በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን አገልግሎት ማስቀደም ያለብን ለምንድን ነው?

የይሖዋን አገልግሎት ማስቀደም ያለብን ለምንድን ነው?

የይሖዋን አገልግሎት ማስቀደም ያለብን ለምንድን ነው?

“አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ ቀኑን ሙሉ ስለ ማዳንህ ይናገራል።”​—መዝ. 71:15

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ኖኅ፣ ሙሴ፣ ኤርምያስና ጳውሎስ በሕይወታቸው ውስጥ ይሖዋን እንዲያስቀድሙ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?

ሕይወትህን እንዴት መጠቀም እንዳለብህ ለመወሰን ምን ነገሮችን ማሰብ ይኖርብሃል?

የይሖዋን አገልግሎት ለማስቀደም ቁርጥ ውሳኔ ያደረከው ለምንድን ነው?

1, 2. (ሀ) አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ ሲወስን ምን እያለ ነው? (ለ) ኖኅ፣ ሙሴ፣ ኤርምያስና ጳውሎስ ያደረጓቸውን ምርጫዎች በመመርመር ምን ትምህርት እናገኛለን?

ራስህን ወስነህ በመጠመቅ የኢየሱስ ተከታይ ከሆንክ በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ እርምጃ ወስደሃል ማለት ነው። ራስን ለአምላክ መወሰን በግለሰብ ደረጃ ልትወስደው የምትችለው ከሁሉ የላቀ ውሳኔ ነው። ራስህን ስትወስን እንዲህ በማለት የተናገርክ ያህል ነው፦ ‘ይሖዋ፣ በማንኛውም የሕይወቴ ዘርፍ አንተ ጌታዬ እንድትሆን እፈልጋለሁ። እኔ ባሪያህ ነኝ። ቅድሚያ ከምሰጣቸው ነገሮች እንዲሁም ጊዜዬን፣ ጥሪቴንና ችሎታዬን ከምጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ አንተ እንድትወስንልኝ እፈልጋለሁ።’

2 በመሆኑም ራስህን በወሰንክበት ጊዜ ለይሖዋ ከላይ ያለውን ቃል ገብተሃል ሊባል ይችላል። ይህን ውሳኔ በማድረግህም ልትመሰገን ይገባሃል፤ ራስህን ለአምላክ መወሰንህ ትክክለኛና የጥበብ እርምጃ ነው። ይሁንና ይሖዋን እንደ ጌታህ አድርገህ መቀበልህ ጊዜህን ከምትጠቀምበት መንገድ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? የኖኅን፣ የሙሴን፣ የኤርምያስንና የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ መመርመራችን ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ያስችለናል። እነዚህ ግለሰቦች፣ በሙሉ ልባቸው ይሖዋን አገልግለዋል። እኛ ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ ነው። ቅድሚያ ሊሰጡት ከሚገባው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያደረጉት ውሳኔ ጊዜያችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን እንድንመረምር ያበረታታናል።​—ማቴ. 28:19, 20፤ 2 ጢሞ. 3:1

ከጥፋት ውኃው በፊት

3. የኖኅ ዘመን ከእኛ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ የኖኅን ዘመን ከእኛ ዘመን ጋር በማወዳደር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። . . . ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም።” (ማቴ. 24:37-39) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች የጊዜውን አጣዳፊነት በተመለከተ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ይላሉ። እነዚህ ሰዎች፣ የአምላክ አገልጋዮች የሚያውጁትን መልእክት አያስተውሉም። እንደ ኖኅ ዘመን ሁሉ ዛሬ ያሉ ብዙ ሰዎችም አምላክ ክፉዎችን እንደሚያጠፋ ሲነገራቸው ይሳለቃሉ። (2 ጴጥ. 3:3-7) ኖኅ፣ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ባይሰሙም ጊዜውን የተጠቀመው እንዴት ነበር?

4. ኖኅ ከይሖዋ ተልእኮ ከተሰጠው በኋላ ጊዜውን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ለምንስ?

4 አምላክ ጥፋት እንደሚያመጣ ለኖኅ የነገረው ሲሆን መርከብ የመሥራት ተልእኮም ሰጠው፤ ኖኅም ሰዎችንና እንስሳትን ለማትረፍ መርከብ ሠራ። (ዘፍ. 6:13, 14, 22) ኖኅ ይሖዋ ስለሚያመጣው ጥፋትም አውጇል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኖኅን “የጽድቅ ሰባኪ” ብሎ መጥራቱ ኖኅ፣ ሰዎች ያሉበትን ወቅት እንዲያስተውሉ ለመርዳት ጥረት ያደርግ እንደነበር ያሳያል። (2 ጴጥሮስ 2:5ን አንብብ።) ኖኅና ቤተሰቡ ንግድ ለመጀመር፣ ከሌሎች ልቀው ለመታየትና የተመቻቸ ሕይወት ለመኖር ጥረት ቢያደርጉ ምክንያታዊ ይሆን ነበር? እንደማይሆን ግልጽ ነው! ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ነገር ስላስተዋሉ ትኩረታቸው እንዲከፋፈል አልፈቀዱም።

አንድ የግብፅ ልዑል ያደረገው ምርጫ

5, 6. (ሀ) ሙሴ በግብፅ ያገኘው ሥልጠና ለየትኛው ኃላፊነት ዝግጁ እንዲሆን ያደርገው ነበር? (ለ) ሙሴ በግብፅ ያገኘውን አጋጣሚ ያልተጠቀመበት ለምንድን ነው?

5 ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የሙሴን ምሳሌ እንመለከታለን። ሙሴ ያደገው በግብፅ በሚገኝ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሲሆን የፈርዖን ልጅ እንደ ገዛ ልጇ አድርጋ አሳድጋዋለች። ይህ ልዑል ገና በለጋ ዕድሜው “የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ” ተምሯል። (ሥራ 7:22፤ ዘፀ. 2:9, 10) ይህ ሥልጠና በፈርዖን ቤተ መንግሥት ሥልጣን እንዲይዝ የሚያዘጋጀው ነበር። ሙሴ በወቅቱ በነበረው ኃያል መንግሥት ውስጥ ትልቅ ቦታ ማግኘትና የቅንጦት ሕይወት መምራት ይችል ነበር፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ መብቶችን ማግኘት እንዲሁም ተድላን ማሳደድ ይችል ነበር። ታዲያ የሙሴ ዋነኛ ግብ እነዚህን ነገሮች ማግኘት ነበር?

6 ሙሴ በልጅነቱ ከወላጆቹ ሥልጠና አግኝቶ ስለነበር ይሖዋ ለዘሮቹ ማለትም ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ስለሰጠው ተስፋ ማወቁ አይቀርም። ሙሴ በእነዚህ ተስፋዎች ላይ እምነት ነበረው። ስለ ወደፊት ሕይወቱና ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ስለሚያሳይበት መንገድ በሚገባ አስቦ መሆን አለበት። ታዲያ የግብፅ ልዑል አሊያም ደግሞ እስራኤላዊ ባሪያ የመሆን ምርጫ ከፊቱ ሲደቀንበት ምን ውሳኔ አደረገ? ሙሴ “በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን” መርጧል። (ዕብራውያን 11:24-26ን አንብብ።) ከጊዜ በኋላም ሙሴ ሕይወቱን ስለሚጠቀምበት መንገድ ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ ተከትሏል። (ዘፀ. 3:2, 6-10) ሙሴ እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ነበረው። ሙሴ በግብፅ ዘላቂ የሆነ ነገር እንደማያገኝ ተረድቶ ነበር። እንዲያውም ብዙም ሳይቆይ አምላክ አሥር መቅሰፍቶችን በማውረድ ግብፃውያንን ቀጥቷል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ክርስቲያኖች ከዚህ ምን ትምህርት ያገኛሉ? ትኩረታችንን በሰብዓዊ ሥራ ወይም ይህ ሥርዓት በሚያቀርባቸው ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች ላይ ከማድረግ ይልቅ በይሖዋና በአገልግሎቱ ላይ ማድረግ ይኖርብናል።

ኤርምያስ ጥፋት እንደሚመጣ ያምን ነበር

7. ኤርምያስ የነበረበት ሁኔታ ከእኛ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

7 የይሖዋን አገልግሎት ያስቀደመው ሌላው ሰው ደግሞ ነቢዩ ኤርምያስ ነው። ይሖዋ በከሃዲዋ ኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ኤርምያስን ነቢይ አድርጎ ሾመው። በመሆኑም ኤርምያስ የሚኖረው “በኋለኛው ዘመን” ማለትም በመጨረሻዎቹ ቀናት ነበር ሊባል ይችላል። (ኤር. 23:19, 20) ኤርምያስ፣ የሚኖርበት ሥርዓት ባለበት እንደማይቀጥል ጠንቅቆ ያውቅ ነበር።

8, 9. (ሀ) የባሮክ አመለካከት መስተካከል የነበረበት ለምንድን ነው? (ለ) እቅዶችን በምናወጣበት ጊዜ የትኛውን ጉዳይ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል?

8 ኤርምያስ፣ ሥርዓቱ እንደሚጠፋ ያለው ጠንካራ እምነት ምን ነገር ከማድረግ እንዲቆጠብ አድርጎታል? ኤርምያስ ሊጠፋ በተቃረበው ሥርዓት ውስጥ የወደፊት ሕይወቱን ስኬታማ ለማድረግ አልተሯሯጠም። ደግሞስ እንዲህ ማድረጉ ምን ጥቅም አለው? የኤርምያስ ጸሐፊ የሆነው ባሮክ ግን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በዚህ ረገድ አመለካከቱ ተዛብቶ ነበር። በመሆኑም ኤርምያስ፣ ለጸሐፊው የሚከተለውን እንዲነግረው አምላክ በመንፈሱ መርቶታል፦ “በምድር ሁሉ የገነባሁትን አፈርሳለሁ፤ የተከልሁትን እነቅላለሁ። ታዲያ፣ ለራስህ ታላቅ ነገር ትሻለህን? በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ጥፋት አመጣለሁና አትፈልገው፤ . . . ነገር ግን በሄድህበት ሁሉ ሕይወትህ እንዲተርፍልህ አደርጋለሁ።”​—ኤር. 45:4, 5

9 ባሮክ የፈለገው “ታላቅ ነገር” ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። * ሆኖም ይህ ታላቅ ነገር ዘላቂነት እንደሌለውና ባቢሎናውያን በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌምን ሲቆጣጠሩ እንደሚጠፋ እናውቃለን። ታዲያ ከዚህ ምን ትምህርት እንደምናገኝ አስተዋልክ? ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት እቅድ ማውጣት እንደሚኖርብን የታወቀ ነው። (ምሳሌ 6:6-11) ይሁንና ዘላቂ ጥቅም ለሌላቸው ነገሮች ጊዜና ጉልበት ማባከን ሞኝነት አይሆንም? እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ድርጅት አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መሥራቱን እንዲሁም ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶችን ማካሄዱን ይቀጥላል። እነዚህ ጥረቶች ግን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ ስለሚያግዙ ዘለቄታዊ ጥቅም አላቸው። በተመሳሳይም ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ፣ እቅዶችን በሚያወጡበት ጊዜ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠታቸው ተገቢ ነው። ታዲያ ሕይወትህን በሐቀኝነት ስትመረምር ‘ከሁሉ አስቀድመህ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ እየፈለግህ’ እንደሆነ ይሰማሃል?​—ማቴ. 6:33

“እንደ ጉድፍ እቆጥረዋለሁ”

10, 11. (ሀ) ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ትኩረቱ ያረፈው በምን ላይ ነበር? (ለ) ጳውሎስ ግቡን ሙሉ በሙሉ የቀየረው ለምንድን ነው?

10 እስቲ አሁን ደግሞ የጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። የክርስትናን እምነት ከመቀበሉ በፊት፣ ሌሎች እንደሚያስቡት ስኬታማ የሆነ ሕይወት የመምራት ተስፋ ነበረው። በዘመኑ ታዋቂ ከሆኑ ምሁራን መካከል አንዱ የአይሁድን ሕግ አስተምሮታል። እንዲሁም ከአይሁድ ሊቀ ካህናት ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። በተጨማሪም በእሱ ዕድሜ ካሉ ከብዙዎች የበለጠ በአይሁድ እምነት የላቀ እድገት እያደረገ ነበር። (ሥራ 9:1, 2፤ 22:3፤ 26:10፤ ገላ. 1:13, 14) ጳውሎስ፣ ይሖዋ አይሁዳውያንን በብሔር ደረጃ የእሱ ሕዝብ እንደሆኑ አድርጎ ማየቱን እንዳቆመ ሲገነዘብ ግን እነዚህን ነገሮች እርግፍ አድርጎ በመተው በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ አደረገ።

11 ጳውሎስ በአይሁድ እምነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ለማግኘት መጣሩ በይሖዋ ዓይን ምንም እርባና እንደሌለው ተገንዝቦ ነበር፤ ደግሞም እንዲህ ያለው ክብር ዘለቄታ የለውም። (ማቴ. 24:2) ፈሪሳዊ የነበረው ጳውሎስ ቀድሞ ትልቅ ግምት ይሰጣቸው የነበሩ ነገሮችን ስለ አምላክ ዓላማ ካገኘው ግንዛቤና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ካገኘው መብት ጋር ሲያነጻጽራቸው ወደኋላው የተዋቸውን ነገሮች “እንደ ጉድፍ” ቆጥሯቸዋል። ጳውሎስ ከአይሁድ እምነት ጋር በተያያዘ ቅድሚያ ይሰጣቸው የነበሩ ነገሮችን እርግፍ አድርጎ የተወ ሲሆን ከዚያ በኋላ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ምሥራቹን በመስበክ ላይ አተኩሯል።​—ፊልጵስዩስ 3:4-8, 15ን አንብብ፤ ሥራ 9:15

ቅድሚያ የምትሰጡትን ነገር መርምሩ

12. ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ትኩረት ያደረገው በምን ላይ ነው?

12 ኖኅ፣ ሙሴ፣ ኤርምያስ፣ ጳውሎስና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች አብዛኛውን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ቲኦክራሲያዊ ጉዳዮችን ለማከናወን ተጠቅመውበታል። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል። እርግጥ ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን ኢየሱስ ነው። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በምድር ላይ የነበረውን ቀሪ ሕይወት ምሥራቹን ለመስበክና ለይሖዋ ክብር ለማምጣት ተጠቅሞበታል። በመሆኑም፣ ይሖዋን እንደ ጌታው አድርጎ የሚመለከት አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ አንደኛውን ቦታ መያዝ ያለበት ይሖዋን ማገልገል እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? በአንድ በኩል አስፈላጊ የሆኑ ሰብዓዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረግን በሌላ በኩል ደግሞ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ማስቀደም የምንችለው እንዴት ነው?​—መዝሙር 71:15ን እና መዝ 145:2ን አንብብ።

13, 14. (ሀ) ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ የትኛውን ጉዳይ እንዲያስቡበት ተበረታተዋል? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ከፍተኛ የእርካታ ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርገው ምንድን ነው?

13 ባለፉት ዓመታት የይሖዋ ድርጅት፣ አቅኚ መሆን እንችል እንደሆነ በጸሎት እንድናስብ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲያበረታታን ቆይቷል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ በወር ውስጥ በአማካይ 70 ሰዓት ለማሳለፍ ሁኔታቸው አይፈቅድላቸውም። በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ሊያዝኑ አይገባም። (1 ጢሞ. 5:8) የአንተስ ሁኔታ እንዴት ነው? አቅኚነት ፈጽሞ ልትደርስበት የማትችል ግብ ነው?

14 ብዙ የአምላክ አገልጋዮች በዚህ ዓመት፣ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ያገኙትን ደስታ መለስ ብለህ አስብ። በመጋቢት ወር ረዳት አቅኚ ሆነው ለሚያገለግሉ ክርስቲያኖች በመስክ አገልግሎት እንደምርጫቸው 30 ወይም 50 ሰዓት ማሳለፍ እንዲችሉ ልዩ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። (መዝ. 110:3) በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች በረዳት አቅኚነት የተካፈሉ ሲሆን በዚህም የተነሳ በጉባኤዎች ውስጥ ልዩ የሆነ የደስታ ስሜት እንደተፈጠረ በግልጽ ይታይ ነበር። ታዲያ እንዲህ ያለውን ደስታ በተደጋጋሚ እንድታጭድ ሁኔታዎችን ማስተካከል ትችል ይሆን? ራሱን የወሰነ አንድ ክርስቲያን በአቅኚነት ሲካፈል ከፍተኛ የእርካታ ስሜት ስለሚሰማው በየዕለቱ ውሎውን መለስ ብሎ ሲያስብ “ይሖዋ፣ አንተን ለማገልገል የምችለውን ሁሉ አድርጌአለሁ” ማለት ይችላል።

15. ወጣት ክርስቲያኖች ከሰብዓዊ ትምህርት ጋር በተያያዘ ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል?

15 ትምህርትህን ልታጠናቅቅ የተቃረብክ ክርስቲያን ልትሆን ትችላለህ፤ ታዲያ በጥሩ ጤንነት ላይ የምትገኝና ብዙ ኃላፊነት የሌለብህ ከሆነ የዘወትር አቅኚ ለመሆን ለምን በቁም ነገር አታስብም? አስተማሪዎችህ ለአንተ በማሰብ ከፍተኛ ትምህርት እንድትከታተልና ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ እንድትይዝ ሊያበረታቱህ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሰዎች የሚተማመኑት ዘላቂነት በሌላቸው ነገሮች ማለትም በሰብዓዊ ድርጅቶችና በገንዘብ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ የምትሰጥ ከሆነ የምትከታተለው ግብ የማያስቆጭና ዘላቂ ይሆናል። እንዲህ ያለውን የጥበብ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ የኢየሱስን ፍጹም ምሳሌ እንደምትከተል የምታሳይ ከመሆኑም ሌላ ደስታ ያመጣልሃል። ጥበቃም ያስገኝልሃል። በተጨማሪም ራስህን ለይሖዋ ስትወስን የገባኸውን ቃል ጠብቀህ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረክ ያሳያል።​—ማቴ. 6:19-21፤ 1 ጢሞ. 6:9-12

16, 17. ከሰብዓዊ ሥራና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

16 ብዙ የአምላክ አገልጋዮች የቤተሰባቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ረጅም ሰዓት ይሠራሉ። ይሁንና አንዳንዶች ከሚያስፈልጋቸው በላይ ለማግኘት ሲሉ ትርፍ ሰዓት ይሠራሉ። (1 ጢሞ. 6:8) የንግዱ ዓለም፣ ለገበያ የሚያቀርባቸውን ምርቶች በሙሉ ካልገዛን ሕይወታችን የተሟላ እንዳልሆነ እኛን ለማሳመን የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን የሰይጣን ዓለም ቅድሚያ በሚሰጡት ነገር ላይ ጫና እንዲያሳድርባቸው አይፈቅዱም። (1 ዮሐ. 2:15-17) ከሰብዓዊ ሥራቸው ጡረታ የወጡ ክርስቲያኖች ጊዜያቸውን በአቅኚነት አገልግሎት ከማሳለፍ የተሻለ ምን ነገር ማድረግ ይችላሉ? አቅኚ በመሆን የይሖዋን አገልግሎት እንደሚያስቀድሙ ማሳየት ይችላሉ።

17 የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ እንደሚከተለው በማለት ራሳቸውን መጠየቅ ይችላሉ፦ በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ምንድን ነው? ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አስቀድማለሁ? የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እከተላለሁ? ኢየሱስ እሱን ያለማቋረጥ እንድንከተለው የሰጠንን ምክር ተግባራዊ አደርጋለሁ? በስብከቱ ሥራ ወይም በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የበለጠ ለመካፈል ስል ፕሮግራሜን ማስተካከል እችላለሁ? አሁን ያለሁበት ሁኔታ አገልግሎቴን ለማስፋት ባያስችለኝም እንኳ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ለማዳበር ጥረት እያደረኩ ነው?

‘ፍላጎት እንዲያድርባችሁና ለተግባር እንድትነሳሱ’

18, 19. ስለ ምን ጉዳይ መጸለይ ትችላለህ? እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን የሚያስደስተው ለምንድን ነው?

18 የአምላክ ሕዝቦች ቅንዓት እንዳላቸው ማየት በጣም ያስደስታል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች፣ ሁኔታቸው ቢፈቅድላቸውም እንኳ አቅኚ ለመሆን ፍላጎቱ ላይኖራቸው ወይም ብቃቱ እንደሌላቸው ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። (ዘፀ. 4:10፤ ኤር. 1:6) ታዲያ ምን ማድረግ ይችላሉ? ጉዳዩን አስመልክተው ሊጸልዩ አይገባም? በእርግጥም እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ ነው። ‘ደስ ለሚሰኝበት ነገር ሲል ፍላጎት እንዲያድርባቸውም ሆነ ለተግባር እንዲነሳሱ በውስጣቸው የሚሠራው’ ይሖዋ እንደሆነ ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ነግሯቸው ነበር። (ፊልጵ. 2:13) አገልግሎትህን ለማስፋት ተነሳሽነቱ ከሌለህ በውስጥህ ፍላጎት እንዲያሳድርብህና ችሎታ እንዲሰጥህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው።​—2 ጴጥ. 3:9, 11

19 ኖኅ፣ ሙሴ፣ ኤርምያስ፣ ጳውሎስና ኢየሱስ ለአምላክ ያደሩ ነበሩ። ጊዜያቸውንም ሆነ ጉልበታቸውን የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት ለማወጅ ተጠቅመውበታል። እንዲሁም ትኩረታቸው እንዲከፋፈል አልፈቀዱም። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ መምጣቱ አይቀሬ ነው፤ እንግዲያው ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ክርስቲያኖች በሙሉ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች የተዉትን ግሩም ምሳሌ ለመከተል የምንችለውን ሁሉ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። (ማቴ. 24:42፤ 2 ጢሞ. 2:15) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋን የምናስደስት ከመሆኑም በላይ አትረፍርፎ ይባርከናል።​—ሚልክያስ 3:10ን አንብብ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በኤርምያስ በኩል የተላለፈልን የአምላክ ቃል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 104-106 እንዲሁም የነሐሴ 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 16-19 እና የጥቅምት 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8, 9 ከአንቀጽ 7-9 ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች፣ ኖኅ የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ለመስማት ፈቃደኞች አልነበሩም

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዘወትር አቅኚ ለመሆን በቁም ነገር አስበህ ታውቃለህ?