በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥበብ የተሞላበት ምርጫ በማድረግ ውርሻችሁን አጥብቃችሁ ያዙ

ጥበብ የተሞላበት ምርጫ በማድረግ ውርሻችሁን አጥብቃችሁ ያዙ

“ክፉ የሆነውን ነገር ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቃችሁ ያዙ።”—ሮም 12:9

1, 2. (ሀ) አምላክን ለማገልገል ውሳኔ ላይ የደረስከው እንዴት ነው? (ለ) መንፈሳዊ ውርሻችንን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን?

እኛን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋ አምላክን ለማገልገልና የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል ጥበብ የተሞላበት ምርጫ አድርገዋል። (ማቴ. 16:24፤ 1 ጴጥ. 2:21) ሕይወታችንን ለአምላክ በመወሰን የገባነውን ቃል አቅልለን አንመለከተውም። እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ላይ የደረስነው ጥራዝ ነጠቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ይዘን ሳይሆን የአምላክን ቃል በሚገባ አጥንተን ነው። ከዚህም የተነሳ ይሖዋ ‘ስለ እሱና እሱ ስለላከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ለሚቀስሙ’ ሰዎች ያዘጋጀውን ውርሻ በተመለከተ እምነት የሚያጠናክሩ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ማወቅ ችለናል።—ዮሐ. 17:3፤ ሮም 12:2

2 ክርስቲያናዊ አቋማችንን ይዘን ለመቀጠል በሰማይ የሚኖረው አባታችን የሚደሰትባቸው ውሳኔዎች ማድረግ ይኖርብናል። እንግዲያው በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ ውርሻችን ምንድን ነው? ውርሻችንን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ውርሻችንን እንድናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጥበብ የተሞላባቸው ምርጫዎች ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?

ውርሻችን ምንድን ነው?

3. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ (ለ) “ሌሎች በጎች” ምን ውርሻ ተዘጋጅቶላቸዋል?

3 በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆነ ክርስቲያኖች ‘የማይበሰብስ፣ የማይረክስና የማይጠፋ ርስት’ ለማግኘት ይጠባበቃሉ፤ አዎ፣ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት በዋጋ ሊተመን የማይችል መብት ያገኛሉ። (1 ጴጥ. 1:3, 4) እነዚህ ሰዎች ይህን ርስት ወይም ውርሻ ለማግኘት ‘ዳግመኛ መወለድ’ ይኖርባቸዋል። (ዮሐ. 3:1-3) በመንፈስ ከተቀቡት የክርስቶስ ተከታዮች ጋር በመተባበር የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩት በሚሊዮን  የሚቆጠሩ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” የሚያገኙት ውርሻስ ምንድን ነው? (ዮሐ. 10:16) ሌሎች በጎች፣ ኃጢአት የፈጸሙት አዳምና ሔዋን ያመለጣቸውን ውርሻ ያገኛሉ፤ ይህም መከራ፣ ሞት ወይም ሐዘን በማይኖርባት ገነት የሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ነው። (ራእይ 21:1-4) በመሆኑም ኢየሱስ አብሮት ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” የሚል ተስፋ ሊሰጠው ችሏል።—ሉቃስ 23:43

4. በአሁኑ ጊዜም እንኳ የትኞቹን በረከቶች አግኝተናል?

4 በአሁኑ ጊዜም እንኳ ውርሻችን የሚያስገኛቸውን አንዳንድ ነገሮች እየተቋደስን ነው። “ክርስቶስ ኢየሱስ [በከፈለው] ቤዛ” ስለምናምን ውስጣዊ ሰላምና ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና ሊኖረን ችሏል። (ሮም 3:23-25) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን አስደናቂ ተስፋዎች በግልጽ ተረድተናል። በተጨማሪም አፍቃሪ የሆነ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ክፍል መሆናችን ወደር የሌለው ደስታ አስገኝቶልናል። የይሖዋ ምሥክር መሆን በራሱ ግሩም መብት ነው። በእርግጥም ውርሻችንን በከፍተኛ አድናቆት መመልከታችን የተገባ ነው!

5. ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ምን ለማድረግ ይጥራል? የእሱን መሠሪ ዘዴዎች ለመቋቋምስ ምን ሊረዳን ይችላል?

5 ድንቅ የሆነው ውርሻችን ከእጃችን እንዳያመልጥ የሰይጣንን ዘዴዎች ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ሰይጣን የአምላክ አገልጋዮች ውርሻቸውን ሊያሳጣ የሚችል ውሳኔ እንዲያደርጉ በእነሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። (ዘኍ. 25:1-3, 9) መጥፊያው እንደቀረበ ስለሚያውቅ እኛን ለማሳሳት የሚያደርገውን ጥረት አፋፍሟል። (ራእይ 12:12, 17ን አንብብ።) “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም [እንድንችል]” ምንጊዜም ውርሻችንን ከፍ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። (ኤፌ. 6:11) በዚህ ረገድ ከይስሐቅ ልጅ ከዔሳው ታሪክ የምናገኘውን ማስጠንቀቂያ ያዘለ ትምህርት ልብ ማለታችን ይጠቅመናል።

እንደ ዔሳው አትሁኑ

6, 7. ዔሳው ማን ነበር? ምን ዓይነት ውርሻስ ይጠብቀው ነበር?

6 ይስሐቅና ርብቃ ዔሳውንና መንትያ ወንድሙን ያዕቆብን የወለዱት የዛሬ 4,000 ዓመት ገደማ ነበር። መንትያዎቹ እያደጉ ሲሄዱ በባሕርይም ሆነ በተግባር ፈጽሞ የማይገናኙ ልጆች ሆኑ። “ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት [“ነቀፋ የሌለበት፣” NW]፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር።” (ዘፍ. 25:27) ሮበርት አልተር የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ “ነቀፋ የሌለበት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ንጹሕ አቋምን ወይም ቅንነትን ያመለክታል” ብለዋል።

7 ዔሳውና ያዕቆብ የ15 ዓመት ልጆች በነበሩበት ጊዜ አያታቸው አብርሃም ሞተ፤ ይሖዋ ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ግን አልሞተም። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የምድር ብሔራት ሁሉ በአብርሃም ዘር አማካኝነት ራሳቸውን እንደሚባርኩ በመግለጽ ለይስሐቅም ያንኑ የተስፋ ቃል ሰጠው። (ዘፍጥረት 26:3-5ን አንብብ።) በዚህ የተስፋ ቃል አማካኝነት፣ ዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰው ታማኝ ‘ዘር’ ማለትም መሲሑ በአብርሃም የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ ተገልጿል። ዔሳው የይስሐቅ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን የዚህ የተስፋ ቃል ወራሽ የመሆን ሕጋዊ መብት ነበረው። ዔሳው እንዴት ያለ ግሩም ውርሻ ይጠብቀው ነበር! ይሁንና ለውርሻው አድናቆት ይኖረው ይሆን?

መንፈሳዊ ውርሻህን አደጋ ላይ አትጣል

8, 9. (ሀ) ዔሳው ከውርሻው ጋር በተያያዘ ያደረገው ምርጫ ምን ነበር? (ለ) ዓመታት ካለፉ በኋላ ዔሳው ያደረገውን ምርጫ በተመለከተ የተገነዘበው ነገር ምንድን ነው? በዚያ ጊዜስ ምን ተሰማው?

8 አንድ ቀን ዔሳው ከዱር ተመልሶ ሲመጣ ያዕቆብን “ወጥ እየሠራ” አገኘው። በዚህ ጊዜ ዔሳው “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ያዕቆብም ዔሳውን “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ዔሳው ምን ምርጫ አደረገ? ዔሳው “ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” የሚል ምላሽ መስጠቱ እጅግ ያስገርማል። አዎ፣ ዔሳው ብኩርናው ከሚያስገኝለት መብት ይልቅ ቀይ ወጡን መርጧል! ያዕቆብ የብኩርና መብቱ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲተላለፍለት ከነበረው ብርቱ ፍላጎት የተነሳ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው። ዔሳው አንዳች ሳያቅማማ የብኩርና መብቱን አሳልፎ ሰጠው። ከዚያም “ያዕቆብ ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። ዔሳው  ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት።”—ዘፍ. 25:29-34

9 ዓመታት ካለፉ በኋላ ይስሐቅ መሞቻው እንደተቃረበ በተሰማው ጊዜ ርብቃ፣ ያዕቆብ ታላቅ ወንድሙ ያስተላለፈለትን የብኩርና መብት በአስተማማኝ ሁኔታ ማግኘት እንዲችል ሁኔታዎችን አመቻቸች። ዔሳው የሞኝነት ምርጫ ማድረጉን የኋላ ኋላ ሲገነዘብ ይስሐቅን “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ። . . . ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ሲል ተማጸነው። ይስሐቅ አንድ ጊዜ ያዕቆብን ከመረቀው በኋላ በረከቱን ለእሱ መልሶ መስጠት እንደማይችል ሲነግረው ዔሳው “ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ።”—ዘፍ. 27:30-38

10. ይሖዋ ለዔሳውና ለያዕቆብ ምን አመለካከት ነበረው? ለምንስ?

10 ቅዱሳን መጻሕፍት ዔሳው ያንጸባረቀውን ዝንባሌ በተመለከተ ምን ይገልጻሉ? ዔሳው ውርሻው ወደፊት የሚያስገኝለትን በረከት ከፍ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ሥጋዊ ፍላጎቶቹን ለማርካት ቅድሚያ ሰጥቷል። ለብኩርና መብቱ አድናቆት አልነበረውም፤ ይህም ለአምላክ እውነተኛ ፍቅር እንደሌለው ያሳያል። በተጨማሪም ዔሳው ያደረገው ምርጫ በዘሮቹ ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ ቆም ብሎ አላሰበም። በአንጻሩ ግን ያዕቆብ ለውርሻው ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። ለአብነት ያህል፣ በሚስት ምርጫ ረገድ ወላጆቹ የሰጡትን መመሪያ ታዟል። (ዘፍ. 27:46 እስከ 28:3) ያዕቆብ በትዕግሥት መጠበቅና መሥዋዕትነት መክፈል የሚጠይቅ ምርጫ በማድረጉ የመሲሑ ቅድመ አያት ለመሆን በቅቷል። አምላክ ለዔሳውና ለያዕቆብ ምን አመለካከት ነበረው? ይሖዋ በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት “ያዕቆብን ወደድሁት፤ ዔሳውን ግን ጠላሁት” ብሏል።—ሚል. 1:2, 3

11. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች ዔሳው ለተወው ምሳሌ ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ፣ ዔሳው ካደረገው ነገር ጋር በተያያዘ ስለ ሴሰኝነት የተናገረው ለምንድን ነው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዔሳው የሚናገረው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች የያዘው ቁም ነገር ይኖራል? አዎ፣ ትልቅ ቁም ነገር ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ሴሰኛ የሆነ ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ዔሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው [በመካከላችሁ] እንዳይገኝ ተጠንቀቁ” ብሏቸዋል። (ዕብ. 12:16) ይህ ማስጠንቀቂያ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችንም ይመለከታል። በሥጋዊ ምኞቶች ተሸንፈን መንፈሳዊ ውርሻችንን እንዳናጣ ለቅዱስ ነገሮች ያለንን አድናቆት ይዘን መቀጠል ይኖርብናል። ይሁንና ጳውሎስ፣ ዔሳው ካደረገው ነገር ጋር በተያያዘ ስለ ሴሰኝነት የተናገረው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ዔሳው የነበረው ዓይነት ሥጋዊ አመለካከት ከተጠናወተው ደስታ ለማግኘት ሲል እንደ ሴሰኝነት ያለ ብልግና በመፈጸም ቅዱስ ነገሮችን አቅልሎ የማየት አጋጣሚው ከፍተኛ ስለሆነ ነው።

ልባችሁን ከወዲሁ አዘጋጁ

12. (ሀ) ሰይጣን በመንገዳችን ላይ ፈተናዎች የሚያስቀምጠው እንዴት ነው? (ለ) አስቸጋሪ ምርጫዎች ሲደቀኑብን ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ተናገር።

12 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን  የፆታ ብልግና እንድንፈጽም ሊገፋፉን ለሚችሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ራሳችንን እንደማናጋልጥ የታወቀ ነው። ይልቁንም አንድ ሰው የይሖዋ አምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ ለማድረግ በሚፈታተነን ጊዜ ተሸንፈን እንዳንወድቅ ይረዳን ዘንድ ወደ እሱ እንጸልያለን። (ማቴ. 6:13) ይሁንና በዚህ ወራዳ ዓለም ውስጥ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ስንጥር ሰይጣን እኛን በመንፈሳዊ ለማዳከም ጥረት ከማድረግ አይቦዝንም። (ኤፌ. 6:12) ዲያብሎስ የዚህ ክፉ ሥርዓት አምላክ እንደመሆኑ መጠን ፍጽምና የሚጎድላቸውን ሰዎች የሚፈታተኑ ነገሮች በመንገዳችን ላይ በማስቀመጥ በመጥፎ ምኞቶቻችን መጠቀም ይፈልጋል። (1 ቆሮ. 10:8, 13) ለምሳሌ ያህል፣ ፍላጎታችሁን መጥፎ በሆነ መንገድ ማርካት የምትችሉበት አጋጣሚ ተከፍቶላችኋል እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ምርጫ ታደርጋላችሁ? ዔሳው ‘ቶሎ በል! ስጠኝ!’ በማለት ያንጸባረቀው ዓይነት ዝንባሌ ታሳያላችሁ? ወይስ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ፣ የጲጥፋራ ሚስት ስትፈትነው እንዳደረገው ፈተናውን ተቋቁማችሁ ከአካባቢው ትሸሻላችሁ?—ዘፍጥረት 39:10-12ን አንብብ።

13. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የዮሴፍ ዓይነት እርምጃ የወሰዱት እንዴት ነው? አንዳንዶች ደግሞ የዔሳው ዓይነት እርምጃ የወሰዱት እንዴት ነው? (ለ) የዔሳው ዓይነት እርምጃ የወሰዱ ሰዎች የደረሰባቸውን ነገር መመልከታችን የትኛውን ወሳኝ ጉዳይ ያስገነዝበናል?

13 ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የዔሳው ወይም የዮሴፍ ዓይነት ምርጫ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። አብዛኞቹ ጥበብ ያለበት እርምጃ የወሰዱ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝተዋል። (ምሳሌ 27:11) በአንጻሩ ደግሞ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን ፈተና ሲደቀንባቸው የዔሳው ዓይነት ምርጫ በማድረግ መንፈሳዊ ውርሻቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። እንዲያውም በየዓመቱ የፍርድ እርምጃ ከሚወሰድባቸውና ከሚወገዱት መካከል አብዛኞቹ የፆታ ብልግና የፈጸሙ ክርስቲያኖች ናቸው። ንጹሕ አቋማችንን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ገና ሳይደቀኑብን ከወዲሁ ልባችንን ማቅናታችን ወይም ማዘጋጀታችን ወሳኝ ነው! (መዝ. 78:8) ፈተናን ለመመከት የሚረዱና ጥበብ የተሞላባቸው ምርጫዎች እንድናደርግ የሚያግዙ ቢያንስ ሁለት እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን።

መዘዙን አጢኑ፤ አቅማችሁንም አጠናክሩ

የይሖዋን ጥበብ ለማግኘት ጥረት በማድረግ የመከላከያ አቅማችንን ማጠናከር እንችላለን

14. ‘ክፉ የሆነውን ነገር እንድንጸየፍና ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቀን እንድንይዝ’ በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን ይረዳናል?

14 የመጀመሪያው እርምጃ የምናደርገው ነገር የሚያስከትልብንን መዘዝ ከማሰብ ጋር የተያያዘ ነው። ለመንፈሳዊ ውርሻችን ያለን አድናቆት ውርሻውን ለሚሰጠው ለይሖዋ ባለን ፍቅር ላይ የተመካ ነው። ደግሞም አንድን ሰው የምንወደው ከሆነ እሱን ማስቀየም እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንጥራለን። እንግዲያው ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ርኩስ ለሆኑ የሥጋ ምኞቶች ብንሸነፍ በእኛና በሌሎች ላይ ምን መዘዝ እንደሚያስከትል ጊዜ ወስደን ማሰባችን ጠቃሚ ነው። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት መፈጸሜ ከይሖዋ ጋር በመሠረትኩት ዝምድና ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? እንዲህ ያለ ስህተት መሥራቴ በቤተሰቤ ላይ ምን መዘዝ ያስከትላል? የጉባኤው አባላት በሆኑት ወንድሞቼና እህቶቼ ላይ ምን ስሜት ያሳድራል? በእኔ ምክንያት ሌሎች ይሰናከሉ ይሆን?’ (ፊልጵ. 1:10) በተጨማሪም እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በብልግና ለሚገኝ ቅጽበታዊ ደስታ ስል ለመከራ የሚዳርግ ምርጫ ማድረጌ ያዋጣል? የሠራሁትን ጥፋት ስገነዘብ፣ አምርሮ እንዳለቀሰው እንደ ዔሳው መሆን እፈልጋለሁ?’ (ዕብ. 12:17) እንዲህ ባሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን ‘ክፉ የሆነውን ነገር እንድንጸየፍና ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቀን እንድንይዝ’ ይረዳናል። (ሮም 12:9) በተለይ ደግሞ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ውርሻችንን አጥብቀን እንድንይዝ ያነሳሳናል።—መዝ. 73:28

15. መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉብንን ተጽዕኖዎች የመከላከል አቅማችንን የሚያጎለብትልን ምንድን ነው?

15 ሁለተኛው እርምጃ የመከላከል አቅማችንን ማጠናከር ነው። ይሖዋ በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉ በመንፈሳዊነታችን ላይ አደጋ የሚያስከትሉ ነገሮችን መከላከል የምንችልበትን አቅም እንድናጠናክር ብዙ ዝግጅቶች አድርጎልናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ የመስክ  አገልግሎትና ጸሎት በዝግጅቱ ውስጥ የታቀፉ ነገሮች ናቸው። (1 ቆሮ. 15:58) በጸሎት የልባችንን አፍስሰን ለይሖዋ በነገርነው ቁጥር እንዲሁም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ትርጉም ያለው ተሳትፎ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ ፈተናዎችን የምንመክትበትን አቅም እያጎለበትን እንሄዳለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19ን አንብብ።) የመከላከያችን ጥንካሬ በአመዛኙ የተመካው በግል ጥረታችን ላይ ነው። (ገላ. 6:7) ምሳሌ ምዕራፍ ሁለት ይህን ጉዳይ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።

‘እሷን ፈልጋት’

16, 17. ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች የማድረግ ችሎታ በማዳበር ረገድ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?

16 ምሳሌ ምዕራፍ 2 ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን እንድናዳብር ያበረታታናል። እነዚህ ባሕርያት ክፉና ደጉን ለይተን እንድናውቅ እንዲሁም እንዳሻን ከመኖር ይልቅ ራሳችንን እንድንገሥጽ ይረዱናል። ይሁንና ስኬታማ ልንሆን የምንችለው ጥረት ለማድረግ ፈቃደኞች ከሆንን ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን አባባል ትክክለኛነት ሲያጎላ እንዲህ ይላል፦ “ልጄ ሆይ፤ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በልብህ ብታኖር፣ ጆሮህን ወደ ጥበብ ብታቀና፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ብትመልስ፣ እንዲሁም የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣ እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣ በዚያን ጊዜ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤ አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።”—ምሳሌ 2:1-6

17 ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ የማድረግ ችሎታ ማዳበራችን የተመካው በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ተግባራዊ በማድረጋችን ላይ ነው። የይሖዋ ቃል ውስጣዊ ማንነታችንን እንዲቀርጽልን ከፈቀድን፣ አምላክ መመሪያ እንዲሰጠን አዘውትረን ከጸለይን እንዲሁም የተሰወሩ ውድ ማዕድናትን የመፈለግ ያህል የአምላክን እውቀት ለማግኘት ፍለጋችንን ከቀጠልን ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም ረገድ ሊሳካልን ይችላል።

18. ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ለምንስ?

18 ይሖዋ እውቀት፣ ማስተዋል፣ ጥልቅ ግንዛቤና ጥበብ የሚሰጠው እነዚህን ስጦታዎች ለማግኘት ከልብ ጥረት ለሚያደርጉ ክርስቲያኖች ነው። እነዚህን ስጦታዎች ለማግኘት ጥረት ባደረግንና በሕይወታችን ውስጥ በተጠቀምንባቸው መጠን ወደ ሰጪው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን። ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትነው የጠበቀ ዝምድና ደግሞ ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ጥበቃ ይሆንልናል። ወደ ይሖዋ መቅረባችንና ለእሱ ጥልቅ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየታችን መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም ይጠብቀናል። (መዝ. 25:14፤ ያዕ. 4:8) ከይሖዋ ጋር አስደሳች ዝምድና መመሥረታችን እንዲሁም አምላካዊ ጥበብን በሥራ ማዋላችን፣ ሁላችንም የይሖዋን ልብ የሚያስደስቱና ውርሻችንን አጥብቀን እንድንይዝ የሚያስችሉ ምርጫዎች ለማድረግ እንዲገፋፋን ምኞታችን ነው።