በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ትዳራችሁን አጠናክሩ

ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ትዳራችሁን አጠናክሩ

“ባግባቡ [“በተገቢው ጊዜ፣” NW] የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው።”—ምሳሌ 25:11

1. አንዳንድ ባለትዳሮች ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው የረዳቸው እንዴት ነው?

በካናዳ የሚኖር አንድ ወንድም “ከሌላ ሰው ጋር ጊዜ ከማሳልፍ ይልቅ ከባለቤቴ ጋር ጊዜ ባሳልፍ እመርጣለሁ። ያስደሰተኝን ነገር ለሚስቴ ስነግራት ደስታዬ በእጥፍ ይጨምራል፤ ሐዘኔን ሳካፍላት ደግሞ ይቀለኛል” በማለት ተናግሯል። በአውስትራሊያ የሚኖር አንድ ባል እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አብረን በኖርንባቸው 11 ዓመታት ከባለቤቴ ጋር ሳልነጋገር አንድም ቀን አልፎ አያውቅም። እኔም ሆንኩ እሷ የትዳራችንን ጥንካሬ በተመለከተ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ወይም ስጋት ተሰምቶን አያውቅም። ለዚህ አስተዋጽኦ ያበረከተው ዋናው ነገር ምንጊዜም ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችን ነው።” በኮስታ ሪካ የምትኖር አንዲት እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችን ትዳራችንን ከማጠንከሩም በላይ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ አድርጎናል፣ ከፈተናዎች ጠብቆናል፣ አንድ እንድንሆን ረድቶናል እንዲሁም ፍቅራችን እንዲያድግ አድርጓል።”

2. ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 አንተና የትዳር ጓደኛህ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ታደርጋላችሁ ወይስ ትርጉም ያለው ጭውውት ማድረግ ይከብዳችኋል? እርግጥ ነው፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ትዳር ፍጽምና የሌላቸው ሁለት ሰዎች ጥምረት ሲሆን እነዚህ ሰዎች ባሕላቸውንና አስተዳደጋቸውን የሚያንጸባርቅ ጠባይን ጨምሮ የተለያየ ስብዕና ያላቸው ናቸው። (ሮም 3:23) በተጨማሪም ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተለያየ ሊሆን ይችላል። በትዳር ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ጆን ጎትመን እና ናን ሲልቨር “ዘላቂ የሆነ ዝምድና ለመመሥረት ድፍረት፣ ቆራጥነትና ቻይነት ወሳኝ ነገሮች ናቸው” በማለት የተናገሩት ያለ ምክንያት አይደለም።

3. ባልና ሚስቶች ትዳራቸውን ለማጠናከር የረዳቸው ምንድን ነው?

3 በእርግጥም የተሳካ ትዳር የብዙ ድካም ውጤት ነው። ይሁንና ይህ ነው የማይባል ደስታ ያስገኛል። እርስ በርሳቸው የሚዋደዱ ባልና ሚስት በደስታ መኖር ይችላሉ። (መክ. 9:9) ፍቅር የሰፈነበትን የይስሐቅንና የርብቃን ትዳር እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ዘፍ. 24:67) ባልና ሚስት ሆነው የተወሰኑ ጊዜያት ካለፉ በኋላ እንኳ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር እየከሰመ እንደሄደ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ አናገኝም። በዛሬው  ጊዜ ስላሉ በርካታ ባለትዳሮችም ተመሳሳይ ነገር መናገር ይቻላል። ሚስጥሩ ምንድን ነው? እንዲህ ያሉ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን አመለካከትና ስሜት በግልጽ ሆኖም በደግነት ማካፈል ለምደዋል፤ ለዚህ የረዳቸው ደግሞ ማስተዋል፣ ፍቅር፣ ጥልቅ አክብሮት እንዲሁም ትሕትና ማዳበራቸውና ማንጸባረቃቸው ነው። ከዚህ ቀጥሎ እንደምንመለከተው እነዚህን አስፈላጊ ባሕርያት በትዳር ውስጥ ማንጸባረቅ ከተቻለ የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግበት መስመር ምንጊዜም ክፍት ይሆናል።

አስተዋይ ሁኑ

4, 5. አንድ ባልና ሚስት አስተዋይ መሆናቸው በደንብ እንዲግባቡ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 ምሳሌ 16:20 (NW) “አንድን ነገር ጠለቅ ብሎ የሚያስተውል ሰው ስኬታማ ይሆናል” ይላል። ይህ ሐሳብ ከትዳርና ከቤተሰብ ሕይወት ጋር በተያያዘ በእጅጉ ይሠራል። (ምሳሌ 24:3ን አንብብ።) ማስተዋልና ጥበብ የሚገኝበት ከሁሉ የተሻለ ምንጭ የአምላክ ቃል ነው። ዘፍጥረት 2:18 እንደሚገልጸው አምላክ ሴትን የሠራት የወንድ ረዳት ወይም ማሟያ እንድትሆን እንጂ በሁሉም ነገር እሱን እንድትመስል አይደለም። ሐሳቧን የምትገልጽበት መንገድ እሷ ያላትን ድርሻ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። እርግጥ ነው፣ ሰው ከሰው ይለያያል፤ በጥቅሉ ሲታይ ግን ሴቶች ስለ ስሜታቸው፣ ስለ ሰዎችና ከሌሎች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ማውራት ይወዳሉ። ሴቶች ሞቅ ባለ ስሜት ልብ ለልብ መነጋገር ያስደስታቸዋል፤ እንዲህ ያለው ሁኔታ እንደሚወደዱ ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋል። በአንጻሩ ደግሞ በርካታ ወንዶች ስለ ስሜታቸው ለማውራት ብዙም አይነሳሱም፤ ከዚህ ይልቅ ስለተለያዩ ክስተቶች እንዲሁም ስለ ችግሮችና መፍትሔያቸው ማውራት ይቀናቸዋል። ደግሞም ወንዶች የመከበር ፍላጎት አላቸው።

5 በብሪታንያ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ተናግሬ እስክጨርስ ድረስ ከመስማት ይልቅ ላነሳኋቸው ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ይቸኩላል። ይህ ደግሞ ያበሳጨኛል፤ እኔ የምፈልገው አብሮኝ ሻይ እየጠጣ ስሜቴን እንዲጋራ ብቻ ነው።” አንድ ባል እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔና ሚስቴ እንደተጋባን አካባቢ ለችግሯ ወዲያውኑ መፍትሔ የመፈለግ ዝንባሌ ነበረኝ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ እሷ የምትፈልገው ሰሚ ጆሮ እንደሆነ ተገነዘብኩ።” (ምሳሌ 18:13፤ ያዕ. 1:19) አስተዋይ የሆነ ባል የሚስቱን ስሜት ግምት ውስጥ የሚያስገባ ከመሆኑም ሌላ እንደ ስሜቷ ለመያዝ ጥረት ያደርጋል። እንዲሁም ለሐሳቧና ለስሜቷ ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጥ በመግለጽ ያጽናናታል። (1 ጴጥ. 3:7) እሷ ደግሞ የእሱን አመለካከት ለመረዳት ጥረት ታደርጋለች። አንድ ባልና ሚስት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድርሻቸውን የሚገነዘቡ፣ የሚያደንቁና የሚወጡ ከሆነ ጥምረታቸው ያማረ ይሆናል። ከዚህም በላይ ጥበብ ያለበትና ሚዛናዊ የሆነ ውሳኔ ለማድረግ እንዲሁም ውሳኔያቸውን በተግባር ለማዋል በአንድነት መሥራት ይችላሉ።

6, 7. (ሀ) በመክብብ 3:7 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ባለትዳሮች አስተዋይ እንዲሆኑ ሊረዳቸው የሚችለው በምን መንገድ ነው? (ለ) አንዲት ሚስት አስተዋይ መሆኗን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? አንድ ባልስ ምን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል?

6 ከዚህ በተጨማሪ አስተዋይ የሆኑ ባልና ሚስት ‘ለዝምታ ጊዜ እንዳለውና ለመናገር ጊዜ’ እንዳለው ይረዳሉ። (መክ. 3:1, 7) በትዳር ዓለም ለአሥር ዓመት የቆየች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንድን ጉዳይ ማንሳት ተገቢ የማይሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ መገንዘብ ችያለሁ። ባለቤቴ ሥራ እንደበዛበት ወይም የተለያዩ ኃላፊነቶች እንደተደራረቡበት ካስተዋልኩ ጉዳዩን የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ማንሳት እመርጣለሁ። በዚህም የተነሳ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ መግባባት ችለናል።” ከዚህም ሌላ አስተዋይ ሚስቶች በደንብ ታስቦበት “ባግባቡ [“በተገቢው ጊዜ፣” NW] የተነገረ ቃል” የሚያስደስት እንደሆነ ስለሚገነዘቡ ንግግራቸው አሳቢነት የተሞላበት ነው።—ምሳሌ 25:11ን አንብብ።

ትናንሽ ነገሮች በትዳር ውስጥ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ

7 አንድ ክርስቲያን ባል፣ ሚስቱ የምትናገረውን በመስማት ብቻ ሳይወሰን የራሱን ስሜት በግልጽ አውጥቶ ለመናገር ጥረት በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል። ለ27 ዓመታት በትዳር ዓለም የኖረ አንድ ሽማግሌ “በልቤ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ለሚስቴ ማካፈልን ለመልመድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጠይቆብኛል” ሲል ተናግሯል። ካገባ 24 ዓመት የሆነው አንድ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “‘ጉዳዩን ካላነሳሁት ተረስቶ ይቀራል’ በሚል አስተሳሰብ አንዳንድ ጉዳዮችን አምቄ ለመያዝ እሞክር ነበር። ሆኖም ስሜቴን መግለጼ የድክመት ምልክት እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። የውስጤን ገልጬ ለማውራት ጥረት ሳደርግ ትክክለኛ ቃላት መጠቀምና በተገቢው መንገድ መናገር እንድችል እጸልያለሁ። ከዚያም በረጅሙ ከተነፈስኩ በኋላ ማውራት እጀምራለሁ።” በተጨማሪም ትክክለኛውን ጊዜና ቦታ መምረጥ ጠቃሚ ነው፤ ምናልባትም ባልና ሚስቱ ለብቻቸው ሆነው የዕለት ጥቅሱን ሲወያዩ ወይም መጽሐፍ  ቅዱስ ሲያነቡ አጋጣሚውን ይህን ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

8. ክርስቲያን ባለትዳሮች ትዳራቸውን ስኬታማ ለማድረግ እንዲጥሩ የሚያነሳሳ ምን ተጨማሪ ምክንያት አላቸው?

8 ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ወደ ይሖዋ መጸለያቸው በጣም አስፈላጊ ነው፤ ደግሞም የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉበትን መንገድ ለማሻሻል ልባዊ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የነበሩትን ልማዶች መለወጥ ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው። ሆኖም አንድ ባልና ሚስት ይሖዋን የሚወዱ፣ መንፈሱን እንዲሰጣቸው የሚጠይቁና ጋብቻቸውን ቅዱስ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ ከሆነ ከብዙዎች በተለየ ሁኔታ ትዳራቸው የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ እንዲጥሩ ያነሳሳቸዋል። ካገባች 26 ዓመት የሆናት አንዲት ሚስት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “እኔና ባለቤቴ ይሖዋ ለትዳር ያለውን አመለካከት በቁም ነገር ስለምንመለከት መለያየት የሚለው ሐሳብ ጨርሶ ወደ አእምሯችን አይመጣም። ይህም ችግሮች ሲነሱ አንድ ላይ ሆነን በመወያየት መፍትሔ ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ አነሳስቶናል።” እንዲህ ያለ ታማኝነትና ለአምላክ ያደሩ መሆን ይሖዋን የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል።—መዝ. 127:1

ፍቅራችሁ ይደግ

9, 10. አንድ ባልና ሚስት ፍቅራቸው እየተጠናከረ እንዲሄድ ምን ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ?

9 “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የሆነው ፍቅር በትዳር ውስጥ በጣም አስፈላጊ ባሕርይ ነው። (ቆላ. 3:14) ታማኝ የሆኑ ባልና ሚስት ደስታውንም ሆነ ችግሩን እየተጋሩ ተደጋግፈው ሲኖሩ በመካከላቸው ያለው እውነተኛ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። በተጨማሪም ይበልጥ እየተቀራረቡ የሚሄዱ ከመሆኑ ሌላ አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ በጣም አስደሳች ይሆንላቸዋል። እንዲህ ያሉ ትዳሮች የሚጠናከሩት በመገናኛ ብዙኃን እንደሚገለጸው አልፎ አልፎ ትላልቅ ነገሮችን በማድረግ ብቻ ሳይሆን በርካታ ትናንሽ ነገሮችን በማድረግ ነው፤ ለምሳሌ ማቀፍ፣ ደግነት የተሞላበት አስተያየት መስጠት፣ አሳቢነት የሚንጸባረቅበት አካላዊ መግለጫና ፍቅርን የሚገልጽ ፈገግታ ማሳየት፣ ወይም “ውሎ እንዴት ነበር?” ብሎ ከልብ በመነጨ ስሜት መጠየቅ ይቻላል። እንዲህ ያሉ ትናንሽ ነገሮች ማድረግ በትዳር ውስጥ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ለ19 ዓመት በትዳር አስደሳች ሕይወት ያሳለፉ አንድ ባልና ሚስት በቀኑ ውስጥ “ደህንነታቸውን ለመጠያየቅ ያህል” እንደሚደዋወሉ ወይም የጽሑፍ መልእክት እንደሚላላኩ ባልየው ገልጿል።

10 በተጨማሪም ፍቅር አንድ ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላውን ባሕርይ ለማወቅ ጥረት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። (ፊልጵ. 2:4) ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ እርስ በርስ በሚገባ መተዋወቃቸው ፍቅራቸው እያደገ እንዲሄድ ይረዳቸዋል። ስኬታማ ትዳር ባለበት አይቆምም፤ ከዚህ ይልቅ በጊዜ ሂደት ይበልጥ አስደሳች እየሆነና እየጠነከረ ይሄዳል። በመሆኑም ያገባህ ከሆንክ ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬን ምን ያህል አውቃታለሁ? ስሜቷንና አመለካከቷን እረዳላታለሁ? መጀመሪያውኑም እንድወዳት ባደረጉኝ  ባሕርያት ላይ በማሰላሰል ስለ ትዳር ጓደኛዬ ምን ያህል አስባለሁ?’

እርስ በርስ ተከባበሩ

11. ለተሳካ ትዳር መከባበር ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? አብራራ።

11 ደስታ የሰፈነባቸው ትዳሮችም እንኳ ሙሉ በሙሉ ከችግር ነፃ አይደሉም፤ ደግሞም የሚዋደዱ ባልና ሚስቶች በሁሉም ነገር ይግባባሉ ማለት አይቻልም። አብርሃምና ሣራ ያልተግባቡባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዘፍ. 21:9-11) ይሁንና በመካከላቸው ያለው ልዩነት ግንኙነታቸውን አላበላሸባቸውም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳቸው ሌላውን በአድናቆትና በአክብሮት ይይዙ ስለነበር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ሣራን ሲያነጋግራት “እባክሽ” የሚለውን ቃል ይጠቀም ነበር። (ዘፍ. 12:11, 13 NW) እሷ ደግሞ አብርሃምን እንደ ‘ጌታዋ’ በመቁጠር ትታዘዘው ነበር። (ዘፍ. 18:12) ባልና ሚስቶች እርስ በርሳቸው የማይከባበሩ ከሆነ ይህ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ በአነጋገራቸው ወይም በድምፃቸው ቃና ይገለጻል። (ምሳሌ 12:18) የችግሩን መንስኤ አውቀው መፍትሔ ካልፈለጉለት ትዳራቸው በአሳዛኝ ሁኔታ ሊደመደም ይችላል።—ያዕቆብ 3:7-10, 17, 18ን አንብብ።

12. አዲስ ተጋቢዎች አክብሮት በተሞላበት መንገድ የመነጋገር ልማድ ለማዳበር ልዩ ጥረት ማድረግ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

12 በተለይ አዲስ ተጋቢዎች ንግግራቸው ደግነትና አክብሮት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው፤ ይህም በነፃነትና በሐቀኝነት የሐሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል። አንድ ባል የቀድሞውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “የትዳር ሕይወት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አስደሳች ቢሆኑም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆኑ ይችላሉ። የሚስታችሁን ስሜት፣ ልማዶችና ፍላጎቶች ለመረዳት ጥረት በምታደርጉበትና እሷም ተመሳሳይ ጥረት በምታደርግበት ጊዜ ነገሮች ትንሽ ዘብረቅረቅ ሊሉ ይችላሉ! ይሁን እንጂ ምክንያታዊና ተጫዋች ከሆናችሁ እንዲሁም ሚዛናችሁን እንድትጠብቁ የሚያስችሏችሁን እንደ ትሕትና፣ ትዕግሥትና በይሖዋ መታመን ያሉ ባሕርያት የምታንጸባርቁ ከሆነ ግንኙነታችሁ እየተሻሻለ ይሄዳል።” ይህ አባባል ምንኛ እውነት ነው!

ልባዊ ትሕትና አሳዩ

13. ትሕትና ስኬታማ ለሆነና ደስታ ለሰፈነበት ትዳር ወሳኝ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው?

13 በትዳር ውስጥ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ በአትክልት ስፍራ መካከል ቀስ እያለ ከሚፈስ ጅረት ጋር ይመሳሰላል። “ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ” ይህ ጅረት መፍሰሱን እንዲቀጥል ቁልፍ ሚና ይጫወታል። (1 ጴጥ. 3:8) በትዳር ሕይወት ለ11 ዓመት የቆየ አንድ ወንድም “ትሕትና ቅራኔዎችን ለመፍታት የሚረዳ አቋራጭ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ባሕርይ ‘አጥፍቻለሁ፣ ይቅርታ’ እንድትሉ ይገፋፋችኋል” በማለት ተናግሯል። ለ20 ዓመት በትዳር ውስጥ  አስደሳች ሕይወት ያሳለፈ አንድ ሽማግሌ “አንዳንድ ጊዜ ‘እወድሻለሁ’ ከሚለው ቃል ይልቅ በጣም አስፈላጊው ‘ይቅርታ’ የሚለው ቃል ነው” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ትሕትናን ለማዳበር የሚረዳን አንዱ አቋራጭ መንገድ ጸሎት ነው። እኔና ባለቤቴ አብረን ወደ ይሖዋ መጸለያችን ፍጽምና እንደሚጎድለንና የአምላክ ጸጋ ተጠቃሚዎች እንደሆንን ያስታውሰናል። ይህን ማስታወሴ ለነገሮች ተገቢ አመለካከት እንዲኖረኝ ይረዳኛል።”

በትዳራችሁ ውስጥ ምንጊዜም ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ

14. ኩራት ትዳርን ሊያናጋ የሚችለው እንዴት ነው?

14 በአንጻሩ ደግሞ ኩራት ሰላም ከማደፍረስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። ኩራት የሐሳብ ልውውጥ እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራል፤ ምክንያቱም ይቅርታ የመጠየቅ ፍላጎትም ሆነ ወኔ ያሳጣል። ኩራት ያለበት ሰው በትሕትና “አጥፍቻለሁ፣ ይቅርታ” ከማለት ይልቅ ሰበብ አስባብ ይደረድራል። የራሱን ድክመት አምኖ በመቀበል ፋንታ የሌላውን ግለሰብ ስህተት ይለቃቅማል። በደል ሲደርስበት ሰላም እንዲሰፍን ከመጣር ይልቅ ይቀየማል፤ ምናልባትም ኃይለ ቃል በመናገር ወይም በማኩረፍ አጸፋውን ይመልሳል። (መክ. 7:9) አዎ፣ ኩራት ትዳርን ሊያቆረቁዝ ይችላል። ‘አምላክ ትዕቢተኞችን እንደሚቃወም፣ ለትሑታን ግን ጸጋን እንደሚሰጥ’ ማስታወስ ጠቃሚ ነው።—ያዕ. 4:6

15. በትዳር ጓደኛሞች መካከል ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ በኤፌሶን 4:26, 27 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጋቸው ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

15 በትዳር ውስጥ ኩራት ጨርሶ ሊታይ አይችልም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይህ ባሕርይ የሚታይብን ከሆነ ችግሩን ተገንዝበን ወዲያውኑ መፍትሔ ልንፈልግለት ይገባል። ጳውሎስ ክርስቲያን ባልደረቦቹን “ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ ዲያብሎስም ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት” ብሏቸዋል። (ኤፌ. 4:26, 27) የአምላክን ቃል አለመታዘዝ አላስፈላጊ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል። አንዲት እህት “እኔና ባለቤቴ በኤፌሶን 4:26, 27 ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ሳናደርግ የቀረንባቸው ጊዜያት አሉ። በእነዚህ ጊዜያት ሌሊቱን ያሳለፍኩት በጣም ተረብሼ ነበር!” በማለት በሐዘን ስሜት ተናግራለች። እርቅ ለመፍጠር በማሰብ ሳይውል ሳያድር በጉዳዩ ላይ መወያየት ምንኛ የተሻለ ነው! እርግጥ ነው፣ የትዳር ጓደኛሞች ቁጣቸው እስኪበርድ ድረስ አንዳቸው ለሌላው የተወሰነ ጊዜ መስጠት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በጥሩ መንፈስ መወያየት እንዲችሉ የይሖዋን እርዳታ በጸሎት መጠየቃቸውም ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ትሑት መሆን ያስፈልጋል፤ ትሕትና በራሳችሁ ላይ ሳይሆን በችግሩ ላይ እንድታተኩሩ ይረዳችኋል። በራሳችሁ ላይ የምታተኩሩ ከሆነ ግን ሁኔታውን ልታባብሱት ትችላላችሁ።—ቆላስይስ 3:12, 13ን አንብብ።

16. ባልና ሚስት በግለሰብ ደረጃ ላላቸው ጠንካራ ጎን ተገቢ አመለካከት እንዲኖራቸው ትሕትና ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?

16 ልክን ማወቅና ትሕትና ባልና ሚስቶች የትዳር ጓደኛቸው ባለው ጠንካራ ጎን ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሚስት ቤተሰቡን በእጅጉ የሚጠቅም ለየት ያለ ተሰጥኦ ይኖራት ይሆናል። ባለቤቷ ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ከሆነ ተሰጥኦዋን እንድትጠቀምበት ያበረታታታል እንጂ እንደተገዳደረችው ሆኖ አይሰማውም፤ ይህ ደግሞ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታትና እንደሚወዳት ያሳያል። (ምሳሌ 31:10, 28፤ ኤፌ. 5:28, 29) በተመሳሳይም ትሑትና ልኳን የምታውቅ ሚስት ልታይ ልታይ አትልም ወይም ባሏን አታንኳስስም። ደግሞም ሁለቱም “አንድ ሥጋ” ስለሆኑ አንዳቸውን የሚጎዳ ነገር ሌላውንም መጉዳቱ አይቀርም።—ማቴ. 19:4, 5

17. በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮች ደስተኞች እንዲሆኑና ለአምላክ ውዳሴ ማምጣት እንዲችሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

17 ትዳራችሁ እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ ወይም እንደ ይስሐቅና እንደ ርብቃ ትዳር እውነተኛ ደስታ የሰፈነበት፣ የዕድሜ ልክ ጥምረትና ለይሖዋ ውዳሴ የሚያመጣ እንዲሆን እንደምትፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ከሆነ አምላክ ለትዳር ያለውን አመለካከት በጥብቅ ተከተሉ። ማስተዋልና ጥበብ ለማግኘት የአምላክን ቃል አጥኑ። ስለ ትዳር ጓደኛችሁ በአድናቆት ስሜት በማሰብ ‘የያህ ነበልባል’ የሆነውን እውነተኛ ፍቅር አዳብሩ። (ማሕ. 8:6 NW) ትሕትናን ለማዳበር ከፍተኛ ጥረት አድርጉ። የትዳር ጓደኛችሁን በአክብሮት ያዙ። እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ትዳራችሁ ለእናንተም ሆነ በሰማይ ለሚኖረው አባታችሁ ደስታ ያስገኛል። (ምሳሌ 27:11) ካገባ 27 ዓመት የሆነው አንድ ባል ስለ ሚስቱ የተናገረውን ሐሳብ ትጋሩ ይሆናል፦ “ያለ እሷ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰብ አልችልም። ትዳራችን በየዕለቱ ይበልጥ እየተጠናከረ ሄዷል። ይህ ሊሆን የቻለው ይሖዋን ስለምንወድና ዘወትር የሐሳብ ልውውጥ ስለምናደርግ ነው።”