በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን አታውቁም’

‘ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን አታውቁም’

“እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”​—ማቴ. 25:13

1-3. (ሀ) ኢየሱስ የተናገራቸውን ሁለት ምሳሌዎች ጎላ አድርገው የሚገልጹት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው? (ለ) ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል?

አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን በጣም አንገብጋቢ የሆነ ቀጠሮ እንዳለውና ወደ ቀጠሮው ቦታ በመኪና እንድትወስደው እንደሚፈልግ ነገረህ እንበል። ሆኖም ባለሥልጣኑን ወደ ስብሰባው ቦታ ለመውሰድ ጥቂት ደቂቃ ሲቀርህ መኪናህ በቂ ነዳጅ እንደሌለው አወቅክ። በመሆኑም ነዳጅ ለመቅዳት በፍጥነት ሄድክ። በዚህ መሃል ባለሥልጣኑ ተዘጋጅቶ ወጣ። ዞር ዞር እያለ ቢመለከትም ሊያገኝህ አልቻለም። በጣም ስለቸኮለ ሌላ ሰው እንዲወስደው አደረገ። ልክ እንደተመለስክ ባለሥልጣኑን ሌላ ሰው እንደወሰደው አወቅክ። በዚህ ጊዜ ምን ይሰማሃል?

2 አሁን ደግሞ አንተ ራስህ ባለሥልጣን እንደሆንክ አድርገህ አስብ፤ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ እንዲሠሩልህ ብቃት ያላቸውን ሦስት ሰዎች መረጥክ እንበል። ስለ ሥራው በደንብ ገለጻ ካደረክላቸው በኋላ ሦስቱም ሥራውን ለመሥራት ፈቃደኞች ሆኑ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ስትመለስ ግን ኃላፊነታቸውን የተወጡት ሁለቱ ብቻ እንደሆኑ ተገነዘብክ። የሚገርመው ደግሞ ኃላፊነቱን ያልተወጣው ግለሰብ ሰበብ አስባብ መደርደር ጀመረ። በዚያ ላይ ሥራውን ለመሥራት ሙከራ እንኳ አላደረገም። ታዲያ ስለዚህ ሰው ምን ይሰማሃል?

3 ኢየሱስ፣ በመጨረሻው ቀን አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝና ልባም መሆናቸውን ሲያሳዩ ሌሎቹ እንዲህ የማያደርጉት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት ከላይ ከቀረቡት ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉትን ስለ ደናግሎቹና ስለ ታላንቱ የሚናገሩትን ምሳሌዎች ተጠቅሟል። * (ማቴ. 25:1-30) ኢየሱስ ሊያስተላልፍ የፈለገውን ነጥብ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ “እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏል፤ ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ‘ቀንና ሰዓት’ የሚያመለክተው በሰይጣን ዓለም ላይ የአምላክን ፍርድ ለማስፈጸም የሚመጣበትን ጊዜ ነው። (ማቴ. 25:13) ይህ ምክር በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው ክርስቲያኖችም ይጠቅማል። ታዲያ ኢየሱስ ማበረታቻ በሰጠን መሠረት ዘወትር ነቅተን መጠበቃችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ለመዳን ዝግጁ ሆነው ሲጠብቁ የነበሩት እነማን ናቸው? በዛሬው ጊዜ ነቅተን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ነቅቶ መጠበቅ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

4. ‘ነቅቶ ለመጠበቅ’ መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ማወቅ አያስፈልግም የምንለው ለምንድን ነው?

4 አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ ፋብሪካ ውስጥ መሥራት፣ ሐኪም ጋ መቅረብና በሕዝብ ማመላለሻ መጓዝ ቀጠሮ ማክበር ይጠይቃሉ። የእሳት ቃጠሎን ማጥፋትን ወይም በአደጋ ጊዜ ሕይወት አድን ሥራ መሥራትን የመሳሰሉ ተግባሮችን በምናከናውንበት ጊዜ ግን ስለ ሰዓት ማሰብ ትኩረት የሚከፋፍል ከመሆኑም በላይ አደገኛ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ስለ ጊዜ ከመጨነቅ ይልቅ አጣዳፊ በሆነው ሥራ ላይ ትኩረት ማድረጉ የተገባ ነው። የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየቀረበ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ሰዎችን ለማዳን ስላደረገው ዝግጅት መናገር የአሁኑን ያህል አጣዳፊ ሆኖ አያውቅም። በመሆኑም ክርስቲያኖች ነቅተው ለመጠበቅ መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ማወቅ አያስፈልጋቸውም። እንዲያውም መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ቀን ወይም ሰዓት አለማወቃችን ቢያንስ አምስት ጥቅሞች ያስገኝልናል።

5. የመጨረሻውን ቀን ወይም ሰዓት አለማወቃችን የልባችንን ዝንባሌ ለማወቅ የሚያስችለን እንዴት ነው?

5 በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ አለማወቃችን የልባችንን ትክክለኛ ዝንባሌ ለማወቅ ያስችለናል። እንዲያውም ቀኑንና ሰዓቱን አለማወቃችን ይሖዋ እንዳከበረን የሚያሳይ ነው፤ ምክንያቱም ነፃ ምርጫችንን ተጠቅመን ለእሱ ያለንን ታማኝነት እንድናሳይ አጋጣሚ ይሰጠናል። ይህ ሥርዓት የሚጠፋበትን ጊዜ በጉጉት የምንጠባበቅ ቢሆንም ይሖዋን የምናገለግለው ሕይወት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን እሱን ስለምንወደው ነው። (መዝሙር 37:4ን አንብብ።) የእሱን ፈቃድ ማድረግ የሚያስደስተን ከመሆኑም ሌላ አምላክ የሚጠቅመንን ነገር እንደሚያስተምረን እንገነዘባለን። (ኢሳ. 48:17) በእርግጥም የአምላክን ትእዛዝ መጠበቅ ከባድ እንደሆነ አይሰማንም።​—1 ዮሐ. 5:3

6. አምላክ፣ ከፍቅር ተነሳስተን ስናገለግለው ምን ይሰማዋል? ለምንስ?

6 በሁለተኛ ደረጃ፣ የመጨረሻውን ቀን ወይም ሰዓት አለማወቃችን የይሖዋን ልብ የማስደሰት አጋጣሚ ይከፍትልናል። ይሖዋን ማገልገል የምንፈልገው መጨረሻው ስለቀረበ ወይም ሽልማት ለማግኘት ስለምንፈልግ ሳይሆን ከፍቅር ተነሳስተን ነው፤ ይህ ደግሞ ሰይጣን በይሖዋ ላይ ለሰነዘራቸው መሠረተ ቢስ ክሶች መልስ ለመስጠት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናደርግ ያስችለናል። (ኢዮብ 2:4, 5፤ ምሳሌ 27:11ን አንብብ።) ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ያደረሰውን ይህ ነው የማይባል ሰቆቃና መከራ ስንመለከት ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጎን በደስታ በመቆም የሰይጣንን ክፉ አገዛዝ ለመቃወም እንነሳሳለን።

7. የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማዳበር አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

7 በሦስተኛ ደረጃ፣ አንድን ቀን በአእምሯችን ይዘን አለማገልገላችን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንድናዳብር ያነሳሳናል። በዛሬው ጊዜ አምላክን የማያውቁ አንዳንድ ሰዎችም እንኳ ይህ ዓለም ለረጅም ጊዜ እንደማይቀጥል ተገንዝበዋል። እነዚህ ሰዎች ጥፋት ይመጣል የሚል ስጋት ስላላቸው “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል ዝንባሌ አዳብረዋል። (1 ቆሮ. 15:32) እኛ ግን እንዲህ ዓይነት ፍርሃት የለንም። በመሆኑም የራሳችንን ፍላጎት ብቻ ከማሳደድ እንርቃለን። (ምሳሌ 18:1) ከዚህ ይልቅ ራሳችንን ክደን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ጥሪታችንን በነፃ በመስጠት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች እናካፍላለን። (ማቴዎስ 16:24ን አንብብ።) አምላክን በማገልገል በተለይ ደግሞ ሌሎች ሰዎች እሱን እንዲያውቁ በመርዳት ደስታ እናገኛለን።

8. በይሖዋና በቃሉ ላይ ይበልጥ መታመን እንዳለብን የሚያሳየው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ነው?

8 በአራተኛ ደረጃ፣ ቀኑን ወይም ሰዓቱን አለማወቃችን በይሖዋ ይበልጥ እንድንታመንና ቃሉን በሕይወታችን ውስጥ በትጋት እንድንተገብር ይረዳናል። ኃጢአተኛ በመሆናችን ከምናሳያቸው ዝንባሌዎች መካከል አንዱ በራስ መታመን ነው። ጳውሎስ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት ለሁሉም ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ኢያሱ የአምላክን ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከማስገባቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሃያ ሦስት ሺህ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ አጥተዋል። በመሆኑም ጳውሎስ ‘እነዚህ ነገሮች የተጻፉት የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ መሆኑን’ ተናግሯል።​—1 ቆሮ. 10:8, 11, 12

9. መከራ የሚያጠራን እንዲሁም ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዴት ነው?

9 በአምስተኛ ደረጃ፣ መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ አለማወቃችን በመከራ ውስጥ በማለፍ እንድንጠራ አጋጣሚ ይከፍትልናል። (መዝሙር 119:71ን አንብብ።) በእርግጥም የዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ‘ለመቋቋም የሚያስቸግሩና በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ’ ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1-5) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ብዙ ሰዎች ስለሚጠሉን በእምነታችን ምክንያት ልንሰደድ እንችላለን። (ዮሐ. 15:19፤ 16:2) እንዲህ ያሉ መከራዎች ሲያጋጥሙን በትሕትና የአምላክን መመሪያ ለማግኘት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ልክ በእሳት ተፈትኖ ያለፈ ያህል እምነታችን ይጠራል። እንዲህ ያለው ፈተና ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንድንል አያደርገንም። እንዲያውም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንቀርባለን።​—ያዕ. 1:2-4፤ 4:8

10. ጊዜው እንደሮጠ እንዲሰማን የሚያደርገው ምንድን ነው?

10 ጊዜው እንደሮጠ ወይም እንደዘገየ ሊሰማን ይችላል። በሥራ ስንጠመድ ሰዓት ስለማናይ ጊዜው ሳናስበው ይከንፋል። በተመሳሳይም ይሖዋ የሰጠንን አስደሳች ሥራ በማከናወን የምንጠመድ ከሆነ ቀኑና ሰዓቱ ሳናስበው ፈጥኖ ሊደርስ ይችላል። በዚህ ረገድ አብዛኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ አንዳንዶቹ ቅቡዓን ዝግጁ የሆኑት ሌሎች ደግሞ ያልሆኑት እንዴት እንደሆነ እስቲ በአጭሩ እንመልከት።

ቅቡዓኑ ዝግጁ ነበሩ

11. ከ1914 በኋላ አንዳንዶቹ ቅቡዓን ጌታ እንደዘገየ የተሰማቸው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ስለ ደናግሎቹና ስለ ታላንቱ የተናገረውን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ የተጠቀሱት ደናግሎች ሙሽራው መቼ እንደሚመጣ፣ ባሮቹ ደግሞ ጌታቸው መቼ እንደሚመለስ ቢያውቁ ኖሮ ምንጊዜም ነቅተው መጠበቅ ባላስፈለጋቸው ነበር። ሆኖም ጊዜውን ስለማያውቁ ዝግጁ ሆነው መጠበቅ ነበረባቸው። ቅቡዓኑ 1914 ልዩ ዓመት እንደሚሆን ከአሥርተ ዓመታት በፊት ቢገነዘቡም በዚህ ወቅት ምን እንደሚፈጸም በትክክል አልተረዱም ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ነገሮች እነሱ እንደጠበቋቸው ሳይሆኑ ሲቀሩ ሙሽራው እንደዘገየ ሆኖ ተሰምቷቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ አንድ ወንድም ሁኔታውን ሲያስታውስ “አንዳንዶቻችን [በ1914] በጥቅምት ወር የመጀመሪያው ሳምንት ላይ ወደ ሰማይ እንደምንሄድ እርግጠኞች ነበርን” ብሏል።

12. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝና ልባም መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?

12 አንድ ሰው መጨረሻው እሱ በጠበቀው ጊዜ ላይ ሳይመጣ ቢቀር ሁኔታው ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደሚሆንበት መገመት አያዳግትም። ቅቡዓኑ የተሰማቸውም እንደዚህ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ እነዚህ ወንድሞች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተቃውሞ አጋጥሟቸው ነበር። በዚህም የተነሳ ቅቡዓኑ የተኙ ያህል ሆነው ነበር። ሆኖም በ1919 እንዲነቁ ጥሪ ተደረገላቸው። ኢየሱስ በወቅቱ ምርመራ ለማድረግ ወደ አምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ መጥቶ ነበር። አንዳንዶች ግን ምርመራውን ባለማለፋቸው ከንጉሡ ጋር ‘የመነገድ’ መብታቸውን አጡ። (ማቴ. 25:16) እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ ዘይታቸውን ለመሙላት ንቁ ባለመሆናቸው እንደ ሞኞቹ ደናግል ሆነው ነበር ሊባል ይችላል። እንዲሁም እንደ ሰነፉ ባሪያ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ሲሉ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች አልነበሩም። ዓለም በጦርነት ይታመስባቸው በነበሩት በእነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት እንኳ አብዛኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጌታቸውን ለማገልገል ያላቸውን ልባዊ ፍላጎትና ለእሱ ያላቸውን ታማኝነት አሳይተዋል።

13. ታማኝና ልባም ባሪያ ከ1914 በኋላ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? በዛሬው ጊዜስ

13 ከ1914 በኋላ መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “ወንድሞች፣ ስለ አምላክ ትክክለኛ አመለካከት ካለን በእሱ ዝግጅቶች ቅር አንሰኝም። የእኛ ፍላጎት እንዲፈጸም አንፈልግም፤ በመሆኑም ጥቅምት 1914 ላይ እንጠብቀው የነበረው ነገር የተሳሳተ እንደሆነ ስንገነዘብ ጌታ ለእኛ ሲል ዕቅዱን ባለመቀየሩ ተደስተናል። እንዲህ እንዲያደርግም ፍላጎታችን አይደለም። የእኛ ፍላጎት ዓላማውንና ዕቅዱን መረዳት ብቻ ነው።” አሁንም ቢሆን ቅቡዓኑ ተለይተው የሚታወቁት እንዲህ ዓይነቱን የትሕትናና ለአምላክ የማደር ባሕርይ በማሳየታቸው ነው። ቅቡዓኑ በመንፈስ መሪነት እንናገራለን አይሉም፤ ሆኖም የጌታን “ንግድ” በምድር ላይ ለማካሄድ ቆርጠዋል። “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሆኑት ‘ሌሎች በጎችም’ ነቅቶ በመጠበቅና ቅንዓት በማሳየት ረገድ የቅቡዓኑን ምሳሌ እየተከተሉ ነው።​—ራእይ 7:9፤ ዮሐ. 10:16

ዝግጁ ሆነን መጠበቅ

14. አምላክ በቅቡዓኑ አማካኝነት የሚያቀርብልንን ትምህርት በጥብቅ መከተላችን ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

14 ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ ንቁ የሆኑ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትም አምላክ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበትን ድርጅት በጥብቅ ይከተላሉ። በዚህም ምክንያት የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት መንፈሳዊ ዘይታቸውን በአምላክ ቃልና በእሱ መንፈስ እንደሞሉ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። (መዝሙር 119:130ን እና ዮሐንስ 16:13ን አንብብ።) ይህ ደግሞ ኃይል ስለሚሰጣቸው በመከራ ውስጥ እያሉም እንኳ የክርስቶስን መመለስ ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ አስችሏቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በናዚ አገዛዝ ወቅት በአንድ ካምፕ ውስጥ ታስረው የነበሩ ወንድሞች መጀመሪያ ላይ የነበራቸው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነበር። ስለዚህ ተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ እንዲሰጣቸው ወደ አምላክ ጸለዩ። ብዙም ሳይቆይ፣ አንድ ወንድም እነሱ ወዳሉበት ካምፕ ታስሮ ሲመጣ አዲስ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን በሰው ሠራሽ እግሩ ውስጥ ደብቆ ማስገባቱን አወቁ። ከናዚ እልቂት በሕይወት የተረፈ ኧርነስት ቫኡር የተባለ አንድ ቅቡዕ ወንድም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሶ ሲናገር “ይሖዋ በመጽሔቶቹ ላይ የወጡትን የሚያበረታቱ ሐሳቦች በአእምሯችን እንድንይዛቸው በማድረግ አስደናቂ በሆነ መንገድ ረድቶናል” ብሏል። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት በጣም ቀላል ነው፤ ይሁንና በየጊዜው እንመገባለን? ይሖዋ በእሱ ላይ ትምክህታቸውን ለሚጥሉ፣ ምንጊዜም ታማኝ ለሚሆኑና ከማዕዱ ለሚመገቡ ሁሉ የተትረፈረፈ በረከት እንዳዘጋጀ እርግጠኛ ነኝ።”

15, 16. አንድ ባልና ሚስት በክርስቲያናዊ አገልግሎት ቅንዓት ማሳየታቸው በረከት ያስገኘላቸው እንዴት ነው? እንዲህ ካሉ ተሞክሮዎች ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

15 በተጨማሪም ሌሎች በጎች በጌታ ሥራ በመጠመድ ለክርስቶስ ወንድሞች ሙሉ ድጋፍ ይሰጣሉ። (ማቴ. 25:40) ኢየሱስ በምሳሌው ላይ ከጠቀሰው ክፉና ሰነፍ ባሪያ በተቃራኒ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም ሲሉ በፈቃደኝነት የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ይሠራሉ። ለምሳሌ ጆን እና ማሳኮ የተባሉ ባልና ሚስት ወደ ኬኒያ በመሄድ ለቻይንኛ ተናጋሪዎች እንዲመሠክሩ በተጠየቁ ጊዜ መጀመሪያ ላይ አመንትተው ነበር። በጸሎት ጭምር በመታገዝ ሁኔታቸውን በጥሞና ከመረመሩ በኋላ ወደዚያ ተዛውረው ለመኖር ወሰኑ።

16 እነዚህ ባልና ሚስት በቅንዓት በማገልገላቸው በእጅጉ ተባርከዋል። “እዚህ ያለው አገልግሎት በጣም አስገራሚ ነው” በማለት ተናግረዋል። እንዲያውም ሰባት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማግኘት ችለዋል። ብዙ አስደናቂ ተሞክሮዎችንም አግኝተዋል። በመጨረሻም “ይሖዋ እዚህ እንድንመጣ ስለፈቀደልን በየቀኑ እናመሰግነዋለን” በማለት ተናግረዋል። መጨረሻው መቼም ይምጣ መቼ በአምላክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ለመጠመድ ያላቸውን ቁርጠኝነት በውሳኔዎቻቸው ያንጸባረቁ ሌሎች በርካታ ወንድሞችና እህቶችም አሉ። ከጊልያድ ትምህርት ቤት ተመርቀው በመውጣት በሚስዮናዊነት አገልግሎት የተሰማሩትን በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ማሰብ ይቻላል። ይህ ልዩ አገልግሎት ምን እንደሚመስል በመጠኑም ቢሆን ለማወቅ የጥቅምት 15, 2001 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እያደረግን ነው!” የሚለውን ርዕስ ለምን አታነብም? በዚህ ርዕስ ውስጥ የተገለጸውን የአንድ ቀን የሚስዮናውያን ውሎ ስታነብ በምን አቅጣጫ አገልግሎትህን ማስፋት እንደምትችል ለማሰብ ሞክር፤ በዚህ ረገድ የምታደርገው ጥረት ለአምላክ ውዳሴ፣ ለአንተ ደግሞ ደስታ እንደሚያስገኝልህ ግልጽ ነው።

እናንተም ነቅታችሁ ጠብቁ

17. ቀኑንና ሰዓቱን አለማወቃችን የጠቀመን እንዴት ነው?

17 በእርግጥም ይህ ሥርዓት የሚጠፋበትን ትክክለኛ ቀንና ሰዓት አለማወቃችን ብዙ ጥቅሞች አስገኝቶልናል። ቀኑንና ሰዓቱን ባለማወቃችን ምክንያት ተስፋ ከመቁረጥና ከመሰላቸት ይልቅ የእሱን ፈቃድ በማድረጉ ሥራ መጠመዳችን አፍቃሪ አባታችን ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንድንቀርብ አድርጎናል። በምሳሌያዊ ሁኔታ እጃችንን ከዕርፉ ላይ አለማንሳታችን ብሎም ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማስወገዳችን በጌታ አገልግሎት ይህ ነው የማይባል ደስታ አስገኝቶልናል።​—ሉቃስ 9:62

18. በአምላክ አገልግሎት በታማኝነት መጽናት የምንፈልገው ለምንድን ነው?

18 ወደ ይሖዋ የፍርድ ቀን በፍጥነት እየቀረብን ነው። ማናችንም ብንሆን ይሖዋንም ሆነ ኢየሱስን ማሳዘን አንፈልግም። በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀኖች፣ ይሖዋና ኢየሱስ ውድ የሆነ የአገልግሎት መብት ሰጥተውናል። ታዲያ በእኛ ላይ እምነት በመጣላቸው በጣም አመስጋኞች አይደለንም?​—1 ጢሞቴዎስ 1:12ን አንብብ።

19. ዝግጁ ሆነን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

19 ተስፋችን ሰማይ መሄድም ይሁን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር፣ አምላክ የሰጠንን ምሥራቹን የመስበኩንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በታማኝነት ማከናወናችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። አዎ፣ የይሖዋ ቀን የሚመጣበትን ትክክለኛ ቀንና ሰዓት አናውቅም፤ ደግሞስ ለምን ማወቅ ያስፈልገናል? ከእኛ የሚጠበቀው ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ብቻ ነው፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ እንችላለን። (ማቴ. 24:36, 44) በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እስከታመንንና መንግሥቱን እስካስቀደምን ድረስ ፈጽሞ አናፍርም።​—ሮም 10:11

^ አን.3 የመጋቢት 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14-18 ተመልከት።