በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋና ኢየሱስ ካሳዩት ትዕግሥት ትምህርት ማግኘት

ይሖዋና ኢየሱስ ካሳዩት ትዕግሥት ትምህርት ማግኘት

“የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን ቁጠሩት።”​—2 ጴጥ. 3:15

1. አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የትኛው ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይችላል?

ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በጽናት የተወጣች አንዲት እህት “ከመሞቴ በፊት መጨረሻው ይመጣ ይሆን?” በማለት ጠይቃ ነበር። ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸዋል። አምላክ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ አስወግዶ ሁሉንም ነገር አዲስ የሚያደርግበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን። (ራእይ 21:5) የሰይጣን ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ የሚያሳምኑን በቂ ምክንያቶች ቢኖሩም ያንን ቀን በትዕግሥት መጠበቅ ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል።

2. አምላክ ካሳየው ትዕግሥት ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥተኛ መሆን እንዳለብን ይናገራል። ከእኛ በፊት እንደነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ጠንካራ እምነት ካለንና አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች የሚፈጽምበትን ጊዜ በትዕግሥት የምንጠብቅ ከሆነ እሱ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ማየት እንችላለን። (ዕብራውያን 6:11, 12ን አንብብ።) ይሖዋ ራሱ ትዕግሥተኛ አምላክ ነው። ይህን ክፉ ሥርዓት በማንኛውም ጊዜ ማጥፋት ቢችልም ትክክለኛውን ጊዜ በትዕግሥት እየጠበቀ ነው። (ሮም 9:20-24) ለመሆኑ አምላክ ይህን ያህል የታገሠው ለምንድን ነው? ኢየሱስ የአምላክ ዓይነት ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? የአምላክ ዓይነት ትዕግሥት የምናዳብር ከሆነ ምን ጥቅሞችን እናገኛለን? ይሖዋ እንደዘገየ ቢሰማን እንኳ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን ትዕግሥተኛ እንድንሆን ብሎም ጠንካራ እምነት እንድናዳብር ይረዳናል።

ይሖዋ የሚታገሠው ለምንድን ነው?

3, 4. (ሀ) ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ ለመፈጸም ትዕግሥት ያሳየው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በኤደን ለተነሳው ዓመፅ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

3 ይሖዋ ትግዕሥተኛ የሚሆንበት በቂ ምክንያት አለው። ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ በኤደን የተነሳው ዓመፅ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ፍጥረታቱን ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ይሖዋ ለእነዚህ ጥያቄዎች የማያዳግም መልስ መስጠት ጊዜ እንደሚወስድ ስላወቀ ታግሷል። በሰማይም ሆነ በምድር ያሉት ፍጥረታት በሙሉ ምን እንደሚያደርጉና ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዳላቸው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ያደረገው ውሳኔ ሁላችንንም እንደሚጠቅም የተረጋገጠ ነው።​—ዕብ. 4:13

4 የይሖዋ ዓላማ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ምድርን እንዲሞሏት ነበር። ሰይጣን ሔዋንን ባታለለበትና አዳም በአምላክ ላይ ባመፀበት ጊዜም ጭምር ይሖዋ ዓላማውን አልለወጠም። በዚህ ወቅት አምላክ ተደናግጦ የችኮላ ውሳኔ አላደረገም፤ ወይም በሰው ልጆች ተስፋ በመቁረጥ በስሜት እርምጃ አልወሰደም። ከዚህ ይልቅ ለሰዎችም ሆነ ለምድር ያለውን ዓላማ ለመፈጸም መንገድ ቀየሰ። (ኢሳ. 55:11) ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸምና ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ ሲል ራሱን ገዝቷል፤ እንዲሁም ታላቅ ትዕግሥት አሳይቷል። እንዲያውም የዓላማው አንዳንድ ገጽታዎች ከሁሉ በተሻለ መንገድ ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ሲል በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በትዕግሥት ጠብቋል።

5. የይሖዋ ትዕግሥት ምን በረከት ያስገኛል?

5 ይሖዋ የታገሠበት ሌላው ምክንያት ብዙ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ነው። ‘እጅግ ብዙ ሕዝብን’ ለማዳን በአሁኑ ጊዜ ዝግጅት እያደረገ ነው። (ራእይ 7:9, 14፤ 14:6) ይሖዋ በስብከቱ ሥራ አማካኝነት ሰዎች ስለ መንግሥቱና ስለ ጽድቅ መሥፈርቶቹ እንዲማሩ ግብዣ እያቀረበ ነው። የመንግሥቱ መልእክት የሰው ዘር መስማት ካለበት ከየትኛውም መልካም ዜና የሚበልጥ ነው፤ በእርግጥም የመንግሥቱ መልእክት ‘የምሥራች’ ነው። (ማቴ. 24:14) ይሖዋ የሚስባቸው ሰዎች በሙሉ፣ ትክክል የሆነውን ለማድረግ የሚፈልጉ እውነተኛ ወዳጆች የሚገኙበት ዓለም አቀፍ ጉባኤ አባል ይሆናሉ። (ዮሐ. 6:44-47) አፍቃሪ የሆነው አምላካችን እንዲህ ያሉ ሰዎች የእሱን ሞገስ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም በሰማይ ለሚገኘው መንግሥቱ አባላት የሚሆኑ ሰዎችን ሲመርጥ ቆይቷል። እነዚህ ለአምላክ ያደሩ ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ይረዷቸዋል። ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ትዕግሥት እያሳየም እንኳ የገባውን ቃል ለመፈጸም በትጋት መሥራቱን አላቆመም፤ ይህ ደግሞ ለእኛ ጥቅም ያስገኛል።

6. (ሀ) ይሖዋ በኖኅ ዘመን ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በዘመናችን ይሖዋ ትዕግሥት እያሳየ ያለው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ፣ ሰዎች የሚያስቆጣውን ነገር ቢያደርጉም ትዕግሥተኛ መሆኑን አሳይቷል፤ ይህን ከጥፋት ውኃው በፊት ካደረገው ነገር መረዳት እንችላለን። በወቅቱ ምድር በሥነ ምግባር ብልግናና በዓመፅ ተሞልታ ነበር፤ የሰው ልጆች ያዘቀጠ ሕይወት በመከተላቸው የይሖዋ “ልብ እጅግ አዝኖ” ነበር። (ዘፍ. 6:2-8) ይህን ሁኔታ ለዘላለም መታገሥ ስላልቻለ ታዛዥ ያልሆኑትን የሰው ልጆች በሙሉ በውኃ ለማጥፋት ወሰነ። ይሖዋ “በኖኅ ዘመን . . . በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ” ኖኅንና ቤተሰቡን ለማዳን ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። (1 ጴጥ. 3:20) በተገቢው ጊዜ ላይ ይህን ውሳኔውን ለኖኅ ያስታወቀው ሲሆን መርከብ እንዲሠራም ተልእኮ ሰጠው። (ዘፍ. 6:14-22) ኖኅ መርከብ ከመሥራት በተጨማሪ “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆን ስለሚመጣው ጥፋት ለሰዎች ይናገር ነበር። (2 ጴጥ. 2:5) ኢየሱስ ጊዜያችን ከኖኅ ዘመን ጋር እንደሚመሳሰል ተናግሯል። ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ ወስኗል። ሆኖም ‘ቀኑንና ሰዓቱን’ የሚያውቅ ማንም ሰው የለም። (ማቴ. 24:36) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ሰዎችን የማስጠንቀቅና መዳን የሚችሉበትን መንገድ የመናገር ተልእኮ ከይሖዋ ተቀብለናል።

7. ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም ይዘገያል? አብራራ።

7 ይሖዋ ይታገሣል ሲባል ጊዜው እንዲሁ በከንቱ እንዲያልፍ ያደርጋል ማለት አይደለም። ይሖዋ ታጋሽ በመሆኑ ግድየለሽ እንደሆነ ወይም ለሰዎች እንደማያስብ አድርገን ልንቆጥረው አይገባም! እውነቱን ለመናገር ግን በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ ወይም በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ መከራ ሲደርስብን ይህን ማስታወስ ሊከብደን ይችላል። በዚህ ጊዜ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ ወይም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች ለመፈጸም እንደዘገየ ሆኖ ይሰማን ይሆናል። (ዕብ. 10:36) ያም ሆኖ አምላክ ታጋሽ የሆነበት በቂ ምክንያት እንዳለውና በዚህ መሃል ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚጠቅም ነገር እያከናወነ እንዳለ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። (2 ጴጥ. 2:3፤ 3:9) እስቲ አሁን ደግሞ ኢየሱስ የአምላክ ዓይነት ትዕግሥት ያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ኢየሱስ ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

8. ኢየሱስ ትዕግሥተኛ መሆኑን ያሳየው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ነበር?

8 ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት በጉጉት ሲያደርግ ቆይቷል። ይሖዋ፣ ሰይጣን ሲያምፅ አንድያ ልጁ መሲሕ ሆኖ ወደ ምድር እንዲመጣ ወሰነ። ይህ ለኢየሱስ ምን ማለት እንደሆነ አስቡ፤ የተወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ለብዙ ሺህ ዓመታት በትዕግሥት መጠበቅ ነበረበት። (ገላትያ 4:4ን አንብብ።) ሆኖም ኢየሱስ በዚህ ወቅት እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፤ ከዚህ ይልቅ አባቱ የሰጠውን ሥራ በትጋት ያከናውን ነበር። ከጊዜ በኋላ ወደ ምድር ሲመጣም በትንቢቱ መሠረት በሰይጣን እጅ መገደል እንዳለበት ያውቅ ነበር። (ዘፍ. 3:15፤ ማቴ. 16:21) ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትልበት ቢሆንም በትዕግሥት የአምላክን ፈቃድ ፈጽሟል። ኢየሱስ ያሳየው ታማኝነት ወደር የማይገኝለት ነው። በራሱም ሆነ ባለው ሥልጣን ላይ ትኩረት አላደረገም፤ እኛም ከዚህ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።​—ዕብ. 5:8, 9

9, 10. (ሀ) ኢየሱስ፣ ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በትዕግሥት እየጠበቀ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

9 ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ በሰማይና በምድር ሥልጣን ተሰጥቶታል። (ማቴ. 28:18) እሱም ሥልጣኑን የይሖዋን ዓላማ በአምላክ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማስፈጸም ይጠቀምበታል። ኢየሱስ ጠላቶቹ ለእግሩ እንደ መርገጫ እስኪደረጉ ማለትም እስከ 1914 ድረስ በአምላክ ቀኝ ተቀምጦ በትዕግሥት ጠብቋል። (መዝ. 110:1, 2፤ ዕብ. 10:12, 13) በቅርቡ ደግሞ የሰይጣንን ሥርዓት ለማጥፋት እርምጃ ይወስዳል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ኢየሱስ፣ ሰዎች የአምላክን ሞገስ እንዲያገኙ በትዕግሥት ይረዳቸዋል፤ እንዲሁም “ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ” ይመራቸዋል።​—ራእይ 7:17

10 ለይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖረን ከሚገባው አመለካከት ጋር በተያያዘ ከኢየሱስ ምን ትምህርት እንደምናገኝ አስተዋላችሁ? ኢየሱስ አባቱ የጠየቀውን ሁሉ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ምንም ጥያቄ የለውም፤ ያም ሆኖ የአምላክን የጊዜ ሰሌዳ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነው። የሰይጣን ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበትን ጊዜ ስንጠባበቅ ሁላችንም የአምላክ ዓይነት ትዕግሥት ማዳበር እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው፤ በሌላ አባባል አምላክን ለመቅደም በፍጹም አንሞክርም፤ ወይም ተስፋ በመቁረጥ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገን አንተውም። ታዲያ የአምላክ ዓይነት ትዕግሥት ለማዳበር ምን ማድረግ እንችላለን?

የአምላክ ዓይነት ትዕግሥት ማዳበር የምችለው እንዴት ነው?

11. (ሀ) በእምነት እና በትዕግሥት መካከል ምን ግንኙነት አለ? (ለ) ጠንካራ እምነት ለማዳበር በቂ ምክንያት አለን የምንለው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ነቢያትና ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በትዕግሥት መጽናት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳይተዋል። እምነት እና ትዕግሥት የተቆራኙ ነገሮች መሆናቸውን ከእነሱ ሕይወት ማየት እንችላለን። (ያዕቆብ 5:10, 11ን አንብብ።) ይሖዋ የነገራቸውን ነገሮች ከልባቸው አምነው ባይቀበሉ፣ በሌላ አባባል እምነት ቢጎድላቸው ኖሮ ይሖዋ ቃሉን የሚፈጽምበትን ጊዜ በትዕግሥት ይጠብቁ ነበር? እምነታቸውን ሊያዳክሙ የሚችሉ አስፈሪና ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በተደጋጋሚ ጊዜያት መጋፈጥ ቢኖርባቸውም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደሚፈጽም እርግጠኞች ነበሩ። (ዕብ. 11:13, 35-40) እኛ ግን ጠንካራ እምነት ለመገንባት ተጨማሪ ምክንያት አለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ “የእምነታችን . . . ፍጹም አድራጊ” ነው። (ዕብ. 12:2) ኢየሱስ ስለ እሱ የተነገሩ ትንቢቶችን ስለፈጸመና የአምላክን ዓላማዎች እንድናውቅ ስላደረገ እምነት ለማዳበር በቂ ምክንያት አለን።

12. እምነታችንን ለመገንባት ምን ማድረግ እንችላለን?

12 እምነታችንን በማጠናከር ይበልጥ ትዕግሥተኞች ለመሆን ከፈለግን ምን ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል? ቁልፉ የአምላክን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሕይወትህ ውስጥ የአምላክን መንግሥት የምታስቀድምበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በማቴዎስ 6:33 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ይበልጥ ጥረት ማድረግ ትችል ይሆን? ይህ ደግሞ በአገልግሎት የምታሳልፈውን ጊዜ ከፍ ማድረግ ወይም በአኗኗርህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይጠይቅብህ ይሆናል። ይሖዋ እስከ ዛሬ ድረስ ጥረትህን እንዴት እንደባረከው መዘንጋት የለብህም። ምናልባትም አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድታገኝ ረድቶህ ይሆናል፤ አሊያም “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም” እንዲኖርህ አድርጎህ ሊሆን ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:7ን አንብብ።) የይሖዋን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ በግለሰብ ደረጃ ምን በረከት እንደሚያስገኝልን ማሰባችን መታገሥ ያለውን ጥቅም እንድንገነዘብ ያደርገናል።​—መዝ. 34:8

13. እምነትና ትዕግሥት የማዳበሩን ሂደት እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል?

13 እምነት ማዳበር ይበልጥ ትዕግሥተኛ ለመሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ገበሬ መጀመሪያ ይዘራል፤ ከዚያም ማሳውን ይኮተኩታል፤ በመጨረሻም ምርቱ ሲደርስ ይሰበስባል። ገበሬው በዘራ ቁጥር ጥሩ ምርት ማግኘቱ በቀጣዩ ጊዜም ምርት እንደሚያገኝ ይበልጥ በመተማመን እንዲዘራ ያደርገዋል። እርግጥ ነው፣ ምርቱን ለመሰብሰብ በትዕግሥት መጠበቅ አለበት። ሆኖም ምርቱን መሰብሰብ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ዘሩን ከመዝራት ወደኋላ እንዲል አያደርገውም፤ እንዲያውም ካለፈው ይበልጥ እርሻውን በማስፋት ብዙ ዘር ሊዘራ ይችላል። ገበሬው ምርቱን እንደሚሰበስብ እርግጠኛ ነው። በተመሳሳይም የይሖዋን መመሪያዎች ስንማርና የተማርነውን ተግባራዊ ስናደርግ እንዲሁም በዚህ ምክንያት በረከት ስናገኝ በይሖዋ ላይ ያለን የመተማመን ስሜት እየጨመረ ይመጣል። እምነታችንም ቢሆን ማደጉ አይቀርም፤ ይህ ደግሞ የይሖዋን በረከት መጠባበቅ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል።​—ያዕቆብ 5:7, 8ን አንብብ።

14, 15. በሰው ልጆች ላይ ስለሚደርሰው ሥቃይ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

14 ትዕግሥት ለማዳበር የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ በዙሪያችን ስላለው ዓለምም ሆነ እኛ ራሳችን ስላለንበት ሁኔታ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት መያዝ ነው። ለምሳሌ ይሖዋ፣ የሰው ልጆችን ሥቃይ እንዴት እንደሚመለከት ለማሰብ ሞክሩ። አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ለረጅም ዓመታት ሲመለከት ቆይቷል፤ ይህ ደግሞ በእሱ ላይ ሥቃይ እንደሚያስከትልበት ግልጽ ነው። ያም ቢሆን ሐዘኑ፣ ጥሩ ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። ‘የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስና’ ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ያደረሰውን ጉዳት እንዲያስተካክል አንድያ ልጁን ወደ ምድር ልኳል። (1 ዮሐ. 3:8) በመሆኑም በዚህ ምድር ላይ ያለው ሥቃይ ጊዜያዊ ሲሆን አምላክ የሚሰጠው መፍትሔ ዘላለማዊ ነው። እኛም የሰይጣን ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበትን ጊዜ ስንጠባበቅ፣ ትዕግሥት አጥተን ከመማረር ይልቅ ለዘላለም በሚቀጥሉት ገና ያልታዩ ነገሮች ላይ እምነት እናሳድር። ይሖዋ ክፋትን የሚያስወግድበትን ጊዜ ቀጥሯል፤ ከቀጠረው ጊዜም ዝንፍ አይልም።​—ኢሳ. 46:13፤ ናሆም 1:9

15 አስቸጋሪ በሆኑት የዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እምነታችንን ሊያዳክሙ የሚችሉ ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። የዓመፅ ድርጊቶች ሰለባ ስንሆን ወይም የምንወዳቸው ሰዎች ሲሠቃዩ ስናይ፣ በሁኔታው ከመበሳጨት ይልቅ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመታመን ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ መጽናት ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ ፍጹማን ስላልሆንን እንዲህ ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 26:39 (ጥቅሱን አንብብ።) ላይ የተናገረውን ሐሳብ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።

16. በቀረው ጊዜ ውስጥ ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል?

16 አንድ ሰው መጨረሻው እንደቀረበ የሚጠራጠር ከሆነ የተሳሳተ ዝንባሌ ሊያዳብር ይችላል። ይህ ሰው፣ ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች ድንገት ሳይፈጸሙ ቢቀሩስ በሚል ስጋት የራሱን አማራጭ መውሰድ እንዳለበት ሊሰማው ይችላል። በሌላ አባባል ይህ ግለሰብ ‘ይሖዋ ቃሉን ይጠብቅ እንደሆነ እስቲ አያለሁ’ ያለ ያህል ነው። በዚህም ምክንያት በዚህ ዓለም ላይ ስሙን ለማስጠራት፣ የአምላክን መንግሥት ከማስቀደም ይልቅ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ አስተማማኝ የሆነ ነገር ለማግኘት ወይም ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል በአሁኑ ጊዜ የተደላደለ ሕይወት እንዲኖረው ለማድረግ ይሞክር ይሆናል። ታዲያ ይህ ሰው እንዲህ ማድረጉ እምነት እንደጎደለው የሚያሳይ አይደለም? ጳውሎስ ‘እምነትና ትዕግሥት’ በማሳየታቸው ይሖዋ ቃል የገባላቸውን ነገሮች ያገኙ ታማኝ ሰዎችን ምሳሌ እንድንከተል እንዳሳሰበን አስታውስ። (ዕብ. 6:12) ይሖዋ ይህ ክፉ ሥርዓት ከዓላማው አንጻር ከሚያስፈልገው በላይ አንዲት ሴኮንድ እንኳ እንዲቆይ አይፈቅድም። (ዕን. 2:3) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ይሖዋን ለይስሙላ ያህል ብቻ ከማገልገል መቆጠብ አለብን። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ንቁዎች መሆንና ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ በትጋት ማከናወን ይኖርብናል፤ ይህ ደግሞ አሁንም እንኳ ቢሆን ወደር የሌለው እርካታ እንድናገኝ ይረዳናል።​—ሉቃስ 21:36

ትዕግሥተኛ መሆን ምን በረከት ያስገኛል?

17, 18. (ሀ) ይሖዋ በመታገሡ ምን አጋጣሚ ተከፍቶልናል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ትዕግሥት ማሳየታችን ምን በረከት ያስገኝልናል?

17 አምላክን ያገለገልነው ለጥቂት ወራትም ይሁን ለብዙ አሥርተ ዓመታት፣ ፍላጎታችን ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል ነው። ይህ ሥርዓት የቀረው ጊዜ ምንም ያህል ይሁን፣ ትዕግሥተኛ መሆናችን መዳን እስክናገኝ ድረስ እንድንጸና ይረዳናል። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ፣ እሱ ባደረገው ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እምነት እንዳለን እንድናሳይ አጋጣሚ ሰጥቶናል፤ ይህ ደግሞ አስፈላጊ ከሆነ ለስሙ ስንል መከራ እንዲደርስብን ፈቃደኛ መሆንን ያካትታል። (1 ጴጥ. 4:13, 14) በተጨማሪም አምላክ ለመዳን የሚያስፈልገንን ትዕግሥት ለማዳበር የሚያስችለንን ሥልጠና እየሰጠን ነው።​—1 ጴጥ. 5:10

18 ኢየሱስ በሰማይና በምድር ሥልጣን ተሰጥቶታል፤ በመሆኑም ራስህ እስካልወጣህ ድረስ ከእሱ ጥበቃ ሥር ነጥቆ ሊያወጣህ የሚችል ምንም ነገር የለም። (ዮሐ. 10:28, 29) የወደፊቱን ጊዜ ሌላው ቀርቶ ሞትን እንኳ የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። እስከ መጨረሻው በትዕግሥት የሚጸኑ ሰዎች ይድናሉ። እንግዲያው ዓለም እንዳያታልለንና በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዳያሳጣን ምንጊዜም ጥንቃቄ እናድርግ። ከዚህ ይልቅ እምነታችን እያደገ እንዲሄድ እንዲሁም አምላክ የታገሠበትን ጊዜ በጥበብ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።​—ማቴ. 24:13፤ 2 ጴጥሮስ 3:17, 18ን አንብብ።