በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለእያንዳንዱ ሰው መልስ መስጠት’ ያለብን እንዴት ነው?

‘ለእያንዳንዱ ሰው መልስ መስጠት’ ያለብን እንዴት ነው?

“ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለው . . . ይሁን።”—ቆላ. 4:6

1, 2. (ሀ) በደንብ የታሰበባቸው ጥያቄዎች መጠየቅ ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) አስቸጋሪ በሚመስሉ ርዕሶች ላይ ከሰዎች ጋር ለመወያየት መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው?

ከብዙ ዓመታት በፊት አንዲት ክርስቲያን ከማያምን ባለቤቷ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እየተወያየች ነበር። ባለቤቷ ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ አባል ነበር። በውይይቱ መሃል ባለቤቷ በሥላሴ እንደሚያምን ተናገረ። እህት፣ የሥላሴ ትምህርት ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ሙሉ በሙሉ እንዳልገባው ስላሰበች እንዲህ ብላ ጠየቀችው፦ “እንዲህ ስትል አምላክም ሆነ ኢየሱስ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆኑ ሆኖም ሦስት አማልክት ሳይሆኑ አንድ አምላክ እንደሆኑ አምናለሁ ማለትህ ነው?” ባለቤቷ ይህ ሐሳብ ስላስገረመው “አይ፣ እኔ የማምነው እንደዚህ አይደለም!” አላት። ከዚያም ስለ አምላክ እውነተኛ ማንነት ጥሩ ውይይት አደረጉ።

2 ይህ ተሞክሮ፣ በደንብ የታሰበባቸው ጥያቄዎችን በዘዴ መጠየቅ ያለውን ጠቀሜታ ይጎላልናል። ከዚህም ሌላ አንድ ጠቃሚ ነጥብ ያስተላልፋል፦ ስለ ሥላሴ፣ ስለ ገሃነመ እሳት ወይም ስለ ፈጣሪ መኖርና እንደ እነዚህ ስላሉት ሌሎች አስቸጋሪ ርዕሶች ከሰዎች ጋር ለመወያየት መፍራት የለብንም። በይሖዋ እንዲሁም እሱ በሚሰጠን ሥልጠና የምንተማመን ከሆነ ብዙውን ጊዜ የምናነጋግራቸውን ሰዎች ልብ ሊነካ የሚችል አሳማኝ መልስ መስጠት እንችላለን። (ቆላ. 4:6) ውጤታማ የአምላክ አገልጋዮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከሰዎች ጋር ሲወያዩ ምን እንደሚያደርጉ  እስቲ እንመልከት። በዚህ ርዕስ ውስጥ (1) የሰዎችን አመለካከት ለማወቅ የሚረዱ ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ (2) በቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅመን ነጥቡን እንዲያገናዝቡ መርዳት እንዲሁም (3) ነጥቡን ግልጽ የሚያደርጉ ምሳሌዎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

የሰዎችን አመለካከት ለማወቅ የሚረዱ ጥያቄዎችን መጠየቅ

3, 4. አንድ ሰው ስለሚያምንባቸው ነገሮች ለማወቅ በጥያቄዎች መጠቀም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

3 ጥያቄዎች፣ ግለሰቡ ስለሚያምንባቸው ነገሮች ለማወቅ ይረዱናል። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ 18:13 “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል” ይላል። በእርግጥም ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ከመናገራችን በፊት ግለሰቡ በዚህ ዙሪያ ምን አመለካከት እንዳለው ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። አለዚያ አንድ ትምህርት ትክክል አለመሆኑን ለማስረዳት ብዙ ከደከምን በኋላ፣ መጀመሪያውኑም ቢሆን ግለሰቡ በዚህ ትምህርት እንደማያምን ልንገነዘብ እንችላለን!—1 ቆሮ. 9:26

4 ለምሳሌ፣ ከአንድ ሰው ጋር ስለ ገሃነም እየተነጋገርን ነው እንበል። ገሃነም፣ ቃል በቃል የማቃጠያ ስፍራ እንደሆነ የሚያምኑት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ብዙዎች፣ ገሃነም የሚለው ቃል ከአምላክ መራቅን የሚያመለክት እንደሆነ ይሰማቸዋል። በመሆኑም እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “ሰዎች ስለ ገሃነም ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው፤ እርስዎ ምን ብለው እንደሚያምኑ ሊነግሩኝ ይችላሉ?” የግለሰቡን መልስ መስማታችን መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል ለሰውየው በተሻለ መንገድ ለማስረዳት ያስችለናል።

5. ጥያቄዎች፣ ግለሰቡ አንድ ዓይነት አመለካከት የያዘው ለምን እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችሉን እንዴት ነው?

5 በዘዴ የምናቀርባቸው ጥያቄዎች ግለሰቡ አንድ ዓይነት አመለካከት የያዘው ለምን እንደሆነ ለመረዳትም ያስችሉናል። ለምሳሌ ያህል፣ አገልግሎት ላይ ያገኘነው አንድ ሰው በአምላክ እንደማያምን ቢነግረንስ? ግለሰቡ እንዲህ ዓይነት አመለካከት የያዘው እንደ ዝግመተ ለውጥ ያሉ የዓለም ጽንሰ ሐሳቦች ተጽዕኖ ስላሳደሩበት እንደሆነ እናስብ ይሆናል። (መዝ. 10:4) ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች በአምላክ እንዳያምኑ ያደረጋቸው በሌሎች ላይ ሲደርስ ያዩት ወይም በራሳቸው ላይ የደረሰው ከባድ መከራ ሊሆን ይችላል። አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ ካለ እንዲህ ያለው መከራ እንዲደርስ ይፈቅዳል ብሎ ማሰብ ከብዷቸው ይሆናል። በመሆኑም የምናነጋግረው ሰው፣ አምላክ መኖሩን እንደሚጠራጠር ከነገረን “በፊቱንም እንዲህ ነበር የሚሰማህ?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። ግለሰቡ “አይደለም” የሚል መልስ ከሰጠን አምላክ መኖሩን እንዲጠራጠር ያደረገው ያጋጠመው ነገር ይኖር እንደሆነ ልንጠይቀው እንችላለን። የሚሰጠን መልስ እሱን በመንፈሳዊ መርዳት የምንችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ለማወቅ ያስችለናል።—ምሳሌ 20:5ን አንብብ።

6. ጥያቄ ከጠየቅን በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

6 ጥያቄ ከጠየቅን በኋላ ግለሰቡ መልስ ሲሰጠን በትኩረት ማዳመጥና ስሜቱን እንደተረዳን ማሳየት ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ መኖሩን እንዲጠራጠር ያደረገው አንድ የሚያሳዝን ሁኔታ እንደሆነ ይነግረን ይሆናል። አምላክ መኖሩን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ከማቅረባችን በፊት፣ በነገሩ ማዘናችንን መግለጻችን እንዲሁም መከራ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ መጠየቁ ስህተት አለመሆኑን ማስረዳታችን ጥሩ ነው። (ዕን. 1:2, 3) በትዕግሥትና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እሱን ለመርዳት የምናደርገው ጥረት፣ ይበልጥ ለማወቅ ሊያነሳሳው ይችላል። *

በቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅመን ነጥቡን እንዲያገናዝቡ መርዳት

በአገልግሎታችን ውጤታማ መሆናችን በአብዛኛው የተመካው በምን ላይ ነው? (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

7. በአገልግሎታችን ውጤታማ መሆናችን በአብዛኛው የተመካው በምን ላይ ነው?

7 አሁን ደግሞ በቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅመን ሰዎች ነጥቡን እንዲያገናዝቡ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በአገልግሎታችን ላይ የምንጠቀምበት ዋነኛው መሣሪያ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ” ለመሆን ያስችለናል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) በአገልግሎታችን ውጤታማ መሆናችን በአብዛኛው የተመካው በምናነባቸው ጥቅሶች ብዛት ላይ ሳይሆን ካነበብናቸው ጥቅሶች አንጻር ሰዎች ነጥቡን እንዲያገናዝቡ በምንረዳበትና ጥቅሱን በምናብራራበት መንገድ ላይ ነው።  (የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማስረዳት እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ምሳሌዎች እንመልከት።

8, 9. (ሀ) ‘ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነው’ ብሎ የሚያምን ሰው ቢያጋጥመን ምን ብለን ማስረዳት እንችላለን? (ለ) ይህን ጉዳይ ለማስረዳት አንተ ውጤታማ ሆኖ ያገኘኸው ጥቅስና ማብራሪያ የትኛው ነው?

8 ምሳሌ 1በአገልግሎት ላይ፣ ‘ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነው’ ብሎ የሚያምን ሰው አጋጠመን። ይህ ግለሰብ ነጥቡን አገናዝቦ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ለመርዳት የትኞቹን ጥቅሶች መጠቀም እንችላለን? ግለሰቡ ዮሐንስ 6:38ን እንዲያነብብ ልንጋብዘው እንችላለን፤ በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “ከሰማይ የመጣሁት የእኔን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” በማለት ተናግሯል። ይህን ጥቅስ ካነበብን በኋላ እንዲህ ልንለው እንችላለን፦ “ታዲያ ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ከሆነ እሱን ከሰማይ የላከው ማን ነው? ኢየሱስን የላከው አካል ከኢየሱስ መብለጥ የለበትም? ደግሞም ላኪ ከተላኪው እንደሚበልጥ የታወቀ ነው።”

9 ከዚሁ ነጥብ ጋር በተያያዘ ፊልጵስዩስ 2:9ን ልናነብለት እንችላለን፤ በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ አምላክ ምን እንዳደረገ ገልጿል። ጥቅሱ “አምላክ [ለኢየሱስ] የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው” ይላል። ግለሰቡ ከዚህ ጥቅስ አንጻር ነጥቡን እንዲያገናዝብ ለመርዳት እንዲህ ብለን ልንጠይቀው እንችላለን፦ “ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከአምላክ ጋር እኩል ከነበረና ከሞት ከተነሳ በኋላ አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ ካደረገው ኢየሱስ ከአምላክ ሊበልጥ ነው ማለት ነው? ታዲያ ከአምላክ የሚበልጥ አካል ሊኖር ይችላል?” ግለሰቡ ለአምላክ ቃል አክብሮት ካለውና ልበ ቅን ከሆነ ይህ ማብራሪያ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለመመርመር እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል።—ሥራ 17:11

10. (ሀ) በገሃነመ እሳት ለሚያምን ሰው አሳማኝ ማስረጃ ለማቅረብ ምን ማለት እንችላለን? (ለ) ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ ሰዎች ወደ ትክክለኛው መደምደሚያ እንዲደርሱ የረዳሃቸው እንዴት ነው?

10 ምሳሌ 2፦ አጥባቂ ሃይማኖተኛ የሆነ ግለሰብ ክፉ ሰዎች በገሃነመ እሳት ለዘላለም አይሠቃዩም የሚለውን ሐሳብ መቀበል ከበደው እንበል። ግለሰቡ እንዲህ ዓይነት አመለካከት የያዘው፣ ክፉ ሰዎች ለሠሩት ነገር መቀጣት እንዳለባቸው ስለሚሰማው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ላለው ሰው አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ክፉዎች መቀጣታቸው እንደማይቀር ልናረጋግጥለት እንችላለን። (2 ተሰ. 1:9) ከዚያም ዘፍጥረት 2:16, 17ን እንዲያነብብ ልንጠይቀው እንችላለን፤ ጥቅሱ ኃጢአት የሚያስከትለው ቅጣት ሞት እንደሆነ ይገልጻል። አዳም፣ ኃጢአት በመሥራቱ መላው የሰው ዘር ኃጢአተኛ ሆኖ እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል። (ሮም 5:12) ያም ቢሆን አምላክ፣ አዳም በገሃነመ እሳት እንደሚቀጣ የሚጠቁም ነገር እንዳልተናገረ ልንገልጽለት እንችላለን። ከዚያም እንዲህ ብለን ልንጠይቀው እንችላለን፦ “አዳምና ሔዋን የሚጠብቃቸው ቅጣት ለዘላለም በገሃነመ እሳት መቃጠል ቢሆን ኖሮ ይህን በተመለከተ አምላክ አስቀድሞ ሊያስጠነቅቃቸው አይገባም ነበር?” በመቀጠልም ዘፍጥረት 3:19ን ማንበብ እንችላለን፤ ጥቅሱ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ስለተፈረደባቸው  ቅጣት የሚገልጽ ቢሆንም ስለ ገሃነመ እሳት ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ለአዳም የተነገረው ወደ አፈር እንደሚመለስ ነው። ቀጥለን ደግሞ “አዳም ሲሞት የሚሄደው ወደ መቃጠያ ቦታ ከሆነ አምላክ ይህን እያወቀ አዳም ወደ አፈር እንደሚመለስ መናገሩ ተገቢ ይመስልሃል?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። ሰውየው ቀና አመለካከት ካለው እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች በጉዳዩ ላይ ቆም ብሎ እንዲያስብ ሊያደርጉት ይችላሉ።

11. (ሀ) ‘ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ’ ብሎ የሚያምን ሰው ቢያጋጥመን ምን ማስረጃ ልናቀርብለት እንችላለን? (ለ) ወደ ሰማይ ከመሄድ ጋር በተያያዘ ሰዎችን ለማስረዳት ውጤታማ ሆኖ ያገኘኸው መንገድ የትኛው ነው?

11 ምሳሌ 3በአገልግሎታችን ላይ፣ ‘ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ’ ብሎ የሚያምን ሰው አጋጠመን። ግለሰቡ እንዲህ ያለ አመለካከት ያለው መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን በሚረዳበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለምሳሌ ራእይ 21:4አነበብንለት እንበል። (ጥቅሱን አንብብ።) ሰውየው፣ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች ስለሚያገኟቸው በረከቶች እንደሆነ ሊያስብ ይችላል። ታዲያ ይህን ሰው እንዴት ልናስረዳው እንችላለን? ማስረጃ የሚሆኑ ሌሎች ጥቅሶች ከመጥቀስ ይልቅ በዚያ ጥቅስ ላይ ያሉትን ሐሳቦች በዝርዝር መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ጥቅሱ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” ይላል። ግለሰቡን “አንድ ነገር ‘ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም’ ሊባል የሚችለው ቀድሞ የነበረ ከሆነ ብቻ ነው ቢባል አትስማማም?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። በዚህ እንደሚስማማ ግልጽ ነው። ከዚያም በሰማይ ላይ ሞት ኖሮ እንደማያውቅና ሰዎች የሚሞቱት እዚህ ምድር ላይ ብቻ እንደሆነ ልንገልጽለት እንችላለን። ከዚህ አንጻር፣ ራእይ 21:4 የሚናገረው ወደፊት በምድር ላይ ስለሚኖሩት በረከቶች ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።—መዝ. 37:29

ነጥቡን ግልጽ የሚያደርጉ ምሳሌዎችን መጠቀም

12. ኢየሱስ በምሳሌዎች የሚጠቀመው ለምን ነበር?

12 ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት ከጥያቄዎች በተጨማሪ ምሳሌዎችን ይጠቀም ነበር። (ማቴዎስ 13:34, 35ን አንብብ።) ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች፣ የሚያዳምጡት ሰዎች ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዳላቸው እንዲታወቅ አድርገዋል። (ማቴ. 13:10-15) በተጨማሪም ምሳሌዎቹ የኢየሱስ ትምህርት ማራኪና የማይረሳ እንዲሆን አድርገዋል። እኛስ በምናስተምርበት ጊዜ ምሳሌዎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

13. አምላክ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ ለማስረዳት የትኛውን ምሳሌ መጠቀም እንችላለን?

13 ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት የሚያስገኙት ቀላል ምሳሌዎች ናቸው። ለምሳሌ፣ አምላክ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ ለማስረዳት የሚከተለውን ዘዴ መጠቀም እንችላለን። አምላክም ሆነ ኢየሱስ በመካከላቸው ስላለው ግንኙነት ለመግለጽ በቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ዝምድና ተጠቅመዋል። አምላክ ስለ ኢየሱስ ሲናገር ልጁ እንደሆነ ገልጿል፤ ኢየሱስም ስለ አምላክ ሲገልጽ አባቱ መሆኑን ተናግሯል። (ሉቃስ 3:21, 22፤ ዮሐ. 14:28) ግለሰቡን እንዲህ ብለን ልንጠይቀው እንችላለን፦ “በቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ዝምድና እንደ ምሳሌ ተጠቅመህ ሁለት ሰዎች እኩል መሆናቸውን ልታስረዳኝ ብትፈልግ እነማንን ትጠቅሳለህ?” ግለሰቡ ሁለት ወንድማማቾችን ምናልባትም መንትያዎችን ይጠቅስ ይሆናል። እንዲህ ካለ፣ ንጽጽሩ ትክክል እንደሆነ ልንገልጽለት እንችላለን። ቀጥሎም እንዲህ ልንል እንችላለን፦ “እኔና አንተ ሁለት ግለሰቦች እኩል መሆናቸውን ለማስረዳት ቶሎ የሚመጣልን እንዲህ ዓይነት ምሳሌ ከሆነ ታላቅ አስተማሪ የነበረው ኢየሱስ ተመሳሳይ ምሳሌ መጠቀም አይችልም ነበር? ኢየሱስ ግን አምላክ አባቱ እንደሆነ ተናግሯል። ከዚህ ማየት እንደምንችለው ኢየሱስ፣ አምላክ ከእሱ በዕድሜና በሥልጣን እንደሚበልጥ እየገለጸ ነበር።”

14. አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ለማሠቃየት በዲያብሎስ ይጠቀማል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ለማሳየት የትኛውን ምሳሌ መጠቀም ይቻላል?

14 ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። አንዳንዶች፣ ገሃነመ እሳትን “እንዲቆጣጠር” የተሾመው ሰይጣን እንደሆነ ያምናሉ። አምላክ፣ ሰዎችን በገሃነመ እሳት እንዲያቃጥል ዲያብሎስን ሾሞታል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ለአንድ ወላጅ ለማስረዳት በምሳሌ መጠቀም እንችላለን። እንዲህ ልንለው እንችላለን፦ “ልጅህ በጣም ዓመፀኛ ሆነብህ እንበል። ብዙ መጥፎ ነገሮች ይፈጽማል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ?” ይህ ወላጅ፣ ልጁ አካሄዱን እንዲያስተካክል እንደሚመክረው ይናገር ይሆናል። አክሎም ልጁ፣ ከመጥፎ ተግባሩ  እንዲመለስ ለመርዳት በተደጋጋሚ ጥረት እንደሚያደርግ ይገልጽልን ይሆናል። (ምሳሌ 22:15) በዚህ ጊዜ ይህን ወላጅ “ምንም ያህል ጥረት ብታደርግም ልጅህ የምትነግረውን አልሰማ ቢልህ ምን ታደርጋለህ?” ልንለው እንችላለን። ብዙ ወላጆች ልጁን ከመቅጣት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ይናገሩ ይሆናል። በዚህ ጊዜ “ልጅህ ዓመፀኛ እንዲሆን ተጽዕኖ የሚያሳድርበት አንድ መጥፎ ሰው እንዳለ ብታውቅ ግን ምን ይሰማሃል?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። አንድ ወላጅ ይህን ሲያውቅ በዚህ ሰው እንደሚናደድ ግልጽ ነው። በምሳሌው ሊተላለፍ የተፈለገውን ነጥብ ግልጽ ለማድረግ “ልጅህን ያበላሸውን ያንኑ ክፉ ሰው ልጅህን እንዲቀጣልህ ትጠይቀዋለህ?” ማለት እንችላለን። ይህ ወላጅ “በፍጹም” የሚል መልስ መስጠቱ አይቀርም። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው አምላክ፣ መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ ዲያብሎስ ያሳሳታቸውን ሰዎች ለመቅጣት በራሱ በዲያብሎስ አይጠቀምም!

ምንጊዜም ሚዛናዊ አመለካከት ይኑራችሁ

15, 16. (ሀ) ምሥራቹን ከሰበክንላቸው ሰዎች መካከል የመንግሥቱን መልእክት የማይቀበሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ውጤታማ አስተማሪዎች ለመሆን የተለየ ችሎታ ሊኖረን ይገባል? አብራራ። (“ መልስ ለመስጠት የሚረዳን መሣሪያ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

15 ምሥራቹን ከሰበክንላቸው ሰዎች መካከል የመንግሥቱን መልእክት የማይቀበሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ እንገነዘባለን። (ማቴ. 10:11-14) ትክክለኛ ጥያቄዎችን ብንጠይቅ፣ ነጥቡን እንዲያገናዝቡ የሚረዱ ጥሩ ሐሳቦችን ብናቀርብ እንዲሁም ግሩም ምሳሌዎችን ብንጠቀም እንኳ ሰዎች መልእክቱን ላይቀበሉ ይችላሉ። ደግሞም በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የላቀ ታላቅ አስተማሪ የነበረው ኢየሱስ፣ ካስተማራቸው ሰዎች መካከል መልእክቱን የተቀበሉት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂቶች ነበሩ።—ዮሐ. 6:66፤ 7:45-48

16 በሌላ በኩል ግን የተለየ ችሎታ እንደሌለን የሚሰማን ቢሆንም እንኳ በአገልግሎታችን ውጤታማ ልንሆን እንችላለን። (የሐዋርያት ሥራ 4:13ን አንብብ።) የአምላክ ቃል “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሁሉ ምሥራቹን እንደሚቀበሉ ይናገራል። (ሥራ 13:48) እንግዲያው ስለ ራሳችንም ሆነ የመንግሥቱን ምሥራች ስለምናካፍላቸው ሰዎች ምንጊዜም ሚዛናዊ አመለካከት ይኑረን። ይሖዋ የሚሰጠን ሥልጠና፣ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን እንደሚጠቅም በመተማመን ከሥልጠናው ሙሉ በሙሉ ጥቅም ለማግኘት ጥረት እናድርግ። (1 ጢሞ. 4:16) ይሖዋ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት” እንደሚገባን ያስተምረናል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው በአገልግሎታችን ውጤታማ ለመሆን ከሚረዱን ነገሮች አንዱ ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ ተብሎ የሚጠራውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ነው።

^ አን.6 በጥቅምት 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ፈጣሪ ስለመኖሩ እምነት ማዳበር ይቻላል?” የሚል ርዕስ ተመልከት።