በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

ስግብግብነት ግያዝን ለውድቀት ዳረገው

ስግብግብነት ግያዝን ለውድቀት ዳረገው

አንድ ነገር እንዲኖርህ በጣም የጓጓህበት ጊዜ ትዝ ይልሃል? * ከሆነ እንዲህ የተሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ይሁንና የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ስትል መዋሸት ትክክል ነው?— በፍጹም አይደለም። እንዲህ የሚያደርግ ሰው ስግብግብ ነው። ግያዝ የተባለ አንድ ሰው ስግብግብ መሆኑ እንዴት ለውድቀት እንደዳረገው እስቲ እንመልከት። ግያዝ፣ የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ነቢይ የሆነው የኤልሳዕ አገልጋይ ነበር።

ኤልሳዕና ግያዝ የኖሩት የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ሰው ሆኖ ምድር ላይ ከመወለዱ ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በፊት ነው። ይሖዋ በኤልሳዕ አማካኝነት በጣም አስደናቂ ነገሮችን ይኸውም ተአምራትን ይፈጽም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በሶሪያ ጦር ሠራዊት ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው አንድ ሰው የሥጋ ደዌ የሚባል መጥፎ በሽታ ይዞት እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከኤልሳዕ በቀር ማንም ይህን ሰው ሊፈውሰው አልቻለም።

ኤልሳዕ በአምላክ እርዳታ ሰዎችን ከበሽታቸው በሚፈውስበት ጊዜ ገንዘብ ተቀብሎ አያውቅም። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኤልሳዕ እነዚህን ተአምራት የፈጸመው በራሱ ሳይሆን በይሖዋ ኃይል እንደሆነ ያውቅ ነበር። ንዕማን ከበሽታው ሲፈወስ በጣም ከመደሰቱ የተነሳ ለኤልሳዕ ወርቅ፣ ብርና ምርጥ ልብሶች ሊሰጠው ፈለገ። ኤልሳዕ ምንም ነገር ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፤ ግያዝ ግን ስጦታዎቹን ለማግኘት በጣም ጓጓ።

ንዕማን መንገድ ከጀመረ በኋላ ግያዝ ለኤልሳዕ ሳይናገር ንዕማንን ተከተለው። ንዕማን ጋ ሲደርስ ምን እንዳለው ታውቃለህ?— ‘ኤልሳዕ ሁለት እንግዶች በድንገት እንደመጡበት እንድነግርህ ልኮኛል። በመሆኑም ለሰዎቹ የሚሆን ሁለት ሙሉ ልብስ እንድትሰጠው ይፈልጋል’ አለው።

ይህ ግን ውሸት ነበር! ግያዝ ስለ ሁለቱ እንግዶች የተናገረው ነገር የፈጠራ ወሬ ነው። ይህን ውሸት የተናገረው፣ ንዕማን ለኤልሳዕ ሊሰጠው የፈለጋቸውን ልብሶች ለማግኘት ስለጓጓ ነው። ንዕማን ግን ይህን አላወቀም። በመሆኑም ደስ እያለው ስጦታዎቹን ለግያዝ ሰጠው። እንዲያውም ንዕማን፣ ግያዝ ከጠየቀው በላይ ሌሎች ነገሮችን ሰጠው። ከዚያስ ምን እንደተፈጸመ ታውቃለህ?

ግያዝ ወደ ቤት ሲመለስ ኤልሳዕ ‘የት ሄደህ ነበር?’ ብሎ ጠየቀው።

ግያዝም ‘የትም አልሄድኩም’ ብሎ መለሰ። ይሁንና ይሖዋ፣ ግያዝ ያደረገውን ነገር ለኤልሳዕ ነግሮት ነበር። በመሆኑም ኤልሳዕ ‘ይህ ገንዘብና ልብስ የምንቀበልበት ጊዜ አይደለም!’ አለው።

ግያዝ የእሱ ያልሆነውን ገንዘብና ልብስ ወስዶ ነበር። በመሆኑም አምላክ፣ የንዕማን በሽታ እሱን እንዲይዘው አደረገ። ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት የምናገኝ ይመስልሃል?— እውነተኛ ያልሆኑ ታሪኮችን ፈጥረን ማውራት እንደሌለብን ያስተምረናል።

ግያዝ እውነተኛ ያልሆነ ታሪክ ፈጥሮ የተናገረው ለምንድን ነው?— ስግብግብ ስለነበረ ነው። የእሱ ያልሆነውን ነገር ለማግኘት ስለፈለገ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ሲል ዋሸ። በዚህም ምክንያት ዕድሜውን ሙሉ በዚህ መጥፎ በሽታ ሲሠቃይ ኖሯል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግያዝ ከሥጋ ደዌ በሽታ የከፋ ነገር ደርሶበታል። ይህ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— የአምላክን ሞገስና ፍቅር አጥቷል። እኛም የአምላክን ሞገስና ፍቅር የሚያሳጣንን ነገር ፈጽሞ አናድርግ! ከዚህ ይልቅ ደጎችና ለጋሶች እንሁን።

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።