በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙስና ምን ያህል ተስፋፍቷል?

ሙስና ምን ያህል ተስፋፍቷል?

“ድርጅታችን ለአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አገልግሎት ይሰጣል። ለሰጠነው አገልግሎት ክፍያ ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት እንጠብቃለን። ይሁንና በዚያ መሥሪያ ቤት የሚሠራ አንድ ሰው በቅርቡ ስልክ ደውሎ ከሚከፈለን ገንዘብ ላይ የተወሰነውን የምንሰጠው ከሆነ ገንዘባችን ቶሎ እንዲከፈለን እንደሚያደርግ ነገረኝ።”—ጆን

አንተስ በሙስና ምክንያት ችግር ደርሶብህ ያውቃል? ምናልባት ከላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት ሁኔታ አላጋጠመህ ይሆናል፤ ይሁንና ሙስና በሚያስከትለው ችግር በሆነ መልኩ መነካትህ አይቀርም።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት የሕዝብ ተቋማት ምን ያህል በሙስና እንደተዘፈቁ የሚጠቁም ግምታዊ መረጃ በ2011 አውጥቶ ነበር፤ በዚህ መረጃ ላይ አገራት ከ0 (ሙስና በጣም የተንሰራፋባቸው) እስከ 10 (ሙስና ጨርሶ የሌለባቸው) ድረስ ደረጃ የተሰጣቸው ሲሆን “ግምገማ ከተደረገባቸው 183 አገራትና ክልሎች ውስጥ አብዛኞቹ . . . ደረጃቸው ከአምስት በታች ነው።” ከሁለት ዓመታት በፊት ይኸው ድርጅት ባወጣው የ2009 ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ሙስና እጅግ የተስፋፋ ነገር መሆኑን ሲገልጽ “በዓለማችን ላይ ከሙስና መቅሰፍት ነፃ የሆነ ቦታ እንደሌለ ግልጽ ነው” ብሎ ነበር።

“ሙስና ሲባል የግል ጥቅም ለማግኘት ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ማለት ነው። ሕልውናው፣ መተዳደሪያው ወይም ደስታው ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሐቀኛ በመሆናቸው ላይ የተመካ ማንኛውም ግለሰብ ሙስና በሚያስከትለው ጉዳት ተጠቂ ነው።”—ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል

በአንዳንድ ሁኔታዎች ሙስና ከፍተኛ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2010 በሄይቲ በደረሰው ከባድ የመሬት መናወጥ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገው “ሙስና እና ግዴለሽነት” እንደሆነ ታይም መጽሔት ዘግቧል። መጽሔቱ ይህ የሆነበትን ምክንያት አክሎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሕንፃዎቹ፣ ችሎታ ያላቸው መሐንዲሶችን ንድፍ የተከተሉ አይደሉም፤ የሕንፃ ጥራት ተቆጣጣሪ ተብለው የተመደቡት የመንግሥት ሠራተኞችም ቢሆኑ ዳጎስ ያለ ጉቦ ይቀበላሉ።”

ታዲያ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋውን ሙስና ለዘለቄታው ማስወገድ ይቻል ይሆን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ለሙስና መንስኤ የሆኑ ነገሮችን ማወቅ ያስፈልጋል። የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ያወሳል።

ስሙ ተቀይሯል።