በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሕይወት ታሪክ

ሕይወታችን ዓላማ ያለው ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

ሕይወታችን ዓላማ ያለው ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

በ1958 ወንድ ልጄ ጋሪ እንደተወለደ አንድ ዓይነት የጤና እክል እንዳለበት ጠረጠርኩ። ይሁንና ዶክተሮቹ በሽታውን ለማወቅ አሥር ወር የፈጀባቸው ሲሆን በለንደን የሚገኙ ስፔሻሊስቶች ደግሞ የበሽታውን ምንነት በእርግጠኝነት ለመናገር ተጨማሪ አምስት ዓመት ወሰደባቸው። ጋሪ ከተወለደ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የተወለደችው ለዊዝ ከወንድሟ በባሰ ሁኔታ የበሽታው ምልክቶች እንደታዩባት ሳውቅ በጣም አዘንኩ።

ዶክተሮቹ “ሁለቱም ልጆችሽ ኤል ኤም ቢ ቢ * የተባለ በሽታ አለባቸው፤ በሽታው ደግሞ ፈውስ የለውም” ብለው አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ነገሩኝ። በዚያን ጊዜ በጂን ውስጥ በሚፈጠር እክል ሳቢያ ስለሚከሰተው ስለዚህ በሽታ እምብዛም የሚታወቅ ነገር አልነበረም። የዚህ በሽታ ዋነኛ መገለጫዎች ወደ ዓይነ ስውርነት የሚሸጋገር የማየት ችግር፣ ከልክ በላይ መወፈር፣ ትርፍ የእግርም ሆነ የእጅ ጣቶች፣ አዝጋሚ እድገት፣ የሰውነት ክፍሎች እንደ ልብ አለመታዘዝ፣ የስኳር በሽታ፣ አርትራይተስና የኩላሊት ችግር ናቸው። በመሆኑም ልጆቼን መንከባከብ እጅግ ተፈታታኝ ነበር። በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በብሪታንያ ከሚኖሩ 125,000 ሰዎች መካከል አንዱ በዚህ በሽታ እንደሚጠቃ ይገመታል፤ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ የዚህ በሽታ ምልክቶች በተወሰነ ደረጃ ይታይባቸዋል።

ይሖዋ “መጠጊያ” ሆኖልናል

ካገባሁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ተወያየሁ፤ በዚህ ወቅት ትምህርታቸው እውነት መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም። ባለቤቴ ግን ምንም ፍላጎት አልነበረውም። በሥራው ምክንያት በየጊዜው ከቦታ ቦታ እንዘዋወር ነበር፤ በዚህም የተነሳ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አልቻልኩም። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤንና ወደ ይሖዋ መጸለዬን አላቋረጥኩም ነበር። ይሖዋ “ለተጨቈኑት አምባ ነው፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል” እንዲሁም ‘የሚሹትን አይተዋቸውም’ የሚለውን ጥቅስ ማንበቤ በጣም አጽናናኝ!—መዝ. 9:9, 10

ጋሪ የማየት ችግር ስለነበረበት በስድስት ዓመቱ ልዩ እርዳታ እየተደረገለት መማር እንዲችል በእንግሊዝ ደቡባዊ ዳርቻ ወደሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ። የሚያስጨንቀው ነገር ሲኖር በየጊዜው ይደውልልኝ የነበረ ሲሆን እኔም ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን እንዲያውቅ መርዳት ችያለሁ። ለዊዝ ከተወለደች የተወሰኑ ዓመታት ካለፉ በኋላ እኔ ራሴ መልቲፕል ስክለሮሲስ የሚባል የነርቭ ሥርዓትን የሚያጠቃ በሽታና ፋይብሮማያልጂያ የተባለ ሰውነትን የሚያዝል በሽታ ያዘኝ። ጋሪ 16 ዓመት ሲሆነው ከአዳሪ ትምህርት ቤት ወደ ቤት ተመለሰ። ይሁንና የማየት ችሎታው በጣም ስለተዳከመ በ1975 ዓይነ ስውር እንደሆነ ተደርጎ መታየት ጀመረ። በ1977 ደግሞ ባለቤቴ ጥሎን ሄደ።

ጋሪ ከተመለሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ያሉበት የአንድ ጉባኤ አባል ሆንን፤ እኔም በ1974 ተጠመቅኩ። ጋሪ በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለ በሰውነቱ ላይ የተከሰቱትን ለውጦች መረዳትና መቀበል እንዲችል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ስለረዳው በጣም አመስጋኝ ነኝ። ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችም ቤት ውስጥ ያለውን ሥራ ያግዙኝ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በአካባቢው ያለ ማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚሰጥ አንድ ድርጅት ከእነሱ መካከል አምስቱ እኛን እንዲንከባከቡ ቀጠራቸው። ይህ ዝግጅት በጣም ጠቅሞናል!

ጋሪ በእውነት ውስጥ ግሩም እድገት ማድረጉን ቀጥሎ በ1982 ተጠመቀ። ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ቆርጦ ስለነበር እኔም ከእሱ ጋር በዚህ አገልግሎት ለመካፈል ወሰንኩ፤ ለበርካታ ዓመታት በዚህ መብት ሳገለግል ቆይቻለሁ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን “ጋሪ፣ ለምን የዘወትር አቅኚ አትሆንም?” ብሎ ሲጠይቀው ልጄ በጣም ተደሰተ። ጋሪ የሚያስፈልገው እንዲህ ያለ ማበረታቻ ነበር፤ በመሆኑም በ1990 አቅኚ ሆኖ ተሾመ።

 ጋሪ ሁለት ጊዜ የዳሌው መጋጠሚያ በቀዶ ሕክምና የተቀየረለት ሲሆን የመጀመሪያውን ሕክምና በ1999 ሁለተኛውን ደግሞ በ2008 አድርጓል፤ የለዊዝ ጤንነት ግን ከዚህ የከፋ ነበር። ስትወለድ ሙሉ በሙሉ ማየት አትችልም ነበር፤ በእግሯ ላይ ትርፍ ጣት ስመለከት እሷም ባርዴ ቢድል ሲንድሮም እንዳለባት ተረዳሁ። ብዙም ሳይቆይ በርካታ የውስጥ አካል ክፍሎቿም ከባድ እክል እንዳለባቸው በምርመራ ተረጋገጠ። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ከባድ ቀዶ ሕክምናዎች ያደረገች ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ኩላሊቷን ለማከም የተካሄዱ ነበሩ። ከዚህም ሌላ እንደ ጋሪ የስኳር በሽተኛ ናት።

ለዊዝ የቀዶ ሕክምና ስታደርግ ችግሮች ሊነሱ እንደሚችሉ ስለምትገነዘብ ቀዶ ሕክምና ለሚያደርጉላት፣ ማደንዘዣ ለሚሰጧትና ለሆስፒታሉ የአስተዳደር ሠራተኞች ያለ ደም መታከም እንደምትፈልግ አስቀድማ ታስረዳቸዋለች። ስለሆነም ጥሩ የሕክምና እርዳታ ከሚሰጧት ባለሙያዎች ሁሉ ጋር መልካም ግንኙነት አላት።

ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር

በቤታችን የተለያዩ ነገሮች የምናከናውን ሲሆን ሁሉም ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ናቸው። ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ከመፈልሰፋቸው በፊት ለጋሪና ለለዊዝ ለበርካታ ሰዓታት አነብላቸው ነበር። አሁን ግን በሲዲዎች፣ በዲቪዲዎችና www.pr418.com በተባለው ድረ ገጻችን ላይ በሚገኙ የድምፅ ቅጂዎች አማካኝነት ሁላችንም በመረጥነው ጊዜ የሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መዘጋጀት ችለናል፤ በመሆኑም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያለው ሐሳብ እንሰጣለን።

በይሖዋ መንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃል ውስጥ ለሚገኘው ውድ እውነት ምንኛ አመስጋኞች ነን!

ጋሪ አንዳንድ ጊዜ መልስ የሚሰጠው ሐሳቡን በቃሉ አጥንቶ ከመሆኑም ሌላ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ክፍል ካለው በራሱ አባባል ያቀርባል። በ1995 የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ የተሾመ ሲሆን ወደ መንግሥት አዳራሽ ለሚመጡት ወንድሞችና እህቶች አቀባበል ያደርጋል እንዲሁም በድምፅ ክፍል በረዳትነት ያገለግላል።

የጉባኤው አባላት ከጋሪ ጋር አገልግሎት የሚወጡ ሲሆን በአርትራይተስ ምክንያት ተሽከርካሪ ወንበር ስለሚጠቀም አብዛኛውን ጊዜ እየገፉ ይወስዱታል። አንድ ወንድም ጋሪ በሚመራው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እየተገኘ ጥናቱን መምራት እንዲችል ያግዘው ነበር። በተጨማሪም ጋሪ ለ25 ዓመታት ቀዝቅዛ የነበረችን አንዲት ክርስቲያን ማበረታታት ችሏል። በአሁኑ ጊዜ ሁለቱም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረዋል።

ለዊዝ የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለች አያቷ የኪሮሽ ሥራ አስተምራታለች፤ እኔና እንክብካቤ ከሚያደርጉላት ሴቶች መካከል አንዷ ደግሞ ጥልፍ መሥራት አስተምረናታል። የእጅ ሥራ በጣም ስለምትወድ ለሕፃናትና በጉባኤያችን ለሚገኙ አረጋውያን በቀለማት ያሸበረቁ ብርድ ልብሶችን ትሠራለች። በተጨማሪም የሚለጠፉ ትናንሽ ሥዕሎችን በመጠቀም ፖስት ካርድ ታዘጋጃለች። ፖስት ካርዶቹን የምትሰጣቸው ግለሰቦች ካርዶቹን በከፍተኛ አድናቆት ይመለከቷቸዋል። ለዊዝ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለች ታይፕ ማድረግ ተምራለች። በአሁኑ ጊዜ፣ ቃላትን ማንበብ የሚችል ኮምፒውተር በመጠቀም ከጓደኞቿ ጋር ዘወትር በኢ-ሜይል ትገናኛለች። ለዊዝ 17 ዓመት ሲሆናት ተጠመቀች። ልዩ የስብከት ዘመቻ በሚኖርበት ጊዜ አብረን ረዳት አቅኚ ሆነን እናገለግላለን። ልክ እንደ ጋሪ ለዊዝ አምላክ ቃል በገባው ዓለም ላይ ያላትን እምነት ለመግለጽ ጥቅሶችን በቃሏ መያዟ ጠቅሟታል፤ በዚያ ዓለም ውስጥ “የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ” እንዲሁም “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳ. 33:24፤ 35:5

በይሖዋ መንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃል ውስጥ ለሚገኘው ውድ እውነት ምንኛ አመስጋኞች ነን! ጉባኤያችን የሚያደርግልንን ፍቅራዊ ድጋፍ ስናስብ ልባችን በአድናቆት ይሞላል፤ እነሱ ባይረዱን ኖሮ ይህን ያህል ተሳትፎ ማድረግ አንችልም ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ በይሖዋ እርዳታ ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ችለናል።

^ አን.5 ሎረንስ-ሙን-ባርዴ-ቢድል ሲንድሮም የተሰየመው በሽታውን ባገኙት አራት ዶክተሮች ስም ነው፤ ይህ በሽታ የሚከሰተው ሁለቱም ወላጆች ሪሴሲቭ ጂን ሲኖራቸው ነው። በዛሬው ጊዜ በሰፊው የሚታወቀው ባርዴ ቢድል ሲንድሮም በሚል ስያሜ ሲሆን በሽታው ፈውስ የለውም።