቄም ይነሳል። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በውስጡ የሚገኘውን መልእክት በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።” (ሮም 15:4) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዓላማ እኛን ለማስተማር፣ ለማጽናናት እንዲሁም ተስፋ ለመስጠት እንደሆነ መጽሐፉ ራሱ ይናገራል።

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ ግሩም የሆነ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ወይም ከሌሎች ቅዱስ መጻሕፍት ያልተለየ መጽሐፍ ከሆነ ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ አስተማማኝ መመሪያ ሊሰጥህ ይችላል? በተለይ ደግሞ በውስጡ ያለው ሐሳብ አንተ ከምታምንበት የተለየ ከሆነ እምነት ልትጥልበት ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ አፈ ታሪኮችን የያዘ መጽሐፍ ከሆነ በውስጡ በሚገኙት ተስፋዎች ላይ እምነት መጣል ብሎም ከእነሱ መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ?

በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህ መጽሐፍ የአምላክ ቃል መሆኑንና ከሌሎች መጻሕፍት የተለየ እንደሆነ ያምናሉ። እንዲህ ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች መጻሕፍት የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? በቀጣዮቹ ርዕሶች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መሆኑን የሚያሳዩ አምስት ነጥቦች ተብራርተዋል፤ እነዚህን ነጥቦች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።