በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ያስፈልገናል?

ይህን ጥያቄ ማንሳት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ይህን ጥያቄ ማንሳት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

“አምላክ እንደማያስፈልግህ ይሰማሃል? ሚሊዮኖች እንደዚያ ይሰማቸዋል።” ይህ ጥቅስ የተወሰደው በአምላክ መኖር የማያምን አንድ ቡድን በቅርቡ ካስተከለው ማስታወቂያ ላይ ነው። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች አምላክ እንደማያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአምላክ እንደሚያምኑ የሚናገሩ ሆኖም በሚያደርጓቸው ምርጫዎች አምላክ የለም ብለው እንደሚያምኑ የሚያሳዩ ብዙ ሰዎች አሉ። ሳልቫቶሬ ፌዜኬላ የተባሉ አንድ የካቶሊክ ሊቀ ጳጳሳት ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው አባላት ሲናገሩ “በአሁኑ ጊዜ ማንም ሰው እኛን ተመልክቶ ክርስቲያኖች ናቸው ሊለን የሚችል አይመስለኝም፤ ምክንያቱም አኗኗራችን ከማያምኑ ሰዎች በምንም አይለይም” ብለዋል።

አንዳንዶች ስለ አምላክ ለማሰብ ጊዜ የላቸውም። እነዚህ ሰዎች አምላክን የሚያስቡት በጣም ሩቅ እንደሆነ ወይም ሊቀረብ እንደማይችል አድርገው ነው፤ ከዚህም የተነሳ በሕይወታቸው ውስጥ የጎላ ሚና መጫወት የሚችል አይመስላቸውም። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ወደ አምላክ ፊታቸውን የሚያዞሩት ምናልባት ችግር ሲደርስባቸው ወይም የሚያስፈልጋቸው ነገር ሲኖር ብቻ ነው፤ በሌላ አባባል አምላክን የሚመለከቱት የእነሱን ፈቃድ ለመፈጸም በተጠንቀቅ እንደሚጠብቅ አገልጋያቸው አድርገው ነው ማለት ይቻላል።

ሌሎች ደግሞ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ለሕይወታቸው ምንም የሚፈይዱት ነገር እንደሌለ ይሰማቸዋል፤ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፣ ቤተ ክርስቲያናቸው የሚያስተምረውን ነገር ተግባራዊ አያደርጉም። አንድ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀስ ያህል፣ በጀርመን ከሚኖሩት ካቶሊኮች መካከል 76 በመቶ የሚሆኑት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሳይጋቡ አብረው መኖራቸው ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል፤ ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናቸውም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር ይቃረናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ዕብራውያን 13:4) እርግጥ ነው፣ ሃይማኖትና ተግባር ለየቅል የሆኑት በካቶሊክ እምነት ውስጥ ብቻ አይደለም። በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ቀሳውስት፣ የምዕመኖቻቸው አኗኗር “አምላክ የለሽ” መሆናቸውን እንደሚያሳይ በምሬት ተናግረዋል።

ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ‘በእርግጥ አምላክ ያስፈልገናል?’ የሚለውን ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ነው። ይህ ጥያቄ የተነሳው ግን ዛሬ አይደለም። ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳው በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች ላይ ነው። ለጥያቄው መልስ ማግኘት እንድንችል ዘፍጥረት በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የተነሱትን ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥተን እንመልከታቸው።