በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን መሲሑን ‘እንዲጠባበቁ’ ምክንያት የሆኗቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

በመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን “ሕዝቡ ክርስቶስን ይጠባበቁ ስለነበር ‘ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን?’ እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያስቡ ነበር።” (ሉቃስ 3:15) አይሁዳውያኑ፣ መሲሑ በዚያ ወቅት ይገለጣል ብለው ይጠባበቁ የነበሩት ለምን ሊሆን ይችላል? ለዚህ ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል።

ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ የይሖዋ መልአክ በቤተልሔም አቅራቢያ ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች ተገልጦ ነበር። መልአኩ “በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ ነው” ሲል ተናገረ። (ሉቃስ 2:8-11) ይህን ከተናገረ በኋላ “ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ አምላክንም እያመሰገኑ እንዲህ አሉ፦ * ‘በሰማያት ለአምላክ ክብር ይሁን፤ በምድርም አምላክ ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን።’”—ሉቃስ 2:13, 14

መልአኩ የተናገረው ነገር ትሑት የሆኑት እነዚያ እረኞች በከፍተኛ አድናቆት እንዲዋጡ እንዳደረጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እረኞቹ ወዲያውኑ ወደ ቤተልሔም አቀኑ፤ ዮሴፍን፣ ማርያምንና ሕፃኑን ኢየሱስን ባገኟቸውም ጊዜ “ስለ እሱ [ሕፃኑ] የተነገራቸውን አወሩ። ይህንንም የሰሙ ሰዎች ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ።” (ሉቃስ 2:17, 18) “የሰሙ ሰዎች ሁሉ” የሚለው አገላለጽ እረኞቹ የተነገራቸውን ነገር ለዮሴፍና ለማርያም ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ማውራታቸውን ይጠቁማል። ከዚያም እረኞቹ “የሰሙትና ያዩት ነገር ሁሉ ልክ እንደተነገራቸው ሆኖ ስላገኙት አምላክን እያከበሩና እያመሰገኑ” ወደ ቤታቸው ተመለሱ። (ሉቃስ 2:20) እነዚህ እረኞች ስለ ክርስቶስ የሰሙትን መልካም ነገር ሁሉ ለሌሎች ከመናገር ወደኋላ አላሉም!

ማርያም የሙሴ ሕግ በሚያዘው መሠረት የበኩር ልጇን በይሖዋ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዛው በመጣች ጊዜ ነቢዪቱ ሐና “አምላክን ታመሰግን ጀመር፤ የኢየሩሳሌምን መዳን ለሚጠባበቁም ሁሉ ስለ ሕፃኑ መናገር ጀመረች።” (ሉቃስ 2:36-38፤ ዘፀ. 13:12) በዚህ መንገድ ስለ መሲሑ መገለጥ የሚናገረው ምሥራች በሰፊው መሰራጨቱን ቀጠለ።

ከጊዜ በኋላ “ኮከብ ቆጣሪዎች ከምሥራቅ አገር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ‘የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የሚገኘው የት ነው? በምሥራቅ ሳለን ኮከቡን ስላየን ልንሰግድለት መጥተናል’ አሉ።” (ማቴ. 2:1, 2) “ንጉሥ ሄሮድስ ይህን ሲሰማ ተደናገጠ፤ መላዋ ኢየሩሳሌምም ተሸበረች፤ የሕዝቡን የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በሙሉ ሰብስቦ መሲሑ የት እንደሚወለድ ይጠይቃቸው ጀመር።” (ማቴ. 2:3, 4) በመሆኑም በጣም ብዙ ሰዎች ‘ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ መጥቷል’ የሚለውን መልእክት ሰምተዋል! *

 ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሉቃስ 3:15 አንዳንድ አይሁዳውያን አጥማቂው ዮሐንስ፣ ክርስቶስ ሊሆን ይችላል ብለው እንዳሰቡ ይናገራል። ይሁንና ዮሐንስ ይህ አመለካከት ትክክል አለመሆኑን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፦ “ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይበረታል፤ እኔ ጫማውን ለማውለቅ እንኳ አልበቃም። እሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።” (ማቴ. 3:11) ዮሐንስ ትሕትና በተሞላበት መንገድ የሰጠው መልስ ሰዎች መሲሑን ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት ይበልጥ አቀጣጥሎታል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዶች በዳንኤል 9:24-27 ላይ ከመሲሑ መምጣት ጋር በተያያዘ ስለ 70 ሳምንታት የሚናገረውን ትንቢት አስልተው ደርሰውበት ይሆን? ይህን አድርገው ሊሆን ቢችልም በእርግጠኝነት መናገር ግን አይቻልም። እንደ እውነቱ ከሆነ በኢየሱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እነዚህን 70 ሳምንታት በተመለከተ እርስ በርስ የሚቃረኑ በርካታ ትንታኔዎች ይሰጡ ነበር፤ ሆኖም አንዳቸውም ቢሆኑ አሁን እኛ እንዳለን ዓይነት ግልጽ ግንዛቤ አልነበራቸውም። *

የአይሁድ እምነት ኑፋቄ እንደሆኑ በሰፊው የሚታመኑትና ገዳም ውስጥ የሚኖሩት ኤሴናውያን በ490ዎቹ ዓመታት ማብቂያ ገደማ ሁለት መሲሖች እንደሚገለጡ ያስተምሩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኤሴናውያን እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት በዳንኤል ትንቢት ላይ ተመሥርተው ስለመሆኑ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። እነዚህ ሰዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት በዳንኤል ትንቢት ላይ ተመሥርተው እንደሆነ አድርገን ብናስብ እንኳ እንዲህ ዓይነቱ ራሱን አግልሎ የሚኖር ቡድን የቀመረው የዘመናት ስሌት በአጠቃላዩ የአይሁድ ማኅበረሰብ አመለካከት ላይ ያን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንዳንድ አይሁዳውያን እነዚህ 70 ሳምንታት የሚሸፍኑት የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ከወደመበት ከ607 ዓ.ዓ. አንስቶ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ እስከወደመበት እስከ 70 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ እንደሆነ ያምኑ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ የትንቢቱ ፍጻሜ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ሰፍኖ ከነበረው የመቃባውያን ዘመን ጋር እንደሚያያዝ ይሰማቸዋል። በመሆኑም የ70 ሳምንታቱን አቆጣጠር በተመለከተ የተለያየ አመለካከት ነበር።

አንድ ሰው ‘በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የ70 ሳምንታቱ ስሌት በትክክል የሚታወቅ ከሆነ ሐዋርያትም ሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በትክክለኛው ጊዜ እንደተገለጠ ለማስረዳት ይህን ማስረጃ ይጠቅሱ ነበር’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዳደረጉ የሚጠቁም ማስረጃ የለም።

ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው ሌላም ነጥብ አለ። የወንጌል ጸሐፊዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ትንቢቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ በተደጋጋሚ ጠቅሰዋል። (ማቴ. 1:22, 23፤ 2:13-15፤ 4:13-16) ይሁንና አንዳቸውም ቢሆኑ ኢየሱስ በምድር ላይ የተገለጠበትን ጊዜ ስለ 70 ሳምንታቱ ከሚናገረው ትንቢት ጋር አያይዘው አልገለጹም።

ለማጠቃለል ያህል፣ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ስለ 70 ሳምንታቱ የሚናገረውን ትንቢት በትክክል ተረድተውት እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ይሁን እንጂ የወንጌል ዘገባዎች በዘመኑ የነበሩት ሰዎች መሲሑን ‘እንዲጠባበቁ’ ያስቻሏቸውን ሌሎች አጥጋቢ ምክንያቶች ይገልጻሉ።

^ አን.4 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ መላእክት “እንደዘመሩ” አይናገርም።

^ አን.7 ‘ኮከብ ቆጣሪዎቹ በምሥራቅ በኩል የታየውን “ኮከብ” ከተወለደው “የአይሁድ ንጉሥ” ጋር ያያያዙት እንዴት ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የእስራኤልን ምድር አቋርጠው በሚሄዱበት ጊዜ ስለ ኢየሱስ መወለድ ሰምተው ይሆን?

^ አን.9 ስለ 70 ሳምንታቱ አሁን ያለንን ግንዛቤ ለማወቅ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።