በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጌላዊ እንደመሆናችሁ መጠን ያለባችሁን ኃላፊነት ተወጡ

ወንጌላዊ እንደመሆናችሁ መጠን ያለባችሁን ኃላፊነት ተወጡ

“የወንጌላዊን ሥራ አከናውን እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።”—2 ጢሞ. 4:5

1. ይሖዋ የመጀመሪያውና አንጋፋው ወንጌላዊ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ለምንድን ነው?

ምሥራች የሚናገር ሰው ወንጌላዊ ይባላል። የመጀመሪያውና አንጋፋው ወንጌላዊ ይሖዋ አምላክ ነው። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ባመፁ ጊዜ ይሖዋ እባቡ ይኸውም ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሚወገድ የሚገልጽ ምሥራች ተናግሯል። (ዘፍ. 3:15) ከዚያ በኋላ ባሉት መቶ ዘመናት ይሖዋ ስሙ ከነቀፋ ነፃ የሚሆነው፣ ሰይጣን ያደረሰው ጉዳት የሚወገደው እንዲሁም ሰዎች አዳምና ሔዋን ያበላሹትን አጋጣሚ መልሰው ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ታማኝ አገልጋዮቹን በመንፈሱ እየመራ ዝርዝር ጉዳዮችን እንዲጽፉ አድርጓል።

2. (ሀ) ከወንጌላዊነቱ ሥራ ጋር በተያያዘ መላእክት ምን ድርሻ ያበረክታሉ? (ለ) ኢየሱስ ወንጌላውያን ሊከተሉት የሚገባ ምን አርዓያ ትቷል?

2 መላእክትም ወንጌላውያን ናቸው። እነሱ ራሳቸው ምሥራች የሚናገሩ ከመሆኑም በተጨማሪ ሌሎች ምሥራቹን እንዲያዳርሱ ይረዳሉ። (ሉቃስ 1:19፤ 2:10፤ ሥራ 8:26, 27, 35፤ ራእይ 14:6) ሊቀ መላእክት ስለሆነው ስለ ሚካኤልስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ የመላእክት አለቃ ማለትም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ወንጌላውያን የሆኑ ሰዎች ሊከተሉት የሚገባ አርዓያ ትቷል። እንዲያውም ኢየሱስ መላ ሕይወቱ ምሥራቹን በማዳረሱ ሥራ ላይ ያተኮረ ነበር!—ሉቃስ 4:16-21

3. (ሀ) ለሰዎች የምናውጀው ምሥራች ምንድን ነው? (ለ) ወንጌላውያን እንደመሆናችን መጠን ለየትኞቹ ጥያቄዎች ትኩረት መስጠት ይኖርብናል?

3 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወንጌላውያን እንዲሆኑ አዟቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ የሥራ ባልደረባው የሆነውን ጢሞቴዎስን “የወንጌላዊን ሥራ አከናውን እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም” ብሎታል። (2 ጢሞ. 4:5) የኢየሱስ ተከታዮች የሆንነው እኛ ልናውጀው የሚገባ ምሥራች ምንድን ነው? በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ እንደሚወደን የሚገልጸው የሚያጽናና እውነት የምሥራቹ አንድ ገጽታ ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ጴጥ. 5:7) ይሖዋ አምላክ ለሰዎች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል፤ ያቋቋመው መንግሥት የፍቅሩ ዋና መገለጫ ነው። በመሆኑም ለመንግሥቱ የሚገዙ፣ አምላክን የሚታዘዙና ጽድቅን የሚያደርጉ ሁሉ የእሱ ወዳጆች የመሆን አጋጣሚ እንዳላቸው ለሌሎች  በደስታ እናበስራለን። (መዝ. 15:1, 2) ደግሞም ይሖዋ ሰዎች የሚደርስባቸውን ግፍ በሙሉ የማስወገድ ዓላማ አለው። በተጨማሪም የደረሰብን መከራ ከአእምሯችን አልጠፋ ማለቱ የሚያስከትልብንን ሥቃይ ያስወግዳል። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ምሥራች ነው! (ኢሳ. 65:17) እኛም ወንጌላዊ እንደመሆናችን መጠን የሚከተሉትን ሁለት ዓበይት ጥያቄዎች እንመርምር፦ በዛሬው ጊዜ ሰዎች ምሥራቹን መስማታቸው አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? ወንጌላዊ እንደመሆናችን መጠን ያለብንን ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ መወጣት የምንችለው እንዴት ነው?

ሰዎች ምሥራቹን መስማት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

ሰዎች ለሚያምኑበት ነገር መሠረት የሆናቸውን ማስረጃ መለስ ብለው እንዲያስቡ እርዷቸው

4. አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አምላክን በተመለከተ ምን ውሸት ይነገራቸዋል?

4 አባትህ አንተንም ሆነ መላ ቤተሰቡን ጥሎ የሄደ ሰው እንደሆነ ሰማህ እንበል። እሱን የሚያውቁት ሰዎች የማይቀረብ፣ ድብቅና ጨካኝ ሰው እንደሆነ ያወራሉ። ይባስ ብሎም አንዳንዶች አባትህ በሕይወት ስለሌለ እሱን ለማግኘት መሞከር ከንቱ ልፋት እንደሆነ አሳምነውሃል። ብዙ ሰዎች አምላክን በተመለከተ ከዚህ የማይተናነስ ነገር ተነግሯቸዋል። አምላክ ሚስጥራዊ እንደሆነ፣ ስለ እሱ ማወቅ እንደማይቻል ወይም ጨካኝ እንደሆነ የሚገልጽ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች አምላክ ክፉ ሰዎችን በአንድ የማሠቃያ ቦታ ለዘላለም እንደሚቀጣ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ የተፈጥሮ አደጋ የሚያስከትለው መከራ የአምላክ እጅ እንዳለበት ያስተምራሉ። እንዲህ ዓይነት ክስተት ጥሩና መጥፎ ሰዎችን አንድ ላይ የሚጨርስ ቢሆንም ከአምላክ የመጣ ቅጣት ነው ተብሎ ይነገራል።

እውነትን እንዲቀበሉ አእምሯቸውንና ልባቸውን ክፈቱ

5, 6. የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብና የውሸት ትምህርቶች በሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረዋል?

5 ሌሎች ደግሞ አምላክ የለም ብለው አስረግጠው ይናገራሉ። በዚህ ረገድ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ እንመልከት። የዚህ ንድፈ ሐሳብ አቀንቃኞች የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ሳይኖር ሕይወት እንዲሁ እንደተገኘ ይናገራሉ። ፈጣሪ የለም የሚል አቋም አላቸው። እንዲያውም አንዳንዶች ሰው አንድ ዓይነት የእንስሳ ዝርያ ነው፤ በመሆኑም አንድ ሰው እንስሳዊ ተግባር ቢፈጽም ሊደንቀን አይገባም ብለው እስከ መናገር ደርሰዋል። ጉልበት ያለው ደካማውን በጭካኔ የሚገዛው የተፈጥሮ ሕግ አስገድዶት ነው ብለው ይከራከራሉ። በመሆኑም ብዙዎች የፍትሕ መጓደል ምንጊዜም አብሮን የሚኖር ነገር እንደሆነ ማመናቸው ምንም አያስደንቅም። ከዚህ የተነሳ በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እውነተኛ ተስፋ የላቸውም።

6 የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብና በውሸት ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶች የሰው ዘር በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ለደረሰበት ሰቆቃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሮም 1:28-31፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) እነዚህ የሰው ፈጠራ የሆኑ ትምህርቶች እውነተኛና ዘላቂ ምሥራች አላመጡም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ሰዎች ‘አእምሯቸው እንዲጨልም እንዲሁም ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት እንዲርቁ’ አድርገዋል። (ኤፌ. 4:17-19) ከዚህም በተጨማሪ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብና የሐሰት ትምህርቶች ሰዎች አምላክ የላከውን ምሥራች እንዳይቀበሉ እንቅፋት ሆነዋል።—ኤፌሶን 2:11-13ን አንብብ።

ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ መድረስ እንዲችሉ ጉዳዩን እንዲያመዛዝኑ እርዷቸው

7, 8. ሰዎች ምሥራቹን በተሟላ መንገድ መረዳት የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው?

7 ሰዎች ከአምላክ ጋር እርቅ ለመፍጠር በመጀመሪያ ይሖዋ መኖሩንና ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚያደርጉን አጥጋቢ ምክንያቶች መኖራቸውን በእርግጠኝነት ማመን ይኖርባቸዋል። ፍጥረትን እንዲመረምሩ በማበረታታት ይህን እውቀት እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንችላለን። ሰዎች ወገናዊ አመለካከት ሳይዙ ፍጥረትን በሚያጤኑበት ጊዜ የአምላክን ጥበብና ኃይል ይማራሉ። (ሮም 1:19, 20) ሰዎች ታላቁ ፈጣሪ ስላከናወናቸው ሥራዎች ሲያስቡ ለእሱ ጥልቅ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርባቸው ለመርዳት በምናደርገው ጥረት ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች በሚሉት ብሮሹሮች መጠቀም እንችላለን። ይሁንና ተፈጥሮን በማየት ብቻ እንማር ካልን በሕይወት ዙሪያ ለሚነሱ አሳሳቢ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አንችልም፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? አምላክ ለእኔ በግለሰብ ደረጃ ያስብልኛል?

 8 ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማው የሚገልጸውን ምሥራች ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲያገኙ ሰዎችን መርዳት መቻል እንዴት ያለ መብት ነው! ሆኖም የአድማጮቻችንን ልብ መንካት እንድንችል ትክክለኛ መረጃዎችን በማካፈል ብቻ መወሰን አይኖርብንም፤ ይልቁንም ልናሳምናቸው ይገባል። (2 ጢሞ. 3:14) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የማሳመን ችሎታችንን ማሻሻል እንችላለን። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ስኬታማ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ይጠቀም ስለነበር ነው። የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ስኬታማ የሆኑ ወንጌላውያን ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ይጠቀማሉ

9. ሰዎችን በመንፈሳዊ መርዳት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

9 የወንጌላዊነቱን ሥራ ስናከናውን እንደ ኢየሱስ በጥያቄዎች መጠቀም የሚኖርብን ለምንድን ነው? እስቲ ይህን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር፦ ሐኪምህ ለአንተ የሚያበስረው ምሥራች እንዳለው ነገረህ። አንድ ከባድ ቀዶ ሕክምና ካደረግክ ከበሽታህ እንደምትድን ገለጸልህ። አንተም ታምነው ይሆናል። ሆኖም ይህን ተስፋ የሰጠህ ስለ ጤንነትህ አንድም ጥያቄ ከመጠየቁ በፊት ቢሆንስ? እንዲህ ከሆነ በእሱ ላይ እምነት የመጣልህ ጉዳይ አጠራጣሪ ይሆናል። ሐኪሙ ምንም ያህል ችሎታ ቢኖረው ስለ ጤንነትህ ሊጠይቅህና ምን እንደሚሰማህ ስትናገር ሊያዳምጥህ ይገባል፤ ጠቃሚ እርዳታ ሊሰጥህ የሚችለው ከዚህ በኋላ ነው። በተመሳሳይ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች እንዲቀበሉ መርዳት የምንፈልግ ከሆነ ውጤታማ የሆኑ ጥያቄዎች የመጠየቅ ችሎታ ማዳበር ይኖርብናል። ልንረዳቸው የምንችለው መንፈሳዊ ሁኔታቸውን በተመለከተ ግልጽ መረጃ ካገኘን ብቻ ነው።

የአድማጮቻችንን ልብ መንካት እንድንችል ልናሳምናቸው ይገባል

10, 11. የኢየሱስን የማስተማሪያ ዘዴ በመከተል ምን ማከናወን እንችላለን?

10 ኢየሱስ የታሰበባቸው ጥያቄዎች ማቅረብ አስተማሪው ስለ ተማሪው እንዲያውቅ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ አድማጩ በውይይቱ እንዲሳተፍ እንደሚያደርግ ያውቅ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለ ትሕትና ማስተማር በፈለገበት ጊዜ በመጀመሪያ ስለ ጉዳዩ ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። (ማር. 9:33) ኢየሱስ፣ ከአንድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያሉትን መመሪያዎች አመዛዝኖ እንዲናገር ጴጥሮስን ለማስተማር የተለያዩ ምርጫዎች ያሉት ጥያቄ አቅርቦለታል። (ማቴ. 17:24-26) በሌላ ወቅት ደግሞ በደቀ መዛሙርቱ ልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ማወቅ በፈለገ ጊዜ በርካታ የአመለካከት ጥያቄዎች ጠይቋቸዋል። (ማቴዎስ 16:13-17ን አንብብ።) ኢየሱስ ጥያቄዎች በመጠየቅና ማብራሪያ በመስጠት ትክክለኛ መረጃዎችን ከማካፈል የበለጠ ነገር አድርጓል። የሰዎችን ልብ መንካት በመቻሉ ከምሥራቹ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስዱ አነሳስቷቸዋል።

11 የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ውጤታማ የሆኑ ጥያቄዎች የምንጠቀም ከሆነ ቢያንስ ሦስት ነገሮችን ማከናወን እንችላለን። ሰዎችን በተሻለ ሁኔታ መርዳት የምንችልበትን መንገድ እንገነዘባለን፣ ውይይታችንን ለማስቆም የሚጥሩ ሰዎች አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ እንችላለን እንዲሁም ትሑት የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን እንዴት መጥቀም እንደሚችሉ እናስተምራለን። በጥያቄዎች በመጠቀም እንዴት ጥሩ ውጤት ማግኘት እንደምንችል የሚያሳዩ ሦስት ሁኔታዎችን እንመልከት።

12-14. አንድ ልጅ ምሥራቹን በልበ ሙሉነት እንዲናገር እንዴት መርዳት ይቻላል? ምሳሌ ስጥ።

12 የመጀመሪያው ሁኔታ፦ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ልጅህ በፍጥረት ላይ ስላለው እምነት አብሮት ከሚማር ልጅ ጋር ሲነጋገር ምን ብሎ ማስረዳት እንደሚችል ቢጠይቅህ ምን ታደርጋለህ? ምሥራቹን በሙሉ ልብ መናገር እንዲችል ልጅህን መርዳት እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ልጅህን ከመውቀስ ወይም ወዲያውኑ ምክር ከመስጠት ይልቅ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለምን አንዳንድ የአመለካከት ጥያቄዎች አትጠይቀውም? እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

 13 የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች ከተባለው ብሮሹር ላይ የተወሰኑ ክፍሎችን ከልጅህ ጋር ካነበብክ በኋላ ትኩረቱን የሳቡት አሳማኝ ነጥቦች የትኞቹ እንደሆኑ ልትጠይቀው ትችላለህ። በፈጣሪ መኖር እንዲያምንና የአምላክን ፈቃድ እንዲያደርግ ያነሳሱትን የግል ምክንያቶቹን መለስ ብሎ እንዲያስብባቸው አበረታታው። (ሮም 12:2) ልጅህ እሱን ያሳመኑት ምክንያቶች አንተን ካሳመኑህ ምክንያቶች ጋር የግድ አንድ ዓይነት መሆን አለባቸው ብሎ ማሰብ እንደሌለበት ንገረው።

14 ልጅህ አብሮት ከሚማር ልጅ ጋር ሲነጋገር አሁን ያሳየኸውን ዘዴ መጠቀም እንደሚችል አስረዳው። ይህም አንዳንድ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ካሳየው በኋላ የአመለካከት ወይም መሪ ጥያቄዎች ሊጠይቀው ይችላል ማለት ነው። ለአብነት ያህል፣ ልጅህ የሕይወት አመጣጥ በተባለው ብሮሹር ገጽ 21 ላይ የሚገኘውን ሣጥን የክፍል ጓደኛውን ሊያስነብበው ይችላል። ከዚያም “የዲ ኤን ኤ መረጃ የመያዝ አቅም በዚህ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ዘመንም እንኳ አቻ ሊገኝለት አልቻለም መባሉ ትክክል ነው?” ብሎ ሊጠይቀው ይችላል። የክፍል ጓደኛው አዎ ብሎ ይመልስ ይሆናል። ልጅህ በመቀጠል እንዲህ ብሎ ሊጠይቀው ይችላል፦ “የኮምፒውተር ባለሙያዎች የሆኑ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ነገር ማድረግ ካልቻሉ ማሰብ የማይችል ቁስ አካል ራሱን ችሎ እንዴት እንዲህ ማድረግ ይችላል?” ልጅህ ስለ እምነቱ ከሌሎች ጋር ሲወያይ ይበልጥ ተማምኖ መናገር እንዲችል በየጊዜው አብረኸው ልምምድ አድርግ። ልጅህ ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲጠቀም ካሠለጠንከው የወንጌላዊነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ትረዳዋለህ።

15. በአምላክ መኖር የማያምንን ግለሰብ ለመርዳት ስንጥር ጥያቄዎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሁለተኛው ሁኔታ፦ የስብከቱን ሥራ ስናከናውን አንዳንድ ጊዜ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ያጋጥሙናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው አምላክ የለም የሚል እምነት እንዳለው ሊነግረን ይችላል። በዚህ ጊዜ ውይይቱን ከማቆም ይልቅ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ከያዘ ምን ያህል ጊዜ እንደሆነውና እንዲህ ያለ አቋም እንዲይዝ ያደረገው ምን እንደሆነ በአክብሮት ልንጠይቀው እንችላለን። መልሱን ካዳመጥንና ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠቱ ካመሰገንነው በኋላ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ ማስረጃ የሚያቀርብ ጽሑፍ ማንበብ  ምንም ጥቅም የለውም ብሎ ያስብ እንደሆነ ልንጠይቀው እንችላለን። የቤቱ ባለቤት አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ ፍላጎት ካለው እንዲህ ዓይነቱን ማስረጃ ማየት አልፈልግም ማለት ምክንያታዊነት የጎደለው አስተሳሰብ እንደሆነ ሊናገር ይችላል። ከዚያም ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የሚለውን ወይም ደግሞ የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹር ልናበረክትለት እንችላለን። በዘዴና በደግነት የሚቀርብ ጥያቄ አንድ ሰው ልቡን ለምሥራቹ እንዲከፍት የሚያስችል ቁልፍ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።

16. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከሚጠናው ጽሑፍ ላይ እያነበበ በሚሰጠው መልስ መርካት የሌለብን ለምንድን ነው?

16 ሦስተኛው ሁኔታ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ተማሪው መልሱን ከመጽሐፉ ላይ እንዳለ ደግሞ ሲናገር ዝም ብለን እናልፈው ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችን የተማሪውን መንፈሳዊ እድገት ሊገታ ይችላል። ለምን? በጉዳዩ ላይ አስቦበት ከመመለስ ይልቅ የመጽሐፉን ሐሳብ ደግሞ የሚናገር ተማሪ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሥር ይሰዳል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። የስደት ንዳድ ሲደርስበት በቀላሉ እንደሚጠወልግ ተክል ይሆናል። (ማቴ. 13:20, 21) ይህ እንዳይደርስበት ለማድረግ ተማሪውን ስለሚማረው ነገር ምን እንደሚሰማው ልንጠይቀው ያስፈልጋል። የቀረቡትን ሐሳቦች ያምንባቸው እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ከዚህ በላይ ደግሞ በቀረበው ሐሳብ ለምን እንደተስማማ ወይም እንዳልተስማማ እንዲናገር ጠይቁት። ከዚያም የጥቅሶቹን ሐሳብ እንዲያገናዝብ እርዱት፤ በዚህ መንገድ እሱ ራሱ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ታስችሉታላችሁ። (ዕብ. 5:14) ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ የምንጠቀም ከሆነ የምናስተምረው ግለሰብ በእምነት ሥር የመስደዱ አጋጣሚ የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ ሰዎች እሱን ተስፋ ለማስቆረጥ ወይም ለማሳሳት የሚያደርጉትን ጥረት የመቋቋም አቅም ይኖረዋል። (ቆላ. 2:6-8) ወንጌላውያን እንደመሆናችን መጠን ኃላፊነታችንን ለመወጣት ሌላስ ልናደርገው የምንችለው ምን ነገር አለ?

ስኬታማ የሆኑ ወንጌላውያን እርስ በርስ ይረዳዳሉ

17, 18. ከአንድ አስፋፊ ጋር አገልግሎት ስንወጣ መረዳዳት የምንችለው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ ለስብከቱ ሥራ ልኳቸው ነበር። (ማር. 6:7፤ ሉቃስ 10:1) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በምሥራቹ ሥራ ከጎኑ ተሰልፈው ብዙ የደከሙ የሥራ ባልደረቦቹን’ ጠቅሷል። (ፊልጵ. 4:3) ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ካለው ከዚህ አሠራር ጋር በሚስማማ መንገድ በ1953 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ለሌሎች የአገልግሎት ሥልጠና መስጠት ጀመሩ።

18 ከአንድ ክርስቲያን ጋር አገልግሎት ስትወጡ መረዳዳት የምትችሉት እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 3:6-9ን አንብብ።) የአገልግሎት ጓደኛህ ጥቅስ ሲያነብ መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ ተከታተል። የአገልግሎት ጓደኛህና የቤቱ ባለቤት ሲነጋገሩ ሁለቱንም በትኩረት አዳምጥ። ውይይቱን በትኩረት መከታተልህ የተቃውሞ ሐሳብ ከተነሳ እንደ አስፈላጊነቱ የአገልግሎት ጓደኛህን ለመርዳት ዝግጁ እንድትሆን ያስችልሃል። (መክ. 4:12) ይሁን እንጂ አንድ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፦ የአገልግሎት ጓደኛህ ሐሳቡን በጥሩ ሁኔታ እየገለጸ ባለበት ወቅት ጣልቃ ገብተህ ላለማቋረጥ ስሜትህን ተቆጣጠር። ጣልቃ ገብተህ በጦፈ ስሜት መናገርህ ጓደኛህን ተስፋ ሊያስቆርጥ፣ የቤቱን ባለቤት ደግሞ ግራ ሊያጋባ ይችላል። እርግጥ የውይይቱ ተሳታፊ መሆን ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ይሁንና ሐሳብ በምትሰጥበት ጊዜ ብዙ ላለመናገር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። ሐሳብህን በአጭሩ ከገለጽክ በኋላ የአገልግሎት ጓደኛህ ውይይቱን እንዲቀጥል አድርግ።

19. የትኛውን ጉዳይ ማስታወሳችን ተገቢ ነው? ለምንስ?

19 አንተና የአገልግሎት ጓደኛህ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት በምትሄዱበት ጊዜ መረዳዳት የምትችሉት እንዴት ነው? አቀራረባችሁን ማሻሻል ስለምትችሉባቸው መንገዶች ለምን አትወያዩም? በክልላችሁ ውስጥ ስላሉት ሰዎች ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ላለመናገር ተጠንቀቁ። በተጨማሪም ሌሎች ወንጌላውያን ስላላቸው የባሕርይ ድክመት በማውራት ከመጠመድ ራቁ። (ምሳሌ 18:24 NW) ሁላችንም የሸክላ ዕቃዎች መሆናችንን ማስታወሳችን ተገቢ ነው። ይሖዋ ምሥራቹን የመስበክ ውድ ሀብት ለእኛ በአደራ በመስጠት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ደግነት አሳይቶናል። (2 ቆሮንቶስ 4:1, 7ን አንብብ።) እንግዲያው ሁላችንም የወንጌላዊነት ኃላፊነታችንን ለመወጣት አቅማችን የሚፈቅደውን በማድረግ ይህን ውድ ሀብት በአድናቆት እንያዝ።