በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክብር የተጎናጸፈውን ንጉሥ ክርስቶስን አወድሱ!

ክብር የተጎናጸፈውን ንጉሥ ክርስቶስን አወድሱ!

“ሞገስን ተጐናጽፈህ በድል አድራጊነት ገሥግሥ።”—መዝ. 45:4

1, 2. ለ45ኛው መዝሙር ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

ክብር የተጎናጸፈ አንድ ንጉሥ ለእውነትና ለጽድቅ ለመዋጋትና ጠላቶቹን ድል ለማድረግ ይገሰግሳል። በእነሱ ላይ የመጨረሻ ድሉን ከተቀዳጀ በኋላ አንዲት ውብ ሙሽራ ያገባል። ንጉሡ በመጪዎቹ ትውልዶች ሁሉ ሲታወስና ሲወደስ ይኖራል። መዝሙር 45 በዋነኝነት የሚናገረው ስለዚህ ጉዳይ ነው።

2 ይሁንና መዝሙር 45 ፍጻሜው ደስ የሚልና ቀልብ የሚስብ ታሪክ ብቻ አይደለም። በመዝሙሩ ውስጥ የተገለጹት ክንውኖች እኛን የሚመለከት መልእክት ያዘሉ ናቸው። ከአሁኑም ሆነ ከወደፊቱ ሕይወታችን ጋር የተያያዙ ናቸው። እንግዲያው ይህን መዝሙር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን መመርመራችን የተገባ ነው።

“መልካም የሆነ ነገር ልቤን አነሳስቶታል”

3, 4. (ሀ) እኛን የሚመለከተው “መልካም የሆነ ነገር” ምንድን ነው? በልባችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረውስ እንዴት ነው? (ለ) “ስለ አንድ ንጉሥ” እንዘምራለን ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? አንደበታችን እንደ ብዕር የሆነውስ እንዴት ነው?

3 መዝሙር 45:1በNW አንብብ። * የመዝሙራዊውን ልብ  የነካውና ‘ያነሳሳው’ “መልካም የሆነ ነገር” አንድን ንጉሥ የሚመለከት ነው። ‘አነሳሳ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ መሠረታዊ ትርጉሙ “መፍለቅለቅ” ወይም “መፍላት” የሚል ነው። ይህ ‘መልካም ነገር’ የመዝሙራዊው ልብ በስሜት እንዲፍለቀለቅና አንደበቱ “የተዋጣለት ገልባጭ እንደሚጠቀምበት ብዕር” እንዲሆን አድርጓል።

4 ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? ስለ መሲሐዊው መንግሥት የሚናገረው ምሥራች ልባችንን የሚነካ መልካም ነገር ነው። የመንግሥቱ መልእክት “መልካም” ነገር መሆኑ በ1914 በጉልህ ታይቷል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ መልእክቱ ወደፊት ስለሚቋቋም መንግሥት ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ በሰማያት እየገዛ ስላለ እውን መስተዳድር የሚገልጽ ሆኗል። ይህ መልእክት “ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” የምንሰብከው “የመንግሥቱ ምሥራች” ነው። (ማቴ. 24:14) የመንግሥቱ መልእክት ልባችንን ‘አነሳስቶታል?’ የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት እየሰበክን ነው? እንደ መዝሙራዊው ሁሉ እኛም የምንዘምረው “ስለ አንድ ንጉሥ” ይኸውም ስለ ንጉሣችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እሱ በሰማይ በዙፋን የተቀመጠ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ እንደሆነ እናውጃለን። በተጨማሪም ሁሉም ሰው ይኸውም ገዢዎችም ሆኑ ተገዢዎች ለዘውዳዊ አገዛዙ እንዲገዙ እናሳስባለን። (መዝ. 2:1, 2, 4-12) በስብከቱ ሥራችን በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል በሰፊው ስለምንጠቀም አንደበታችን “የተዋጣለት ገልባጭ እንደሚጠቀምበት ብዕር” ሆኗል።

ስለ ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን ምሥራች በደስታ እናውጃለን

‘ከንጉሡ ከንፈሮች የጸጋ ቃል ይፈልቃል’

5. (ሀ) ኢየሱስ “ውብ” ነበር ሊባል የሚችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) ከንጉሡ ‘ከንፈሮች የጸጋ ቃል የፈለቀው’ እንዴት ነው? እኛስ ምሳሌውን መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

5 መዝሙር 45:2ን አንብብ። ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ኢየሱስ መልክ ብዙም የሚናገሩት ነገር የለም። ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን “ውብ” እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ጎልቶ የሚታየው ውበቱ ለይሖዋ ያለው ታማኝነትና የማይታጠፈው ንጹሕ አቋሙ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት ይሰብክ በነበረበት ጊዜ ‘ጸጋ የተላበሱ ቃላት’ ይጠቀም ነበር። (ሉቃስ 4:22፤ ዮሐ. 7:46) እኛስ በግለሰብ ደረጃ በስብከቱ ሥራችን የእሱን ምሳሌ ለመከተልና የሰዎችን ልብ የሚነኩ ቃላት ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን?—ቆላ. 4:6

6. አምላክ ኢየሱስን “ለዘላለም” የባረከው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደረ ስለነበር ይሖዋ በምድር ላይ ያከናወነውን አገልግሎት የባረከለት ከመሆኑም ሌላ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ በኋላ ወሮታ ከፍሎታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ኢየሱስ] በሰው አምሳል በመጣ ጊዜ ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል። በዚህም ምክንያት አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው፤ ምላስም ሁሉ አባት ለሆነው አምላክ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በይፋ እውቅና እንዲሰጥ ነው።” (ፊልጵ. 2:8-11) ይሖዋ ከሞት አስነስቶ የማይሞት ሕይወት በመስጠት ኢየሱስን “ለዘላለም” ባርኮታል።—ሮም 6:9

ንጉሡ ‘ከጓደኞቹ’ የላቀ ቦታ ተሰጠው

7. አምላክ ኢየሱስን ‘ከጓደኞቹ ይልቅ’ የቀባው እንዴት ነው?

7 መዝሙር 45:6, 7ን አንብብ። ኢየሱስ ለጽድቅ ጥልቅ ፍቅር ስላለውና አባቱን ሊያስነቅፍ  የሚችልን ማንኛውንም ነገር ስለሚጠላ ይሖዋ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ኢየሱስ ‘ከጓደኞቹ’ ይኸውም የዳዊት ዘር ከሆኑት የይሁዳ ነገሥታት ይልቅ ‘በደስታ ዘይት’ ተቀብቷል። እንዴት? በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስን የቀባው ይሖዋ ራሱ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ንጉሥም ሊቀ ካህናትም አድርጎ ቀብቶታል። (መዝ. 2:2፤ ዕብ. 5:5, 6) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የተቀባው በዘይት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ነው፤ የነገሠውም በምድር ሳይሆን በሰማይ ነው።

8. ‘አምላክ የኢየሱስ ዙፋን ነው’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? መንግሥቱ ጽድቅ የሰፈነበት እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋ ልጁን በ1914 በሰማያት በመሲሐዊ መንግሥቱ ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ‘የመንግሥቱ በትር የቅንነት በትር’ ስለሆነ በእሱ አገዛዝ ጽድቅና እኩልነት እንደሚሰፍን የተረጋገጠ ነው። ሥልጣኑ ሕጋዊ መሠረት አለው፤ ምክንያቱም ‘አምላክ ዙፋኑ ነው።’ (NW) በሌላ አባባል የመንግሥቱ መሠረት ይሖዋ ነው። በተጨማሪም የኢየሱስ ዙፋን “ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራል።” አምላክ በሾመው ኃያል ንጉሥ አመራር ሥር ሆነህ ይሖዋን በማገልገልህ ኩራት አይሰማህም?

ንጉሡ ‘ሰይፉን ይታጠቃል’

9, 10. (ሀ) ክርስቶስ ሰይፉን የታጠቀው መቼ ነበር? ወዲያውኑ የተጠቀመበትስ እንዴት ነው? (ለ) ክርስቶስ ወደፊት ሰይፉን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

9 መዝሙር 45:3ን አንብብ። ይሖዋ ‘ሰይፉን በወገቡ እንዲታጠቅ’ ለንጉሡ መመሪያ ሰጥቶታል፤ በዚህ መንገድ ኢየሱስ የአምላክን ሉዓላዊነት በሚቃወሙ ሁሉ ላይ ጦርነት እንዲያውጅና መለኮታዊ ፍርዱን በእነሱ ላይ እንዲያስፈጽም ሥልጣን ተሰጥቶታል። (መዝ. 110:2) ክርስቶስ የማይበገር ተዋጊ ንጉሥ በመሆኑ “ኀያል ሆይ” ተብሎ ተጠርቷል። ሰይፉን የታጠቀው በ1914 ሲሆን በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ድል በመቀዳጀት ከሰማይ ወደ ምድር ወርውሯቸዋል።—ራእይ 12:7-9

10 ይህ የንጉሡ የድል ግስጋሴ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው። ይሁንና ‘ድሉን ገና አላጠናቀቀም።’ (ራእይ 6:2) በምድር ላይ ያሉት የሰይጣን ሥርዓት ክፍሎች በሙሉ የይሖዋ የቅጣት ፍርድ ይጠብቃቸዋል፤ በዚያን ጊዜ ሰይጣንና አጋንንቱ በቁጥጥር ሥር ይውላሉ። በመጀመሪያ የምትጠፋው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ናት። ይሖዋ የፖለቲካ ገዢዎች ይህችን ክፉ “ጋለሞታ” እንዲያጠፏት ያደርጋል። (ራእይ 17:16, 17) በመቀጠል ተዋጊው ንጉሥ በሰይጣን የፖለቲካ ሥርዓት ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዳልነበረ ያደርገዋል። ከዚያ በኋላ፣ “የጥልቁ መልአክ” ተብሎ የተጠራው ክርስቶስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ጥልቁ በመወርወር ድሉን ያጠናቅቃል። (ራእይ 9:1, 11፤ 20:1-3) መዝሙር 45 ላይ እነዚህ አስደሳች ክንውኖች እንዴት በትንቢት እንደተገለጹ እስቲ እንመልከት።

ንጉሡ “ስለ እውነት” ሲል ይገሰግሳል

11. ክርስቶስ “ስለ እውነት” ሲል የሚገሰግሰው እንዴት ነው?

11 መዝሙር 45:4ን አንብብ። ተዋጊው ንጉሥ ጦርነት የሚያውጀው ግዛቱን ለማስፋትና ሰዎችን ለማስገበር አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተቀደሰ ዓላማ ይዞ የጽድቅ ጦርነት ያውጃል። “ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትና ስለ ጽድቅ” ይገሰግሳል። ከሁሉ ይበልጥ ጥብቅና ሊቆምለት የሚገባው ታላቅ እውነት የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ነው። ሰይጣን በይሖዋ ላይ ባመፀ ጊዜ የእሱን አገዛዝ ሕጋዊነት ተገዳድሯል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ አጋንንትም ሆኑ ሰዎች ይህን መሠረታዊ እውነት ሲቃረኑ ቆይተዋል። ይሖዋ የቀባው ንጉሥ የይሖዋን ሉዓላዊ አገዛዝ ትክክለኛነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ደርሷል።

12. ንጉሡ “ስለ ትሕትና” ሲል የሚገሰግሰው እንዴት ነው?

12 በተጨማሪም ንጉሡ “ስለ ትሕትና” ሲል ይገሰግሳል። የአምላክ አንድያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን እሱ ራሱ ትሕትና በማሳየትና ለአባቱ ሉዓላዊነት በታማኝነት በመገዛት ረገድ አቻ የማይገኝለት ምሳሌ ትቷል። (ኢሳ. 50:4, 5፤ ዮሐ. 5:19) የንጉሡ ታማኝ ተገዢዎች ሁሉ የእሱን  ምሳሌ መከተልና በሁሉም ረገድ ለይሖዋ ሉዓላዊነት በትሕትና መገዛት ይኖርባቸዋል። አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈቀድላቸው እንዲህ ዓይነት ሰዎች ብቻ ናቸው።—ዘካ. 14:16, 17

13. ክርስቶስ “ስለ ጽድቅ” ሲል የሚፋለመው እንዴት ነው?

13 ከዚህም ሌላ ክርስቶስ ለጽድቅ ሲል ይፋለማል። ንጉሡ ጥብቅና የሚቆምለት ጽድቅ “የአምላክ ጽድቅ” ይኸውም ይሖዋ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ያወጣው መሥፈርት ነው። (ሮም 3:21፤ ዘዳ. 32:4) ኢሳይያስ ንጉሡን ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክቶ “ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል” ሲል ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳ. 32:1) የኢየሱስ አገዛዝ በተስፋ ሲጠበቁ የቆዩትን “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” የሚያመጣ ሲሆን “በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።” (2 ጴጥ. 3:13) በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖር ሰው ሁሉ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ይጠበቅበታል።—ኢሳ. 11:1-5

ንጉሡ “ድንቅ ተግባር” ያከናውናል

14. የክርስቶስ ቀኝ እጅ “ድንቅ ተግባር” የሚያከናውነው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

14 ንጉሡ ሰይፍ በወገቡ ታጥቆ ይገሰግሳል። (መዝ. 45:3) ይሁንና ሰይፉን በቀኝ እጁ መዞ የሚጠቀምበት ጊዜ ይመጣል። መዝሙራዊው “ቀኝ እጅህም ድንቅ ተግባር ታሳይ” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 45:4) ኢየሱስ ክርስቶስ በአርማጌዶን የይሖዋን ፍርድ ለማስፈጸም ሲገሰግስ በጠላቶቹ ላይ “ድንቅ ተግባር” ይፈጽማል። የሰይጣንን ሥርዓት ለማጥፋት የሚጠቀምበትን መሣሪያ በተመለከተ የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና ይህ እርምጃ ለንጉሡ አገዛዝ እንዲገዙ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ችላ ያሉትን የምድር ነዋሪዎች ልብ ማሸበሩ አይቀርም። (መዝሙር 2:11, 12ን አንብብ።) ኢየሱስ ስለ ፍጻሜው ዘመን በተናገረው ትንቢት ላይ “የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ” ሲል ገልጿል። አክሎም ሲናገር “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል” ብሏል።—ሉቃስ 21:26, 27

15, 16. ክርስቶስ ለውጊያ ሲወጣ የሚከተለው “ሠራዊት” እነማንን ያካትታል?

15 የራእይ መጽሐፍ ንጉሡ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ “በኃይልና በታላቅ ክብር” እንደሚመጣ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “እኔም ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ፈረስ ነበር። በእሱም ላይ የተቀመጠው ‘የታመነና እውነተኛ’ ተብሎ ይጠራል፤ እሱም በጽድቅ ይፈርዳል እንዲሁም ይዋጋል። በተጨማሪም በሰማይ ያሉት ሠራዊት በነጭ ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፤ እነሱም ነጭና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ ለብሰው ነበር። ብሔራትን ይመታበት ዘንድ ከአፉ ረጅም ስለታም ሰይፍ ይወጣል፤ እንደ እረኛም በብረት በትር ያግዳቸዋል። በተጨማሪም ሁሉን ቻይ የሆነውን የአምላክን የመዓቱን የቁጣ ወይን ጠጅ መጭመቂያ ይረግጣል።”—ራእይ 19:11, 14, 15

16 ከክርስቶስ ጋር አብረው ለውጊያ የሚዘምቱት የሰማይ “ሠራዊት” አባላት የሆኑ ተዋጊዎች እነማን ናቸው? ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ለማባረር ለመጀመሪያ ጊዜ ሰይፉን ሲታጠቅ “መላእክቱ” አብረውት ነበሩ። (ራእይ 12:7-9) በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት የክርስቶስ ሠራዊት ቅዱሳን መላእክትን ያቀፈ ይሆናል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። ሠራዊቱ ሌሎችንም ያካትት ይሆን? ኢየሱስ ለተቀቡት ወንድሞቹ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ድል ለሚነሳና በሥራዬ እስከ መጨረሻ ለሚጸናም በሕዝቦች ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤ እሱም ሕዝቦችን እንደ ሸክላ ዕቃ እንዲደቁ እንደ እረኛ በብረት በትር ያግዳቸዋል፤ ይህም እኔ ከአባቴ ሥልጣን እንደተቀበልኩት ዓይነት ነው።” (ራእይ 2:26, 27) ስለዚህ በሰማይ ያለው የክርስቶስ ሠራዊት የተቀቡ ወንድሞቹን ያካትታል፤ በዚያን ጊዜ የክርስቶስ ወንድሞች ሰማያዊ ሽልማታቸውን ተቀብለው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ብሔራትን እንደ  እረኛ በብረት በትር በሚያግድበትና “ድንቅ ተግባር” በሚያከናውንበት ጊዜ የተቀቡት ተባባሪ ገዢዎች ከእሱ ጎን ይሰለፋሉ።

ንጉሡ ድሉን ያጠናቅቃል

17. (ሀ) ክርስቶስ የሚጋልበው ነጭ ፈረስ ምን ያመለክታል? (ለ) ሰይፉና ቀስቱ ምን ያመለክታሉ?

17 መዝሙር 45:5ን አንብብ። ንጉሡ ነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጧል፤ ይህም እሱ የሚያካሂደው ውጊያ በይሖዋ ዓይን ሲታይ ንጹሕና የጽድቅ ጦርነት እንደሆነ ያሳያል። (ራእይ 6:2፤ 19:11) ንጉሡ ሰይፍ ብቻ ሳይሆን ቀስትም ታጥቋል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደፊት ገሠገሠ።” ሰይፉም ሆነ ቀስቱ ክርስቶስ በጠላቶቹ ላይ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ የሚጠቀምበትን መሣሪያ ያመለክታሉ።

ወፎች ምድርን እንዲያጸዱ ይጠራሉ (አንቀጽ 18ን ተመልከት)

18. የክርስቶስ ‘ፍላጻዎች የሾሉ’ መሆናቸው የሚታየው እንዴት ነው?

18 መዝሙራዊው ቅኔያዊ አነጋገር ተጠቅሞ በተናገረው ትንቢት ላይ የንጉሡ ‘ፍላጻዎች የሾሉ እንደሆኑና በጠላቶቹ ልብ ላይ እንደሚሰኩ’ እንዲሁም ‘ሕዝቦች ከእግሩ በታች እንደሚወድቁ’ ገልጿል። ምድር በአስከሬን ትሞላለች። ኤርምያስ የተናገረው ትንቢት “በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ” ይላል። (ኤር. 25:33) ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አንድ ትንቢት እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በተጨማሪም አንድ መልአክ በፀሐይ መካከል ቆሞ አየሁ፤ እሱም በታላቅ ድምፅ ጮኾ በሰማይ መካከል ለሚበሩት ወፎች ሁሉ እንዲህ አለ፦ ‘ወደዚህ ኑ፤ ወደ ታላቁ የአምላክ ራት ተሰብሰቡ፤ የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ እንዲሁም የሁሉንም ሥጋ ይኸውም የነፃ ሰዎችንና የባሪያዎችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ ብሉ።’”—ራእይ 19:17, 18

19. ክርስቶስ ‘በድል አድራጊነት የሚገሰግሰውና’ ድሉን የሚያጠናቅቀው እንዴት ነው?

19 ክርስቶስ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ከምድር ገጽ ካጠፋ በኋላ ‘ሞገስ ተጎናጽፎ በድል አድራጊነት ይገሰግሳል።’ (መዝ. 45:4) ለሺህ ዓመት በሚቆየው የግዛት ዘመን ሰይጣንንና አጋንንቱን በጥልቁ ውስጥ በማሰር ድሉን ያጠናቅቃል። (ራእይ 20:2, 3) በዚያን ጊዜ ዲያብሎስና መላእክቱ የሞቱ ያህል ሆነው እንዳይንቀሳቀሱ ስለሚደረጉ የምድር ነዋሪዎች ከሰይጣን ተጽዕኖ የሚገላገሉ ከመሆኑም ሌላ ድል አድራጊ ለሆነውና ክብር ለተላበሰው ንጉሣቸው ፍጹም ተገዢ ሆነው ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ምድር ሙሉ በሙሉ ወደ ገነትነት ተለውጣ ከማየታቸው በፊት ከንጉሣቸውና በሰማይ ካሉት ተባባሪዎቹ ጋር ሐሴት ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ ምክንያት ይኖራቸዋል። ይህ አስደሳች ክንውን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

^ አን.3 መዝሙር 45:1 (NW)፦ “መልካም የሆነ ነገር ልቤን አነሳስቶታል። ‘መዝሙሬ ስለ አንድ ንጉሥ ነው’ እላለሁ። አንደበቴ የተዋጣለት ገልባጭ እንደሚጠቀምበት ብዕር ይሁን።”