በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለመልካም ሥራ እየተጣጣርክ’ ነው?

‘ለመልካም ሥራ እየተጣጣርክ’ ነው?

ፈርናንዶ * ሁለት ሽማግሌዎች ሊያናግሩት እንደሚፈልጉ ስለገለጹለት በጣም ተጨንቋል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያቸውን በጎበኘባቸው ጊዜያት ሽማግሌዎቹ፣ ፈርናንዶ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ መብት ለማግኘት ብቁ እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለበት ጠቁመውታል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ሽማግሌ ሆኖ መሾም መቻሉን መጠራጠር ጀመረ። በቅርቡ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያቸውን ጎብኝቷል። ታዲያ ሽማግሌዎቹ ምን ሊሉት ይሆን?

ፈርናንዶ አንደኛው ሽማግሌ በሚናገርበት ጊዜ በጥሞና አዳመጠው። ወንድም 1 ጢሞቴዎስ 3:1ን ከጠቀሰ በኋላ የጉባኤው ሽማግሌዎች፣ ፈርናንዶ በሽምግልና መሾሙን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ገለጸለት። ፈርናንዶ በመገረም ቀና ብሎ እየተመለከተው “ምን አልከኝ?” አለው። ወንድም የተናገረውን ደገመለት፤ በዚህ ጊዜ ፈርናንዶ ፈገግ አለ። ከዚያም ሹመቱ ለጉባኤው ሲነገር ሁሉም ደስ አላቸው።

በጉባኤ ውስጥ መብት ለማግኘት መፈለግ ስህተት ነው? በፍጹም። 1 ጢሞቴዎስ 3:1 “የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ማንኛውም ሰው መልካም ሥራን ይመኛል” ይላል። በርካታ ክርስቲያን ወንዶች ይህን ምክር በሥራ ላይ የሚያውሉ ሲሆን መንፈሳዊ እድገት በማድረግ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ መብቶች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም ምክንያት የአምላክ ሕዝቦች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በማግኘት ተባርከዋል። ይሁንና የጉባኤዎች ቁጥር እየበዛ በመሆኑ ተጨማሪ ወንድሞች እዚህ መብት ላይ ለመድረስ መጣጣር ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚቻልበት ትክክለኛው አካሄድ ምንድን ነው? ደግሞስ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚፈልጉ ወንድሞች ‘እዚህ መብት ላይ የምደርሰው መቼ ነው?’ የሚለው ጉዳይ ልክ እንደ ፈርናንዶ ነጋ ጠባ ሊያሳስባቸው ይገባል?

‘መጣጣር’ ሲባል ምን ማለት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የሚጣጣር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ አጥብቆ መፈለግን እና አንድ ነገር ላይ ለመድረስ መንጠራራትን ያመለክታል። ይህም አንድን ጣፋጭ ፍሬ ከዛፍ ላይ ለመቅጠፍ የሚንጠራራን ሰው ወደ አእምሮህ ያመጣ ይሆናል። መጣጣር ሲባል ግን በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ  “የበላይ ተመልካች ለመሆን” መፈለግ ማለት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሽማግሌ ለመሆን በቅንነት የሚጣጣሩ ወንድሞች ግባቸው ሥልጣን ማግኘት ሳይሆን “መልካም ሥራ” መሥራት ነው።

ለዚህ መልካም ሥራ ብቁ ለመሆን የሚያስፈልጉት መሥፈርቶች በ1 ጢሞቴዎስ 3:2-7 እና በቲቶ 1:5-9 ላይ ተዘርዝረዋል። ሬይመንድ የተባለ ተሞክሮ ያለው ሽማግሌ እነዚህን ከፍ ያሉ መሥፈርቶች በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “እንደ እኔ አመለካከት ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ማንነታችን ነው። አንድ የበላይ ተመልካች የመናገርና የማስተማር ችሎታ ያለው መሆኑ አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም እነዚህ ችሎታዎች ያሉት መሆኑ የማይነቀፍ፣ በልማዶቹ ልከኛ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ሥርዓታማ፣ እንግዳ ተቀባይና ምክንያታዊ የመሆኑን አስፈላጊነት አይቀንሰውም።”

በጉባኤ ውስጥ የተለያዩ ኃላፊነቶችን በመወጣት ‘ለመልካም ሥራ ተጣጣር’

ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር በሚስማማ መንገድ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ወንድም ከማንኛውም ዓይነት ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ወይም ርኩሰት በመራቅ የማይነቀፍ ለመሆን ጥረት ያደርጋል። በልማዶቹ ልከኛ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ሥርዓታማና ምክንያታዊ ስለሆነ የእምነት ባልንጀሮቹ እሱ በሚሰጠው አመራር ይተማመናሉ፤ እንዲሁም ችግር ሲያጋጥማቸው እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ናቸው። እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ለወጣቶችም ሆነ ለአዲሶች የብርታት ምንጭ ነው። ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወድ ስለሆነ የታመሙትንና አረጋውያንን ያጽናናል፤ እንዲሁም ይረዳል። እነዚህን ባሕርያት የሚያዳብረው ወንድሞቹን ለመርዳት ስለሚፈልግ እንጂ ሹመት ለማግኘት ብሎ አይደለም። *

የሽማግሌዎች አካል፣ ኃላፊነት ላይ ለመድረስ ለሚጣጣር አንድ ወንድም ምክርና ማበረታቻ የሚሰጥ ቢሆንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶቹን የማሟላቱ ኃላፊነት በዋነኝነት የሚወድቀው በግለሰቡ ላይ ነው። ሄንሪ የተባለ ተሞክሮ ያካበተ የበላይ ተመልካች “ኃላፊነት ላይ ለመድረስ የምትጣጣር ከሆነ ብቃቶቹን ማሟላትህን ለማሳየት ጠንክረህ ሥራ” በማለት ተናግሯል። ሄንሪ መክብብ 9:10ን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “‘እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው።’ ሽማግሌዎቹ የሚሰጡህን ኃላፊነት ሁሉ ለመወጣት የምትችለውን ያህል ጥረት አድርግ። ወለል ማጽዳትን ጨምሮ በጉባኤ ውስጥ የሚሰጥህን ማንኛውንም ሥራ ውደደው። የምታከናውነው ሥራና ጥረትህ ውሎ አድሮ ልብ መባሉ አይቀርም።” በሽምግልና የማገልገል ግብ ካለህ በሁሉም የቅዱስ አገልግሎት ዘርፎች ትጉህ ሠራተኛ እንዲሁም እምነት የሚጣልብህ መሆንህን አሳይ። በሕይወትህ ውስጥ  ጎልቶ መታየት ያለበት ባሕርይ ትሕትና እንጂ ኩራትና የሥልጣን ጥም ሊሆን አይገባም።—ማቴ. 23:8-12

ተገቢ ያልሆነ አመለካከትንና ድርጊትን አስወግድ

በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ማግኘት የሚፈልጉ አንዳንድ ወንድሞች ሽማግሌ መሆን እንደሚፈልጉ ለመጠቆም ወይም በሽማግሌዎች አካል ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክሩ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ሽማግሌዎች ምክር ሲሰጧቸው ላይደሰቱ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ወንድሞች ‘ፍላጎቴ የራሴን ጥቅም ማራመድ ነው? ወይስ የይሖዋን በጎች በትሕትና መንከባከብ?’ ብለው ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል።

ኃላፊነት ለማግኘት የሚጣጣሩ ወንድሞች ሊዘነጉት የማይገባው ሌላው ነገር ደግሞ ሽማግሌዎች “ለመንጋው ምሳሌ [መሆን]” እንዳለባቸው ነው። (1 ጴጥ. 5:1-3) ለጉባኤው ምሳሌ የሚሆን ወንድም ተንኮል ከሚንጸባረቅበት አስተሳሰብና ድርጊት መራቅ ይኖርበታል። ሽማግሌ ሆነም አልሆነ በትዕግሥት የመጽናትን ባሕርይ ለማዳበር ይጥራል። አንድ ወንድም፣ ሽማግሌ ሲሆን ድክመቶቹ ሁሉ በተአምር ይወገዳሉ ማለት አይደለም። (ዘኍ. 12:3፤ መዝ. 106:32, 33) ከዚህም ሌላ አንድ ወንድም ‘ሕሊናውን የሚወቅሰው ምንም ነገር’ ባይኖርም እንኳ ሌሎች ስለ እሱ ጥሩ አመለካከት እንዳይኖራቸው የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ይኖሩ ይሆናል። (1 ቆሮ. 4:4) በመሆኑም ሽማግሌዎች ለአንተ በማሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ቢሰጡህ ሳትበሳጭ ለማዳመጥ ሞክር። ከዚያም ምክሩን በተግባር ለማዋል ጥረት አድርግ።

ለረጅም ጊዜ እንደጠበቅህ ቢሰማህስ?

በርካታ ወንድሞች ሽማግሌ ሆነው ከመሾማቸው በፊት ለረጅም ጊዜ እንደጠበቁ ይሰማቸዋል። ‘የበላይ ተመልካች ለመሆን ስትጣጣር’ ብዙ ዓመታት ቢያልፉ ትዕግሥትህ ያልቅ ይሆን? ከሆነ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ “ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል፤ የተሳካ ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ነው።”—ምሳሌ 13:12

አንድ ሰው የሚወደው ግብ ላይ መድረስ እንደማይችል ሲሰማው ልቡ ያዝን ይሆናል። አብርሃም እንዲህ ተሰምቶት ነበር። ይሖዋ፣ ልጅ እንደሚሰጠው ቃል ቢገባለትም እሱና ሣራ ልጅ ሳይወልዱ ዓመታት አለፉ። (ዘፍ. 12:1-3, 7) አብርሃም ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “አምላክ ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለ ሆንሁ፣ . . . ምን ትሰጠኛለህ? . . . አንተ ልጆች [አልሰጠኸኝም]።” ይሖዋም ልጅ እንደሚሰጠው የገባውን ቃል እንደሚፈጽም አረጋገጠለት። ሆኖም አምላክ ይህን ካለ በኋላ ቃሉን ከመፈጸሙ በፊት ቢያንስ 14 ዓመታት አልፈዋል።—ዘፍ. 15:2-4፤ 16:16፤ 21:5

አብርሃም፣ ይህ እስኪሆን ይጠባበቅ በነበረበት ወቅት በይሖዋ አገልግሎት የሚያገኘውን ደስታ አጥቶ ይሆን? በፍጹም። አብርሃም፣ አምላክ የገባውን ቃል ተጠራጥሮ አያውቅም። መልካም ነገር እንደሚመጣ ይጠብቅ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ይህን የተስፋ ቃል አገኘ” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 6:15) ከጊዜ በኋላም፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይህን ታማኝ ሰው ከጠበቀው በላይ አትረፍርፎ ባርኮታል። ታዲያ ከአብርሃም ምን ትምህርት ታገኛለህ?

በሽምግልና ማገልገል ብትፈልግም ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ እዚህ ግብ ላይ አልደረስክ ይሆናል፤ ያም ቢሆን በይሖዋ መታመንህን ቀጥል። እንዲሁም በእሱ አገልግሎት የምታገኘውን ደስታ ላለማጣት ጥረት አድርግ። በርካታ ወንድሞች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የረዳ ዎረን የተባለ አንድ ወንድም ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሽማግሌ ሆኖ ለመሾም የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ጊዜ ይፈልጋል። የአንድ ወንድም ችሎታና ዝንባሌ ከምግባሩ እንዲሁም የተሰጠውን ኃላፊነት  ከሚወጣበት መንገድ በጊዜ ሂደት ይታያል። አንዳንዶች በይሖዋ አገልግሎት ጥሩ ነገር አከናወኑ የሚባለው ሽማግሌ ሆነው ከተሾሙ ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የተሳሳተ ከመሆኑም ሌላ መብት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል። ይሖዋን በታማኝነት እስካገለገልክ ድረስ የትም ብትሆን እንዲሁም ምንም ብታከናውን ስኬታማ ነህ።”

አንድ ወንድም፣ ሽማግሌ ለመሆን ከአሥር ዓመት በላይ ጠብቋል። ይህ ወንድም በሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 ላይ የሚገኘውን የታወቀ ሐሳብ በመጥቀስ፣ ያገኘውን ትምህርት እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “ይሖዋ ሠረገላውን ማለትም ድርጅቱን የሚያንቀሳቅሰው እሱ በፈለገው ፍጥነት ነው። ለውጥ የሚያመጣው እኛ ኃላፊነት ለማግኘት ብቁ እንደሆንን የምናስብበት ጊዜ ሳይሆን ይሖዋ ብቃቱን እንዳሟላን የሚያስብበት ጊዜ ነው። ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ከመፈለግ ጋር በተያያዘ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እኔ የምፈልገው ወይም ለመሆን የምመኘው ነገር አይደለም። እኔ የምፈልገው ነገር፣ ይሖዋ እንደሚያስፈልገኝ ከሚሰማው ነገር የተለየ ሊሆን ይችላል።”

የክርስቲያን ጉባኤ የበላይ ተመልካች በመሆን መልካም ሥራ ለማከናወን የምትፈልግ ከሆነ ለጉባኤው ደስታ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነገር ለመሥራት መጣጣር ይኖርብሃል። እዚህ መብት ላይ የምትደርስበት ጊዜ እንደዘገየ ቢሰማህም እንኳ ታጋሽ ሁን። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሬይመንድ እንዲህ ብሏል፦ “መብት ለማግኘት በጣም የሚጓጓ ሰው ባለው ሊረካ አይችልም። በትዕግሥት መጠበቅ የማይችሉ ሰዎች ይሖዋን ከማገልገል የሚገኘውን ታላቅ ደስታ ማጣጣም አይችሉም።” የአምላክን መንፈስ ፍሬ በተለይም ትዕግሥትን ይበልጥ ለማዳበር ጥረት አድርግ። ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት መንፈሳዊነትህን ለማጎልበት ተግተህ ሥራ። ምሥራቹን በመስበክና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናቱ ሥራ ይበልጥ ተሳትፎ አድርግ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችና በቤተሰብ አምልኮ ቅድሚያውን ወስደህ ቤተሰብህን ምራ። ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሞክር። ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ በይሖዋ አገልግሎት ደስታ ታገኛለህ።

በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለማግኘት የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ጥረት ማድረግ ይሖዋ የሰጠን ግሩም መብት ነው፤ ይሖዋም ሆነ ድርጅቱ ኃላፊነት ለማግኘት የሚጣጣሩ ወንድሞች በእሱ አገልግሎት ተስፋ እንዲቆርጡ ወይም ደስታ እንዲያጡ አይፈልጉም። አምላክ በቅን ልቦና ተነሳስተው የሚያገለግሉትን ሁሉ ይደግፋል እንዲሁም ይባርካቸዋል። እንደ ሌሎቹ በረከቶች ሁሉ ይሖዋ ይህንን በረከት ሲሰጥ ‘መከራ አያክልበትም።’—ምሳሌ 10:22

ኃላፊነት ላይ ለመድረስ ረዘም ላለ ጊዜ ስትጣጣር ብትቆይም በመንፈሳዊ እድገት ማድረግህን መቀጠል ትችላለህ። አስፈላጊ የሆኑትን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት የምታደርግና ቤተሰብህን ችላ ሳትል በጉባኤ ውስጥ ተግተህ የምትሠራ ከሆነ ይሖዋ እሱን ለማገልገል ያደረግከውን ነገር ፈጽሞ አይረሳውም። በሕይወትህ ውስጥ ምንም ዓይነት ኃላፊነት ቢሰጥህ ይሖዋን ማገልገል ምንጊዜም አስደሳች እንዲሆንልህ እንመኛለን።

^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.8 በዚህ ርዕስ ላይ የቀረቡት መሠረታዊ ሥርዓቶች የጉባኤ አገልጋይ መሆን ለሚፈልጉም ይሠራሉ። ማሟላት የሚጠበቅባቸው ብቃቶች በ1 ጢሞቴዎስ 3:8-10, 12, 13 ላይ ይገኛሉ።