በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ከቅዱስ አገልግሎታችን የተማርነው “ሚስጥር”

ከቅዱስ አገልግሎታችን የተማርነው “ሚስጥር”

ኦሊቪዬ ራንድሪአሞራ እንደተናገረው

“በትንሽ ነገር እንዴት መኖር እንደሚቻል አውቃለሁ፣ ብዙ አግኝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻልም አውቃለሁ። በማንኛውም ነገርና በሁሉ ሁኔታ ጠግቦም ሆነ ተርቦ . . . መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬያለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ።”​—ፊልጵ. 4:12, 13

እነዚህ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ለእኔም ሆነ ለባለቤቴ ለኦሊ ለረጅም ጊዜ የብርታት ምንጭ ሆነውልናል። በማዳጋስካር ስናገለግል እኛም እንደ ጳውሎስ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ የመተማመንን “ሚስጥር” ተምረናል።

የኦሊ እናት በ1982 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ እኔና ኦሊ ተጫጭተን ነበር። እኔም መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ የተቀበልኩ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ኦሊም አብራኝ ማጥናት ጀመረች። እኔና ኦሊ በ1983 ተጋባን፤ እንዲሁም በ1985 ተጠመቅን፤ ከዚያ ወዲያውኑ ረዳት አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን። ሐምሌ 1986 ደግሞ የዘወትር አቅኚ ሆንን።

መስከረም 1987 ልዩ አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን። የመጀመሪያው የአገልግሎት ምድባችን በሰሜናዊ ምዕራብ ማዳጋስካር የምትገኝ አንዲት አነስተኛ ከተማ ነበረች፤ በዚያም ምንም ጉባኤ አልነበረም። በማዳጋስካር ዋና ዋና የሚባሉ 18 ብሔሮችና በርካታ ጎሣዎች ሲኖሩ የሕዝቡ ልማድና ባሕል ከቦታ ቦታ በጣም የተለያየ ነው። የሥራ ቋንቋቸው ማላጋሲ ቢሆንም የተለያዩ ቀበሌኛዎችም ይነገራሉ። ስለዚህ በአዲሱ ምድባችን ያለው ሕዝብ የሚናገረውን ቀበሌኛ መማር የጀመርን ሲሆን ይህ ደግሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት እንድናገኝ ረድቶናል።

መጀመሪያ ላይ በየሳምንቱ የሕዝብ ንግግር አቀርብ ነበር፤ ልክ ስጨርስ ኦሊ ሥራዬ ብላ ታጨበጭብልኛለች። ተሰብሳቢዎቹ ሁለታችን ብቻ ነበርን። በተጨማሪም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ላይ ያሉትን ክፍሎች በሙሉ እናቀርብ የነበረ ሲሆን ኦሊ የቤቱ ባለቤት አጠገቧ እንዳለ አድርጋ በማሰብ ክፍሏን ታቀርብ ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሊጎበኘን በመጣበት ወቅት፣ ስብሰባዎቻችንን የምናካሂድበትን መንገድ በተመለከተ አንዳንድ ማስተካከያዎችን እንድናደርግ በደግነት ሐሳብ ሲያቀርብልን ትልቅ እፎይታ ተሰማን!

የፖስታ አገልግሎት አስተማማኝ ስላልነበረ ወርኃዊ አበላችን ወቅቱን ጠብቆ የማይደርሰን ጊዜያት ነበር። በመሆኑም በትንሽ ነገር እንዴት መኖር እንደሚቻል ተምረናል። በአንድ ወቅት፣ 130 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ የወረዳ ስብሰባ ሊካሄድ ነበር፤ ወደዚያ ለመሄድ ግን ለአውቶቡስ የሚሆን በቂ ገንዘብ አልነበረንም። አንድ የእምነት ባልንጀራችን “ችግራችሁን ለይሖዋ ንገሩት። ደግሞም እኮ እየሠራችሁ ያላችሁት የእሱን ሥራ ነው” በማለት የሰጠንን ጥሩ ምክር አስታወስን። ስለዚህ ጉዳዩን ለይሖዋ በጸሎት ከነገርነው በኋላ በእግራችን ለመጓዝ ወሰንን። ይሁን እንጂ ልክ ጉዞ ለመጀመር ስንነሳ አንድ ወንድም ሳናስበው ሊጠይቀን መጣና ለመሳፈሪያ የሚበቃን ያህል ገንዘብ በስጦታ መልክ ሰጠን!

የወረዳ ሥራ

የካቲት 1991 የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። በወቅቱ ትንሹ ቡድናችን እድገት አድርጎ አስፋፊዎቹ 9 ደርሰው ነበር። ከእነዚህ መካከል 3ቱ ተጠምቀው ነበር፤ እንዲሁም በአማካይ እስከ 50 ሆነን እንሰበሰብ ነበር። ሥልጠና ከተሰጠን በኋላ በዋና ከተማዋ በአንታናናሪቮ በሚገኝ ወረዳ ውስጥ ማገልገል ጀመርን። በ1993 በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኝ ሌላ ወረዳ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ የነበረው የኑሮ ሁኔታ በከተማ ውስጥ ካለው ሕይወት በጣም የተለየ ነበር።

ወደምንጎበኛቸው ጉባኤዎችና ገለልተኛ ቡድኖች ለመድረስ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ ተራሮችን እያቋረጥን እስከ 145 ኪሎ ሜትር ድረስ በእግር የምንጓዝባቸው ጊዜያት ነበሩ። በተቻለ መጠን ጓዛችንን ቀላል ለማድረግ እንሞክራለን። እርግጥ ነው፣ በምጎበኝበት ወቅት የማቀርበው የሕዝብ ንግግር በዚያን ጊዜ ይደረግ እንደነበረው ስላይድ ፊልም ማሳየትን የሚጨምር በሚሆንበት ጊዜ ጓዛችን ከባድ ይሆን ነበር። ኦሊ የስላይድ ማሳያውን (ፕሮጀክተር) ስትይዝ እኔ ደግሞ የመኪና ባትሪ እሸከም ነበር።

ብዙውን ጊዜ ወደ ቀጣዩ ጉባኤ ለመድረስ በቀን 40 ኪሎ ሜትር ያህል እንጓዝ ነበር። በምንጓዝበት ወቅት ተራራ መውጣትና መውረድ፣ ወንዞችን ማቋረጥ እንዲሁም በጭቃ ውስጥ መሄድ ነበረብን። አንዳንድ ጊዜ መንገድ ዳር እንተኛ የነበረ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ማደሪያ ቦታ ልናገኝ የምንችልበትን መንደር እናፈላልግ ነበር። ፈጽሞ የማናውቃቸውን ሰዎች እንዲያሳድሩን የምንጠይቅበት ጊዜም ነበር። ማደሪያ ቦታ ካገኘን በኋላ ምግባችንን ማዘጋጀት እንጀምራለን። ኦሊ ድስት ትዋስና በአቅራቢያው ወዳለ ወንዝ ወይም ሐይቅ በመሄድ ውኃ ትቀዳለች። እኔ ደግሞ መጥረቢያ ተውሼ ለማገዶ የሚሆን እንጨት እፈልጣለሁ። እነዚህን ነገሮች ማድረግ ጊዜ ይወስዳል። አንዳንዴ ደግሞ ዶሮ ከገዛን በኋላ አርደን እንበላ ነበር።

ምግባችንን ከበላን በኋላ ለገላ መታጠቢያ የሚሆን ውኃ እንቀዳለን። አንዳንድ ጊዜ የምንተኛው ማድቤት ውስጥ ነው። ያደርንበት ቤት ጣራው የሚያፈስ ከሆነ ዝናብ ሲጥል እንዳንበሰብስ ግድግዳውን ተጠግተን እንተኛ ነበር።

ምንጊዜም፣ ማደሪያ ለሚሰጡን ሰዎች እንመሠክርላቸው ነበር። ወዳሰብንበት ቦታ ስንደርስ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያሳዩን ደግነት እንዲሁም የሚያደርጉልን አቀባበል ልብ የሚነካ ነበር። ለጉብኝቱ ያላቸው ልባዊ አድናቆት በመንገድ ላይ ያጋጠመንን ማንኛውንም ፈታኝ ሁኔታ እንድንረሳ የሚያደርግ ነው።

በእምነት ባልንጀሮቻችን ቤት ስናርፍ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት እነሱን ማገዝ ያስደስተን ነበር። ይህ ደግሞ በመስክ አገልግሎት ከእኛ ጋር አብረው ለመካፈል ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላቸው ነበር። በእንግድነት የተቀበሉን ወንድሞችና እህቶች ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉልን ወይም የተለየ ዓይነት ምግብ አንዲያቀርቡልን አንጠብቅም።

ገለልተኛ ቡድኖችን መጎብኘት

ገለልተኛ ቡድኖችን መጎብኘት ያስደስተን ነበር፤ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ወንድሞች ምንም የማያላውስ ፕሮግራም አውጥተው ይጠብቁናል። “ትንሽ አረፍ” ለማለት እንኳ ፋታ አናገኝም ነበር። (ማርቆስ 6:31) አንድ አካባቢ ስንጎበኝ 40 ጥናት ያላቸው አንድ ባልና ሚስት በጥናቶቻቸው ላይ እንድንካፈል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸውን በሙሉ ቤታቸው ጠሯቸው። ኦሊና እህት 20ዎቹን ሲያስጠኑ እኔና ወንድም ደግሞ የተቀሩትን 20 ጥናቶች አስጠናን። አንዱ ተማሪ ሲጨርስ ወዲያውኑ ሌላኛው ይቀጥላል። ትንሽ ፋታ የምናገኘው የጉባኤ ስብሰባዎችን ስናደርግ ነው፤ ከስብሰባው በኋላ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናታችንን እንቀጥላለን። ለረጅም ሰዓታት በሥራ ተወጥረን ከዋልን በኋላ የዕለቱ እንቅስቃሴያችን በአብዛኛው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ያበቃል!

አንድ ቀን ከወንድሞች ጋር ሆነን ሌላ ቡድን ለመጎብኘት ተነሳን፤ ቡድኑ ወደሚገኝበት መንደር ጉዞ የጀመርነው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ነበር። በዚህ ወቅት ሁላችንም የለበስነው አሮጌ ልብስ ነበር። በጫካው ውስጥ ረጅም ጉዞ ካደረግን በኋላ እኩለ ቀን ላይ ወደ ክልሉ ደረስን። ወዲያውኑ ንጹሕ ልብስ ቀይረን ከቤት ወደ ቤት መስበክ ጀመርን። በዚያ አካባቢ ያሉት ቤቶች ጥቂት ሲሆኑ አስፋፊዎች ግን ብዙ ነበሩ። ስለዚህ ክልሉን 30 ደቂቃ በሚያህል ጊዜ ውስጥ ሸፈንነው። ከዚያም ወደ ቀጣዩ መንደር አመራን። በዚያም የስብከቱን ሥራ ስናከናውን ከቆየን በኋላ ወደ ቤታችን ለመመለስ ረጅሙን ጉዞ ተያያዝነው። መጀመሪያ አካባቢ ይህ ሁኔታ ትንሽ ተስፋ አስቆርጦን ነበር። ምክንያቱም ወደ ክልሎቹ ለመድረስ የሚወስድብን ጊዜና የምናጠፋው ጉልበት ብዙ ሲሆን ከቤት ወደ ቤት የምናገለግለው ግን ለአንድ ሰዓት ያህል ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች ምንም አላጉረመረሙም። ምንጊዜም ደስተኞች ነበሩ።

በታቪራናምቦ ያለ አንድ ቡድን የሚገኘው በተራራው ጫፍ አካባቢ ነበር። በዚያም አንድ ክፍል ቤት ውስጥ የሚኖር የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ቤተሰብ አገኘን። በአቅራቢያቸው የሚገኝ አንድ አነስተኛ ቤት ደግሞ መሰብሰቢያ ቦታ ሆኖ ያገለግል ነበር። በእንግድነት የተቀበለን ወንድም ድንገት ድምፁን ከፍ አድርጎ “ወንድሞች!” ብሎ ተጣራ። ከሌላኛው ተራራ ጫፍ ላይ ደግሞ አንድ ሰው “አቤት!” ብሎ መለሰ። ከዚያም ወንድም “የወረዳ የበላይ ተመልካቹ መጥቷል!” ብሎ ተናገረ። ከማዶ “እሺ!” የሚል ድምፅ ተሰማ። መልእክቱ ከዚያም አልፎ በሚገኙ አካባቢዎች እንደደረሰ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ብዙም ሳይቆይ ሰዎች ወደ ስብሰባው ቦታ መምጣት ጀመሩ፤ እንዲያውም ስብሰባው ሲጀመር ከ100 የሚበልጡ ሰዎች ተገኝተው ነበር።

የመጓጓዣ ችግር

በ1996 ለአንታናናሪቮ ቅርብ በሆነ ተራራማ አካባቢ በሚገኝ አንድ ወረዳ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። ወረዳው የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ነበሩት። ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ለመሄድ የሚያስችል መደበኛ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረም። በአንድ ወቅት፣ ከአንታናናሪቮ 240 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቢአንካና (በሳካይ) በተባለ ቦታ የሚገኝን አንድ ቡድን እንድንጎበኝ ቀጠሮ ተይዞልን ነበር። ወደዚያ አቅጣጫ የሚሄድ አንድ አነስተኛ የጭነት መኪና ስናገኝ ከሹፌሩ ጋር ተደራድረን ተሳፈርን። በጭነት መኪናው ላይ 30 የሚያህሉ ሌሎች መንገደኞችም ተሳፍረው ነበር፤ የተወሰኑት የመኪናው አናት ላይ ሲቀመጡ የተቀሩት ደግሞ ከመኪናው ኋላ ተንጠላጥለው ነበር።

አብዛኛውን ጊዜ እንደሚያጋጥመው መኪናው ብዙም ሳንርቅ በመበላሸቱ በእግራችን መጓዝ ጀመርን። ለጥቂት ሰዓታት ካዘገምን በኋላ አንድ ትልቅ የጭነት መኪና መጣ። መኪናው ሰውና ዕቃ ጥቅጥቅ አድርጎ ጭኖ ነበር፤ ያም ሆኖ ሹፌሩ አቆመልን። ያለው ቦታ ለእግር ማቆሚያ ብቻ ቢሆንም ተሳፍረን ጉዟችንን ቀጠልን። በኋላም ወደ አንድ ወንዝ ደረስን፤ ነገር ግን ድልድዩ ጥገና እየተደረገለት ነበር። አሁንም እንደገና በእግራችን መጓዙን ተያያዝነው፤ በመጨረሻ ልዩ አቅኚዎች ወደሚኖሩባት አንዲት ትንሽ መንደር ደረስን። እነሱን ለመጎብኘት ፕሮግራም ባይኖረንም ድልድዩ ተጠግኖ እስኪያበቃና ሌላ መኪና እስክናገኝ ድረስ ከእነሱ ጋር አብረን አገለገልን።

ከአንድ ሳምንት በኋላ መኪና አገኘንና ጉዟችንን ቀጠልን። መንገዱ ጉድጓድ የበዛበት ነበር። መኪናው እስከ ጉልበት የሚደርስ ጥልቀት ባለው ውኃ ውስጥ ሲያልፍ በተደጋጋሚ ጊዜ እየወረድን እንገፋ ነበር፤ በዚህ ወቅት ብዙ ጊዜ ተደናቅፈን እንወድቅ ነበር። ሊነጋጋ ሲል ወደ አንዲት ትንሽ መንደር ደረስንና ከመኪናው ወረድን። ከዚያም ከዋናው መንገድ ተገንጥለን በእግራችን መጓዝ ጀመርን፤ እስከ ወገብ በሚደርስ ድፍርስ ውኃ የተሸፈኑትን የሩዝ ማሳዎችን በማቋረጥ ጉዟችንን ቀጠልን።

ይህንን አካባቢ ስንጎበኝ የመጀመሪያችን ስለነበረ በሩዝ ማሳዎች ላይ ለሚሠሩት ሰዎች ምሥራቹን ለመንገርና የዚያ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙበትን አቅጣጫ እንዲያመላክቱን ለመጠየቅ ወሰንን። ይሁንና እነሱ ራሳቸው መንፈሳዊ ወንድሞቻችን መሆናቸውን ስናውቅ በጣም ተደሰትን!

ሌሎች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡ ማበረታታት

ባለፉት ዓመታት ሌሎች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡ ማበረታታታችን ያስገኘውን ውጤት ማየታችን ትልቅ ደስታ አምጥቶልናል። ዘጠኝ የዘወትር አቅኚዎች የነበሩበትን አንድ ጉባኤ በምንጎበኝበት ጊዜ እያንዳንዱ አቅኚ አንድ ሌላ አስፋፊ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገባ የመርዳት ግብ ይዞ እንዲንቀሳቀስ አበረታትተናቸው ነበር። ከስድስት ወር በኋላ ስንጎበኛቸው የዘወትር አቅኚዎቹ ቁጥራቸው አድጎ 22 ደርሶ ነበር። አቅኚ የሆኑ ሁለት እህቶች የጉባኤ ሽማግሌ የሆኑትን አባቶቻቸውን የዘወትር አቅኚዎች እንዲሆኑ አበረታቷቸው። እነዚያ የጉባኤ ሽማግሌዎች በተራቸው ሌላ አንድ ሽማግሌ አቅኚ እንዲሆን አበረታቱት። ብዙም ሳይቆይ ይህ ሽማግሌ ልዩ አቅኚ ሆኖ ተሾመ። በኋላም እሱና ሚስቱ በወረዳ ሥራ ማገልገል ጀመሩ። ሁለቱ የጉባኤ ሽማግሌዎችስ? አንደኛው በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እያገለገለ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ውስጥ በፈቃደኝነት እየሠራ ነው።

በራሳችን ብርታት ምንም ነገር ማከናወን እንደማንችል ስለምናውቅ ይሖዋን ላደረገልን እርዳታ በየቀኑ እናመሰግነዋለን። እውነት ነው፣ የድካም ስሜት የሚሰማን እንዲሁም የምንታመምበት ጊዜ አለ፤ ሆኖም የአገልግሎታችንን ውጤት መለስ ብለን ስናስብ ደስ ይለናል። ይሖዋ፣ ሥራው ፍሬ እንዲያስገኝ እያደረገው ነው። እኛም በአሁኑ ጊዜ ልዩ አቅኚዎች ሆነን በማገልገል በዚህ ሥራ ውስጥ ትንሽም ቢሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻላችን ደስተኞች ነን። በእርግጥም፣ ‘ኃይልን በሚሰጠን’ በይሖዋ የመተማመንን “ሚስጥር” ተምረናል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በይሖዋ የመተማመንን “ሚስጥር” ተምረናል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ካርታ/​ሥዕል]

ማዳጋስካር ትልቋ ቀይ ደሴት ተብላ የምትጠራ ሲሆን በምድር ላይ በትልቅነቷ አራተኛ ደረጃ የያዘች ደሴት ናት። አፈሯ ቀይ ከመሆኑም ሌላ በርካታ ብርቅዬ እንስሳትና ዕፅዋት ይገኙባታል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ያስደስተናል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከገጠሙን ከባድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ወደተለያዩ ቦታዎች ጉዞ ማድረግ ነበር