በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የድካማችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ’

‘የድካማችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ’

‘የድካማችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ’

ንጉሥ አሳ ሠራዊቱን እየመራ ከይሁዳ ተራሮች ተነስቶ ወደ ረባዳው የባሕር ጠረፍ ለመድረስ ጥልቅ የሆነውን ሸለቆ ተከትሎ እየገሰገሰ ነው። ሠራዊቱ ሰፋ በሚለው የሸለቆው ክፍል ላይ ሲደርስ አየር ለመውሰድ አረፍ አለ። በዚህ ጊዜ አሳ አሻግሮ ሲመለከት በጣም ብዙ የጠላት ሠራዊት ሰፍሮ በማየቱ ደነገጠ! ይህ የኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥሩ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ሲሆን የአሳ ሠራዊት ግን ከዚህ የጠላት ሠራዊት በግማሽ ያህል ያንሳል።

አሳ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ተፋጦ ባለበት በዚህ ወቅት መጀመሪያ ማድረግ የሚፈልገው ምን ይሆን? ለጦር አዛዦቹ ትእዛዝ መስጠት? ለሠራዊቱ ማበረታቻ መስጠት? ወይስ ለቤተሰቡ ደብዳቤ መጻፍ? አሳን እነዚህ ነገሮች ከማድረግ ይልቅ በዚህ አስጨናቂ ሰዓት ወደ አምላኩ ጸለየ።

ይህን ጸሎትና በዚያ ወቅት የነበሩትን ክንውኖች ከመመርመራችን በፊት አሳ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ እስቲ እንመልከት። አሳ ወደ አምላክ ዞር እንዲል ያደረገው ምንድን ነው? ደግሞስ የአምላክን እርዳታ መጠየቁ ተገቢ ነበር? ስለ አሳ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጥረት ስለሚባርክበት መንገድ ምን ያስተምረናል?

አሳ ያስመዘገበው ታሪክ

እስራኤል ለሁለት ከተከፈለች በኋላ ባሉት 20 ዓመታት ይሁዳ በጣዖት አምልኮ ተዘፍቃ ነበር። አሳ በ977 ዓ.ዓ. ሥልጣን ላይ ሲወጣ በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ የከነዓናውያንን የመራባት አማልክት ያመልኩ ነበር። ይሁን እንጂ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአሳ የግዛት ታሪክ እንዲህ ይላል፦ “አሳ በአምላኩ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤ ባዕዳን መሠዊያዎችንና ማምለኪያ ኰረብታዎችን አስወገደ፤ ማምለኪያ ዐምዶችን አፈረሰ፤ አሼራ ለተባለች ጣዖት አምላክ የቆሙ የዕንጨት ቅርጽ ምስሎችንም ቈራረጠ።” (2 ዜና 14:2, 3) በተጨማሪም አሳ በቤተ መቅደስ ውስጥ በሃይማኖት ስም ግብረ ሰዶም ይፈጽሙ የነበሩትን “ወንደቃዎች” ከይሁዳ ግዛት አስወጣ። አሳ በዚህ ብቻ አላበቃም። ሕዝቡ “የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] እንዲፈልጉ፣ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲፈጽሙ የይሁዳን ሕዝብ” አሳሰባቸው።​—1 ነገ. 15:12, 13፤ 2 ዜና 14:4

አሳ ለእውነተኛው አምልኮ ባሳየው ቅንዓት ይሖዋ በመደሰቱ ረጅም ዘመን ሰላምን በመስጠት ባረከው። ንጉሡም “አምላካችንን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] . . . ፈለግነው፤ እርሱም በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጠን” ማለት ችሎ ነበር። ሕዝቡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የይሁዳን ከተሞች ቅጥር አጠናከረ። መጽሐፍ ቅዱስ “እነርሱም ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም” ይላል።​—2 ዜና 14:1, 6, 7

በጦር ሜዳ

አሳ ካስመዘገበው ታሪክ አንጻር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተጠቀሱት ሁሉ የሚበልጠውን ሠራዊት ሲጋፈጥ መጸለዩ የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። አምላክ እምነት እንዳላቸው በተግባር ለሚያሳዩ ሰዎች ወሮታ እንደሚከፍል አሳ ያውቃል። በመሆኑም ይህ ንጉሥ ይሖዋ እንዲረዳው በጸሎት ተማጸነ። በይሖዋ እስከተማመነና የእሱን እርዳታ እስካገኘ ድረስ የመጣበት ጠላት ምንም ያህል ኃያል ቢሆን ወይም የቱንም ያህል ብዛት ቢኖረው ምንም እንደማይሆን ተገንዝቦ ነበር። ጦርነቱ የይሖዋን ስም የሚነካ በመሆኑ አሳ አምላክን ሲለምን ይህን ጉዳይ ግምት ውስጥ አስገብቷል። ንጉሡ እንዲህ አለ፦ “አምላካችን እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ በአንተ ታምነናልና፣ ይህን ታላቅ ሰራዊት በስምህ እንገጥመዋለን፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም።” (2 ዜና 14:11) አሳ እንዲህ በማለት ልመና ያቀረበ ያህል ነበር፦ ‘አቤቱ ይሖዋ፣ የኢትዮጵያውያኑ ወረራ በአንተ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው። ደካማ የሆኑ ሰዎች፣ ስምህን የሚሸከሙትን ሕዝቦች በማጥፋት ስምህ ላይ ነቀፌታ እንዲያደርሱ አትፍቀድ።’ በመሆኑም ይሖዋ “ኢትዮጵያውያንን በአሳና በይሁዳ ፊት መታቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ሸሹ።”​—2 ዜና 14:12

ዛሬም ቢሆን የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ ኃይለኛ ተቃዋሚዎች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህን ጠላቶች በሰብዓዊ ጦር መሣሪያዎች አማካኝነት ቃል በቃል አንዋጋቸውም። ያም ሆኖ ይሖዋ ለስሙ ሲሉ መንፈሳዊ ውጊያ የሚያካሂዱ ታማኝ አገልጋዮቹን ድል በመስጠት እንደሚባርካቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በግለሰብ ደረጃ የምናደርገው ውጊያ በዓለም ላይ የተስፋፋውን ልቅ ሥነ ምግባር መቋቋምን፣ ከግል ድክመቶቻችን ጋር መታገልን ወይም ቤተሰባችንን ከበካይ ተጽዕኖዎች መጠበቅን ሊያካትት ይችላል። የሚያጋጥመን ተፈታታኝ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አሳ ካቀረበው ጸሎት ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን። አሳ ድል እንዲያደርግ የረዳው ይሖዋ ነው። ይህ ሁኔታ፣ በይሖዋ የሚታመኑ ሁሉ ምን ውጤት እንደሚያገኙ አሳይቷል። ይሖዋን ማሸነፍ የሚችል ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ኃይል የለም።

ማበረታቻና ማስጠንቀቂያ

አሳ ከጦርነቱ ሲመለስ ከአዛርያስ ጋር ተገናኘ። ይህ ነቢይ ለአሳ እንደሚከተለው በማለት ማበረታቻ እንዲሁም ማስጠንቀቂያ ሰጠው፦ “አሳ፣ እናንተም ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፤ አድምጡኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] ጋር ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተውት ግን፣ ይተዋችኋል። . . . የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ እጃችሁም አይላላ።”​—2 ዜና 15:1, 2, 7

ይህ ሐሳብ የእኛንም እምነት ሊያጠናክር ይችላል። ይሖዋን በታማኝነት እስካገለገልነው ድረስ ምንጊዜም ከእኛ ጋር እንደሚሆን ዋስትና ይሰጠናል። ይሖዋ ለእርዳታ ወደ እሱ ከጮኽን እንደሚሰማን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አዛርያስ “በርቱ” በማለት ተናግሯል። ብዙ ጊዜ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ብርቱ ወይም ደፋር መሆን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የምንችለው በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ እናውቃለን።

አሳ፣ አያቱ መዓካ “አስጸያፊውን የአሼራ ምስል ዐምድ በማቆሟ” እሷን “ከእቴጌነቷ” የመሻር ፈታኝ እርምጃ መውሰድ ነበረበት። ያም ሆኖ ይህን ቆራጥ እርምጃ የወሰደ ከመሆኑም በላይ ጣዖቷን አቃጠለው። (1 ነገ. 15:13) አሳ ቆራጥ አቋም በመያዙና ድፍረት በማሳየቱ ተባርኳል። እኛም ዘመዶቻችን ለአምላክ ታማኝ ሆኑም አልሆኑ ከይሖዋና ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ውልፍት ማለት አይገባንም። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ለታማኝነታችን ወሮታ ይከፍለናል።

አሳ ታማኝ በመሆኑ ካገኛቸው በረከቶች አንዱ ከሃዲ በሆነው ሰሜናዊ መንግሥት ይኖሩ የነበሩ በርካታ እስራኤላውያን ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሆነ በመመልከታቸው ወደ ይሁዳ ሲጎርፉ ማየት መቻሉ ነው። እነዚህ እስራኤላውያን ለንጹሕ አምልኮ ከፍተኛ አድናቆት ስለነበራቸው በይሖዋ አምላኪዎች መካከል ለመኖር ሲሉ የትውልድ አገራቸውን ለመተው መርጠዋል። ከዚያም አሳና መላው የይሁዳ ሕዝብ ይሖዋን “በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ።” ውጤቱስ ምን ሆነ? አምላክ “ተገኘላቸው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጣቸው።” (2 ዜና 15:9-15) ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ ሲቀበሉ ማየት ምንኛ ደስ ያሰኛል!

ነቢዩ አዛርያስ የተናገረው ነገር ማስጠንቀቂያም ያዘለ ነበር። “[አምላክን] ብትተውት ግን፣ ይተዋችኋል” ብሎት ነበር። ማናችንም ብንሆን እንዲህ ያለ ነገር እንዲደርስብን አንፈልግም፤ ምክንያቱም መዘዙ የከፋ ነው። (2 ጴጥ. 2:20-22) ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ይህን መልእክት ለአሳ የላከበትን ምክንያት አይነግሩንም፤ ያም ሆነ ይህ ንጉሡ ማስጠንቀቂያውን ችላ ብሎ ነበር።

‘የሞኝነት ሥራ ሠርተሃል’

አሳ በነገሠ በ36ኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ። ባኦስ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን 8 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኘውን ራማን አጠረ፤ ምናልባትም እንዲህ ያደረገው ሕዝቡ ወደ አሳና ወደ ንጹሕ አምልኮ እንዳይሄዱ ለማድረግ አስቦ ሊሆን ይችላል። አሳ ኢትዮጵያውያን ሊወሩት በመጡ ጊዜ እንዳደረገው የአምላክን ድጋፍ ከመጠየቅ ይልቅ ሰብዓዊ እርዳታ ፈለገ። ለሶርያው ንጉሥ እጅ መንሻ በመላክ የሰሜኑን የእስራኤል መንግሥት እንዲወጋለት ጠየቀው። ባኦስ ሶርያውያን ሊወጉት እንደመጡ ሲመለከት ከራማ አፈገፈገ።​—2 ዜና 16:1-5

ይሖዋ አሳ ባደረገው ነገር ስላልተደሰተ ነቢዩ አናኒን ላከበት። አሳ፣ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በተያያዘ አምላክ ያደረገውን ስለሚያውቅ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ [እንደሚመለከቱ]” መገንዘብ ነበረበት። ምናልባትም አሳ መጥፎ መካሪ አጋጥሞት ይሆናል፤ አሊያም ባኦስና ሠራዊቱ ያን ያህል አስጊ መስለው ስላልታዩት ወረራውን በራሱ ሊወጣው እንደሚችል ተሰምቶት ይሆናል። ያም ሆነ ይህ፣ አሳ ሰብዓዊ አመለካከት በመያዙ በይሖዋ ሳይታመን ቀርቷል። በመሆኑም አናኒ እንዲህ አለው፦ “የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራህ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።”​—2 ዜና 16:7-9

በዚህ ጊዜ አሳ ጥሩ ምላሽ አልሰጠም። እንዲያውም በጣም ስለተናደደ አናኒን እስር ቤት አስገባው። (2 ዜና 16:10) ምናልባትም ‘ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት የጸናሁ ሰው አሁን መገሠጽ ይገባኛል?’ በማለት አስቦ ሊሆን ይችላል። አሊያም አሳ በዕድሜ በመግፋቱ ምክንያት በትክክል ማመዛዘን አቅቶት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሁኔታ ምንም የሚናገረው የለም።

አሳ በነገሠ በ39ኛው ዓመት እግሮቹን ክፉኛ ታመመ። ዘገባው “ሕመሙ ቢጸናበትም እንኳ፣ በዚያ ሁሉ ሕመም የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም” ይላል። በዚህ ጊዜ አሳ ለመንፈሳዊ ጤንነቱ ቸልተኛ የሆነ ይመስላል። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው አሳ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ በ41ኛ ዘመነ መንግሥቱ ሞተ።​—2 ዜና 16:12-14

ያም ቢሆን ይሖዋ ትኩረት ያደረገው አሳ በሠራቸው ስህተቶች ላይ ሳይሆን በመልካም ባሕርያቱና ለንጹሕ አምልኮ በነበረው ቅንዓት ላይ ይመስላል። አሳ ይሖዋን ማገልገሉን አላቆመም ነበር። (1 ነገ. 15:14) ከዚህ አንጻር የአሳ ታሪክ ምን ሊያስተምረን ይችላል? ይሖዋ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዴት እንደረዳን ማሰላሰል እንዳለብን ያስገነዝበናል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉትን ልዩ ትዝታዎች ማሰባችን ወደፊት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲጋረጡብን ለእርዳታ ወደ ይሖዋ እንድንጸልይ ሊገፋፋን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን በማገልገል ምንም ያህል ዓመታት ብናሳልፍም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እንደማያስፈልገን ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ምንም ዓይነት የታማኝነት ታሪክ ብናስመዘግብ ስህተት ከሠራን ይሖዋ ይገሥጸናል። እንዲህ ካለው እርማት ተጠቃሚዎች እንድንሆን፣ የሚሰጠንን ተግሣጽ በገርነት መንፈስ መቀበል ይኖርብናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ እኛ ከእሱ ጋር እስከሆንን ድረስ የሰማዩ አባታችን ምንጊዜም ከእኛ ጋር ይሆናል። የይሖዋ ዓይኖች ለእሱ ታማኝ የሆኑትን ለመፈለግ በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ። ከዚያም ኃይሉን ተጠቅሞ ዋጋቸውን ወይም ወሮታቸውን ይከፍላቸዋል። ይሖዋ ለአሳ እንዲህ አድርጎለት ነበር፤ ለእኛም ያደርግልናል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ በመንፈሳዊ ውጊያ ላይ የሚገኙትን ታማኝ ሕዝቦቹን ዋጋቸውን ይከፍላቸዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ለማድረግ ድፍረት ያስፈልጋል