በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታሳዩት መንፈስ ምን ዓይነት ነው?

የምታሳዩት መንፈስ ምን ዓይነት ነው?

“የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እናንተ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን።”—ፊል. 25

1. ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለእነሱ ምን ምኞት እንዳለው ገልጿል?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ ጉባኤዎቹ የሚያሳዩት መንፈስ በአምላክና በክርስቶስ ፊት ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ምኞቱን ደጋግሞ ገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ ለገላትያ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ወንድሞች፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን። አሜን” ብሏል። (ገላ. 6:18) ጳውሎስ “ከምታሳዩት መንፈስ ጋር” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

2, 3. (ሀ) ጳውሎስ “መንፈስ” የሚለውን ቃል አንዳንድ ጊዜ የተጠቀመበት ምንን ለማመልከት ነው? (ለ) እኛ የምናሳየውን መንፈስ በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

2 ጳውሎስ በዚህ አገባቡ “መንፈስ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት፣ በሆነ መንገድ እንድንናገር ወይም የሆነ ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋንን ኃይል ለማመልከት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ደግ፣ አሳቢ፣ ገር፣ ለጋስ ወይም ይቅር ባይ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጭምትና ገር መንፈስ” እንዲሁም ‘የረጋ መንፈስ’ ማንጸባረቅ ጥሩ እንደሆነ ይናገራል። (1 ጴጥ. 3:4፤ ምሳሌ 17:27) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው አሽሙረኛ፣ ቁሳዊ ነገሮችን የሚወድ፣ በቀላሉ ስሜቱ የሚጎዳ ወይም በራስ የመመራት ዝንባሌ የተጠናወተው ሊሆን ይችላል። ይባስ ብሎም ብልሹ የሆነ መንፈስ እንዲሁም የእምቢተኝነትና የዓመፀኝነት መንፈስ የሚያሳዩ ሰዎች አሉ።

3 በመሆኑም ጳውሎስ ‘ጌታ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን’ የሚሉትን ዓይነት አገላለጾች ሲጠቀም ወንድሞቹ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማና እንደ ክርስቶስ ያለ ስብዕና እንዲያሳዩ ማበረታታቱ ነበር። (2 ጢሞ. 4:22፤ ቆላስይስ 3:9-12ን አንብብ።) እኛም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘የማሳየው መንፈስ ምን ዓይነት ነው? ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ አምላክን የሚያስደስት መንፈስ ማሳየት የምችለው እንዴት ነው? በጉባኤው ውስጥ ለሰፈነው ጥሩ መንፈስ ይበልጥ አስተዋጽኦ ማበርከት የምችለው እንዴት ነው?’ ለምሳሌ ያህል፣ በሱፍ አበቦች በተሸፈነ መስክ ላይ እያንዳንዱ አበባ ያለው ውበት መስኩ በአጠቃላይ አምሮ እንዲታይ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እኛስ እንደነዚህ “አበቦች” ለአጠቃላዩ የጉባኤው ውበት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን? በእርግጥም አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት ማድረግ አለብን። አምላክን የሚያስደስት መንፈስ ለማሳየት ምን ማድረግ እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

የዓለምን መንፈስ አስወግዱ

4. ‘የዓለም መንፈስ’ ምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ “ከአምላክ የሆነውን መንፈስ ተቀበልን እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም” ይላል። (1 ቆሮ. 2:12) ‘የዓለም መንፈስ’ ምንድን ነው? ይህ መንፈስ በ⁠ኤፌሶን 2:2 ላይ ከተገለጸው መንፈስ ጋር አንድ ዓይነት ነው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ሥርዓት ተከትላችሁ የአየሩ ሥልጣን ገዥ በሚፈልገው መንገድ ትመላለሱ ነበር፤ ይህም አየር በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ ያለ መንፈስ ነው።” ይህ “አየር” የዓለም መንፈስ ወይም አስተሳሰብ ነው፤ እንደምንተነፍሰው አየር ሁሉ በዙሪያችን ይገኛል። አዎ በሁሉም ቦታ አለ። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች፣ ‘ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማንም ሊነግረኝ አይገባም!’ ወይም ‘ለመብትህ መታገል አለብህ!’ የሚል አመለካከት አላቸው። እነዚህ ሰዎች የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆኑ ‘የማይታዘዙ ልጆች’ ናቸው።

5. አንዳንድ እስራኤላውያን ምን ዓይነት መጥፎ መንፈስ አሳይተዋል?

5 እንዲህ ያለ አመለካከት ድሮም የነበረ ነው። በሙሴ ዘመን፣ ቆሬ በእስራኤል ጉባኤ በተሾሙ ሰዎች ላይ ዓምፆ ነበር። ቆሬ በተለይ ትኩረት ያደረገው ካህናት ሆነው የማገልገል መብት ባገኙት በአሮንና በልጆቹ ላይ ነበር። ምናልባት ጉድለታቸውን ተመልክቶ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሙሴ ለዘመዶቹ ልዩ መብት በመስጠት አዳልቷል የሚል ስሜት አድሮበት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ቆሬ ጉዳዩን ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር እንደተመለከተው ምንም ጥርጥር የለውም፤ በመሆኑም በይሖዋ የተሾሙትን በመናቅ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም! . . . በእግዚአብሔር ማኀበር ላይ የምትታበዩት ለምንድነው?” ሲል ተናግሯል። (ዘኍ. 16:3) በተመሳሳይም ዳታንና አቤሮን በሙሴ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በመግለጽ “በእኛ ላይ ጌታ መሆን ያምርሃል?” ብለውታል። ሙሴ ባስጠራቸው ጊዜ በእብሪት ስሜት “በጭራሽ አንመጣም!” በማለት መለሱ። (ዘኍ. 16:12-14) ይሖዋ ባሳዩት መንፈስ እንዳልተደሰተ ግልጽ ነው። ዓመፀኞቹን በሙሉ አጥፍቷቸዋል።—ዘኍ. 16:28-35

6. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች መጥፎ አመለካከት እንደነበራቸው ያሳዩት እንዴት ነው? ምክንያቱስ ምን ሊሆን ይችላል?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ‘ጌትነትን በመናቅ’ በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉትን ይተቹ ነበር። (ይሁዳ 8) እነዚህ ሰዎች ባላቸው መብት አልረኩ ይሆናል፤ ደግሞም አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት በትጋት በሚወጡ የተሾሙ ወንዶች ላይ እንዲያምፁ ሌሎችን ለማነሳሳት ሞክረው ሊሆን ይችላል።—3 ዮሐንስ 9, 10ን አንብብ።

7. በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት መንፈስ እንዳይኖር መጠንቀቅ ይኖርብናል?

7 እንዲህ ያለ መንፈስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መታየት እንደሌለበት ግልጽ ነው። በመሆኑም በዚህ ረገድ ጠንቃቃ መሆን አስፈላጊ ነው። በሙሴና በሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን የነበሩት ሽማግሌዎች ፍጹማን እንዳልነበሩ ሁሉ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎችም ፍጹማን አይደሉም። ሽማግሌዎች እኛን በግለሰብ ደረጃ ሊጎዳ የሚችል ስህተት ሊፈጽሙ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ አንድ የጉባኤ አባል “ፍትሕ ማግኘት አለብኝ!” ወይም “ይህ ወንድም እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል!” ብሎ ድርቅ ያለ አቋም በመያዝ የዓለምን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ምላሽ ቢሰጥ ተገቢ አይሆንም! ይሖዋ አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶችን ችላ ብሎ ለማለፍ ሊመርጥ ይችላል። እኛስ እንዲህ ማድረግ አንችልም? የጉባኤ አባል የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በሽማግሌዎች ላይ ጉድለት እንዳዩ ስለተሰማቸው ብቻ ከባድ ኃጢአት ከፈጸሙ በኋላ እርዳታ እንዲሰጧቸው በተመደቡ ሽማግሌዎች ፊት ለመቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይህ ሁኔታ፣ በሚያክመው ዶክተር ላይ አንድ የማይወደው ነገር ስላየ ብቻ የሚሰጠውን ሕክምና አልቀበልም ከሚል ታካሚ ጋር ይመሳሰላል።

8. በጉባኤ ውስጥ አመራር ለሚሰጡ ወንድሞች ተገቢ አመለካከት ይዘን እንድንኖር የትኞቹ ጥቅሶች ሊረዱን ይችላሉ?

8 እንዲህ የመሰለውን መንፈስ ለማስወገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ‘በቀኝ እጁ ሰባት ከዋክብት እንደያዘ’ ተደርጎ መገለጹን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እነዚህ “ከዋክብት” በዋነኝነት ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾችን የሚያመለክቱ ሲሆን በጉባኤ ያሉትን ሁሉንም የበላይ ተመልካቾች ሊያመለክቱም ይችላሉ። ኢየሱስ በእጁ ውስጥ ያሉትን “ከዋክብት” ተገቢ ሆኖ ባገኘው መንገድ ሁሉ መምራት ይችላል። (ራእይ 1:16, 20) ስለዚህ ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደመሆኑ መጠን የሽማግሌዎችን አካል ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። በሽማግሌዎች አካል ውስጥ የሚያገለግል አንድ ወንድም በእርግጥ እርማት ካስፈለገው ‘እንደ እሳት ነበልባል ያሉ ዓይኖች’ ያሉት ኢየሱስ በራሱ ጊዜና መንገድ ይህ ወንድም እርማት እንዲሰጠው ያደርጋል። (ራእይ 1:14) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ለተሾሙት ወንድሞች ተገቢውን አክብሮት ማሳየታችንን መቀጠል ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ነፍሳችሁን ተግተው ስለሚጠብቁና ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ፤ ይህንም የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ነው፤ አለበለዚያ ሥራቸውን በሐዘን ያከናውናሉ፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።”—ዕብ. 13:17

ኢየሱስ ባለው ኃላፊነት ላይ ማሰላሰልህ ምክር በሚሰጥህ ጊዜ በምታሳየው መንፈስ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

9. (ሀ) አንድ ክርስቲያን እርማት ወይም ተግሣጽ ሲሰጠው ምን ፈተና ሊደቀንበት ይችላል? (ለ) ወቀሳ በሚሰጠን ጊዜ ምን ምላሽ መስጠታችን የተሻለ ነው?

9 አንድ ክርስቲያን እርማት ሲሰጠው ወይም በጉባኤ ውስጥ የነበረውን መብት ሲያጣ ምን ዓይነት መንፈስ እንዳለው ይታያል። አንድ ወጣት ወንድም ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው የቪዲዮ ጨዋታዎችን ይጫወት ስለነበር ሽማግሌዎች በዘዴ ምክር ሰጡት። የሚያሳዝነው ግን የተሰጠውን ምክር ባለመቀበሉና በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን ብቃቶች በማጓደሉ የጉባኤ አገልጋይነት መብቱን አጣ። (መዝ. 11:5፤ 1 ጢሞ. 3:8-10) በዚህ ጊዜ ወንድም በውሳኔው አለመስማማቱን ለብዙዎች ማውራት ጀመረ፤ ከዚያም ሽማግሌዎቹን የሚነቅፍ ደብዳቤ ለቅርንጫፍ ቢሮው በተደጋጋሚ ጻፈ፤ አልፎ ተርፎም አንዳንድ የጉባኤው አባላት ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ሞከረ። ድርጊታችን ትክክል እንደሆነ ለማስመሰል በምናደርገው ጥረት የመላውን ጉባኤ ሰላም አደጋ ላይ መጣል ትርፉ ጉዳት ነው። የተሰጠን ወቀሳ ያላስተዋልናቸውን ድክመቶች ለማየት የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ አድርገን ማሰባችንና ከዚያም እርማቱን ምንም ሳናንገራግር ዝም ብለን መቀበላችን ምንኛ የተሻለ ነው!—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:28, 29ን አንብብ።

10. (ሀ) ጥሩና መጥፎ መንፈስን በተመለከተ ከ⁠ያዕቆብ 3:16-18 ምን ትምህርት እንደምናገኝ ግለጽ። (ለ) ‘ከላይ የሆነውን ጥበብ’ ማንጸባረቅ ምን ውጤት ያስገኛል?

10 አንድ ሰው በጉባኤ ውስጥ ሊያሳይ የሚገባውንም ሆነ የማይገባውን መንፈስ በተመለከተ ያዕቆብ 3:16-18 ላይ ጥሩ መመሪያ ሰፍሯል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ቅናትና ምቀኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገር ሁሉ አለ። ከላይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም በአድልዎ ሰዎችን የማይለያይና ግብዝነት የሌለበት ነው። ከዚህም በላይ ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች የጽድቅን ዘር ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ይዘሩና የጽድቅ ፍሬ ያጭዳሉ።” ‘ከላይ ከሆነው ጥበብ’ ጋር የሚስማማ ነገር ስናደርግ የምናንጸባርቃቸው አምላካዊ ባሕርያት በወንድሞች መካከል ጥሩ መንፈስ እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት ይረዱናል።

በጉባኤ ውስጥ አክብሮት የተሞላበት መንፈስ አሳዩ

11. (ሀ) ተገቢ የሆነ መንፈስ መያዛችን ምን እንድናስወግድ ይረዳናል? (ለ) ዳዊት ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?

11 ይሖዋ፣ ሽማግሌዎች ‘የአምላክን ጉባኤ እንዲጠብቁ’ ኃላፊነት እንደሰጣቸው ማስታወስ ይኖርብናል። (ሥራ 20:28፤ 1 ጴጥ. 5:2) በመሆኑም በሽምግልና የማገልገል መብት ኖረንም አልኖረን የአምላክን ዝግጅት ማክበራችን ጥበብ መሆኑን እንገነዘባለን። ተገቢውን መንፈስ መያዛችን ለሥልጣን የተጋነነ አመለካከት እንዳይኖረን ሊረዳን ይችላል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል፣ ዳዊት በንግሥናው ላይ ስጋት እንደሚፈጥር በተሰማው ጊዜ “በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር።” (1 ሳሙ. 18:9) ንጉሡ መጥፎ መንፈስ ያደረበት ከመሆኑም በላይ ዳዊትን ለመግደል ፈለገ። እንደ ሳኦል ለሥልጣን ከልክ በላይ ከመጨነቅ ይልቅ እንደ ዳዊት መሆናችን ምንኛ የተሻለ ነው! ይህ ወጣት ብዙ በደል ቢፈጸምበትም አምላክ የሾመውን ሰው በአክብሮት ይመለከት ነበር።—1 ሳሙኤል 26:23ን አንብብ።

12. በጉባኤ ውስጥ ያለው አንድነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ምንድን ነው?

12 የአመለካከት ልዩነት በጉባኤ ውስጥ ሌላው ቀርቶ በበላይ ተመልካቾች መካከል የውዝግብ መንስኤ ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” እንዲሁም “ራሳችሁን ልባሞች አድርጋችሁ አትቁጠሩ” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሊረዱን ይችላሉ። (ሮም 12:10, 16) ትክክል ነን ብለን ድርቅ ያለ አቋም ከመያዝ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ነገር ሊከናወን የሚችልበት በርካታ አማራጭ መኖሩን መገንዘብ ይኖርብናል። የሌሎችን አመለካከት ለመረዳት ከሞከርን ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።—ፊልጵ. 4:5

13. የራሳችንን ሐሳብ በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ይህን የሚያሳይ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ አለ?

13 እንዲህ ሲባል ግን በጉባኤ ውስጥ ማስተካከያ የሚያስፈልገው ነገር እንዳለ ተሰምቶን ሐሳብ ብናቀርብ ስህተት ነው ማለት ነው? በፍጹም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እጅግ አወዛጋቢ የሆነ ጉዳይ ተከስቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ወንድሞች “ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም ከመካከላቸው አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ጉዳዩን በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ” ወሰኑ። (ሥራ 15:2) እነዚህ ወንድሞች በጉዳዩ ላይ የራሳቸው አመለካከትና የመፍትሔ ሐሳብ ሊኖራቸው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና እያንዳንዳቸው ሐሳባቸውን ከገለጹና በመንፈስ መሪነት ውሳኔ ላይ ከተደረሰ በኋላ የራሳቸውን አመለካከት ዳግመኛ አላነሱም። ጉባኤዎቹ ውሳኔውን የያዘ ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ “ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ”፤ እንዲሁም ‘በእምነት እየጠነከሩ ሄዱ።’ (ሥራ 15:31፤ 16:4, 5) ዛሬም በተመሳሳይ አንድን ጉዳይ ለሚመለከታቸው ወንድሞች ከተናገርን በኋላ ጉዳዩን በጸሎት አስበውበት ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ ልንተማመን ይገባል።

ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ጥሩ መንፈስ አሳዩ

14. ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ጥሩ መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ጥሩ መንፈስ ማሳየት የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። እያንዳንዳችን ሌሎች ሲበድሉን የይቅር ባይነት መንፈስ ማሳየታችን ከፍተኛ ጥቅም አለው። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላ. 3:13) “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው” የሚለው አባባል በሌሎች ልንከፋ የምንችልባቸው አጥጋቢ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያሳያል። ይሁንና የሌሎችን ጥቃቅን ድክመቶች አጋንነን ከመመልከትና የጉባኤውን ሰላም ከማደፍረስ ይልቅ የይሖዋን የይቅር ባይነት መንፈስ በማንጸባረቅ አገልግሎታችንን በጋራ ማከናወናችንን እንቀጥላለን።

15. (ሀ) ይቅር ባይነትን በተመለከተ ከኢዮብ ምን እንማራለን? (ለ) ጸሎት ጥሩ መንፈስ ማሳየት እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?

15 ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ከኢዮብ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሦስቱ አጽናኝ ተብዬዎች አሳቢነት የጎደላቸው ቃላት በማዥጎድጎድ ጎድተውታል። ያም ሆኖ ኢዮብ ይቅር ባይ ነበር። ‘ለወዳጆቹ መጸለዩ’ ይህን ያሳያል። (ኢዮብ 16:2፤ 42:10) ለሌሎች መጸለያችን ለእነሱ ያለን አመለካከት እንዲቀየር ሊያደርግ ይችላል። ለሁሉም ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን መጸለያችን የክርስቶስ ዓይነት መንፈስ ለማዳበር ይረዳናል። (ዮሐ. 13:34, 35) ለወንድሞቻችን ከመጸለይ በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:13) የአምላክ መንፈስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊያፈሯቸው የሚገቡትን ባሕርያት እንድናሳይ ይረዳናል።—ገላትያ 5:22, 23ን አንብብ።

በአምላክ ድርጅት ውስጥ ጥሩ መንፈስ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አበርክቱ

16, 17. ‘የምናሳየውን መንፈስ’ በተመለከተ አንተ በግለሰብ ደረጃ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?

16 እያንዳንዱ የጉባኤ አባል በጉባኤ ውስጥ ጥሩ መንፈስ እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ልባዊ ጥረት ቢያደርግ እጅግ አስደሳች ውጤት ይገኛል! ይህን ርዕስ ካጠናን በኋላ የሚያንጽ መንፈስ ለማሳየት በግለሰብ ደረጃ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብን ይሰማን ይሆናል። እንዲህ ከተሰማን በአምላክ ቃል እየታገዝን ራሳችንን ለመመርመር ማመንታት አይኖርብንም። (ዕብ. 4:12) ጳውሎስ ከጉባኤዎቹ ጋር ባለው ግንኙነት የሚያደርገው ነገር በጣም ያሳስበው ስለነበር እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “እኔ ሕሊናዬን የሚወቅሰኝ ምንም ነገር የለም። ሆኖም ይህ ጻድቅ መሆኔን ያረጋግጣል ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እኔን የሚመረምረኝ ይሖዋ ነው።”—1 ቆሮ. 4:4

17 ለራሳችን ወይም ለኃላፊነት ቦታ የተጋነነ አመለካከት ሳንይዝ ከላይ ከሆነው ጥበብ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ ስንጥር በጉባኤ ውስጥ ጥሩ መንፈስ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናበረክታለን። የይቅር ባይነት መንፈስ የምናሳይ ከሆነና ለሌሎች አዎንታዊ አመለካከት ካለን ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረናል። (ፊልጵ. 4:8) እነዚህን ነገሮች ስናደርግ ይሖዋና ኢየሱስ ‘በምናሳየው መንፈስ’ እንደሚደሰቱ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ፊል. 25