በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጊዜም ወደ ይሖዋ ቅረቡ

ምንጊዜም ወደ ይሖዋ ቅረቡ

“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕ. 4:8

1, 2. (ሀ) የሰይጣን “ዕቅድ” ምንድን ነው? (ለ) ወደ አምላክ ለመቅረብ ምን ሊረዳን ይችላል?

ይሖዋ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ወደ እሱ የመቅረብ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። የሰይጣን ፍላጎት ግን የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን ማለትም ይሖዋ እንደማያስፈልገን ሆኖ እንዲሰማን ማድረግ ነው። ሰይጣን በኤደን የአትክልት ስፍራ ሔዋንን ካሳሳተበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ውሸት ሲያስፋፋ ቆይቷል። (ዘፍ. 3:4-6) አብዛኛው የሰው ዘርም ባለፉት ዘመናት ሁሉ ይህን ስህተት ሲደግም ቆይቷል።

2 እኛ ግን በሰይጣን ወጥመድ ላለመግባት መጠንቀቅ እንችላለን። ምክንያቱም “የእሱን ዕቅድ እናውቀዋለን።” (2 ቆሮ. 2:11) ሰይጣን፣ የተሳሳቱ ምርጫዎችን እንድናደርግ በመገፋፋት ከይሖዋ ሊያርቀን ይሞክራል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው በሥራ፣ በመዝናኛና በቤተሰብ ጉዳዮች ረገድ ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ እንችላለን። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ ለቴክኖሎጂ፣ ለጤና፣ ለገንዘብ እንዲሁም ለኩራት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ‘ወደ አምላክ እንድንቀርብ’ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።—ያዕ. 4:8

ቴክኖሎጂ

3. ቴክኖሎጂ ጥሩም መጥፎም ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

3 በዛሬው ጊዜ በየትኛውም የዓለም ክፍል የተራቀቁ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። እነዚህን መሣሪያዎች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ግን ከሰማዩ አባታችን ሊያርቁን ይችላሉ። እስቲ ኮምፒውተርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አሁን እያነበብክ ያለኸው መጽሔት የተዘጋጀው በኮምፒውተር እገዛ ነው። ኮምፒውተር ለምርምርና ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ዓይነተኛ መሣሪያ ከመሆኑም በላይ አልፎ አልፎ ዘና ለማለትም ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ለኮምፒውተር ከልክ ያለፈ ፍቅር ሊኖረን ይችላል። የንግዱ ዓለም አዲስ የወጡ ምርቶች የግድ እንደሚያስፈልጉን በዘዴ ሊያሳምነን ይሞክራል። አንድ ወጣት ታብሌት የሚባል ዘመናዊ ኮምፒውተር እንዲኖረው በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ ይህን ዕቃ ለመግዛት ሲል አንዱን ኩላሊቱን በድብቅ ሸጧል። እንዴት የሚያሳዝን ውሳኔ ነው!

4. አንድ ክርስቲያን በኮምፒውተር ከመጠን በላይ የመጠቀም ልማዱን ያሸነፈው እንዴት ነው?

4 አንድ ሰው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አላግባብ ወይም ከመጠን  በላይ በመጠቀም ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና መሥዋዕት ቢያደርግ ደግሞ ይበልጥ አሳዛኝ ይሆናል። ጆን * የተባለ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኝ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ለመንፈሳዊ ነገሮች ‘አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ’ በማለት እንደሚናገር አውቃለሁ። ያም ቢሆን በኮምፒውተር አጠቃቀም ረገድ ዋነኛው ጠላቴ እኔው ራሴ ነበርኩ።” አብዛኛውን ጊዜ ጆን በጣም መሽቶ እንኳ ከኢንተርኔት ላይ አይነሳም። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም በደከመኝ መጠን ከሰዎች ጋር በኢንተርኔት የጽሑፍ መልእክት መለዋወጤን ወይም ጤናማ ባይሆኑም እንኳ አጫጭር ቪዲዮዎችን መመልከቴን ማቆም እየከበደኝ ይሄዳል።” ይህን መጥፎ ልማዱን ለማቆም ሲል የመኝታ ሰዓቱ ሲደርስ ኮምፒውተሩ ራሱን በራሱ እንዲዘጋ አደረገው።—ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እርዷቸው

5, 6. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸው ከሌሎች ጋር የሚያንጽ ጊዜ እንዲያሳልፉ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

5 ወላጆች እያንዳንዱን የልጆቻችሁን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ባይኖርባችሁም የኮምፒውተር አጠቃቀማቸውን ግን መከታተል ይገባችኋል። ከፊታችሁ ዘወር እንዲሉ ወይም እንዳያስቸግሯችሁ ስትሉ ብቻ በኢንተርኔት ብልግናንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንዲመለከቱ፣ የጭካኔ ድርጊት የሚንጸባረቅባቸውን የኮምፒውተር ጨዋታዎች እንዲጫወቱ ወይም ከመጥፎ ጓደኞች ጋር እንዲገጥሙ አትፍቀዱላቸው። አለበለዚያ ልጆቻችሁ ‘አባትና እናቴ ዝም ካሉኝ ምንም ችግር የለውም ማለት ነው’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ ልጆቻችሁን ከይሖዋ ከሚያርቃቸው ከማንኛውም ነገር የመጠበቅ ኃላፊነት አለባችሁ። እንስሳት እንኳ ልጆቻቸውን ከአደጋ ይጠብቃሉ። አንዲት ድብ፣ ጠላት ግልገሎቿን ሊያጠቃ ቢመጣ ምን እንደምታደርግ ለማሰብ ሞክሩ!—ከሆሴዕ 13:8 ጋር አወዳድር።

6 ልጆቻችሁ፣ በማንኛውም ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ምሳሌ ከሚሆኑ ክርስቲያኖች ጋር የሚያንጽ ጊዜ እንዲያሳልፉ ዝግጅት አድርጉ። እንዲሁም ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር አብረው መዋል እንደሚፈልጉ አትዘንጉ! እንግዲያው ከልጆቻችሁ ጋር ለመሳቅ፣ ለመጫወት፣ ለመሥራት እንዲሁም ‘ወደ አምላክ ለመቅረብ’ ጊዜ መድቡ። *

ጤና

7. ሁላችንም ጤነኛ መሆን የምንፈልገው ለምንድን ነው?

7 “ጤንነትህ እንዴት ነው?” ይህ የተለመደ አባባል በተዘዋዋሪ አንድን አሳዛኝ እውነታ መቀበላችንን ያሳያል። የመጀመሪያ ወላጆቻችን፣ ሰይጣን ከይሖዋ እንዲያርቃቸው ስለፈቀዱ ሁላችንም እንታመማለን። ሕመም የሰይጣንን ዓላማ ለማሳካት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፤ ምክንያቱም ከታመምን ይሖዋን ማገልገል ከባድ ይሆንብናል። ከሞትን ደግሞ ከነአካቴው ይሖዋን ማገልገላችንን እናቆማለን። (መዝ. 115:17) በመሆኑም ሁላችንም ጤነኛ ለመሆን መፈለጋችን የሚጠበቅ ነገር ነው። * ስለ ወንድሞቻችን ጤንነትና ደኅንነት ማሰባችንም ተገቢ ነው።

8, 9. (ሀ) ስለ ጤንነታችን ከመጠን በላይ ከመጨነቅ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ደስታችንን መጠበቃችን ምን ጥቅም አለው?

8 ያም ሆኖ ስለ ጤንነታችን ከልክ በላይ ከመጨነቅ መራቅ ይኖርብናል። አንድን ዓይነት የአመጋገብ  ሥርዓት፣ የሕክምና ዓይነት ወይም ምርት በትጋት የሚያስተዋውቁ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማወጅ እንኳ የዚህን ያህል አይተጉ ይሆናል። እንዲያውም ሌሎችን እየረዱ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ያም ሆኖ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትላልቅ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ከስብሰባ በፊትም ሆነ በኋላ፣ ጤናን ወይም ውበትን ለመጠበቅ የሚረዱ ምርቶችን ማስተዋወቅ ተገቢ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

9 በስብሰባዎች ላይ የምንገኘው፣ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመጨዋወትና የአምላክ መንፈስ ውጤት የሆነውን ደስታን ለማግኘት ነው። (ገላ. 5:22) እንዲህ ባሉ ወቅቶች፣ ተጠይቀንም ሆነ ሳንጠየቅ ጤናን አስመልክቶ ምክር መስጠት ወይም አንድን ዓይነት ምርት ማስተዋወቅ የመጣንበትን ዓላማ እንድንስት የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ የሌሎችን ደስታ ሊሰርቅ ይችላል። (ሮም 14:17) ደግሞም አንድ ሰው ጤናውን በተመለከተ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። በተጨማሪም ለሁሉም በሽታዎች መፍትሔ ማግኘት የሚችል ሰው የለም። በጣም ጎበዝ የሚባል ሐኪምም እንኳ ያረጃል፣ ይታመማል ውሎ አድሮም ይሞታል። በመሆኑም ስለ ጤንነታችን ከልክ በላይ መጨነቃችን ሕይወታችንን አያራዝምልንም። (ሉቃስ 12:25) በሌላ በኩል ግን “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው።”—ምሳሌ 17:22

10. (ሀ) አንድን ሰው በይሖዋ ዘንድ ውብ የሚያሰኘው ምንድን ነው? (ለ) የተሟላ ጤንነት የሚኖረን መቼ ነው?

10 ስለ መልካችን ማሰባችንም የተገባ ነው። ይሁንና የእርጅና ምልክቶችን ሁሉ ለማጥፋት መሞከሩ አስፈላጊ አይደለም። እንዲያውም እነዚህ ምልክቶች የጉልምስና፣ የክብርና የውስጣዊ ውበት መገለጫዎች ናቸው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) ይሖዋ የሚመለከተን እንደዚህ ነው፤ እኛም ራሳችንን በይሖዋ ዓይን ማየት አለብን። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4ን አንብብ።) ታዲያ መልካችንን ለማሳመር ብለን ጤናችንን አልፎ ተርፎም ሕይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ቀዶ ሕክምና (ፕላስቲክ ሰርጀሪ) ወይም ሌሎች ሕክምናዎችን ማድረጋችን ጥበብ ነው? የዕድሜያችንና የጤንነታችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እውነተኛ የሆነውና ከውስጣችን የሚወጣው ውበት ምንጭ ‘የይሖዋ ደስታ’ ነው። (ነህ. 8:10) የተሟላ ጤንነትና የወጣትነት ውበት የምናገኘው በአዲሱ ዓለም ብቻ ነው። (ኢዮብ 33:25፤ ኢሳ. 33:24) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ጥበበኞች መሆናችንና እምነት ማዳበራችን አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከሁሉ በተሻለ መንገድ በመጠቀም ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ይረዳናል።—1 ጢሞ. 4:8

ገንዘብ

11. ገንዘብ ወጥመድ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

11 ገንዘብ በራሱ መጥፎ አይደለም፤ መነገድም ቢሆን ስህተት አይደለም። (መክ. 7:12፤ ሉቃስ 19:12, 13) “የገንዘብ ፍቅር” ማዳበር ግን ከይሖዋ እንደሚያርቀን ምንም አያጠያይቅም። (1 ጢሞ. 6:9, 10) “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት” ማለትም ለሕይወታችን ስለሚያስፈልጉ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ በመንፈሳዊ እንዳናድግ ሊያንቀን ይችላል። ‘ሀብት ያለው የማታለል ኃይልም’ ይኸውም ሀብት ዘላቂ ደስታና ደኅንነት ያስገኛል የሚለው የተሳሳተ እምነትም ቢሆን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። (ማቴ. 13:22) ኢየሱስ አምላክንም ሆነ ሀብትን በአንድነት ማገልገል የሚችል ማንም ሰው እንደሌለ በግልጽ ተናግሯል።—ማቴ. 6:24

12. በአሁኑ ጊዜ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ወጥመዶች የተለመዱ ሆነዋል? ከእነዚህስ ልንርቅ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ለገንዘብ የተሳሳተ አመለካከት ማዳበር ወደ ስህተት ጎዳና ሊመራ ይችላል። (ምሳሌ 28:20) በአቋራጭ ለመክበር ካላቸው ጉጉት የተነሳ ሎተሪ የቆረጡ ወይም ደግሞ እንደ ሠንሰለት ተያይዘው በመሄድ ብዙ ሰዎችን በሚያነካኩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የገቡ ክርስቲያኖች አሉ፤ እንዲያውም አንዳንዶች በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችን በዚህ ንግድ ውስጥ ለማስገባት ጥረት አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ ሊታመን የማይችል ትርፍ ያስገኛሉ በሚባሉ የንግድ ዘርፎች ላይ ገንዘባቸውን እንዲያፈሱ በቀረበላቸው ሐሳብ ተታልለዋል። አንተም ስግብግብነት የአጭበርባሪዎች ሰለባ እንዳያደርግህ ተጠንቀቅ! ስለዚህ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ አዳብር። አንድ ግብዣ የማይታመን እስኪመስል ድረስ ጥሩ ከሆነ እውነትም የማይታመን ሊሆን ይችላል።

13. ይሖዋ ለገንዘብ ያለው አመለካከት ዓለም ካለው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

 13 ‘መንግሥቱንና ጽድቁን’ የምናስቀድም ከሆነ ይሖዋ ሚዛናችንን ሳንስት መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት የምናደርገውን ጥረት ይባርክልናል። (ማቴ. 6:33፤ ኤፌ. 4:28) ይሖዋ ከመጠን በላይ በመሥራታችን ምክንያት ጉባኤ ውስጥ እንድናንቀላፋ ወይም መንግሥት አዳራሽ ቁጭ ብለን ስለ ገንዘብ እንድንጨነቅ አይፈልግም። ይሁን እንጂ በዙሪያችን ያሉ ብዙ ሰዎች የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ማድረግና በኋላ ላይ ዘና ያለ ሕይወት መኖር የሚችሉት አሁን ገንዘብ ለማግኘት ከተሯሯጡ ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በአብዛኛው ልጆቻቸውም ለቁሳዊ ነገሮች ተመሳሳይ ግብ እንዲኖራቸው ይጫኗቸዋል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ማስተዋል የጎደለው እንደሆነ ገልጿል። (ሉቃስ 12:15-21ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነት ሰው በአንድ በኩል የስግብግብነት ፍላጎቱን እያሟላ በሌላ በኩል ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና መጠበቅ እንደሚችል አድርጎ ያስብ የነበረውን ግያዝን ያስታውሰናል።—2 ነገ. 5:20-27

14, 15. ገንዘብ አስተማማኝ የሆነ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችል ማሰብ ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

14 አንዳንድ ንስሮች በጥፍሮቻቸው ሊያነሷቸው ከሚችሉት በላይ ክብደት ያላቸውን ዓሣዎች ከያዙ በኋላ ዓሣውን መልሰው ባለመልቀቃቸው እንደሰጠሙ ታይቷል። አንድ ክርስቲያንስ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል? አሌክስ የተባለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በባሕርዬ በጣም ቆጣቢ ነኝ። ሻምፖ ስጠቀም እንኳ ብዙ እንዳወጣሁ ከተሰማኝ ትርፉን መልሼ ዕቃ ውስጥ እጨምረዋለሁ።” ይሁንና አሌክስ ሥራውን ለቅቆ አቅኚ ለመሆን ሲል የአክስዮን ንግድ ውስጥ መግባት ፈለገ። ከዚያም የአክሲዮኖችን ዋጋና የገበያውን ሁኔታ በማጥናቱ ሥራ ተጠመደ። በመጨረሻም አንድ አክሲዮን በፍጥነት ዋጋው እንደሚጨምር የገበያ ጥናት ተንታኞች የተናገሩትን በማመን፣ ባጠራቀመው ገንዘብ ላይ ብድር ጨምሮ አክሲዮኑን ገዛ። የአክሲዮኑ ዋጋ ግን እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ በፍጥነት አሽቆለቆለ። አሌክስ እንዲህ ብሏል፦ “ገንዘቤን መልሼ ማግኘት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ትንሽ ብቆይ የአክሲዮኑ ዋጋ ከፍ ሊል ይችላል ብዬ አሰብኩ።”

15 አሌክስ ለብዙ ወራት ከአክሲዮኑ ውጪ የሚያስበው ነገር አልነበረም። በዚህም የተነሳ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር አቃተው፤ እንዲሁም እንቅልፍ እንቢ አለው። ይሁንና የአክሲዮኑ ዋጋ እንደወረደ ቀረ። አሌክስ ያጠራቀመውን ገንዘብ ያጣ ከመሆኑም በላይ ቤቱን መሸጥ ነበረበት። “ቤተሰቤን ለከባድ ሥቃይ ዳረግኩት” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ይሁንና ከደረሰበት ነገር ጥሩ ትምህርት አግኝቷል። “በሰይጣን ሥርዓት የሚታመን ሁሉ ለከፋ ሐዘን እንደሚዳረግ አሁን ተገንዝቤያለሁ” ብሏል። (ምሳሌ 11:28) በእርግጥም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ባጠራቀምነው ገንዘብ ወይም በንግዳችን አሊያም ገንዘብ ለማግኘት ባለን ችሎታ ላይ ተስፋ መጣል “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በሆነው በሰይጣን ላይ ተስፋ ከማድረግ ተለይቶ አይታይም። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ጢሞ. 6:17) አሌክስ “ስለ ምሥራቹ ሲል” ቀላል ሕይወት መኖር ጀምሯል። እንዲህ ማድረጉ እሱም ሆነ ቤተሰቡ ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑና ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ እንደረዳቸው ይናገራል።ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።

ኩራት

16. መኩራት ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው? ተገቢ የማይሆነውስ?

16 በአንዳንድ ነገሮች መኩራት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ የይሖዋ ምሥክር በመሆናችን ምንጊዜም ኩራት ሊሰማን ይገባል። (ኤር. 9:24) በተወሰነ መጠን ለራሳችን አክብሮት ካለን ጥሩ ውሳኔ እናደርጋለን፤ እንዲሁም የሥነ ምግባር አቋማችንን አናላላም። ይሁንና ቦታችንን የማንጠብቅ ወይም ለራሳችን ያለን ግምት ከልክ ያለፈ ከሆነ ይህ ሁኔታ ከይሖዋ ሊያርቀን ይችላል።—መዝ. 138:6፤ ሮም 12:3

በጉባኤ ውስጥ መብት ለማግኘት ከመጓጓት ይልቅ ትኩረታችሁን በአገልግሎታችሁ ላይ አድርጉ!

17, 18. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትሑት በመሆናቸው አሊያም በኩራታቸው የተጠቀሱ ሰዎችን ተናገር። (ለ) አንድ ወንድም ኩራት ከይሖዋ እንዳያርቀው ያደረገው እንዴት ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስ ኩሩ ስለነበሩና ትሑት ስለነበሩ ሰዎች የሚናገሩ ታሪኮችን ይዟል። ንጉሥ ዳዊት ትሑት በመሆን የይሖዋን መመሪያ ይጠይቅ ስለነበር ይሖዋ ባርኮታል። (መዝ. 131:1-3) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ትዕቢተኛ የነበሩት ንጉሥ ናቡከደነፆርና ቤልሻዛር ልካቸውን እንዲያውቁ አድርጓል። (ዳን. 4:30-37፤ 5:22-30) በዛሬው ጊዜም ትሕትናችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። ዕድሜው 32 ዓመት የሆነ ራየን የተባለ አንድ የጉባኤ አገልጋይ  ጉባኤ በቀየረበት ወቅት ያጋጠመውን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ወዲያው ሽማግሌ ሆኜ እንደምሾም ጠብቄ ነበር። ሆኖም ያሰብኩት ሳይሆን አንድ ዓመት አለፈ።” ታዲያ ራየን ሽማግሌዎቹ ተገቢውን አክብሮት እንዳላሳዩት ተሰምቶት ይናደድ ወይም ይበሳጭ ይሆን? ኩራት ከይሖዋና ከሕዝቡ እንዲያርቀው በመፍቀድ ጉባኤ መሄዱን ያቆም ይሆን? አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር?

18 ራየን “ስለሚዘገይ ተስፋ የሚናገሩ ጽሑፎችን በሙሉ አነበብኩ” ብሏል። (ምሳሌ 13:12 የ1954 ትርጉም) አክሎም “ትዕግሥትንና ትሕትናን ማዳበር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይሖዋ እንዲያሠለጥነኝ መፍቀድ ነበረብኝ” ብሏል። ራየን በራሱ ላይ ከማተኮር ይልቅ በጉባኤ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ የሚያገኛቸውን ሰዎች በመርዳት ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ እድገት የሚያደርጉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ጀመረ። ራየን እንዲህ ብሏል፦ “ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ሽማግሌ ሆኜ ስሾም ያልጠበቅኩት ነገር ሆነብኝ። ምክንያቱም ትኩረቴ ሁሉ አገልግሎቴ ላይ ስለነበር ስለ መብት ማሰቤን ትቼ ነበር።”—መዝሙር 37:3, 4ን አንብብ።

ከይሖዋ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ!

19, 20. (ሀ) የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎቻችን ከይሖዋ እንዳያርቁን ምን ማድረግ እንችላለን? (ለ) ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር የእነማንን ምሳሌ መከተል እንችላለን?

19 በዚህና ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ የተወያየንባቸው ነገሮች በሙሉ በሕይወታችን ውስጥ ተገቢውን ቦታ እስከሰጠናቸው ድረስ በራሳቸው ስህተት አይደሉም። የይሖዋ አገልጋይ በመሆናችን ልንኮራ ይገባል። ይሖዋ ከሰጠን ውድ ስጦታዎች መካከል ደስተኛ ቤተሰብና ጥሩ ጤንነት ይገኙበታል። ሥራና ገንዘብም ቢሆን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት እንደሚረዱን እንገነዘባለን። በተጨማሪም መዝናኛ መንፈሳችንን እንደሚያድስ፣ ቴክኖሎጂም ጠቃሚ አገልግሎት ሊሰጠን እንደሚችል እናውቃለን። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ተገቢ ባልሆነ ጊዜ ወይም ከመጠን በላይ አሊያም አምልኳችንን በሚነካ መንገድ የምንጠቀምባቸው ከሆነ ከይሖዋ ሊያርቁን ይችላሉ።

ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ!

20 የሰይጣን ፍላጎት እኛን ከይሖዋ ማራቅ እንደሆነ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ በእናንተም ሆነ በቤተሰባችሁ ላይ እንዳይደርስ ማድረግ ትችላላችሁ! (ምሳሌ 22:3) ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ከእሱ ጋር ምንጊዜም ተቀራርባችሁ ለመኖር ጥረት አድርጉ። በዚህ ረገድ ትምህርት የሚሰጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹ በርካታ ምሳሌዎች አሉ። ሄኖክና ኖኅ ‘አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አድርገዋል።’ (ዘፍ. 5:22፤ 6:9) ሙሴ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል።” (ዕብ. 11:27) ኢየሱስ ሁልጊዜ በሰማይ የሚገኘው አባቱን የሚያስደስት ነገር ያደርግ ስለነበረ የአምላክ ድጋፍ አልተለየውም። (ዮሐ. 8:29) እንዲህ ያሉ ሰዎችን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርጉ። “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ። ያለማቋረጥ ጸልዩ። ስለ ሁሉም ነገር አመስግኑ።” (1 ተሰ. 5:16-18) እንዲሁም ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ!

^ စာပိုဒ်၊ 4 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ စာပိုဒ်၊ 6 “ልጆችን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ” የሚለውን የጥቅምት 2011 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።

^ စာပိုဒ်၊ 7 “ጤናን ለማሻሻል የሚረዱ አምስት ቁልፍ ነገሮች” የሚለውን የመጋቢት 2011 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።