በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በጣም የሚገርም ሥዕል ነው!”

“በጣም የሚገርም ሥዕል ነው!”

አዲስ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሲደርስህ ለራስህ ወይም ለሌሎች ከላይ ያለው ዓይነት የአድናቆት መግለጫ ተናግረህ ታውቃለህ? ማራኪ የሆኑት ሥዕሎችና ፎቶግራፎች ብዙ ተለፍቶባቸው የሚዘጋጁት በዓላማ ነው። ስለ ትምህርቱ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረንና ስሜታችን በጥልቅ እንዲነካ የሚያደርጉ የማስተማሪያ መሣሪያዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስንዘጋጅና ተሳትፎ ስናደርግ ሊጠቅሙን ይችላሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ በእያንዳንዱ የጥናት ርዕስ ላይ የሚቀርበው የመጀመሪያው ሥዕላዊ መግለጫ ወይም ፎቶግራፍ ለዚያ ትምህርት የተመረጠው ለምን እንደሆነ ጊዜ ወስደህ ለማሰብ ሞክር። ምን መልእክት ያስተላልፋል? ከርዕሱ ወይም ጥናቱ ከተመሠረተበት ጥቅስ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ሌሎቹን ሥዕላዊ መግለጫዎችና ፎቶግራፎች ስትመለከትም ከሚጠናው ርዕሰ ጉዳይም ሆነ ከግል ሕይወትህ ጋር የሚያያዙት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር።

የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪው የጉባኤው አባላት በእያንዳንዱ ሥዕል ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ ይኸውም ሥዕሉ ከትምህርቱ ጋር ምን ተያያዥነት እንዳለው ወይም ከሥዕሉ ለግል ሕይወታቸው የሚጠቅም ምን ነገር እንዳገኙ እንዲናገሩ መጋበዙ አይቀርም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሥዕሉ ከየትኛው አንቀጽ ጋር ሊዛመድ እንደሚችል የሚጠቁም መግለጫ ከሥዕሉ አጠገብ ይቀመጣል። እንዲህ ያለ መግለጫ ካልተሰጠ እያንዳንዱ ሥዕል ከየትኛው አንቀጽ ጋር ውይይት ቢደረግበት እንደሚሻል የጥናቱ መሪ ሊወስን ይችላል። በዚህ መንገድ፣ በጥናቱ ላይ የተገኙት ሁሉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት ሕያው በሆነ መንገድ ለማስተማር ከተደረገው ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠቀም ይችላሉ።

አንድ ወንድም ስለ ሥዕሎቹ ሲናገር “ግሩም በሆነ ሁኔታ የተዘጋጀን አንድ ርዕስ ካነበብኩ በኋላ ሥዕሎቹን የምመለከታቸው አንድ ኬክ የሚያስጎመጅ እንዲሆን ለማድረግ ከላይ እንደሚነሰነሱት ነገሮች አድርጌ ነው” ብሏል።