በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመንፈሳዊ ውርሻችን አድናቆት አላችሁ?

ለመንፈሳዊ ውርሻችን አድናቆት አላችሁ?

“አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ትኩረቱን . . . ወደ እነሱ [አዞረ]።” —ሥራ 15:14

1, 2. (ሀ) ‘የዳዊት ድንኳን’ ወይም ‘የዳዊት ዳስ’ የተባለው ምንድን ነው? እንደገና የተገነባውስ እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋን በአንድነት እያገለገሉ ያሉት እነማን ናቸው?

በኢየሩሳሌም በ49 ዓ.ም. በተካሄደው ታሪካዊ ስብሰባ ላይ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ትኩረቱን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ወደ እነሱ እንዳዞረ ስምዖን [ጴጥሮስ] በሚገባ ተርኳል። እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል፦ ‘ከዚህ በኋላ ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ዳስ ዳግመኛ እገነባለሁ፤ ፍርስራሹንም ዳግም በመገንባት እንደገና አቆመዋለሁ፤ ይህንም የማደርገው የቀሩት ሰዎች በስሜ ከተጠሩት ይኸውም ከአሕዛብ ከመጡት ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያከናውነው ይሖዋ ተናግሯል፤ እነዚህንም ነገሮች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ያውቃል።’”—ሥራ 15:13-18

2 ‘የዳዊት ድንኳን’ ወይም የንግሥና መስመር የፈረሰው ንጉሥ ሴዴቅያስ ከዙፋኑ እንዲወርድ በተደረገበት ወቅት ነው። (አሞጽ 9:11) ይሁንና ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጣው ኢየሱስ ዘላለማዊ ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ይህ “ዳስ” ወይም “ድንኳን” ዳግመኛ ተገንብቷል። (ሕዝ. 21:27፤ ሥራ 2:29-36) ያዕቆብ በዚያ ታሪካዊ ስብሰባ ወቅት እንደጠቆመው የመንግሥቱ ወራሾች ከአይሁዳውያንም ሆነ ከአሕዛብ እየተሰበሰቡ በመሆናቸው ይህ የአሞጽ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነበር። በዛሬው ጊዜ ቅቡዓን ቀሪዎችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” አንድ ላይ ሆነው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማወጅ ይሖዋን እያገለገሉ ነው።—ዮሐ. 10:16

የይሖዋ ሕዝቦች ተፈታታኝ ሁኔታ ገጠማቸው

3, 4. የይሖዋ ሕዝቦች በባቢሎን እያሉም እንኳ መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት እንዴት ነው?

3 አይሁዳውያን በግዞት ወደ ባቢሎን በተወሰዱበት ወቅት ‘የዳዊት ዳስ’ ፈርሷል። የሐሰት ሃይማኖት በገነነባት በባቢሎን የአምላክ ሕዝቦች ከ607 ዓ.ዓ. እስከ 537 ዓ.ዓ. ባሉት 70 ዓመታት በምርኮ ቆይተዋል፤ ታዲያ በዚያ ወቅት መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው መቆየት  የቻሉት እንዴት ነው? እነሱንም ሆነ ሰይጣን በሚቆጣጠረው በዚህ ዓለም ውስጥ የምንኖር የይሖዋ ሕዝቦችን የረዳን ነገር ተመሳሳይ ነው። (1 ዮሐ. 5:19) ሁላችንም ቢሆን መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን እንድንኖር የረዳን ያገኘነው ታላቅ መንፈሳዊ ውርሻ ነው።

4 ካሉን መንፈሳዊ ቅርሶች መካከል አንዱ በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ነው። በባቢሎን የነበሩት አይሁዳውያን ምርኮኞች ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ አልነበራቸውም፤ ይሁን እንጂ አሥርቱን ትእዛዛት የያዘውን የሙሴ ሕግ ያውቁ ነበር። ‘የጽዮን መዝሙሮችን’ እና በርካታ ምሳሌዎችን ማስታወስ ይችሉ ነበር፤ ከዚህም ሌላ ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ያከናወኗቸውን ነገሮች ያውቁ ነበር። እነዚህ ምርኮኞች ጽዮንን ሲያስታውሱ ያለቀሱ ሲሆን ይሖዋንም አልረሱም። (መዝሙር 137:1-6ን አንብብ።) እነዚህ ነገሮች፣ የአምላክ ሕዝቦች የሐሰት ትምህርቶችና ሃይማኖታዊ ልማዶች በተስፋፉባት በባቢሎን እያሉም እንኳ መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው ለመኖር አስችለዋቸዋል።

ሥላሴ አዲስ መሠረተ ትምህርት አይደለም

5. በጥንት ዘመን በባቢሎን እና በግብፅ ሦስት ጣምራ አማልክት ወይም ሥላሴዎች ይመለኩ እንደነበር የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

5 የሦስት ጣምራ አማልክት ወይም የሥላሴ አምልኮ በባቢሎናውያን ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ከባቢሎናውያን ሥላሴዎች አንዱ ሲን (የጨረቃ አምላክ)፣ ሻማሽ (የፀሐይ አምላክ) እና ኢሽታር (የመራባትና የጦርነት እንስት አምላክ) የተባሉትን አማልክት ያቀፈ ነበር። በጥንቷ ግብፅ ደግሞ አንድ አምላክ፣ አንዲት እንስት አምላክ ካገባ በኋላ ወንድ ልጅ እንደምትወልድለት ይታሰብ ነበር፤ “እነዚህ ሦስቱ፣ ጥምር አምላክ ወይም ሥላሴ ይሆናሉ፤ አባትየው የአምላክነት ቦታ የሚኖረው ሁልጊዜ አይደለም፤ በዚህ ጊዜ የእንስቷ አምላክ ባል ከመሆን ያለፈ ልዩ ቦታ አይኖረውም። እንስቷ አምላክ ግን የአምላክነት ቦታዋን ይዛ ትቀጥላለች።” (ኒው ላሩስ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሚቶሎጂ) ግብፃውያን ከነበሯቸው ሥላሴዎች አንዱ ኦሳይረስ የተባለውን አምላክ፣ አይስስ የተባለችውን እንስት አምላክ እና ሆረስ የተባለውን ልጃቸውን ያቀፈ ነበር።

6. የሥላሴን መሠረተ ትምህርት እንዴት ትገልጸዋለህ? በዚህ የተሳሳተ ትምህርት ከመታለል ልንጠበቅ የቻልነው ለምንድን ነው?

6 ሕዝበ ክርስትናም በሦስት ጣምራ አማልክት በሌላ አባባል በሥላሴ ታምናለች። አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እንደሆኑ ቀሳውስቷ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ የሦስት ጣምራ አማልክት አንዱ ክፍል እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርበው ይህ ትምህርት በሉዓላዊነቱ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው። የይሖዋ ሕዝቦች ግን “እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ ስለሚያውቁ በዚህ የተሳሳተ ትምህርት ከመታለል ተጠብቀዋል። (ዘዳ. 6:4) ኢየሱስም ይህን ሐሳብ ጠቅሶ የተናገረ ሲሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች እሱ የተናገረውን ያምናሉ።—ማር. 12:29

7. አንድ ሰው በሥላሴ የሚያምን ከሆነ ተቀባይነት ባለው መንገድ ራሱን ለአምላክ ወስኖ መጠመቅ የማይችለው ለምንድን ነው?

7 የሥላሴ መሠረተ ትምህርት፣ ኢየሱስ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ለተከታዮቹ ከሰጣቸው መመሪያ ጋር ይቃረናል። (ማቴ. 28:19) አንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያን ሆኖ ለመጠመቅና የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ከፈለገ አብ ወይም ይሖዋ ከሁሉ የበላይ መሆኑን መገንዘብ እንዲሁም ወልድ የተባለውና የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ያለውን ሥልጣንና ቦታ ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም መጠመቅ የሚፈልገው ሰው፣ መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል እንጂ የሥላሴ ክፍል እንዳልሆነ ማመን ይኖርበታል። (ዘፍ. 1:2) ጥምቀት አምላክ በሚፈልገው መንገድ ራሳችንን ለይሖዋ እንደወሰንን የሚያሳይ እርምጃ እንደመሆኑ መጠን አንድ ሰው በሥላሴ ማመኑን ካላቆመ ጥምቀቱ ተቀባይነት አይኖረውም። መንፈሳዊ ቅርሳችን አምላክን በሚያቃልለው በዚህ ትምህርት ከመታለል ስለጠበቀን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

መናፍስታዊ ትምህርት ብቅ አለ

8. ባቢሎናውያን ስለ አማልክትና ስለ አጋንንት ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው?

8 በባቢሎን በርካታ የሐሰት ትምህርቶች የነበሩ ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡ ከአማልክቱ በተጨማሪ ለአጋንንትና ለመናፍስታዊ ድርጊቶች የተለየ ቦታ ይሰጥ  ነበር። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎችን በተለያዩ የአካልም ሆነ የአእምሮ በሽታዎች እንደሚቀስፉ የሚታመኑት አጋንንት በባቢሎናውያን ሃይማኖት ውስጥ ከአማልክቱ ቀጥሎ ትልቅ ትኩረት ይሰጣቸው ነበር። የሃይማኖቱ ዋነኛ ገጽታ፣ ሰዎች ከእነዚህ አጋንንት ጋር የሚያደርጉት ከባድ ትግል የነበረ ይመስላል፤ ሰዎች፣ አማልክቱ ከእነዚህ አጋንንት እንዲያስጥሏቸው በየቦታው ጸሎት ያቀርቡ ነበር።”

9. (ሀ) በርካታ አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ በሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች የተታለሉት እንዴት ነው? (ለ) እያወቅን ከአጋንንት ጋር የተያያዘ ነገር ውስጥ እንዳንገባ የጠበቀን ምንድን ነው?

9 በርካታ አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሐሳቦችን መቀበል ጀመሩ። የግሪካውያን ጽንሰ ሐሳቦች ተጽዕኖ ስላደረጉባቸው፣ ጥሩም ሆነ መጥፎ አጋንንት አሉ የሚል አስተሳሰብ ያዳበሩ ሲሆን ይህም ለአጋንንት ጥቃት አጋልጧቸዋል። መንፈሳዊ ቅርሳችን፣ እያወቅን ከአጋንንት ጋር የተያያዘ ነገር ውስጥ እንዳንገባ ጠብቆናል፤ ምክንያቱም አምላክ ባቢሎናውያን ይፈጽሟቸው የነበሩትን መናፍስታዊ ድርጊቶች እንዳወገዘ እናውቃለን። (ኢሳ. 47:1, 12-15) ከዚህም ሌላ አምላክ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች የሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ እናደርጋለን።—ዘዳግም 18:10-12ን እና ራእይ 21:8ን አንብብ።

10. ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ትምህርቶችና ሃይማኖታዊ ልማዶች ምን ማለት ይቻላል?

10 መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይፈጽሙ የነበሩት የጥንቶቹ ባቢሎናውያን ብቻ አይደሉም፤ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው የታላቂቱ ባቢሎን ደጋፊዎችም በመናፍስታዊ ድርጊቶች ይካፈላሉ። (ራእይ 18:21-24) ዚ ኢንተርፕሬተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል፦ “[ታላቂቱ] ባቢሎን አንድን ግዛት ወይም ባህል የምትወክል አይደለችም። በተወሰነ ጊዜ ወይም ቦታ የምትገደብም አይደለችም። ከዚህ ይልቅ ተስፋፍተው የሚገኙ የተለያዩ ጣዖት አምልኮዎችን ታመለክታለች።” (ጥራዝ 1 ገጽ 338) በመናፍስታዊ እምነት፣ በጣዖት አምልኮና በሌሎች ኃጢአቶች የተጠላለፈችው ታላቂቱ ባቢሎን ዛሬም አለች፤ ይሁን እንጂ የምትጠፋበት ጊዜ ቀርቧል።—ራእይ 18:1-5ን አንብብ።

11. መናፍስታዊ ድርጊትን አስመልክቶ በጽሑፎቻችን ላይ ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያዎች ወጥተዋል?

11 ይሖዋ “የምትፈጽሙትን አስማታዊ ድርጊት መታገሥ አልችልም” በማለት ተናግሯል። (ኢሳ. 1:13 NW) ሙታንን ማነጋገር በ19ኛው መቶ ዘመን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነገር ነበር። በመሆኑም የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በግንቦት 1885 እትሙ ላይ የሚከተለውን ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ሙታን በሌላ ቦታ ወይም ሁኔታ ይኖራሉ የሚለው እምነት አዲስ አይደለም። በጥንት ዘመን የነበሩ ሃይማኖቶች ይህን ትምህርት ያስተምሩ የነበረ ሲሆን የሐሰት ትምህርቶች ሁሉ መሠረት ነው።” መጠበቂያ ግንቡ አክሎ እንደገለጸው ሙታን ከሕያዋን ጋር እንደሚነጋገሩ የሚገልጸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት “‘አጋንንት’፣ የሞቱ ሰዎችን መስለው በመቅረብ ሰዎችን ለማታለል አመቺ ሽፋን ፈጥሮላቸዋል። በዚህ መንገድ ማንነታቸው ደብቀው ሰዎችን የሚቀርቡ ሲሆን ይህም የብዙዎችን አእምሮና ሕይወት ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል።” ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ መናፍስታዊ ድርጊት ምን ይላሉ? (እንግሊዝኛ) የሚለውን የቆየ ቡክሌት ጨምሮ በቅርብ ጊዜ የወጡ ጽሑፎቻችንም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ነፍስ በሙታን ዓለም ትሠቃያለች?

12. ሰለሞን ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ በአምላክ መንፈስ መሪነት ምን ብሏል?

12 “እውነትን ያወቁ ሁሉ” ይህን ጥያቄ መመለስ ይችላሉ። (2 ዮሐ. 1) ሰለሞን እንደሚከተለው በማለት በተናገረው ሐሳብ እንደምንስማማ የታወቀ ነው፦ “በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና! ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ . . . እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።”—መክ. 9:4, 5, 10

13. የግሪካውያን ባህል እና ሃይማኖት በአይሁዳውያን ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

13 አይሁዳውያን ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እውነቱን ማወቅ ይችሉ ነበር። ይሁንና አራቱ የታላቁ እስክንድር ጄኔራሎች የግሪክን ግዛት ሲከፋፈሉ ይሁዳ ከሶርያ ጋር እንድትቀላቀል ለማድረግ ተሞክሮ ነበር፤ ይህን ለማሳካትም ሕዝቡ የግሪክን ሃይማኖትና ባሕል እንዲቀበል ለማድረግ ተሞክሯል። በዚህም ምክንያት  አይሁዳውያን የሰው ነፍስ እንደማትሞት እንዲሁም በሙታን ዓለም የመሠቃያ ቦታ እንዳለ የሚገልጸውን የሐሰት ትምህርት ተቀበሉ። በእርግጥ የሞቱ ነፍሳት የሚሠቃዩበት የሙታን ዓለም እንዳለ የሚገልጸውን ሐሳብ ያመነጩት ግሪካውያን አይደሉም፤ ባቢሎናውያንም “የታችኛው ዓለም . . . አስፈሪ ነገሮች የሞሉበትና . . . ከፍተኛ ኃይል ባላቸው ጨካኝ አማልክትና አጋንንት” የሚተዳደር እንደሆነ ያስቡ ነበር። (ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎንያ ኤንድ አሲርያ) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ባቢሎናውያን ነፍስ እንደማትሞት ያምኑ ነበር።

14. ኢዮብ እና አብርሃም ስለ ሞትና ስለ ትንሣኤ ምን ያውቁ ነበር?

14 ጻድቅ ሰው የሆነው ኢዮብ፣ በኖረበት ወቅት ቅዱሳን ጽሑፎች ባይኖሩም ስለ ሞት እውነቱን ያውቅ ነበር። ከዚህም በላይ አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ እሱን ከሞት ለማስነሳት እንደሚናፍቅ ተገንዝቦ ነበር። (ኢዮብ 14:13-15) አብርሃምም ሙታን እንደሚነሱ ያምን ነበር። (ዕብራውያን 11:17-19ን አንብብ።) እነዚህ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ነፍስ እንደማትሞት በሚገልጸው ትምህርት እንደማያምኑ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ትንሣኤ ሊያገኝ የሚችለው የሞተ ነፍስ ብቻ ነው። ኢዮብም ሆነ አብርሃም ሙታን ያሉበትን ሁኔታ እንዲያውቁና በትንሣኤ ላይ እምነት እንዲኖራቸው የረዳቸው የአምላክ መንፈስ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። እነዚህ እውነቶችም የመንፈሳዊ ውርሻችን ክፍል ናቸው።

‘ቤዛው የሚያስገኘው ነፃነት’ በጣም አስፈላጊ ነው

15, 16. ከኃጢአትና ከሞት ነፃ መውጣት የምንችለው እንዴት ነው?

15 አምላክ፣ ከአዳም ከወረስነው ኃጢአትና ሞት እኛን ነፃ ስለሚያወጣበት መንገድ እውነቱን እንድናውቅ ስላስቻለንም አመስጋኞች ነን። (ሮም 5:12) ኢየሱስ “የመጣው ለማገልገልና በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” እንደሆነ እንገነዘባለን። (ማርቆስ 10:45) “ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ [ስለሚያስገኘው] ነፃነት” ማወቅ ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ሮም 3:22-24

16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያንና አሕዛብ ከኃጢአታቸው ንስሐ መግባትና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። ይህን ካላደረጉ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት አይችሉም። ዛሬም  ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (ዮሐ. 3:16, 36) አንድ ሰው እንደ ሥላሴና ነፍስ አትሞትም በሚሉት የሐሰት ትምህርቶች ማመኑን ካልተወ ከቤዛው ጥቅም ማግኘት አይችልም። እኛ ግን ከቤዛው መጠቀም ችለናል። አምላክ ስለሚወደው ልጁና ይህ ልጅ “ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ” እንዳደረገን እናውቃለን።—ቆላ. 1:13, 14

ይሖዋን ማገልገላችሁን ቀጥሉ!

17, 18. ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ የሚገልጽ መረጃ ከየት ማግኘት እንችላለን? ይህን ታሪክ በመመርመር ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

17 በዛሬው ጊዜ የምናውቃቸውን እውነተኛ ትምህርቶች፣ የአምላክ ሕዝቦች ሆነን ያሳለፍናቸውን ተሞክሮዎች እንዲሁም ያሉንን መንፈሳዊና ቁሳዊ በረከቶች በተመለከተ ብዙ ማለት ይቻላል። የዓመት መጽሐፋችን (እንግሊዝኛ) በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች ስለምናደርገው እንቅስቃሴ የሚገልጹ አስደናቂ ተሞክሮዎችን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይዞ ሲወጣ ቆይቷል። በተጨማሪም በተግባር የተደገፈ እምነት (እንግሊዝኛ) በተባለው ቪዲዮ ክፍል 1 እና ክፍል 2 እንዲሁም የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍና በሌሎች ጽሑፎች ላይ ስለ ታሪካችን የሚገልጽ ዘገባ ወጥቷል። ከዚህም ሌላ ተወዳጅ የሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችንን የሕይወት ታሪክ የያዙ ልብ የሚነኩ ርዕሶች ብዙውን ጊዜ በመጽሔቶቻችን ላይ ይወጣሉ።

18 የእስራኤል ሕዝብ፣ አምላክ ከግብፅ ባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው ማስታወሳቸው እንደጠቀማቸው ሁሉ እኛም ሚዛናችንን ሳንስት የይሖዋ ድርጅትን ታሪክ መመርመራችን ይጠቅመናል። (ዘፀ. 12:26, 27) አምላክ ያደረጋቸውን አስደናቂ ነገሮች በሕይወቱ የተመለከተው አረጋዊው ሙሴ፣ እስራኤላውያንን “የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርሃልም፤ ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ያስረዱሃል” በማለት አሳስቧቸው ነበር። (ዘዳ. 32:7) ‘የይሖዋ ሕዝብ እና የማሰማሪያው በጎች’ እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም በደስታ እሱን እናወድሳለን፤ እንዲሁም ያከናወናቸውን ታላላቅ ሥራዎች ለሌሎች እናውጃለን። (መዝ. 79:13) ከዚህም በተጨማሪ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ መመርመራችን እንዲሁም ከዚያ ትምህርት መቅሰማችን እና ሕይወታችንን ከዚያ ጋር በሚስማማ መንገድ መምራታችን አስፈላጊ ነው።

19. ላገኘነው መንፈሳዊ ብርሃን ያለን አድናቆት ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

19 በጨለማ ከመዳከር ድነን አምላክ በፈነጠቀልን መንፈሳዊ ብርሃን መመላለስ በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን። (ምሳሌ 4:18, 19) እንግዲያው የአምላክን ቃል በትጋት እናጥና፤ እንዲሁም ያገኘነውን እውነት ለሌሎች በቅንዓት እናካፍል። የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ለሆነው ለይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ በመጸለይ ያወደሰው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ይኑረን፦ “የአንተን ጽድቅ ብቻ እናገራለሁ። አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ። አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ።”—መዝ. 71:16-18

20. ለይሖዋ ታማኝ መሆናችን ምን ያረጋግጣል? ስለ ይሖዋ ሉዓላዊ ገዥነትና ለእሱ ስለምናቀርበው አምልኮ ምን ይሰማሃል?

20 ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን ሕዝቦቹ እንደመሆናችን መጠን ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን ከአምላክ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንደሚያስችል እንገነዘባለን። በእርግጥም ታማኝነታችንን ስንጠብቅ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥና በሙሉ ልብ የምናቀርበው አምልኮ የሚገባው አካል መሆኑ አሌ የማይባል ሐቅ እንደሆነ እናረጋግጣለን። (ራእይ 4:11) የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ በመሆኑ ለድኾች የምሥራች እንሰብካለን፣ ልባቸው የተሰበረውን እንጠግናለን እንዲሁም የሚያለቅሱትን እናጽናናለን። (ኢሳ. 61:1, 2) ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦችና መላውን የሰውን ዘር ለመቆጣጠር ቢፍጨረጨርም ጥረቱ መቼም ቢሆን አይሳካም፤ እኛ ግን ውድ የሆነ መንፈሳዊ ውርሻችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅና ሉዓላዊ ጌታ የሆነውን ይሖዋን አሁንም ሆነ ለዘላለም ለማወደስ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—መዝሙር 26:11ን በNW እና 86:12ን አንብብ። *

^ စာပိုဒ်၊ 20 መዝሙር 26:11 (NW)፦ “እኔ በበኩሌ፣ ንጹሕ አቋሜን ጠብቄ እመላለሳለሁ። ታደገኝ፤ ሞገስም አሳየኝ።”