በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸው ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነው መቼ ነው?

▪ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልም ያየው ግዙፉ ምስል በዓለም ላይ የተነሱ ኃያላን መንግሥታትን በሙሉ የሚወክል አይደለም። (ዳን. 2:31-45) ከዚህ ይልቅ ምስሉ የሚያመለክተው በዳንኤል ዘመንና ከዚያ ወዲህ የተነሱ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ አምስት ኃያላን መንግሥታትን ብቻ ነው።

ዳንኤል ስለ ምስሉ የሰጠው ማብራሪያ እንደሚያመለክተው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ወደ ዓለም መድረክ ብቅ የሚለው ሮምን ድል አድርጎ ሳይሆን ከራሱ ከሮም መንግሥት በመውጣት ነው። የምስሉ ቅልጥሞች ላይ ያለው ብረት እግሮቹን ጨምሮ እስከ ጣቶቹ ድረስ እንደሚዘልቅ ዳንኤል ተመልክቷል። (እግሮቹና ጣቶቹ ላይ ብረቱ ከሸክላ ጋር ተቀላቅሏል።) * ይህም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ከብረት እግሮቹ እንደሚወጣ ያመለክታል። ታሪክም ቢሆን የዚህን ማብራሪያ ትክክለኛነት ያረጋግጣል። ቀደም ሲል የሮም ግዛት ክፍል የነበረችው ብሪታንያ በ1700ዎቹ መጨረሻ ላይ በዓለም መድረክ ጎላ ብላ መታየት ጀመረች። በኋላም ዩናይትድ ስቴትስ ኃያል መንግሥት መሆን ጀመረች። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸው ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ገና አልተቋቋመም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ የሆነ ጥምረት ገና አልፈጠሩም። ይህ ጥምረት የተፈጠረው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው።

በዚያ ጊዜ “የመንግሥቱ ልጆች” ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው በብሩክሊን ኒው ዮርክ ስለሆነ በአብዛኛው እንቅስቃሴ የሚያደርጉት በዩናይትድ ስቴትስ ነበር። (ማቴ. 13:36-43) ቅቡዓኑ በብሪታንያ መንግሥት ሥር በሚገኙ አገሮች ውስጥ በቅንዓት እየሰበኩ ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብሪታንያና አሜሪካ የጋራ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት ልዩ የሆነ ጥምረት ፈጠሩ። በተጨማሪም እነዚህ አገሮች ‘የሴቲቱ’ ዘር ክፍል የሆኑት ቅቡዓን የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በማገድና የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይመሩ የነበሩትን በማሰር ጠላትነታቸውን አሳይተዋል፤ በጦርነቱ ምክንያት የተቀሰቀሰው ብሔራዊ ስሜት በጣም እየተጋጋለ መምጣቱ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።​—ራእይ 12:17

በመሆኑም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አኳያ ስንመለከተው ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የተቋቋመው ብሪታንያ በዓለም መድረክ ጎላ ብላ መታየት በጀመረችበት በ1700ዎቹ መጨረሻ ላይ ሳይሆን በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ነው። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ከብረቱ ጋር የተቀላቀለው ሸክላ የሚያመለክተው በብረት የተመሰለው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ተጽዕኖ በሚያሳድርባቸው የምድር ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን የእሱን አቅም የሚያዳክሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ነው። ባለፉት ዓመታት፣ ይህ ኃያል መንግሥት መሆን የሚፈልገውን ያህል ጠንክራ እንዳይሆን ሸክላው እንቅፋት ሆኖበታል።

^ አን.6 ይህ፣ የዳንኤል ትንቢት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 57 አንቀጽ 24 ላይ በወጣው ትምህርት እንዲሁም በገጽ 56 እና 139 ላይ ለሚገኙት ሥዕላዊ መግለጫዎች በተሰጡት ማብራሪያዎች ላይ የተደረገ ማስተካከያ ነው።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዋናው መሥሪያ ቤት ይሠሩ የነበሩ ስምንት ወንድሞች ሰኔ 1918 ወደ ወኅኒ ወርደው ነበር