በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ነገሮችን በተደራጀ መልክ የሚያከናውን አምላክ ነው

ይሖዋ ነገሮችን በተደራጀ መልክ የሚያከናውን አምላክ ነው

“አምላክ የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም።”—1 ቆሮ. 14:33

1, 2. (ሀ) የመጀመሪያው የአምላክ ፍጥረት ማን ነው? ይሖዋ የተጠቀመበትስ እንዴት ነው? (ለ) መላእክት የተደራጁ መሆናቸውን የሚጠቁመው ምንድን ነው?

የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውነው በተደራጀ መልኩ ነው። ከፍጥረት ሥራዎቹ የመጀመሪያው፣ መንፈሳዊ አካል የሆነው አንድያ ልጁ ነው፤ እሱም የአምላክ ዋና ቃል አቀባይ ስለሆነ “ቃል” ተብሎ ይጠራል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከአምላክ ጋር ነበር” ስለሚል ቃል ይሖዋን ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት አገልግሏል። በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በእሱ [በቃል] በኩል ነው፤ ያለ እሱ ወደ ሕልውና የመጣ አንድም ነገር እንኳ የለም” ይላል። አምላክ የዛሬ 2,000 ዓመታት ገደማ ቃልን ወደ ምድር ላከው፤ ቃል ፍጹም ሰው ሆኖ በምድር ላይ በኖረበት ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ የተጠራ ሲሆን የአባቱን ፈቃድ በታማኝነት አከናውኗል።—ዮሐ. 1:1-3, 14

2 የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የአምላክ “ዋና ባለሙያ” በመሆን እሱን በታማኝነት አገልግሏል። (ምሳሌ 8:30) ይሖዋ፣ በሰማይ የሚኖሩት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ወደ ሕልውና እንዲመጡ ያደረገው በእሱ አማካኝነት ነው። (ቆላ. 1:16) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መንፈሳዊ ፍጥረታት ስለሆኑት ስለ እነዚህ መላእክት ሲናገር “ሺህ ጊዜ ሺሆች [ይሖዋን] ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል” ይላል። (ዳን. 7:10) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ስፍር ቁጥር  የሌላቸውን እነዚህን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያቀፈ በሚገባ የተደራጀ ‘ሰራዊት’ እንዳለው ይገልጻል።—መዝ. 103:21

3. ምን ያህል ከዋክብትና ፕላኔቶች አሉ? የተደራጁትስ በምን መንገድ ነው?

3 ሕልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ከዋክብትና ፕላኔቶች እንዲሁም እንደ እነዚህ ያሉትን ሌሎች ግዑዝ ፍጥረታት በተመለከተስ ምን ማለት ይችላል? ሂዩስተን፣ ቴክሳስ ክሮኒክል የተባለው ጋዜጣ ስለ ከዋክብት በቅርብ የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሶ እንደገለጸው “300 ሴክስትሊዮን በሌላ አባባል የሳይንስ ሊቃውንት ከዚህ በፊት ካሰቡት በሦስት እጥፍ” የሚበልጡ ከዋክብት አሉ። በዚህ ጋዜጣ ላይ የወጣው ሪፖርት አክሎ እንዲህ ይላል፦ “ይህም ከ3 ቁጥር በኋላ 23 ዜሮዎችን መጻፍ ማለት ነው። አሊያም 3 ትሪሊዮን ሲባዛ በ100 ቢሊዮን ማለት ነው።” ከዋክብት በሕዋ ውስጥ የሚገኙት በተደራጀ መልክ ነው፤ እነዚህ ከዋክብት በተለያዩ ጋላክሲዎች የሚታቀፉ ሲሆን እያንዳንዱ ጋላክሲ በቢሊዮን እንዲያውም በትሪሊዮን የሚቆጥሩ ከዋክብትን እና በርካታ ፕላኔቶችን ይይዛል። ጋላክሲዎች ሲሰባሰቡ ክላስተሮችን (የጋላክሲዎች ስብስብ) ይፈጥራሉ፤ የእነዚህ ክላስተሮች ስብስቦች ደግሞ ሱፐርክላስተሮች (ትላልቅ የጋላክሲ ክምችቶች) ይሆናሉ።

4. በምድር ያሉ የአምላክ አገልጋዮች የተደራጁ እንደሚሆኑ መጠበቁ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 በሰማይ እንዳሉት ጻድቅ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሁሉ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ግዑዝ ነገሮችም አስደናቂ በሆነ መንገድ ተደራጅተዋል። (ኢሳ. 40:26) ከዚህ አንጻር ይሖዋ በምድር የሚገኙ አገልጋዮቹንም ያደራጃቸዋል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በተደራጀ መልኩ ነገሮችን እንዲያከናውኑ ይፈልጋል፤ ብዙ የሚያከናውኑት ሥራ ስላለ ይህን ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በጥንት ጊዜ የኖሩትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች በታማኝነት ያከናወኑት አገልግሎት፣ አምላክ ምንጊዜም ከእነሱ ጋር እንዳለና እሱ “የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ” እንዳልሆነ ግሩም ማስረጃ ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 14:33, 40ን አንብብ።

በጥንት ዘመን የነበረው የአምላክ የተደራጀ ሕዝብ

5. ሰብዓዊው ቤተሰብ ሥርዓት ባለው መልኩ ምድርን እንዲሞላ አምላክ ያደረገው ዝግጅት የተስተጓጎለው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ፣ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ሲፈጥር እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።” (ዘፍ. 1:28) አምላክ ምድርን ለመሙላት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በአንድ ጊዜ አልፈጠረም፤ ከዚህ ይልቅ ዓላማው፣ ሰብዓዊው ቤተሰብ ሥርዓት ባለው መልኩ ቀስ በቀስ ቁጥሩ እየጨመረ ሄዶ ምድርን እንዲሞላና መላዋን ፕላኔት ገነት እንዲያደርጋት ነበር። ሥርዓት ባለው መልኩ የተደራጀው ይህ ዝግጅት በአዳምና ሔዋን አለመታዘዝ ምክንያት ለጊዜው ተስተጓጎለ። (ዘፍ. 3:1-6) ከጊዜ በኋላ “አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ።” የሰው ልጆች እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያላቸው በመሆኑ “ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች።” በመሆኑም አምላክ ክፉዎችን ለማስወገድ ሲል ዓለም አቀፋዊ የጥፋት ውኃ ለማምጣት ወሰነ።—ዘፍ. 6:5, 11-13, 17

6, 7. (ሀ) ኖኅ በይሖዋ ዘንድ ሞገስ ያገኘው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) በኖኅ ዘመን የነበሩት እምነት የሌላቸው ሰዎች በሙሉ ምን አጋጠማቸው?

6 ይሁንና “ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው” በመሆኑ “በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ።” ኖኅ ‘አካሄዱን ከአምላክ ጋር ስላደረገ’ ይሖዋ ትልቅ መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። (ዘፍ. 6:8, 9, 14-16) የመርከቧ ንድፍ፣ የሰው ዘርንም ሆነ የእንስሳትን ሕይወት ለመታደግ በሚያስችል መንገድ የተሠራ ነበር። ኖኅ ታዛዥ በመሆን “እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።” እንዲሁም ከቤተሰቡ ጋር በመተባበር የመርከቡን ግንባታ በተደራጀ መልኩ አከናወነ። ሕያዋን ፍጥረታት ወደ መርከቡ ከገቡ በኋላ ይሖዋ የመርከቡን በር ‘ከውጭ ዘጋው።’—ዘፍ. 7:5, 16

7 ይሖዋ በ2370 ዓ.ዓ. የጥፋት ውኃ በማምጣት “ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከምድር ገጽ” እንዲጠፉ  አደረገ፤ በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ታማኙ ኖኅና ቤተሰቡ ግን ከጥፋቱ ተረፉ። (ዘፍ. 7:23) በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያለው ሰው በሙሉ የተገኘው ከኖኅ፣ ከልጆቹና ከሚስቶቻቸው ነው። ከመርከቧ ውጭ የነበሩት እምነት የሌላቸው ሰዎች በሙሉ ግን “የጽድቅ ሰባኪ” የሆነውን ኖኅን ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጠፍተዋል።—2 ጴጥ. 2:5

በጥሩ ሁኔታ መደራጀት ስምንት ሰዎችን ከጥፋት ውኃ እንዲተርፉ ረድቷቸዋል (አንቀጽ 6, 7ን ተመልከት)

8. አምላክ፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ ለእስራኤላውያን መመሪያ በሰጣቸው ወቅት ብሔሩ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 የጥፋት ውኃው ከተከሰተ ከስምንት መቶ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ አምላክ እስራኤላውያንን በብሔር መልክ አደራጃቸው። ይሖዋ፣ ሕዝቡን ያደራጀበት መንገድ ሁሉንም የሕይወታቸውን ዘርፍ በተለይም አምልኳቸውን የሚነካ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በእስራኤል ከነበሩት በርካታ ካህናትና ሌዋውያን በተጨማሪ “በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ በተደራጀ መልክ [የሚያገለግሉ] ሴት አገልጋዮች” ነበሩ። (ዘፀ. 38:8 NW) ይሁንና ይሖዋ አምላክ፣ እስራኤላውያን ወደ ከነዓን እንዲገቡ መመሪያ ሲሰጣቸው በወቅቱ የነበረው ትውልድ ታዛዥ አልሆነም፤ በዚህም ምክንያት ይሖዋ “መኖሪያችሁ እንድትሆን በጽኑ ወደ ማልሁላችሁ ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር ከእናንተ አንዳችሁም አትገቡባትም” ብሏቸዋል። ኢያሱና ካሌብ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ተስፋይቱን ምድር ከሰለሉ በኋላ ጥሩ ዜና ይዘው ስለተመለሱ ነበር። (ዘኍ. 14:30, 37, 38) ሙሴ ከጊዜ በኋላ አምላክ ባዘዘው መሠረት፣ በእሱ ምትክ እስራኤልን እንዲመራ ኢያሱን ሾመው። (ዘኍ. 27:18-23) ኢያሱ እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ከነዓን ሊገባ ሲል እንዲህ ተብሎ ነበር፦ “በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ።”—ኢያሱ 1:9

9. ረዓብ ለይሖዋ እና ለሕዝቡ ምን አመለካከት ነበራት?

9 በእርግጥም ኢያሱ በሄደበት ሁሉ ይሖዋ አምላክ ከእሱ ጋር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን የከነዓናውያን ከተማ በሆነችው በኢያሪኮ አቅራቢያ በሰፈሩ ጊዜ የተከናወነውን ሁኔታ እንመልከት። በ1473 ዓ.ዓ. ኢያሱ ሁለት ሰላዮችን ወደ ኢያሪኮ የላከ ሲሆን እነሱም ረዓብ ከተባለች ጋለሞታ ጋር ተገናኙ። ረዓብ፣ ሰላዮቹን የኢያሪኮ ንጉሥ የላካቸው ሰዎች እንዳያገኟቸው ስትል በቤቷ ጣሪያ ላይ ደበቀቻቸው። ረዓብ፣ እስራኤላውያኑን ሰላዮች እንዲህ አለቻቸው፦ “እግዚአብሔር ይህችን  ምድር እንደሰጣችሁ . . . ዐውቃለሁ። . . . ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ . . . ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት . . . ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል።” አክላም “አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነው” አለቻቸው። (ኢያሱ 2:9-11) ረዓብ በወቅቱ ከነበረው የይሖዋ ድርጅት ጋር በመተባበሯ እስራኤላውያን ኢያሪኮን ድል ሲያደርጉ ይሖዋ እሷና ቤተሰቧ እንዲተርፉ አድርጓል። (ኢያሱ 6:25) ረዓብ እምነት ነበራት፤ እንዲሁም ይሖዋን እንደምትፈራና ለሕዝቡ አክብሮት እንዳላት አሳይታለች።

በመጀመሪያ መቶ ዘመን የነበረው የአምላክ ድርጅት

10. ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ምን ብሏቸዋል? እንዲህ ያላቸውስ ለምንድን ነው?

10 እስራኤላውያን በኢያሱ እየተመሩ የተለያዩ ከተሞችን ድል ያደረጉ ሲሆን በመጨረሻም የከነዓንን ምድር ተቆጣጠሩ። ይሁንና ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ምን ተከሰተ? እስራኤላውያን በከነዓን ምድር በኖሩባቸው ብዙ መቶ ዓመታት ውስጥ የአምላክን ሕግጋት በተደጋጋሚ ጊዜ ይጥሱ ነበር። ይሖዋ፣ ልጁን ወደ ምድር በላከበት ወቅት እስራኤላውያን አምላክን ለመታዘዝና መልእክተኞቹን ለመስማት ጨርሶ ፈቃደኞች አልነበሩም፤ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ፣ ስለ ኢየሩሳሌም ሲናገር “ነቢያትን የምትገድል” እንደሆነች ገልጿል። (ማቴዎስ 23:37, 38ን አንብብ።) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ታማኝ ባለመሆናቸው አምላክ ትቷቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል” ብሏቸዋል።—ማቴ. 21:43

11, 12. (ሀ) ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የእስራኤልን ብሔር እንደተወውና ሌላ ድርጅት እንዳቋቋመ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው አዲስ ድርጅት አባላት እነማን ነበሩ?

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ይሖዋ ታማኝ ያልሆነውን የእስራኤል ብሔር ሙሉ በሙሉ ተወው። ይህ ሲባል ግን በምድር ላይ ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹን ያቀፈ ድርጅት አይኖረውም ማለት አይደለም። ይሖዋ፣ ትኩረቱን ኢየሱስ ክርስቶስንና ትምህርቶቹን የሚከተሉ ታማኝ ሰዎችን ባቀፈ አዲስ ድርጅት ላይ አደረገ። ይህን ማድረጉን ያሳየው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ቀን ነበር። በዚያ ዕለት 120 የሚያህሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር፤ “ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው። የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።” (ሥራ 2:1-4) ይህ አስገራሚ ክስተት፣ ይሖዋ የክርስቶስን ተከታዮች ያቀፈውን ይህን አዲስ ድርጅት እየደገፈው እንዳለ የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ነበር።

12 በዚያ አስደሳች ቀን በኢየሱስ ተከታዮች ላይ “ሦስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ነፍሳት ተጨመሩ።” ከዚህም በላይ “ይሖዋ የሚድኑ ሰዎችን በየዕለቱ በእነሱ ላይ ይጨምር ነበር።” (ሥራ 2:41, 47) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እነዚያ ሰባኪዎች የሚያከናውኑት ሥራ እጅግ ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ “የአምላክ ቃል እያደገ ሄደ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ።” ሌላው ቀርቶ “በጣም ብዙ ካህናትም ይህን እምነት ተቀበሉ።” (ሥራ 6:7) የዚህ አዲስ ድርጅት አባላት የሚያውጁትን እውነት በርካታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሊቀበሉ ችለዋል። ውሎ አድሮ ደግሞ ይሖዋ ‘ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች’ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እንዲመጡ ባደረገበት ወቅት ይህን ድርጅት እየደገፈው መሆኑን የሚያሳይ ተመሳሳይ ነገር አድርጓል።—የሐዋርያት ሥራ 10:44, 45ን አንብብ።

13. የአምላክ አዲስ ድርጅት ሥራ ምን ነበር?

13 አምላክ፣ ለክርስቶስ ተከታዮች የሰጣቸው ሥራ ምን እንደሆነ ምንም የሚያጠራጥር ነገር አልነበረም። ኢየሱስ ራሱ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ ስለ “መንግሥተ ሰማያት” መስበክ ስለጀመረ ለተከታዮቹ ምሳሌ ትቶላቸዋል። (ማቴ. 4:17) ኢየሱስ ይህንኑ ሥራ እንዲያከናውኑ ደቀ መዛሙርቱን አሠልጥኗቸዋል። “በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ሥራ 1:8) በጥንት  ጊዜ የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች ከእነሱ የሚጠበቀው ምን እንደሆነ በግልጽ ተረድተው ነበር። ለምሳሌ ጳውሎስና በርናባስ፣ በጵስድያ በምትገኘው በአንጾኪያ ይቃወሟቸው ለነበሩ አይሁዳውያን እንዲህ ሲሉ በድፍረት ተናግረዋል፦ “የአምላክ ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገሩ አስፈላጊ ነበር። እናንተ ግን ወደ ጎን ገሸሽ እያደረጋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ እየፈረዳችሁ ስለሆነ እነሆ እኛ ወደ አሕዛብ ዞር እንላለን። እንዲያውም ይሖዋ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ መዳንን እንድታበስር የአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሾሜሃለሁ’ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶናል።” (ሥራ 13:14, 45-47) የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል፣ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ አምላክ ሰዎችን ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ሲያሳውቅ ቆይቷል።

ብዙዎች ቢጠፉም የአምላክ አገልጋዮች ተርፈዋል

14. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም ምን ሆነች? ሆኖም እነማን ተርፈዋል?

14 በጥቅሉ ሲታይ አይሁዳውያን ምሥራቹን አልተቀበሉም፤ ከፊታቸው ደግሞ ጥፋት ተደቅኖ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋቸዋል፦ “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ። በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማይቱ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ተፈጸመ። አይሁዳውያን በማመፃቸው ምክንያት በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው የሮም ሰራዊት በ66 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን ከበበ። ይሁንና ይህ ሰራዊት በድንገት ወደኋላ አፈገፈገ፤ ይህም የኢየሱስ ተከታዮች ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ እንዲወጡ አጋጣሚ ሰጣቸው። ዩሲቢየስ የተባለው የታሪክ ምሁር እንደገለጸው ብዙዎች ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር በፔሪያ ወደምትገኘው ፔላ ሸሽተዋል። በ70 ዓ.ም. በጄኔራል ቲቶ የሚመራው የሮም ሰራዊት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ በመምጣት ከተማዋን ድምጥማጧን አጠፋት። ታማኝ ክርስቲያኖች ግን የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመስማታቸው ሊድኑ ችለዋል።

15. የትኞቹ ሁኔታዎች እያሉም ክርስትና ሊስፋፋ ችሏል?

15 የክርስቶስ ተከታዮች መከራ፣ ስደትና ሌሎች የእምነት ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና መስፋፋት ችሎ ነበር። (ሥራ 11:19-21፤ 19:1, 19, 20) እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች የአምላክ በረከት ስላልተለያቸው በመንፈሳዊ በልጽገው ነበር።—ምሳሌ 10:22

16. እያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጤንነቱን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ነበረበት?

16 እያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጤንነቱን ለመጠበቅ በግሉ ጥረት ማድረግ ነበረበት። ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ማጥናት፣ ለአምልኮ አዘውትሮ መሰብሰብና በመንግሥቱ ስብከት ሥራ በቅንዓት መካፈል አስፈላጊ ነገሮች ነበሩ። በጥንት ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም እነዚህ ነገሮች ለይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊ ጤንነትም ሆነ አንድነት አስፈላጊ ናቸው። በጥንት ጊዜ ከነበሩት በሚገባ የተደራጁ ጉባኤዎች ጋር የሚተባበሩ ክርስቲያኖች፣ የበላይ ተመልካቾችና አገልጋዮች በፈቃደኝነት ከሚያከናውኑት ሥራ ትልቅ ጥቅም ያገኙ ነበር። (ፊልጵ. 1:1፤ 1 ጴጥ. 5:1-4) ጉባኤዎቹ እንደ ጳውሎስ ያሉ ተጓዥ ሽማግሌዎች እየመጡ ሲጎበኟቸው ምን ያህል ይደሰቱ እንደነበር መገመት አያዳግትም! (ሥራ 15:36, 40, 41) በዛሬው ጊዜ አምልኳችንን የምናከናውንበት መንገድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች አምልኳቸውን ከሚያካሂዱበት መንገድ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ ጥንትም ሆነ ዛሬ አገልጋዮቹን በማደራጀቱ ምንኛ አመስጋኝ ነን! *

17. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንወያየው ስለ ምንድን ነው?

17 የሰይጣን ዓለም ለመጥፋት በተቃረበበት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በከፍተኛ ፍጥነት ወደፊት እየገሰገሰ ነው። አንተስ ከዚህ ድርጅት እኩል እየተጓዝክ ነው? በመንፈሳዊ እድገት እያደረግክ ነው? ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

^ አን.16 “ክርስቲያኖች አምላክን በመንፈስና በእውነት ያመልካሉ” እና “በእውነት ይመላለሳሉ” የሚሉትን በሐምሌ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡ ርዕሶች ተመልከት። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? በተባለው ብሮሹር ላይ በዛሬው ጊዜ ስላለው የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል በሰፊው ተብራርቷል።