በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተሰብ አምልኮ—ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ትችላላችሁ?

የቤተሰብ አምልኮ—ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ትችላላችሁ?

በብራዚል የሚኖር አንድ አባት “በቤተሰብ አምልኳችን ወቅት በውይይቱ በጣም ስለምንመሰጥ ውይይቱ እንዲቆም ካላደረግሁ ብዙውን ጊዜ ይመሽብናል” ብሏል። በጃፓን የሚኖር አንድ የቤተሰብ ራስ ደግሞ የአሥር ዓመት ልጁ፣ ሰዓቱ መሄዱ እንደማይታወቀውና የቤተሰብ ጥናቱ እንዲቀጥል እንደሚፈልግ ገልጿል። ለምን? አባቱ “ውይይቱን ስለሚወደው ነው” በማለት ተናግሯል፤ “ይህ ደግሞ በጥናቱ እንዲደሰት አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብሏል።

እርግጥ ነው፣ የቤተሰብ አምልኮን የዚህን ያህል የሚወዱት ሁሉም ልጆች አይደሉም፤ እንዲያውም አንዳንዶች የቤተሰብ ጥናት አያስደስታቸውም። ለምን? በቶጎ የሚኖር አንድ አባት “የይሖዋ አምልኮ አሰልቺ መሆን የለበትም” ብሏል። አሰልቺ ከሆነ ይህ እንዲሆን ያደረገው የቤተሰብ አምልኮው የሚመራበት መንገድ ይሆን? ነቢዩ ኢሳይያስ ሰንበት ‘የደስታ’ ምንጭ እንደሆነ ተናግሯል፤ በርካታ ቤተሰቦችም የቤተሰብ አምልኮን አስደሳች ማድረግ እንደሚቻል ተገንዝበዋል።—ኢሳ. 58:13, 14

ክርስቲያን አባቶች፣ ቤተሰባቸው በቤተሰብ አምልኮው እንዲደሰት ከፈለጉ በጥናቱ ወቅት ዘና ያለ መንፈስ እንዲኖር ማድረግ እንዳለባቸው አስተውለዋል። ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጅ ያለው ራልፍ የተባለ አባት፣ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው የጥናት ጊዜ እንደሆነ እንደማይሰማቸው ከዚህ ይልቅ ሁሉም ዘና ብለው የሚጨዋወቱበት ወቅት እንደሆነ ተናግሯል። በእርግጥ የእያንዳንዱን የቤተሰብ አባል ስሜት የሚማርክና ሁሉም ተመስጠው የሚከታተሉት ፕሮግራም ማዘጋጀት ተፈታታኝ ነው። አንዲት እናት “የቤተሰብ ጥናቱን አስደሳች ማድረግ ብፈልግም አንዳንድ ጊዜ ይህን ለማድረግ ኃይል አይኖረኝም” በማለት ተናግራለች። እናንተስ ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት ትችሉ ይሆን?

እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ እና የተለያዩ ነገሮችን ያካተተ

በጀርመን የሚኖር የሁለት ልጆች አባት “ፕሮግራሙ እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ ሊሆን ይገባል” ብሏል። ናታሊያ የተባለች የሁለት ልጆች እናት ደግሞ ለቤተሰባቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ፕሮግራሙ የተለያዩ ነገሮችን ያካተተ እንዲሆን ማድረጋቸው እንደሆነ ጎላ አድርጋ ተናግራለች። በርካታ ቤተሰቦች የቤተሰብ አምልኳቸው የተለያየ  ክፍል እንዲኖረው ያደርጋሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሁለት ልጆች ያሉትና በብራዚል የሚኖር ክሌተን የተባለ አባት “ይህ ዘዴ የቤተሰብ ጥናቱ አስደሳችና ሁሉንም የቤተሰብ አባላት የሚያካትት እንዲሆን ያደርጋል” ብሏል። በተለይ ልጆቹ ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ካላቸው ወላጆች የጥናት ጊዜውን ከፋፍለው በመጠቀም እያንዳንዱ ልጅ ለሚያስፈልገው ነገር ትኩረት መስጠት ይችላሉ። ወላጆች እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሚያስፈልገውን ነገር ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም የሚያጠኑትን ነገርና የሚያጠኑበትን መንገድ እንደ ሁኔታው መለዋወጥ ይችላሉ።

አንዳንድ ቤተሰቦች በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ የተለያዩ ነገሮችን ለማካተት ምን አድርገዋል? የቤተሰብ አምልኳቸውን በመዝሙር የሚጀምሩ ቤተሰቦች አሉ። ክዋን የተባለ በሜክሲኮ የሚኖር አንድ አባት “መዝሙር መዘመራችን ጥሩ መንፈስ እንዲሰፍን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ለምናጠናው ነገር አእምሯችንን ለማዘጋጀት ይረዳናል” ብሏል። የክዋን ቤተሰብ አባላት ከሚያጠኑት ትምህርት ጋር የሚስማማ መዝሙር ይመርጣሉ።

ስሪ ላንካ

ብዙ ቤተሰቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰነ ክፍል አብረው ያነብባሉ። መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነብቡበት ወቅት የቤተሰቡ አባላት የተለያዩ ባለታሪኮችን ወክለው በማንበብ ጥናቱ ለየት ያለ እንዲሆን ለማድረግ ይሞክራሉ። በጃፓን የሚኖር አንድ አባት “መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ ማንበብ መጀመሪያ ላይ እንግዳ ሆኖብኝ ነበር” ብሏል። ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ግን በዚህ መንገድ ከወላጆቻቸው ጋር ማንበባቸው አስደስቷቸዋል። አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በድራማ መልክ ይሠራሉ። ሮጀር የተባለ በደቡብ አፍሪካ የሚኖር የሁለት ልጆች አባት “እኛ ወላጆች ከታሪኩ ውስጥ ልብ ያላልነውን ነገር ብዙውን ጊዜ ልጆቹ ያስተውላሉ” ብሏል።

ደቡብ አፍሪካ

የቤተሰብ ጥናቱ የተለያዩ ነገሮችን ያካተተ እንዲሆን ማድረግ የሚቻልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን አብሮ ማከናወን ነው፤ ለምሳሌ የኖኅን መርከብ ወይም የሰለሞንን ቤተ መቅደስ መሥራት ይቻላል። እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች ምርምር ማድረግ የሚጠይቁ ሲሆን ይህ ደግሞ ጥናቱ አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለምሳሌ በእስያ የሚኖር አንድ ቤተሰብ ምን እንደሚያደርግ እንመልከት፦ አንዲት የአምስት ዓመት ልጅ፣ ወላጆቿ እንዲሁም አያቷ አንድ ላይ ሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ባደረገው የሚስዮናዊ ጉዞ ላይ የተመሠረተ የሰሌዳ ጨዋታ (ቦርድ ጌም) ያዘጋጃሉ። ሌሎች ቤተሰቦች ደግሞ በዘፀአት መጽሐፍ ላይ ያለውን ዘገባ መሠረት በማድረግ ተመሳሳይ ጨዋታ አዘጋጅተዋል። በቶጎ የሚኖረው የ19 ዓመቱ ዳነልድ፣ የቤተሰብ አምልኳቸው የተለያዩ ነገሮችን ያካተተ መሆኑ “ጥናቱ ይበልጥ ሕያው እንዲሆን አድርጓል፤ የቤተሰብ ሕይወታችንንም ለውጦታል” ብሏል። እናንተስ የቤተሰብ አምልኳችሁን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት መሥራት ትችላላችሁ?

ዩናይትድ ስቴትስ

ዝግጅት በጣም አስፈላጊ ነው

የቤተሰብ አምልኮው የተለያዩ ነገሮችን ያካተተና እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ መሆኑ ጥናቱን አስደሳች የሚያደርገው ቢሆንም ፕሮግራሙ ትምህርት የሚያስጨብጥ እንዲሆን ሁሉም መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ሕፃናት ሊሰለቻቸው ይችላል፤ በመሆኑም አባቶች፣ የሚመርጡትን ትምህርት አስቀድመው ሊያስቡበትና በደንብ ሊዘጋጁበት ይገባል። አንድ አባት “እኔ ተዘጋጅቼ ከመጣሁ የቤተሰብ ጥናቱ ለሁሉም የቤተሰቡ አባል ትርጉም ያለው ይሆንለታል” ብሏል። በጀርመን የሚኖር አንድ አባት በሚቀጥለው ሳምንት የሚያጠኑትን ነገር ለቤተሰቡ አስቀድሞ ይናገራል። በቤኒን የሚኖርና ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ስድስት ልጆች ያሉት አባት ደግሞ በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ዲቪዲ የሚመለከቱ ከሆነ አስቀድሞ ጥያቄዎችን ያዘጋጃል። በእርግጥም፣ ዝግጅት የቤተሰብ አምልኳችን ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ሚና ይጫወታል።

የቤተሰቡ አባላት ስለሚያጠኑት ነገር አስቀድመው ካወቁ በሳምንቱ መሃል በዚህ ጉዳይ ላይ ሊወያዩ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ለጥናቱ ይበልጥ እንዲጓጉ ያደርጋቸዋል። እንዲሁም ሁሉም ሰው የየራሱ ድርሻ ከተነገረው፣ የቤተሰብ አምልኮው እሱንም የሚያካትት እንደሆነ ይሰማዋል።

ቋሚ እንዲሆን ጥረት አድርጉ

የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸውን ቋሚ ማድረግ ተፈታታኝ የሆነባቸው ቤተሰቦች ብዙ ናቸው።

በርካታ አባቶች የቤተሰባቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ለረጅም ሰዓት ይሠራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በሜክሲኮ የሚኖር አንድ አባት ወደ ሥራ ለመሄድ ከቤት የሚወጣው ጠዋት አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ሲሆን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በፊት ወደ ቤት አይመለስም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራሙን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ሊያስፈልግ ይችላል።

ያም ቢሆን የቤተሰብ አምልኳችንን በቋሚነት ለማከናወን ቁርጥ አቋም ሊኖረን ይገባል። በቶጎ የምትኖር ሎይስ የተባለች የ11 ዓመት ልጅ ቤተሰቧ በዚህ ረገድ ያላቸውን አቋም ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በቀኑ ውስጥ በሚያጋጥሙን የተለያዩ ነገሮች የተነሳ አንዳንድ ጊዜ የቤተሰብ አምልኳችንን አምሽተን ለመጀመር እንገደድ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የቤተሰብ አምልኳችንን ሳናደርግ አናድርም።” አንዳንድ ቤተሰቦች የቤተሰብ አምልኳቸውን በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀናት የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። እንዲህ ማድረጋቸው፣ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ቢከሰት እንኳ የቤተሰብ አምልኳቸውን በሳምንቱ ውስጥ በሌሎቹ ቀናት ለማከናወን ያስችላቸዋል።

“የቤተሰብ አምልኮ” የሚለው ስያሜ እንደሚያመለክተው ይህ ዝግጅት ለይሖዋ የምታቀርቡት አምልኮ ክፍል ነው። የቤተሰባችሁ አባላት በሙሉ ለይሖዋ ‘የከንፈራቸውን ፍሬ’ በየሳምንቱ ያቅርቡ። (ሆሴዕ 14:2) የይሖዋ “ደስታ ብርታታችሁ ስለሆነ” የቤተሰብ አምልኮ የምታደርጉበት ጊዜ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አስደሳች እንዲሆን እንመኛለን።—ነህ. 8:9, 10