በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ አምላክ ቅረብ

‘ነፍስህ እኔን ለመርዳት ታጎነብሳለች’

‘ነፍስህ እኔን ለመርዳት ታጎነብሳለች’

ትሕትና ተወዳጅ ባሕርይ ነው። ብዙውን ጊዜ ትሑት የሆኑ ሰዎች ይማርኩናል። የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ትሕትና የሚያሳዩ ሰዎች ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ በተለይም ሥልጣን ወይም የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ሰዎች ይህን ባሕርይ ማሳየት ይከብዳቸዋል። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ኃያል የሆነው ይሖዋ አምላክስ ትሑት ነው? በ⁠ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:20, 21 (NW) ላይ ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ እንመርምር።​—ጥቅሱን አንብብ። *

ይህ ነቢይ፣ የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍን የጻፈው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳዛኝ የሆነ ክስተት በደረሰበት ወቅት ነው። መጽሐፉን በጻፈበት ወቅት የሚወዳት ከተማ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን በመጥፋቷ በጥልቅ አዝኖ ነበር። ነቢዩ በሁኔታው ቢያዝንም እስራኤላውያን የኃጢአት ጎዳና በመከተላቸው እንዲህ ያለ መለኮታዊ ፍርድ መቀበላቸው ተገቢ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይሁንና ኤርምያስ ምንም ተስፋ እንደሌለ አስቦ ይሆን? ይሖዋ ከእነሱ በጣም እንደራቀና ከሕዝቡ መካከል ንስሐ የገቡትን ተመልክቶ ከመከራቸው ለማዳን ፈቃደኛ እንደማይሆን ተሰምቶት ይሆን? ኤርምያስ ሕዝቡን ወክሎ ሲናገር እስቲ እናዳምጠው።

አብዛኛው ሕዝብ በሐዘን ቢዋጥም ኤርምያስ በተስፋ ተሞልቶ ነበር። “ነፍስህ * [ይሖዋ ራሱ ማለት ነው] ያለጥርጥር ታስታውሳለች፣ እኔን ለመርዳትም ታጎነብሳለች” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (ቁጥር 20) ኤርምያስ በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ነበረው። ይሖዋ እሱንም ሆነ በሕዝቡ መካከል ያሉ ንስሐ የገቡ ሰዎችን እንደማይረሳቸው ያውቃል። ታዲያ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ምን ያደርግ ይሆን?​—ራእይ 15:3

ይሖዋ ከልባቸው ንስሐ የገቡ ሰዎችን ‘ለመርዳት እንደሚያጎነብስ’ ኤርምያስ እርግጠኛ ነበር። አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “አስታውሰኝ፤ ወደ እኔም አዘንብል” በማለት አስቀምጦታል። እነዚህ ቃላት ይሖዋ ምን ያህል ደግ እና ገር እንደሆነ በዓይነ ሕሊናችን እንድንስል ይረዱናል። “በምድር ሁሉ ላይ . . . ልዑል” የሆነው ይሖዋ በምሳሌያዊ አነጋገር ጎንበስ በማለት አምላኪዎቹን ከወደቁበት የውርደት አዘቅት አውጥቶ እንደገና ሞገሱን ያሳያቸዋል። (መዝሙር 83:18) ኤርምያስ እንዲህ ዓይነት ተስፋ ስላለው በሐዘን የተደቆሰው ልቡ ሊጽናና ችሏል። ይህ ታማኝ ነቢይ፣ ይሖዋ ንስሐ የገቡትን ሰዎች ለማዳን የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ በትዕግሥት ለመጠባበቅ ቆርጦ ነበር።​—ቁጥር 21

ኤርምያስ ያሰፈረው ሐሳብ ስለ ይሖዋ ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል። አንደኛ፣ ይሖዋ ትሑት ወይም ራሱን ዝቅ የሚያደርግ አምላክ ነው። (መዝሙር 18:35) ይሖዋ “በኀይል . . . ታላቅ” ቢሆንም በጭንቅ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ወደ እኛ ጎንበስ ያለ ያህል ራሱን ዝቅ አድርጎ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ ነው። (ኢዮብ 37:23፤ መዝሙር 113:5-7) ይህ የሚያጽናና ሐሳብ አይደለም? ሁለተኛ፣ ይሖዋ መሐሪ ነው፤ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ‘ይቅር ለማለት’ እና ለእነዚህ ሰዎች እንደገና ሞገሱን ለማሳየት ዝግጁ ነው። (መዝሙር 86:5) በመሆኑም እነዚህ ሁለት ባሕርያት ማለትም ትሕትናና ምሕረት የተያያዙ ናቸው።

ይሖዋ፣ ኩራተኛ በመሆናቸው ግትር እና ለሌሎች ጉዳይ ደንታ ቢስ ከሆኑት ሰብዓዊ መሪዎች የተለየ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! አንተስ አምላኪዎቹ በጭንቅ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ለእነሱ ተስፋ ለመስጠት ሲል ‘ጎንበስ ለማለት’ ዝግጁ ስለሆነው ትሑት አምላክ ይበልጥ ለማወቅ አትፈልግም?

በሰኔ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ኤርምያስ 51-52; ሰቆቃወ ኤርምያስ 1-5ሕዝቅኤል 1-5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.1 ኤርምያስ 3:20, 21 (NW)፦ “ነፍስህ ያለጥርጥር ታስታውሳለች፣ እኔን ለመርዳትም ታጎነብሳለች። ይህን አስታውሳለሁ። ከዚህም የተነሳ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።”

^ አን.3 የጥንት ጸሐፊዎች በዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን “ነፍስህ” የሚለውን ቃል “ነፍሴ” በሚለው በመቀየር ኤርምያስን እንዲያመለክት አድርገው አስቀምጠውታል። ይህን ያደረጉት መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ያሉ ፍጥረታትን ለማመልከት የሚጠቀምበትን ነፍስ የሚለውን ቃል ለአምላክ መጠቀም እሱን አለማክበር እንደሆነ ተሰምቷቸው መሆን አለበት። ይሁንና ስለ አምላክ መረዳት እንድንችል ሲባል ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምላክ የተገለጸው ሰዎች በቀላሉ በሚገባቸው መንገድ ነው። “ነፍስ” የሚለው ቃል “ሕይወታችንን” ሊያመለክት ስለሚችል “ነፍስህ” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ “አንተ” ማለት ነው።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ጭንቅ ውስጥ ስንሆን ወደ እኛ ጎንበስ ያለ ያህል ራሱን ዝቅ አድርጎ ይረዳናል