በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ”

“በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ”

“በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ”

“ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።”​—2 ጴጥ. 1:21

ልናሰላስልባቸው የሚገቡ ነጥቦች

የአምላክ መልእክት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የደረሰው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ለመሆኑ የትኞቹን ማስረጃዎች መጥቀስ ይቻላል?

ለአምላክ ቃል ያለህን አድናቆት ይዘህ ለመቀጠል በየዕለቱ ምን ማድረግ ትችላለህ?

1. በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

የመጣነው ከየት ነው? ምድር ላይ የምንኖረው ለምንድን ነው? የሰው ልጆች የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? ምድር እንዲህ የሆነችው ለምንድን ነው? ስንሞት ምን እንሆናለን? በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች እነዚህን ጥያቄዎች ይጠይቃሉ። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ባይኖረን ኖሮ የእነዚህንም ሆነ አስፈላጊ የሆኑ የሌሎች ጥያቄዎችን መልስ ማወቅ ባልቻልን ነበር። ቅዱሳን መጻሕፍት ባይኖሩ ኖሮ እውቀት ለመቅሰም የሚረዳን ዋነኛው ምንጭ የሕይወት ተሞክሯችን ይሆን ነበር። ታዲያ ትምህርት የምንቀስመው ከራሳችን ተሞክሮ ብቻ ቢሆን ኖሮ መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ ‘ሕግ’ የተሰማው ዓይነት ስሜት ይኖረን ነበር?​—መዝሙር 19:7ን አንብብ።

2. ከአምላክ ላገኘነው ውድ ስጦታ ማለትም ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ምን ሊረዳን ይችላል?

2 የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል መጀመሪያ የነበራቸው ፍቅር እየቀዘቀዘ እንዲሄድ ፈቅደዋል። (ከ⁠ራእይ 2:4 ጋር አወዳድር።) በዚህም የተነሳ ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ መመላለስ አቁመዋል። (ኢሳ. 30:21) እኛ ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲደርስብን አንፈልግም። ለመጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ ላሉት ትምህርቶች ያለን አድናቆት እንዳይቀዘቅዝ ጥረት ማድረግ እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አፍቃሪ ከሆነው ፈጣሪያችን ያገኘነው ልዩ ስጦታ ነው። (ያዕ. 1:17) ‘ለአምላክ ቃል’ ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ምን ሊረዳን ይችላል? ለዚህ ቁልፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመጻፍ እንዴት በመንፈስ እንደተመሩ ማሰብ ነው። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን ከሚያረጋግጡት በርካታ ማስረጃዎች መካከል የተወሰኑትን መመርመር ይጠይቃል። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክን ቃል በየዕለቱ ለማንበብና የምናገኘውን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ያነሳሳናል።​—ዕብ. 4:12

‘በመንፈስ ቅዱስ የተመሩት’ እንዴት ነው?

3. ነቢያትና ሌሎች ጸሐፊዎች ‘በመንፈስ ቅዱስ ተመርተዋል’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከ1513 ዓ.ዓ. እስከ 98 ዓ.ም. ባሉት ዘመናት ማለትም 1,610 ዓመታትን በሚሸፍን ጊዜ ውስጥ ሲሆን የጻፉት 40 የሚያህሉ ሰዎች ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ‘በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ’ ነቢያት ናቸው። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21ን አንብብ።) ‘መመራት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማጓጓዝ ወይም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ” የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን “መነሳሳት፣ መነዳት፣ መገፋፋት ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።” * ለምሳሌ ይህ ቃል በ⁠የሐዋርያት ሥራ 27:15 ላይ፣ አንድ መርከብ እንቅስቃሴው ከተገታ በኋላ በነፋስ እየተነዳ ወደ አንድ አቅጣጫ መጓዙን ለመግለጽ ተሠርቶበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ‘በመንፈስ ቅዱስ ተመርተዋል’ ሲባል አምላክ በሥራ ላይ ባለው ኃይሉ አማካኝነት ያነጋግራቸው፣ ያነሳሳቸው እንዲሁም መመሪያ ይሰጣቸው ነበር ማለት ነው። በዚህም ምክንያት እነዚህ ሰዎች የጻፉት የራሳቸውን ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ ነው። እንዲያውም በመንፈስ የተመሩ ነቢያትና ሌሎች ጸሐፊዎች ራሳቸው የተናገሩትን ትንቢትም ሆነ የጻፉትን ነገር የማይረዱበት ጊዜ ነበር። (ዳን. 12:8, 9) አዎን፣ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ” በመሆኑ ከሰዎች አመለካከት የጸዳ ነው።​—2 ጢሞ. 3:16

4-6. ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መልእክቱን እንዲጽፉ ያደረገው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 ይሁንና የአምላክ መልእክት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የደረሰው እንዴት ነው? ጸሐፊዎቹ፣ የሚጽፉት እያንዳንዱ ነገር ቃል በቃል ተነግሯቸው ነው? ወይስ ሐሳቡ ከተነገራቸው በኋላ በራሳቸው አባባል ያሰፍሩታል? እስቲ፣ አንድ ሥራ አስኪያጅ ደብዳቤ የሚጽፍበትን መንገድ ለማሰብ እንሞክር። ቃል በቃል መጻፍ ያለበት ነገር በሚኖርበት ጊዜ ደብዳቤውን ራሱ ይጽፋል፤ አሊያም ቃል በቃል በመንገር ጸሐፊውን ያጽፋታል። ጸሐፊዋ ደብዳቤውን ጽፋ ስትጨርስ ሥራ አስኪያጁ ይፈርምበታል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ዋናውን ሐሳብ ከነገራት በኋላ ጸሐፊዋ ደብዳቤውን በራሷ አባባል ወይም የአጻጻፍ ስልት ትጽፈዋለች። ከዚያም ሥራ አስኪያጁ ደብዳቤውን ያነበውና አንዳንድ ማስተካከያዎችን እንድታደርግ ሊነግራት ይችላል። በመጨረሻም ደብዳቤው ላይ የሥራ አስኪያጁ ፊርማ ስለሚሰፍር ደብዳቤው ከእሱ እንደመጣ ተደርጎ ይቆጠራል።

5 በተመሳሳይም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቀጥታ ‘በአምላክ ጣት’ የተጻፉ ናቸው። (ዘፀ. 31:18) በተጨማሪም ይሖዋ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ መጻፍ ያለበትን ነገር ቃል በቃል ይናገር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በ⁠ዘፀአት 34:27 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ እናገኛለን፦ “እግዚአብሔር ሙሴን፣ ‘እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው፤ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና’ አለው።” በተመሳሳይም ይሖዋ ለነቢዩ ኤርምያስ “የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፈው” ብሎት ነበር።​—ኤር. 30:2

6 አብዛኛውን ጊዜ ግን አምላክ፣ መጻፍ ያለበትን ነገር ቃል በቃል ከመንገር ይልቅ ሐሳቡን በመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ ልብና አእምሮ ውስጥ በማኖር የራሳቸውን ቃላት ተጠቅመው እንዲጽፉት ይፈቅድላቸው ነበር። መክብብ 12:10 (የ1954 ትርጉም) “ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ” ይላል። የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ “ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ [ስለመረመረ] ታሪኩን በቅደም ተከተል” ጽፏል። (ሉቃስ 1:3) የሰዎች አለፍጽምና ተጽዕኖ በማድረግ የአምላክን ቃል እንዳያዛባው መንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ያደርግ ነበር።

7. አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጻፍ ሰዎችን መጠቀሙ ጥበበኛ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

7 አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጻፍ የሰው ልጆችን መጠቀሙ ታላቅ ጥበብ እንዳለው ያሳያል። ቃላት፣ መረጃ ከማስተላለፍ ባለፈ ስሜትን ይገልጻሉ። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው መላእክትን ተጠቅሞ ቢሆንስ? ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን እንደ ፍርሃት፣ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ ያሉ ስሜቶችን መላእክት ጥሩ አድርገው መግለጽ ይችሉ ነበር? አምላክ፣ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተቀበሉትን ሐሳብ በራሳቸው መንገድ እንዲጽፉት በማድረጉ መልእክቱ ፍቅር በሚንጸባረቅበትና የሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ ሊጻፍ ችሏል!

ማስረጃዎቹን ማስተዋል

8. ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሊወዳደር የሚችል ሌላ የሃይማኖት መጽሐፍ የለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል አምላክን ለማወቅ ሊረዳን የሚችል የሃይማኖት መጽሐፍ የለም። ለምሳሌ የሂንዱይዝም መጻሕፍትን ብንመለከት የቬዲክ መዝሙሮችና እነዚህን መዝሙሮች አስመልክቶ የተዘጋጁ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች፣ ኡፓኒሻድ ተብለው የሚጠሩ የፍልስፍና ጽሑፎች እንዲሁም ራማያና እና ማሃባራታ ተብለው የሚጠሩ አፈ ታሪኮች ስብስብ ነው። ማሃባራታ የሥነ ምግባር መመሪያዎች የሚገኙበትን ባጋቫድ ጊታ የተባለውን መጽሐፍም ይዟል። ቲፒታካ ከሚባሉት የቡድሂዝም ቅዱስ መጻሕፍት (ሦስት ጥራዝ ናቸው) ውስጥ አንደኛው በዋነኝነት የሚያወሳው በኅብረት የሚኖሩት መነኮሳት ስለሚመሩባቸው ሕግጋትና ደንቦች ነው። ሁለተኛው ጥራዝ በአብዛኛው የያዘው የሃይማኖቱን መሠረተ ትምህርት ነው። ሦስተኛው ጥራዝ ደግሞ የቡድሃን የቃል ትምህርት ይዟል። ቡድሃ፣ ራሱን እንደ አምላክ ቆጥሮ አያውቅም፤ ስለ አምላክም ቢሆን ብዙ ነገር አልጠቀሰም። የኮንፊሺያኒዝም ጽሑፎች ስለተለያዩ ክንውኖች የሚተርኩ ዘገባዎች፣ የሥነ ምግባር ደንቦች፣ የአስማት አሠራሮችና የመዝሙሮች ስብስብ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት የሚመራበት ቅዱስ መጽሐፍ፣ አምላክ አንድ እንደሆነና የወደፊቱን ጊዜ ጨምሮ ሁሉን ነገር ማወቅ እንደሚችል ቢያስተምርም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ የሚገኘውን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም እንኳ አይጠቅስም።

9, 10. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን ያስተምረናል?

9 ዋና ዋና የሚባሉት አብዛኞቹ የሃይማኖት መጻሕፍት ስለ አምላክ ምንም አይናገሩም፤ ቢናገሩም ጥቂት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ ይሖዋ አምላክም ሆነ እሱ ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል። የእሱን ማንነት በደንብ እንድንረዳ የሚያስችሉንን በርካታ ሐሳቦች በውስጡ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን የሚገልጸው ገደብ የለሽ ኃይል ያለው እንዲሁም ጥበበኛና ፍትሐዊ እንደሆነ አድርጎ ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ፍቅር ያለው አምላክ እንደሆነም ጭምር ነው። (ዮሐንስ 3:16ን እና 1 ዮሐንስ 4:19ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ አያዳላም፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው’ ይላል። (ሥራ 10:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች የሚገኝ መሆኑ በራሱ የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት ያረጋግጣል። የቋንቋ ምሁራን እንደሚናገሩት ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ወደ 6,700 ቋንቋዎች የሚነገሩ ሲሆን 90 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የሚጠቀምባቸው ቋንቋዎች ግን ወደ 100 ገደማ ብቻ ናቸው። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ከ2,400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። በሌላ አባባል በዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው ማለት ይቻላል ቢያንስ በከፊል መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት ይችላል።

10 ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም መሥራቴን እቀጥላለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 5:17) ይሖዋ ‘ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ’ ነው። እስቲ እስከ ዛሬ ድረስ ያከናወናቸውን ነገሮች ለማሰብ ሞክር! (መዝ. 90:2) አምላክ ባለፉት ዘመናትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ አልፎ ተርፎም ወደፊት ሊያደርጋቸው ስላሰባቸው ነገሮች የሚነግረን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን የሚያስደስተውንና የማያስደስተውን ነገር ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ወደ እሱ መቅረብ የምንችለው እንዴት እንደሆነም ይገልጽልናል። (ያዕ. 4:8) እንግዲያው ልባችን የሚመኛቸው ነገሮች ወይም ያሉብን ጭንቀቶች ከአምላክ እንዳያርቁን እንጠንቀቅ።

11. መጽሐፍ ቅዱስ የትኞቹን ጉዳዮች በተመለከተ አስተማማኝ ምክር ይሰጣል?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ ነው እንድንል የሚያደርገን ሌላው ምክንያት መጽሐፉ የጥበብ ጎተራ እንዲሁም የሚሰጠው ምክር አስተማማኝ መሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 2:16) ይህ ጥቅስ የተወሰደው ከኢሳይያስ መጽሐፍ ሲሆን ነቢዩ በዘመኑ የነበሩ እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፦ “የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] መንፈስ የተረዳ፣ አማካሪውስ ሆኖ ያስተማረው ማነው?” (ኢሳ. 40:13) መልሱ ‘ማንም’ የሚል እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን፣ ልጆችን፣ መዝናኛን፣ ወዳጅነትን፣ ትጋትን፣ ሐቀኝነትን እና ሥነ ምግባርን አስመልክቶ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ወደር የሌለው ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑ ምንም አይደንቅም! በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር እንከን አይወጣለትም። በሌላ በኩል ግን የሰው ልጆች፣ ምንጊዜም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር መስጠት አይችሉም። (ኤር. 10:23) ከዚህ በፊት የሰጡት ምክር የተሳሳተ እንደሆነ በተረዱ ቁጥር በየጊዜው ማስተካከያ ያደርጋሉ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሰው ሐሳብ ከንቱ እንደ ሆነ’ መናገሩ ተገቢ ነው።​—መዝ. 94:11

12. ባለፉት ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ምን ዓይነት ሙከራዎች ተደርገዋል?

12 የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት እውነተኛው አምላክ እንደሆነ የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ ደግሞ መጽሐፉን ለማጥፋት የተደረጉት ጥረቶች አለመሳካታቸው ነው፤ በዚህ ረገድ ታሪክ ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት። በ168 ዓ.ዓ. አንታይከስ አራተኛ የተባለ የሶርያ ንጉሥ በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን የሕጉን መጻሕፍት ከያሉበት ታድነው እንዲቃጠሉ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅላጢያን ክርስቲያኖች የሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች እንዲወድሙና የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እንዲቃጠሉ የሚያዝ አዋጅ በ303 ዓ.ም. አውጥቶ ነበር። የክርስቲያኖችን የመሰብሰቢያ ቦታና ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ለአሥር ዓመታት ቀጥሎ ነበር። ከ11ኛው መቶ ዘመን በኋላ ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መጽሐፍ ቅዱስ ተራው ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋ እንዳይተረጎም በማገድ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳያውቁ ለማድረግ ሞክረዋል። ሰይጣንና ወኪሎቹ እንዲህ የመሰለ ጥረት ቢያደርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ሳይጠፋ እስከ ዘመናችን መዝለቅ ችሏል። ይሖዋ፣ ለሰው ልጆች የሰጠው ይህ መጽሐፍ በምንም ዓይነት መንገድ እንዲጠፋ አልፈቀደም።

ብዙዎችን ያሳመኑ ማስረጃዎች

13. መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ለመሆኑ የትኞቹን ማስረጃዎች መጥቀስ እንችላለን?

13 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ። ለምሳሌ በውስጡ ያለው ሐሳብ እርስ በርስ መስማማቱን፣ ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ መሆኑን፣ ትንቢቶቹ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን፣ የጸሐፊዎቹን ግልጽነት፣ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል ያለው መሆኑንና ከታሪክ አኳያ ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፉን እንዲሁም በአንቀጽ 1 ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የያዘ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ መሆኑን እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

14-16. (ሀ) አንድ ሙስሊምና አንዲት ሂንዱ እንዲሁም አምላክ መኖሩን ትጠራጠር የነበረች አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ መሆኑን እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው? (ለ) በአገልግሎት ላይ ለምታገኛቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን ለማስረዳት የትኛውን ማስረጃ መጠቀም አስበሃል?

14 መካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ አንድ አገር ውስጥ ይኖር የነበረው አንዋር * ያደገው በእስልምና እምነት ውስጥ ነው። ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ በኖረበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ አገኙት። አንዋር፣ ብዙዎች በክርስትና ስም የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ማጥፋታቸውን በመስማቱ ለክርስቲያኖች መጥፎ አመለካከት እንደነበረው ተናግሯል። “ይሁንና በተፈጥሮዬ አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት ስላለኝ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ” ብሏል። አንዋር ወደ አገሩ ሲመለስ ግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋረጠ። በዚህ ሁኔታ የተወሰኑ ዓመታት ካለፉ በኋላ ወደ አውሮፓ ተዛውሮ መኖር ጀመረ። በዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ቀጠለ፤ በኋላም የደረሰበትን መደምደሚያ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውና ቅዱሳን መጻሕፍት እርስ በርሳቸው የሚስማሙ መሆናቸው እንዲሁም በይሖዋ አገልጋዮች መካከል ያለው ፍቅር መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንዳምን አደረገኝ።” አንዋር በ1998 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል።

15 የአሥራ ስድስት ዓመት ወጣት የሆነችው አይሻ ያደገችው ቀናተኛ የሂንዱ እምነት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ቀደም ሲል የነበራትን ሕይወት አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “የምጸልየው ወደ ቤተ መቅደስ ስሄድ ወይም ችግር ሲያጋጥመኝ ብቻ ነበር። ይሁንና ሁሉ ነገር ከተመቻቸልኝ በፍጹም ስለ አምላክ አላስብም።” አክላም “የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ መጥተው ሲያናግሩኝ ግን ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ” ብላለች። አይሻ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የአምላክ ወዳጅ መሆን ችላለች። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን እንድታምን ያደረጋት ምንድን ነው? “መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቼ በሙሉ መልስ ሰጥቶኛል። በአምላክ ላይ እምነት እንዳሳድር ረድቶኛል፤ በመሆኑም አምላክን ማየት፣ ማለቴ ወደ ቤተ መቅደስ ሄጄ በምስል ፊት መስገድ አያስፈልገኝም” በማለት ተናግራለች።

16 ፓውላ ያደገችው በካቶሊክ እምነት ውስጥ ቢሆንም የወጣትነት ዕድሜ ላይ ስትደርስ አምላክ መኖሩን መጠራጠር ጀመረች። ይሁንና አንድ ቀን ሕይወቷን የሚቀይር ነገር አጋጠማት። እንዲህ ትላለች፦ “ለወራት ተጠፋፍተን ከነበረ አንድ ጓደኛዬ ጋር ተገናኘን። በዚያን ወቅት ብዙዎች የሂፒ ሕይወት ይመሩ ነበር። ይህ ሰው በጣም እንደተለወጠ ማለትም ሥርዓታማና ደስተኛ እንደሆነ ስመለከት ‘ምን አገኘህ? ለመሆኑ እስከ ዛሬ የት ጠፍተህ ነው?’ ብዬ ጠየቅኩት። እሱም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ከነገረኝ በኋላ ለእኔም ምሥክርነቱን መስጠት ጀመረ።” ቀደም ሲል አምላክ መኖሩን ትጠራጠር የነበረችው ፓውላ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው እውነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ስትመለከት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ፍላጎት አደረባት፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን አምና ተቀበለች።

‘ሕግህ ለእግሬ መብራት ነው’

17. የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበብህና ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰልህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

17 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለሰው ልጆች የሰጠው ድንቅ ስጦታ ነው። በየዕለቱ የአምላክን ቃል በማንበብ የምትደሰት ከሆነ ለመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የዚህ መጽሐፍ ምንጭ ለሆነው አምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። (መዝ. 1:1, 2) ምንጊዜም ቃሉን ማጥናት ከመጀመርህ በፊት የምታነበውን ነገር መረዳት እንድትችል አምላክን በጸሎት ጠይቅ። (ሉቃስ 11:13) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሐሳቦች ይዟል፤ በመሆኑም ባነበብከው ነገር ላይ የምታሰላስል ከሆነ የአምላክን አስተሳሰብ እያዳበርክ ስለምትመጣ በእሱ መንገድ ማሰብ ትጀምራለህ።

18. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን መቀጠል ያለብህ ለምንድን ነው?

18 የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እየቀሰምክ ስትመጣ የተማርከውን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብሃል። (መዝሙር 119:105ን አንብብ።) ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደ መስተዋት ተጠቀምባቸው። ማስተካከያ ማድረግ ያለብህ ነገር ሲኖር ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትበል። (ያዕ. 1:23-25) እምነትህን ለሌሎች ለማስረዳትም ሆነ ትሑት በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን የሐሰት ትምህርት ቆርጠህ ለማስወገድ እንደ ሰይፍ የሆነውን የአምላክን ቃል ተጠቀም። (ኤፌ. 6:17) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በምትጠቀምበት ጊዜ ሁሉ አምላክ፣ ነቢያትንና ሌሎች ሰዎችን ‘በቅዱስ መንፈሱ በመምራት’ በውስጡ የሚገኘውን መልእክት እንዲጽፉ በማድረጉ አመስጋኝ ሁን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ኤ ግሪክ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ኤንድ አዘር ኧርሊ ክርስቺያን ሊትሬቸር

^ አን.14 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የምታነብ ከሆነ የመጽሐፉ ምንጭ ለሆነው አምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ደብዳቤ ከተፈረመበት ደብዳቤውን የላከው ፊርማውን ያኖረው ሰው እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል