በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆችና ልጆች—በፍቅር የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ

ወላጆችና ልጆች—በፍቅር የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ

“ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።”—ያዕ. 1:19

1, 2. በጥቅሉ ሲታይ ወላጆችና ልጆች በመካከላቸው ስላለው ግንኙነት ምን ስሜት አላቸው? ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?

“ወላጆችህ ነገ እንደሚሞቱ በሆነ መንገድ ብታውቅ ኖሮ ዛሬ ከምንም በላይ ልትነግራቸው የምትፈልገው ነገር ምን ይሆን ነበር?” ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆች ይህ ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ወደ 95 በመቶ የሚሆኑት ልጆች በመካከላቸው ባሉት ችግሮች ወይም አለመግባባቶች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ወላጆቻቸውን “ይቅርታ አድርጉልኝ” እና “በጣም እወዳችኋለሁ” እንደሚሏቸው ተናግረዋል።—ፎር ፓረንትስ ኦንሊ በሾንቲ ፌልድሃን እና በሊሳ ራይስ የተዘጋጀ

2 በጥቅሉ ሲታይ ልጆች ወላጆቻቸውን ይወዳሉ፤ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ይወዳሉ። በተለይ በክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ ይህ ሁኔታ ጎልቶ ይታያል። ወላጆችና ልጆች እርስ በርስ የመቀራረብ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም አንዳንድ ጊዜ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ሊቸገሩ ይችላሉ። በሐቀኝነትና በግልጽ የሚነጋገሩ ቢሆኑም እንኳ አንዳንድ ርዕሶችን ከማንሳት የሚቆጠቡት ለምንድን ነው? በጥሩ ሁኔታ የሐሳብ ልውውጥ እንዳያደርጉ እንቅፋት የሚሆኑባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እንቅፋቶቹን እንዴት ማሸነፍ ይችላሉ?

ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችና አብሮ ጊዜ አለማሳለፍ የሐሳብ ልውውጥ ፀር ናቸው

የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ “ጊዜ ግዙ”

3. (ሀ) በርካታ ቤተሰቦች ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ተፈታታኝ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው? (ለ) በጥንቷ እስራኤል፣ ቤተሰቦች አብሮ ጊዜ የማሳለፍ ችግር ያልነበረባቸው ለምንድን ነው?

3 ብዙ ቤተሰቦች ትርጉም ባለው መንገድ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ በቂ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲህ ዓይነት ችግር አልነበረም። ሙሴ ለእስራኤላውያን አባቶች ይህን መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ለልጆችህም [የአምላክን ቃል] አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።” (ዘዳ. 6:6, 7) ልጆች ቤት ውስጥ ከእናታቸው ጋር አሊያም በእርሻ ቦታ ወይም በሥራ ቦታ ከአባታቸው ጋር ይውሉ ነበር። ልጆችና ወላጆች አብረው የሚሆኑበትም ሆነ የሚነጋገሩበት ሰፊ ጊዜ ያገኛሉ። በመሆኑም ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎቶች፣ ምኞቶችና ባሕርያት በሚገባ የማወቅ አጋጣሚ  ነበራቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ ልጆችም የወላጆቻቸውን ማንነት ማወቅ የሚችሉበት ጊዜና በቂ አጋጣሚ ያገኙ ነበር።

4. በዛሬው ጊዜ ብዙ ቤተሰቦች የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚቸገሩት ለምንድን ነው?

4 ዛሬ ግን ሁኔታዎች በጣም ተለውጠዋል! በአንዳንድ አገሮች ልጆች በሕፃንነታቸው፣ አንዳንድ ጊዜ ገና የሁለት ዓመት ልጅ እያሉ መዋዕለ ሕፃናት ይገባሉ። ብዙ አባቶችና እናቶች ከቤታቸው ውጭ ተቀጥረው ሥራ ይሠራሉ። ወላጆችና ልጆች አብረው በሚያሳልፏት ጥቂት ጊዜ ኮምፒውተር፣ ቴሌቪዥንና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ጊዜውን የሚጫረቷቸው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ እነዚህ ነገሮች ቅድሚያውን ይይዛሉ። በአመዛኙ ልጆችና ወላጆች ሕይወታቸውን የሚመሩት በየፊናቸው ነው፤ አይተዋወቁም ቢባል ይቀላል። ደግሞም የሐሳብ ልውውጥ አያደርጉም ሊባል የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

5, 6. አንዳንድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ሰፋ ያለ ጊዜ ‘መግዛት’ የቻሉት እንዴት ነው?

5 ከሌሎች ጉዳዮች ላይ ጊዜ ‘በመግዛት’ ከቤተሰባችሁ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ ትችላላችሁ? (ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።) አንዳንድ ቤተሰቦች ቴሌቪዥን በማየት ወይም ኮምፒውተር በመጠቀም ከሚያሳልፉት ጊዜ ጋር በተያያዘ ገደብ ለማውጣት ተስማምተዋል። አንዳንዶች ቢያንስ በቀን አንዴ አብረው ለመመገብ ጥረት ያደርጋሉ። የቤተሰብ አምልኮ ዝግጅት ደግሞ ወላጆችና ልጆች እርስ በርስ እንዲቀራረቡና ዘና ባለ መንፈስ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ ግሩም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል! በሳምንት አንድ ሰዓት ገደማ የሚሆን ጊዜ ለዚህ ዓላማ መመደብ ጥሩ ጅምር ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ልብ ለልብ መነጋገር የሚቻልበትን በር ክፍት ለማድረግ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ እንዲሳካ በየጊዜው በቋሚነት የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ልጃችሁ ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዱ በፊት የሚያበረታታ ቃል ጣል አድርጉ፣ በዕለቱ ጥቅስ ላይ ተወያዩ ወይም ከልጃችሁ ጋር አብራችሁ ጸልዩ። እንዲህ ማድረጋችሁ በውሎው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

6 አንዳንድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ሲሉ በአኗኗር ዘይቤያቸው ላይ የተወሰኑ ለውጦች ማድረግ ችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሎረ * ለዚሁ ዓላማ ስትል የሙሉ ጊዜ ሥራዋን ለቅቃለች።  እንዲህ ብላለች፦ “ጠዋት ላይ ሁላችንም ወደ ሥራና ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ተጣድፈን እንወጣ ነበር። ማታ ወደ ቤት ስመለስ ሞግዚቷ ልጆቹን ስለምታስተኛቸው ተኝተው ይጠብቁኛል። ሥራውን ማቆሜ አነስ ባለ ገንዘብ እንድንኖር አስገድዶናል፤ ሆኖም አሁን ልጆቼ ምን እንደሚያስቡና ምን ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ማወቅ እንደቻልኩ ይሰማኛል። በጸሎታቸው ላይ የሚጠቅሱትን ጉዳይ ሰምቼ መመሪያ፣ ማበረታቻና ትምህርት መስጠት ችያለሁ።”

‘ለመስማት የፈጠናችሁ ሁኑ’

7. ልጆችም ሆኑ ወላጆች የሚያሰሙት ተመሳሳይ ቅሬታ ምንድን ነው?

7 ፎር ፓረንትስ ኦንሊ የተባለው መጽሐፍ አዘጋጆች ለበርካታ ልጆች ቃለ ምልልስ ካደረጉ በኋላ ለሐሳብ ልውውጥ እንቅፋት የሚሆን ሌላም ነገር ጠቅሰዋል። “አብዛኞቹ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያሰሙት ዋናው ቅሬታ ‘ወላጆቻችን አይሰሙንም’ የሚል ነው” ብለዋል። ይሁንና ይህ አንደኛው ወገን ብቻ የሚያሰማው ቅሬታ አይደለም። ወላጆችም ብዙ ጊዜ ልጆቻቸውን በተመለከተ ተመሳሳይ ቅሬታ ያሰማሉ። የቤተሰብ አባላት የሐሳብ ልውውጥ መስመሩን ምንጊዜም ክፍት ለማድረግ እርስ በርሳቸው መደማመጥ፣ አዎ ከልብ መደማመጥ ይኖርባቸዋል።ያዕቆብ 1:19ን አንብብ።

8. ወላጆች ልጆቻቸውን ከልብ ማዳመጥ የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ሲናገሩ በእርግጥ ትሰሟቸዋላችሁ? ደክሟችሁ ባለበት ጊዜ ወይም ልጆቻችሁ የሚያወሩት ተራ ነገር መስሎ በሚታያችሁ ጊዜ ማዳመጥ ይከብዳችሁ ይሆናል። ይሁንና ለእናንተ ተራ ነገር መስሎ የታያችሁ ጉዳይ ለልጃችሁ አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ‘ለመስማት የፈጠኑ’ መሆን ሲባል ልጃችሁ የሚናገረውን ነገር በትኩረት ከማዳመጥ በተጨማሪ የሚናገርበትንም መንገድ በጥሞና መከታተል ማለት ነው። አንድ ልጅ የሚናገርበት የድምፅ ቃናና አካላዊ መግለጫው ምን እንደሚሰማው ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል። ጥያቄ መጠየቅም በጣም ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል” ይላል። (ምሳሌ 20:5) ጥንቃቄ የሚሹ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስታችሁ ከልጆቻችሁ ጋር በምትወያዩበት ጊዜ አስተዋይ መሆናችሁ እጅግ አስፈላጊ ነው።

9. ልጆች ወላጆቻቸውን ማዳመጥ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

9 እናንት ልጆች፣ ወላጆቻችሁን ትታዘዛላችሁ? የአምላክ ቃል “ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው” ይላል። (ምሳሌ 1:8) ወላጆቻችሁ እንደሚወዷችሁና ጥሩ ነገር እንደሚመኙላችሁ አትዘንጉ፤ በመሆኑም እነሱን መስማትና መታዘዝ ጥበብ ነው። (ኤፌ. 6:1) ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ሲኖርና እንደምትወደዱ ስታውቁ ታዛዥ መሆን ይበልጥ ቀላል ይሆንላችኋል። ስለተለያዩ ነገሮች ያላችሁን ስሜት ለወላጆቻችሁ ንገሯቸው። ይህ ስለ እናንተ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። እርግጥ ነው፣ እናንተም እነሱን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል።

10. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሮብዓም ከሚናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

10 እኩዮቻችሁ የሚሰጧችሁን ምክር መስማትን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው። መስማት የምትፈልጉትን ነገር ይነግሯችሁ ይሆናል፤ ሆኖም ምክራቸው ምንም የማይጠቅም ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የሚሰጧችሁ ምክር ጭራሽ ጉዳት ላይ ሊጥላችሁ ይችላል። አብዛኞቹ ወጣቶች በዕድሜ የበሰሉ ሰዎች ያላቸው ጥበብና ተሞክሮ ስለሚጎድላቸው ነገሮችን አርቀው መመልከት አይችሉም፤ እንዲሁም ድርጊታቸው ምን መዘዝ እንደሚያስከትል ማስተዋል ሊሳናቸው ይችላል። የንጉሥ ሰለሞን ልጅ የነበረውን የሮብዓምን ሁኔታ አስታውሱ። በእስራኤል ላይ ከነገሠ በኋላ በዕድሜ የገፉት ሰዎች የሰጡትን ምክር ቢከተል የተሻለ ነበር። እሱ ግን በዕድሜ የሚያንሱ አብሮ አደጎቹ የሰጡትን የሞኝነት ምክር ሰማ። በመሆኑም በግዛቱ ውስጥ ያሉትን የአብዛኞቹን እስራኤላውያን ድጋፍ አጣ። (1 ነገ. 12:1-17) ሮብዓም የተከተለውን የሞኝነት ጎዳና ከመከተል ይልቅ ከወላጆቻችሁ ጋር የምታደርጉት የሐሳብ ልውውጥ መስመር ክፍት እንዲሆን የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ። ሐሳባችሁን ለወላጆቻችሁ አካፍሏቸው። ከሚሰጧችሁ ምክር ጥቅም አግኙ፤ ከጥበባቸውም ትምህርት ቅሰሙ።—ምሳሌ 13:20

11. ወላጆች የማይቀረቡ ከሆኑ ምን ሊከሰት ይችላል?

 11 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ እኩዮቻቸውን ሳይሆን እናንተን ምክር እንዲጠይቁ የምትፈልጉ ከሆነ በቀላሉ የምትቀረቡ ሁኑ። በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “የአንድ ወንድ ልጅ ስም ከጠቀስኩ ወላጆቼ ወዲያው ይደናገጣሉ። ይህ ሁኔታ እንድረበሽ ያደርገኛል፤ ከዚያ በኋላ ማውራት ያስጠላኛል።” ሌላ ወጣት እህት ደግሞ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ብዙ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ምክር ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ይሁንና ወላጆቻቸው በቁም ነገር የማይመለከቷቸው ከሆነ እርዳታ ለማግኘት ወደ ሌላ ሰው አልፎ ተርፎም ብዙም ተሞክሮ ወደሌላቸው ይሄዳሉ።” ልጆቻችሁ ማንኛውንም ጉዳይ አንስተው ሲነግሯችሁ አሳቢነት በማሳየት የምታዳምጧቸው ከሆነ ስሜታቸውን በነፃነት ሊነግሯችሁና መመሪያችሁን በደስታ ሊቀበሉ ይችላሉ።

‘ለመናገር የዘገያችሁ ሁኑ’

12. ወላጆች የሚሰጡት ምላሽ ከልጆቻቸው ጋር የሚያደርጉትን የሐሳብ ልውውጥ ሊያስተጓጉል የሚችለው እንዴት ነው?

12 ወላጆች ልጆቻቸው ሐሳባቸውን ሲያካፍሏቸው በስሜታዊነት አፍራሽ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ የሐሳብ ልውውጥ መስመሩ ሊቋረጥ ይችላል። ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ከአደጋ መጠበቅ እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። እነዚህ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ በመንፈሳዊም ሆነ በሌሎች ዓይነት አደጋዎች የተሞሉ ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1-5) ይሁን እንጂ ወላጆች ጥበቃ ለማድረግ ብለው የሚወስዱት እርምጃ በልጆቹ ዓይን ከልክ ያለፈ ቁጥጥር ሊመስል ይችላል።

13. ወላጆች በችኮላ ከመናገር መቆጠብ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

13 ወላጆች በችኮላ ከመናገር ቢቆጠቡ ጥበብ ይሆናል። እርግጥ ልጆቻችሁ አንድ የሚያስጨንቅ ነገር ሲነግሯችሁ ስሜትን ተቆጣጥሮ ዝም ማለት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ሆኖም መልስ ከመስጠት በፊት በጥሞና ማዳመጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 18:13) የሰከነ መንፈስ ካላችሁ ብዙ ነገር መስማት ትችላላችሁ፤ ልጆቻችሁም መናገራቸውን ይቀጥላሉ። እርዳታ መስጠት እንድትችሉ በቅድሚያ ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላ መረጃ ማግኘት ይኖርባችኋል። ልጃችሁ ‘በኃይለ ቃል’ ወይም በድፍረት የሚናገረው ነገር ከተረበሸ ልብ የሚመነጭ ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 6:1-3) አፍቃሪ ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ጆሯችሁን ሁኔታውን ለመረዳት፣ አንደበታችሁን ደግሞ ለመፈወስ ተጠቀሙበት።

14. ልጆች ለመናገር የዘገዩ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

14 ልጆች፣ እናንተም ብትሆኑ ‘ለመናገር የዘገያችሁ’ መሆን ይኖርባችኋል እንጂ የወላጆቻችሁን ሐሳብ ለመቃወም መቸኮል የለባችሁም፤ ምክንያቱም እነሱ እናንተን የማሠልጠን መለኮታዊ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። (ምሳሌ 22:6) ወላጆቻችሁ አሁን እናንተ የሚያጋጥሟችሁ ዓይነት ሁኔታዎች አሳልፈው ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ወጣት ሳሉ የፈጸሟቸው ስህተቶች ይጸጽቷቸው ይሆናል፤ በመሆኑም እናንተም ተመሳሳይ ስህተት እንዳትፈጽሙ መርዳት ይፈልጋሉ። እንግዲያው ወላጆቻችሁን እንደ አጋር እንጂ እንደ ጠላት እንዲሁም እንደ መካሪ እንጂ እንደ ባላንጣ ልታዩአቸው አይገባም። (ምሳሌ 1:5ን አንብብ።) ‘አባታችሁንና እናታችሁን አክብሩ’፤ እነሱ እንደሚወዷችሁ ሁሉ እናንተም እንደምትወዷቸው በተግባር አሳዩአቸው። እንዲህ ማድረጋችሁ እናንተን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ [በውስጣችሁ] በመቅረጽ” ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት ያቀልላቸዋል።—ኤፌ. 6:2, 4

‘ለቁጣ የዘገያችሁ ሁኑ’

15. ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ትዕግሥት አጥተን እንዳንበሳጭ ምን ሊረዳን ይችላል?

15 ለምንወዳቸው ሰዎች ትዕግሥት ሳናሳይ የምንቀርባቸው ጊዜያት አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በቆላስይስ ለሚገኙ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ላላቸው ቅዱሳንና ታማኝ ወንድሞች” እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው። አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።” (ቆላ. 1:1, 2፤ 3:19, 21) ጳውሎስ በኤፌሶን ያሉ ክርስቲያኖችን “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ” ሲል መክሯቸዋል። (ኤፌ. 4:31) የአምላክ  መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች የሆኑትን ትዕግሥትን፣ ገርነትንና ራስን መግዛትን ማዳበር ውጥረት በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ እንድንረጋጋ ይረዳናል።—ገላ. 5:22, 23

16. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እርማት የሰጣቸው እንዴት ነው? ምላሽ የሰጠበት መንገድስ በጣም አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

16 እስቲ የኢየሱስን ምሳሌ እንመልከት። ከሐዋርያቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ራት በበላበት ወቅት ምን ያህል ተጨንቆ ሊሆን እንደሚችል አስቡ። ኢየሱስ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ ተሠቃይቶ እንደሚሞት ያውቅ ነበር። የአባቱ ስም መቀደስና የሰው ዘር መዳን እሱ ታማኝ በመሆኑ ላይ የተመካ ነው። ሆኖም ገበታ ላይ በነበሩበት በዚያው ሰዓት “‘ከመካከላችን ታላቅ ሊሆን የሚችለው ማን ነው?’ በሚል [በሐዋርያቱ መካከል] የጦፈ ክርክር ተነሳ።” በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አልጮኸባቸውም ወይም አልተመረረባቸውም። ከዚህ ይልቅ በረጋ መንፈስ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ ፈታኝ በሆኑ ወቅቶች እንኳ ከጎኑ እንዳልተለዩ አስታወሳቸው። ሰይጣን ሐዋርያቱን እንደ ስንዴ ለማበጠር ጥያቄ ቢያቀርብም ኢየሱስ ታማኝነታቸውን እንደሚያስመሠክሩ እርግጠኛ ነበር። እንዲያውም ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል።—ሉቃስ 22:24-32

ልጆቻችሁን በጥሞና ታዳምጣላችሁ?

17. ልጆች የሰከነ መንፈስ እንዲኖራቸው ምን ሊረዳቸው ይችላል?

17 ልጆችም የሰከነ መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል። በተለይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ወላጆቻቸው የሚሰጧቸው መመሪያ በእነሱ ላይ እምነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ሆኖ ይሰማቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው እንዲህ ሊመስል ቢችልም የወላጆቻችሁ አሳቢነት ለእናንተ ያላቸው ፍቅር መገለጫ እንደሆነ አትዘንጉ። ወላጆቻችሁ የሚሏችሁን ነገር በረጋ መንፈስ የምታዳምጡና ከእነሱ ጋር የምትተባበሩ ከሆነ የእነሱን አክብሮት ታተርፋላችሁ፤ ደግሞም ኃላፊነት የሚሰማው ልጅ አድርገው ይመለከቷችኋል። እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ማሳየታችሁ በአንዳንድ መስኮች የበለጠ ነፃነት እንድታገኙ ያስችላችኋል። ራስን መግዛት የጥበብ አካሄድ ነው። “ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል” የሚለው ምሳሌ ጥበብ ያዘለ ነው።—ምሳሌ 29:11

18. ፍቅር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ የሚረዳው እንዴት ነው?

18 የተወደዳችሁ ወላጆችና ልጆች፣ ቤተሰባችሁ እናንተ የምትፈልጉትን ያህል ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንደማያደርግ ቢሰማችሁ እንኳ ተስፋ አትቁረጡ። የሐሳብ ልውውጥ የምታደርጉበት መንገድ እንዲሻሻል የማያቋርጥ ጥረት አድርጉ፤ ደግሞም በእውነት መንገድ መመላለሳችሁን ቀጥሉ። (3 ዮሐ. 4) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ፍጹም የሆኑ ሰዎች በመካከላቸው አለመግባባትና ጭቅጭቅ ሳይኖር ፍጹም በሆነ መንገድ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ ግን ሁላችንም የኋላ ኋላ የሚጸጽተንን ነገር ማድረጋችን አይቀርም። በዚህ ጊዜ ይቅርታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበሉ። ደግሞም በነፃ ይቅር ተባባሉ። ‘ስምም ሆናችሁ በፍቅር እርስ በርስ ተሳሰሩ።’ (ቆላ. 2:2) ፍቅር ኃይል አለው። ‘ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። አይበሳጭም። የበደል መዝገብ የለውም። ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።’ (1 ቆሮ. 13:4-7) ፍቅርን ማዳበራችሁን ቀጥሉ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ በመካከላችሁ ያለው የሐሳብ ልውውጥ እየተሻሻለ ይሄዳል። ይህም ለቤተሰባችሁ ደስታ፣ ለይሖዋ ደግሞ ውዳሴ ያመጣል።

^ አን.6 ስሟ ተቀይሯል።