በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች

ውሸት 2—ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም

ውሸት 2—ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም

ብዙዎች ምን ብለው ያምናሉ?

የክርስትና ሃይማኖት “ሦስቱ ዋና ዋና ክፍሎች ይኸውም የሮም ካቶሊክ፣ ምሥራቃዊ ኦርቶዶክስ እንዲሁም ፕሮቴስታንት አምላክ አንድም ሦስትም እንደሆነ ያምናሉ፤ በሌላ አባባል አምላክን እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብለው ይገልጹታል። በክርስትና ሃይማኖታዊ ትምህርት መሠረት፣ ይህ ሦስት አማልክት እንዳሉ የሚገልጽ ሳይሆን ሦስቱም አንድ እንደሆኑ የሚጠቁም ነው።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ ከአባቱ ጋር እኩል እንደሆነ ወይም በመለኮት አንድ እንደሆኑ በፍጹም ተናግሮ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ብሏል፦ “የምትወዱኝ ቢሆን ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ ምክንያቱም አብ ከእኔ ይበልጣል።” (ዮሐንስ 14:28) በተጨማሪም ከተከታዮቹ ለአንዷ “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው” ብሎ ነግሯታል።—ዮሐንስ 20:17

መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የቀድሞ ክርስቲያኖች “በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ” ይላል፤ ይሖዋም “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4, 17) ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ ክፍል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሥራ ላይ የዋለ የአምላክ ኃይል ነው።

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

የካቶሊክ ምሁራን የሆኑት ካርል ራነ እና ኸርበርት ፎርግሪምለ እንደገለጹት የሥላሴን ትምህርት “አንድ ሰው ራእይ ካልተገለጠለት በቀር ሊረዳው አይችልም፤ ራእይ ቢታየውም እንኳ ሙሉ በሙሉ ሊገነዘበው አይችልም።” ታዲያ ልታውቀው የማትችለውን አካል ልትወደው ትችላለህ? ከዚህ አንጻር የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አምላክን እንዳናውቀውና እሱን እንዳንወድደው እንቅፋት ይሆንብናል ማለት ይቻላል።

ቀደም ባለ ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ማርኮ፣ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አምላክን እንዳያውቅ እንቅፋት እንደሆነበት ተሰምቶት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ማንነቱን እንደደበቀኝ ተሰምቶኝ ነበር፤ ይህ ደግሞ ሊቀረብ እንደማይችልና ሚስጥራዊ እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ።” ይሁን እንጂ “አምላክ ግራ የሚያጋባ አምላክ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 14:33 አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን) አምላክ ማንነቱን አልደበቀንም። እንዲያውም እንድናውቀው ይፈልጋል። ኢየሱስ “የምናውቀውን እናመልካለን” ብሏል።—ዮሐንስ 4:22

ማርኮ “አምላክ ሥላሴ እንዳልሆነ ሳውቅ ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት ቻልኩ” ብሏል። ይሖዋን፣ ማንነቱ በግልጽ ሊታወቅ እንደሚችል አካል አድርገን የምንመለከተው ከሆነ እሱን መውደድ ከባድ አይሆንብንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም፤ ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው” ይላል።—1 ዮሐንስ 4:8