በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

‘እስከ ዛሬ ተሰምቶ የማያውቅ ግሩም መልእክት’

‘እስከ ዛሬ ተሰምቶ የማያውቅ ግሩም መልእክት’

ጆርጅ ናሽ በካናዳ፣ ሳስካችዋን ግዛት በምትገኘው የሳስከቱን ከተማ አንድ መጋዘን ውስጥ የተከመሩ 18 ሜትር ርዝመት ያላቸው አጣናዎችን ሲመለከት “ይህ ሁሉ የተከማቸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ እነዚህ አጣናዎች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የምልክት መስጫ ማማዎችን ለመገንባት ያገለገሉ እንደነበሩ ተነገረው። ወንድም ናሽ “አጣናዎቹን የሬዲዮ ጣቢያ ማማዎች ለመሥራት ልንጠቀምባቸው እንደምንችል አሰብኩ። ቲኦክራሲያዊ የሬዲዮ ጣቢያ የማቋቋም ሐሳብ የመጣልን በዚህ ጊዜ ነበር” በማለት ከጊዜ በኋላ ተናግሯል። ልክ ከዓመት በኋላ ማለትም በ1924 ሲ ኤች ዩ ሲ የተባለው ሬዲዮ ጣቢያ ስርጭቱን ጀመረ። ይህ ጣቢያ ካናዳ ውስጥ ሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በሬዲዮ ከሚያስተላልፉ የመጀመሪያዎቹ ጣቢያዎች አንዱ ነበር።

(1) በአልበርታ፣ ኤድመንተን የነበረው የሬዲዮ ጣቢያ (2) በኦንታሪዮ፣ ቶሮንቶ አንድ ወንድም የማሰራጫውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሲያስተካክል

የአውሮፓን ያህል የቆዳ ስፋት ባላት በካናዳ በሬዲዮ መስበክ ጥሩ አማራጭ ነበር። በሳስከቱን በሚገኘው ሬዲዮ ጣቢያ ትሠራ የነበረችው ፍሎረንስ ጆንሰን “በሬዲዮ በምናሰራጫቸው መልእክቶች አማካኝነት በአካል ልናገኛቸው ለማንችላቸው በርካታ ሰዎች እውነት ሊዳረስ ችሏል” ብላለች። በወቅቱ ሬዲዮ ብርቅ ስለነበር ሰዎች በሬዲዮ የሚተላለፍ ማንኛውንም ነገር የመስማት ጉጉት ነበራቸው። በ1926 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) በአራት የካናዳ ከተሞች ውስጥ የራሳቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች ነበሯቸው። *

(3)በሳስካችዋን ግዛት በሳስከቱን ከተማ የነበረው የሲ ኤች ዩ ሲ ስቱዲዮ

ከእነዚህ የሬዲዮ ጣቢያዎች አንዱን ብትከፍት ምን ትሰማ ነበር? በአካባቢው ባለ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ዘማሪዎች የሙዚቃ መሣሪያዎች በሚጫወቱ ሰዎች ሌላው ቀርቶ በአነስተኛ ኦርኬስትራ ታጅበው ሲዘምሩ ልትሰማ ትችላለህ። በዋነኝነት ደግሞ ወንድሞች የስብከት ንግግር ያቀርቡና የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችን ያደርጉ ነበር። በእነዚህ ውይይቶች ላይ ትካፈል የነበረችው ኤሚ ጆንስ “ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ለማገኛቸው ሰዎች ስሜን ስነግራቸው ‘ድምፅሽን በሬዲዮ ሰምቼዋለሁ’ የሚሉኝ ጊዜ ነበር” በማለት ተናግራለች።

“የስልክ ጥሪዎቹ እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉንም ማስተናገድ አልቻልንም”

በኖቫ ስኮሸ፣ ሃሊፋክስ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አድማጮች ስልክ ደውለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን የሚጠይቁበት የሬዲዮ ፕሮግራም የጀመሩ ሲሆን ይህ በወቅቱ አዲስ ግኝት ነበር። አንድ ወንድም “ይህ ፕሮግራም በብዙዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ሆኖ ነበር” በማለት ጽፏል። አክሎም “የስልክ ጥሪዎቹ እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉንም ማስተናገድ አልቻልንም” ብሏል።

ሐዋርያው ጳውሎስ አጋጥሞት እንደነበረው ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ለሚሰብኩት መልእክት ያገኙት ምላሽ የተለያየ ነው። (ሥራ 17:1-5) አንዳንድ አድማጮች መልእክቱ አስደስቷቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሄክተር ማርሻል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ በሬዲዮ ሲያስተዋውቁ በሰማ ጊዜ የመጽሐፉ ስድስት ጥራዞች እንዲላኩለት ጠየቀ። ሄክተር “መጽሐፎቹን በሰንበት ትምህርት ቤት ለማስተማር እጠቀምባቸዋለሁ ብዬ አስቤ ነበር” በማለት ከጊዜ በኋላ ጽፏል። ይሁን እንጂ ሄክተር ጥራዝ አንድን አንብቦ እንደጨረሰ ቤተ ክርስቲያኑን ለቆ ለመውጣት ወሰነ። ሄክተር ቀናተኛ ወንጌላዊ የሆነ ሲሆን በ1998 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። በምሥራቅ ኖቫ ስኮሸ “የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት” የሚለው ንግግር በተላለፈ ማግስት ኮሎኔል ጆን ማክዶናልድ በዚያ ለሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ አሉት፦ “የኬፕ ብሬትን ደሴት ነዋሪዎች በትናንትናው ዕለት ያዳመጡት ግሩም መልእክት በዚህ አካባቢ እስከ ዛሬ ድረስ ተሰምቶ አያውቅም።”

በሌላ በኩል ደግሞ ቀሳውስቱ በቁጣ ተሞሉ። በሃሊፋክስ የሚገኙ አንዳንድ ካቶሊኮች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን ፕሮግራሞች የሚያስተላልፈውን የሬዲዮ ጣቢያ እንደሚያጋዩ ዛቱ። በሃይማኖት መሪዎቹ ቆስቋሽነት በ1928 መንግሥት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ንብረት የሆኑትን የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ እንደማያድስ በድንገት አስታወቀ። በዚህ ጊዜ ወንድሞችና እህቶች የአየሩ ባለቤት ማን ነው? የሚል ጽሑፍ በማሰራጨት እንዲህ ያለውን ፍትሐዊ ያልሆነ እርምጃ ተቃወሙ። ያም ቢሆን የመንግሥት ባለሥልጣናቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ለማደስ አልተስማሙም።

ታዲያ ይህ እርምጃ በካናዳ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችን መንፈስ አዳፍኗል? ኢዘቤል ዌይንራይት “መጀመሪያ ላይ ጠላት ከፍተኛ ድል የተቀዳጀ ይመስል ነበር” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ሆኖም ይሖዋ ከዓላማው ጋር የሚስማማ ቢሆን ኖሮ ሁኔታውን ማስቀረት እንደሚችል አውቃለሁ። በመሆኑም የመንግሥቱን ምሥራች የምናውጅበት ከዚህ የተሻለ ሌላ መንገድ መፈለግ እንደሚኖርብን የሚጠቁም ሁኔታ ነበር።” በካናዳ የሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምሥራቹን ለማዳረስ በአብዛኛው በሬዲዮ ከመጠቀም ይልቅ ሰዎችን ቤታቸው ድረስ ሄዶ ለማነጋገር ትኩረት መስጠት ጀመሩ። ይሁን እንጂ በዚያን ወቅት ሬዲዮ ‘እስከ ዛሬ ተሰምቶ የማያውቀውን ግሩም መልእክት’ በማሰራጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ምንም ጥያቄ የለውም።—በካናዳ ካለው የታሪክ ማኅደራችን

^ አን.4 በካናዳ የሚገኙ ወንድሞች ምሥራቹን ለመስበክ ከሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎች የአየር ሰዓት ይገዙ ነበር።