በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ዮሐንስ 11:35 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ በፊት እንባውን ያፈሰሰው ለምንድን ነው?

አንድ የቤተሰባችን አባል ወይም ወዳጃችን በሞት ሲለየን እንባችንን ማፍሰሳችን ተፈጥሯዊ ነው። ኢየሱስ አልዓዛርን ይወደው የነበረ ቢሆንም እንባውን ያፈሰሰው አልዓዛር በመሞቱ አይደለም። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ኢየሱስ እንባውን ያፈሰሰው የአልዓዛር ቤተሰብና የወዳጅ ዘመዶቹ ሁኔታ ስላሳዘነው ነው።—ዮሐ. 11:36

ኢየሱስ፣ አልዓዛር መታመሙን ሲሰማ እሱን ለመፈወስ ተጣድፎ አልሄደም። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “[ኢየሱስ] አልዓዛር መታመሙን በሰማ ጊዜ በዚያው በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቆየ።” (ዮሐ. 11:6) ኢየሱስ የዘገየው ለምንድን ነው? እንዲህ ያደረገው በዓላማ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የዚህ ሕመም የመጨረሻ ውጤት ሞት ሳይሆን ለአምላክ ክብር ማምጣትና የአምላክ ልጅም በዚህ ምክንያት እንዲከበር ማድረግ ነው።” (ዮሐ. 11:4) የአልዓዛር ሕመም የመጨረሻ ውጤት ሞት አልነበረም። ኢየሱስ በአልዓዛር ሞት አማካኝነት “ለአምላክ ክብር ማምጣት” አስቦ ነበር። ይሁንና እንዲህ የሚያደርገው እንዴት ነው? ኢየሱስ ወዳጁን ከመቃብር ውስጥ እንዲወጣ በማድረግ አስደናቂ የሆነ ተአምር ለመፈጸም አስቧል።

ኢየሱስ ይህን ጉዳይ አንስቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተነጋገረበት ወቅት ሞትን ከእንቅልፍ ጋር አመሳስሎት ነበር። “[አልዓዛርን] ከእንቅልፍ ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ” ያላቸው ለዚህ ነው። (ዮሐ. 11:11) ለኢየሱስ፣ አልዓዛርን ከሞት ማስነሳት ለአንድ ወላጅ ልጁን ከእንቅልፍ የመቀስቀስ ያህል ቀላል ነው። በመሆኑም አልዓዛር በመሞቱ የሚያዝንበት ምንም ምክንያት የለም።

ታዲያ ኢየሱስ እንባውን እንዲያፈስ ያደረገው ምንድን ነው? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል። ኢየሱስ፣ የአልዓዛር እህት የሆነችው ማርያምና ሌሎች ሰዎች ሲያለቅሱ ሲመለከት “መንፈሱ ታወከ፤ ውስጡም ተረበሸ።” የአልዓዛር ሞት በሰዎቹ ላይ ምን ያህል ሐዘን እንዳስከተለባቸው መመልከቱ ‘መንፈሱ እስኪታወክ’ ድረስ እንዲያዝን አድርጎታል። ኢየሱስ ‘እንባውን ያፈሰሰው’ በዚህ ምክንያት ነው። ኢየሱስ፣ ወዳጆቹ በሐዘን በጣም እንደተጎዱ መመልከቱ በጣም አሳዝኖታል።—ዮሐ. 11:33, 35

ኢየሱስ በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከሞት ለማስነሳትና የተሟላ ጤንነት ለመስጠት ኃይል እንዳለው ይህ ታሪክ በግልጽ ያሳያል። በተጨማሪም ዘገባው ኢየሱስ፣ አዳም ባመጣው ጣጣ ምክንያት የሚወዱትን የቤተሰብ አባል ወይም ወዳጅ ዘመድ በሞት ለተነጠቁ ሰዎች ከልብ እንደሚያዝን ያስተምረናል። ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ሌላው ትምህርት ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት ለተነጠቁ ሰዎች ማዘን እንዳለብን ነው።

ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሳው ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን ለወዳጆቹ ጥልቅ ፍቅር ስላለውና የእነሱ ሁኔታ አንጀቱን ስለበላው እንባውን አፍስሷል። በተመሳሳይም የሌሎችን ስሜት መረዳታችን ‘ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር እንድናለቅስ’ ያነሳሳናል። (ሮም 12:15) አንድ ክርስቲያን በዚህ መንገድ ሐዘኑን መግለጹ በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት እንደጎደለው የሚያሳይ አይደለም። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ለማስነሳት ቢያስብም እንኳ በሐዘን ላይ ላሉ ሰዎች ማዘኑ አልፎ ተርፎም አብሯቸው ማልቀሱ የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ በጣም ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።