በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጥንት ዘመን የነበሩ መዋቢያዎች

በጥንት ዘመን የነበሩ መዋቢያዎች

በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሴቶች የዓይን፣ የፊትና የቆዳ መዋቢያዎችን ይጠቀሙ ነበር

ሴትየዋ ሰውነቷን ከታጠበች በኋላ ቆዳዋ እንዲለሰልስ መልካም መዓዛ ያለው ዘይት ትቀባለች። ከዚያም ከብርጭቆ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከዛጎል ወይም ከድንጋይ የተሠሩ ብልቃጦችና ትናንሽ መያዣ ዕቃዎች የተቀመጡበትን በተለያዩ ቀለማት ያጌጠ ሣጥን ትከፍታለች። በእነዚህ ብልቃጦች ውስጥ ጥሩ መዓዛ እንዲኖራቸው ሲባል ከበለሳን፣ ከሄል፣ ከቀረፋ፣ ከነጭ ዕጣን፣ ከማር፣ ከከርቤና ከመሳሰሉት ነገሮች በጥንቃቄ የተቀመሙ ልዩ ልዩ ዘይቶችና ሽቶዎች ተቀምጠዋል።

ከሣጥኑ ውስጥ የሚያምር ቅርጽ ያላቸው የተለያዩ ማንኪያዎችን እንዲሁም ዝርግና ጎድጓዳ ሳህኖችን ታወጣለች። ከዚያም በዕለቱ ልትቀባው ያሰበችውን መዋቢያ ትቀምማለች። ቀጥላም በነሐስ መስተዋቷ ውስጥ መልኳን እያየች የቀመመችውን መዋቢያ ትቀባባለች።

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሴቶች ራሳቸውን ለማስዋብ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ የነበረ ይመስላል። በጥንታዊ መቃብሮች ላይ የሚገኙ ሥዕሎች፣ በግድግዳ ላይ የተቀረጹ ምስሎችና በጠጠር የተሠሩ ሥዕሎች እንደሚያመለክቱት በጥንት ዘመን በሜሶጶጣሚያና በግብፅ በመዋቢያዎች መጠቀም የተለመደ ነበር። በግብፃውያን ምስሎች ላይ ዓይናቸውን በአልሞንድ ቅርጽ በደማቁ የተኳሉ ሴቶች የሚታዩ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ቅርጽ ያለው ዓይን በጣም ይወደድ ነበር።

ይሁንና ስለ እስራኤላውያንስ ምን ማለት ይቻላል? በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ሴቶች መዋቢያዎችን ይጠቀሙ ነበር? ከሆነስ ምን ዓይነት መዋቢያዎችን? እርግጥ ነው፣ ስለዚህ ጉዳይ መረጃ ሊሰጠን የሚችል በጥንቷ እስራኤል የተገኘ በመቃብር ላይ የተሠራ ሥዕል ወይም በግድግዳ ላይ የተቀረጸ ምስል የለም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘገባዎችና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ አካባቢዎች በቁፋሮ የተገኙ ጥንታዊ ቁሳቁሶች በጥንት ዘመን ስለነበሩት መዋቢያዎች ፍንጭ ሊሰጡን ይችላሉ።

ለመዋቢያነት የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች

ከኖራ የተሠሩ ለመዋቢያ የሚያገለግሉ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ እስራኤል

በመላው የእስራኤል ምድር በተደረጉ ቁፋሮዎች ከመዋቢያዎችና ከሽቶዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ብዙ ዕቃዎች ተገኝተዋል። በቁፋሮ ከተገኙት ቁሳቁሶች መካከል ለመዋቢያ የሚውሉ ነገሮችን ለመፍጨትና ለማደባለቅ የሚያገለግሉ ከድንጋይ የተሠሩ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ የካሮት ቅርጽ ያላቸው የሽቶ ብልቃጦች፣ የአልባስጥሮስ የቅባት ብልቃጦችና እንዲያንጸባርቅ ተደርጎ በደንብ ከታሸ ነሐስ የተሠሩ የእጅ መስተዋቶች ይገኙበታል። ከዝሆን ጥርስ የተሠራ አንድ ማንኪያ በእጀታው ላይ በአንድ በኩል የዘንባባ ቅጠሎች በሌላው በኩል ደግሞ ዙሪያውን እርግቦች የከበቡት የሴት ፊት ተቀርጾበታል።

ሀብታሞች መዋቢያዎቻቸውን ለማስቀመጥ ያጌጡ ዛጎሎችን ይመርጡ የነበረ ይመስላል። በግብፅና በከነዓን አካባቢ ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ወይም ከእንጨት የተሠሩ ከመዋቢያዎች ጋር በተያያዘ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ትናንሽ ማንኪያዎች የተገኙ ሲሆን አንዳንዶቹ በሚዋኙ ልጃገረዶች ቅርጽና በተለያዩ የረቀቁ ቅርጾች የተሠሩ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ቁሳቁሶች በዚያ ዘመን የነበሩ ሴቶች በመዋቢያዎች መጠቀማቸው የተለመደ እንደነበር ይጠቁማሉ።

የዓይን መዋቢያ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው ከኢዮብ ሴቶች ልጆች የአንዷ ስም “ቄሬንሀፉክ” ነው። ይህ ስም በዕብራይስጥ “የኩል ቀንድ” የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን የመዋቢያ ቁሳቁሶች ምናልባትም የኩል (በዕብራይስጥ ኮል) መያዣ የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። (ኢዮብ 42:14 የ1980 ትርጉም) የኢዮብ ልጅ ይህ ስም የተሰጣት ውብ መሆኗን ለማመልከት ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ግን በዚያ ዘመን መዋቢያዎች ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበረም የሚጠቁም ይሆናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዓይንን መኳል የተጠቀሰው ዓመፀኛ ከሆኑ ሴቶች ጋር ተያይዞ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ከእነዚህም መካከል ተንኮለኛ የነበረችው ንግሥት ኤልዛቤል እንዲሁም ኤርምያስና ሕዝቅኤል የተባሉት ነቢያት በአመንዝራ ሴት የመሰሏት ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ይገኙበታል።  (2 ነገሥት 9:30፤ ኤርምያስ 4:30፤ ሕዝቅኤል 23:40) ትናንሽ የኩል መቀቢያዎችና በርካታ የጠርሙስ ወይም የድንጋይ የኩል ማስቀመጫዎች በቁፋሮ መገኘታቸው እስራኤላውያን ከአምላክ በራቁበት ወቅት የነበሩ በርካታ ሴቶች በተለይም የንጉሣውያን ቤተሰብ አባላትና ባለጸጎች በደማቁ የመኳልና ሌሎች መዋቢያዎችን የመጠቀም ልማድ እንደነበራቸው የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

ለአምልኮና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚውል መዓዛ ያለው ዘይት

በጥንቷ እስራኤል ወይራ ዘይትን መልካም መዓዛ ካላቸው ቅመሞች ጋር በማዋሃድ ሽቶዎች የመሥራትና የመጠቀም ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ልማድ ነበረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፀአት መጽሐፍ ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገልግሎት ሲያቀርቡ የሚጠቀሙበት መልካም መዓዛ ያለው የተቀደሰ ዘይት እንዴት እንደሚቀመም ይገልጻል። ይህ ዘይት የሚቀመመው ቀረፋ፣ ከርቤና ሌሎች ደስ የሚል ሽታ ያላቸው ዕፅዋትን በመቀላቀል ነበር። (ዘፀአት 30:22-25) የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚውል ሽቶና ዕጣን ይዘጋጅበት እንደነበረ የሚገመት ቤት በኢየሩሳሌም ባደረጉት ቁፋሮ አግኝተዋል። መልካም መዓዛ ያለው ዘይት ለአምላክ ከሚቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ጋር በተያያዘም ይሁን በዕለት ተዕለት ሕይወት ጥቅም ላይ ይውል እንደነበረ የሚገልጹ ሐሳቦችን  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ እናገኛለን።—2 ዜና መዋዕል 16:14፤ ሉቃስ 7:37-46፤ 23:56

ከሸክላ የተሠራ የሽቶ መያዣ፣ እስራኤል

በዚያ አካባቢ ውኃ እንደ ልብ ስለማይገኝ መልካም መዓዛ ያላቸው ዘይቶች ከንጽሕና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ተፈላጊነት ነበራቸው። እነዚህ ዘይቶች ሞቃትና ደረቅ በሆነው የአየር ንብረት የቆዳን ልስላሴ ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለመዋቢያነትም ያገለግሉ ነበር። (ሩት 3:3 የ1954 ትርጉም፤ 2 ሳሙኤል 12:20) አስቴር የተባለችው አይሁዳዊት ቆንጆ በንጉሥ አርጤክስስ ፊት ከመቅረቧ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል የቁንጅና እንክብካቤ ተደርጎላታል፤ ይኸውም ለመጀመሪያዎቹ 6 ወራት በከርቤ ዘይት፣ ለቀሪዎቹ 6 ወራት ደግሞ በበለሳን ዘይት ታሽታለች።—አስቴር 2:12 የ1980 ትርጉም

ሽቶዎች ወይም መልካም መዓዛ ያላቸው ዘይቶች የብር እና የወርቅ ያህል እንደ ውድ ነገር ይታዩ ነበር። ንጉሥ ሰለሞንን ለማየት ታዋቂ የሆነውን ረጅም ጉዞ ያደረገችው የሳባ ንግሥት፣ ለንጉሡ ከሰጠችው ውድ ስጦታዎች መካከል ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮችና የበለሳን ዘይት ይገኙበታል። (1 ነገሥት 10:2, 10 NW) ንጉሥ ሕዝቅያስም ከባቢሎን ለመጡት ልዑካን ሀብትና ንብረቱን በኩራት ባስጎበኛቸው ጊዜ ከብሩ፣ ከወርቁና ከጦር መሣሪያው ሌላ ‘የበለሳን ዘይቱንና ምርጡን ዘይት’ አሳይቷቸው ነበር።—ኢሳይያስ 39:1, 2 NW

አነስተኛ መጠን ያለው ሽቶ ወይም ዘይት ለመሥራት ብዛት ያላቸው አበቦች፣ ፍሬዎች፣ ቅጠሎች፣ በአንዳንድ ዛፎች ላይ የሚገኙ መዓዛ ያላቸው ሙጫዎች ወይም የዛፍ ቅርፊቶች ያስፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው በርካታ ዕፅዋትን ይጠቅሳል፤ ከእነዚህም መካከል ሙጫ፣ ሳፍሮን፣ እሬት፣ ቀረፋ፣ በለሳን፣ ብርጉድ፣ ነጭ ዕጣን፣ ናርዶስ፣ ከርቤ እና ጠጅ ሣር ይገኙበታል። አንዳንዶቹ የሚገኙት በዚያ አካባቢ ብቻ ሲሆን የሚበቅሉትም በዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ከሕንድ፣ ከደቡብ አረብ እና ከሌሎች አካባቢዎች በሚመጡት ታዋቂ የንግድ መስመሮች በኩል ወደ እስራኤል ይገቡ ነበር።

እንቆቅልሽ የሆነው የበለሳን ዘይት

ከላይ እንደተመለከትነው የበለሳን ዘይት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከንግሥት አስቴር፣ ከሳባ ንግሥት እና ከንጉሥ ሕዝቅያስ ጋር በተያያዘ ተጠቅሷል። በ1988 በኩምራን አቅራቢያ ከሙት ባሕር በስተ ምዕራብ ባለው ዳርቻ ላይ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ አንድ ትንሽ የዘይት ማሰሮ ተገኘ። ይህን ግኝት አስመልክቶ የተለያዩ ግምታዊ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። በዚህ ማሰሮ ውስጥ ያለው ዘይት በጥንት ዘመን ከነበረው ታዋቂ የበለሳን ዘይት የመጨረሻው ይሆን? ተመራማሪዎች ስለተገኘው ዘይት ምንነት እርግጠኞች መሆን አልቻሉም። እስከ አሁን ድረስ ገበሬዎች በአንድ ወቅት ታዋቂ የነበረውን የበለሳን ዛፍ እንደገና ለማብቀል ጥረት እያደረጉ ነው።

ከዝሆን ጥርስ የተሠራ የመዋቢያዎች ማስቀመጫ፣ እስራኤል

ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የበለሳን ዘይት የሚገኝበት ዛፍ የሚበቅለው በዓይንጋዲ አካባቢ ይመስላል። በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የነበሩ ምድጃዎች፣ ማሰሮዎችና ሌሎች ከብረትና ከአጥንት የተሠሩ ቁሳቁሶች በዚህ አካባቢ በቁፋሮ የተገኙ ሲሆን እነዚህ ቁሳቁሶች በሌሎች አካባቢዎች ሽቱ ለማዘጋጀት ከሚውሉት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። አብዛኞቹ ምሁራን የበለሳን ዛፍ መጀመሪያ የተገኘው ከአረብ አገር ወይም ከአፍሪካ እንደሆነ ያምናሉ። ሽቶው የሚሠራው ከዛፉ ከሚገኝ ፈሳሽ ነው። የበለሳን ዘይት እንደ ውድ ነገር ስለሚቆጠር ምርቱ የሚገኝበትና የሚዘጋጅበት መንገድ በሚስጥር ይያዝ ነበር።

አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በለሳንን ይጠቀሙበት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የታሪክ ምሁር የሆነው ጆሴፈስ እንደዘገበው ማርክ አንቶኒ በርከት ያሉ የበለሳን ዛፎች የሚገኙበትን ማሳ ነጥቆ ከወሰደ በኋላ የግብፅ ንግሥት ለነበረችው ለክሊዮፓትራ ሰጥቷታል። ሮማዊው የታሪክ ምሁር ፕሊኒ ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በተካሄደው የአይሁድ ጦርነት ወቅት አይሁዳውያን ጦረኞች፣ ድል አድራጊዎቹ ሮማውያን የበለሳን ተክሎቹን እንዳይወስዷቸው ሲሉ ሁሉንም ዛፎች ለማጥፋት እንደሞከሩ ጽፏል።

በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎች ይጠቀሙባቸው ስለነበሩት መዋቢያዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችና ከአርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች የተወሰነ ግንዛቤ ማግኘት ችለናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ መዋቢያዎችንም ሆነ ሌሎች ጌጣጌጦችን መጠቀምን አያወግዝም፤ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች በልከኝነትና በማስተዋል እንድንጠቀምባቸው ያበረታታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጭምትና ገር መንፈስ” ማዳበር “በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ” እንዳለው ገልጿል። በየጊዜው ከሚለዋወጠው ፋሽን አንጻር በየትኛውም ዕድሜ የሚገኙ ክርስቲያን ሴቶች ይህን ግሩም ምክር መከተላቸው ተገቢ ነው።—1 ጴጥሮስ 3:3, 4