በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አእምሯችሁ ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ’

‘አእምሯችሁ ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ’

“አእምሯችሁ በምድር ባሉት ነገሮች ላይ ሳይሆን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ።”—ቆላ. 3:2

1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የቆላስይስ ጉባኤ ምን አደገኛ ሁኔታ ተጋርጦበት ነበር? (ለ) የቆላስይስ ወንድሞች እንዲጸኑ ለመርዳት ምን ምክር ተሰጥቷቸው ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የቆላስይስ ጉባኤ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነበር! አንዳንድ የጉባኤው አባላት የሙሴን ሕግ መከተል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ በጉባኤው ውስጥ መከፋፈል ፈጥረው ነበር። ሌሎች ደግሞ ከመጠን በላይ ራስን በመጨቆን የባሕታዊ ዓይነት ሕይወት መምራትን የሚያበረታታውን የአረማውያን ፍልስፍና ያስፋፉ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን የሐሰት ትምህርቶች በመቃወም የቆላስይስን ክርስቲያኖች የሚያበረታታ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል፤ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፦ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።”—ቆላ. 2:8

2 እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አእምሯቸው በዚህ “ዓለም መሠረታዊ ነገሮች” ላይ እንዲያተኩር ካደረጉ ለይሖዋ የመዳን ዝግጅት ጀርባቸውን መስጠት ይሆንባቸዋል። (ቆላ. 2:20-23) ጳውሎስ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ውድ ዝምድና ጠብቀው እንዲቆዩ ለመርዳት ሲል “አእምሯችሁ በምድር ባሉት ነገሮች ላይ ሳይሆን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ቆላ. 3:2) አዎን፣ የክርስቶስ ወንድሞች አእምሯቸው ‘በሰማይ በሚጠብቃቸው’ የማይጠፋ ውርሻ ላይ ምንጊዜም እንዲያተኩር  ማድረግ ነበረባቸው።—ቆላ. 1:4, 5

3. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች አእምሯቸው ምንጊዜም በየትኛው ተስፋ ላይ ያተኮረ ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት እና ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ ለመሆን ባላቸው ተስፋ ላይ አእምሯቸው ምንጊዜም እንዲያተኩር ያደርጋሉ። (ሮም 8:14-17) ይሁንና ምድራዊ ተስፋ ስላላቸው ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል? ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ ለእነሱ የሚሠራው እንዴት ነው? “ሌሎች በጎች” አእምሯቸው “ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር” ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ዮሐ. 10:16) ሁላችንም ብንሆን፣ የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም አእምሯቸው ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ያደረጉ እንደ አብርሃምና ሙሴ ያሉ የጥንት ታማኝ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ በመመርመር ጥቅም ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው?

አእምሯችን በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?

4. ሌሎች በጎች አእምሯቸው ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

4 ሌሎች በጎች ሰማያዊ ተስፋ ባይኖራቸውም እነሱም አእምሯቸው ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይችላሉ። እንዴት? በሕይወታቸው ውስጥ ለይሖዋ አምላክና ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ነው። (ሉቃስ 10:25-27) በዚህ ረገድ ክርስቶስ አርዓያ ይሆነናል። (1 ጴጥ. 2:21) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ወንድሞቻችን ሁሉ እኛም በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ ስለምንኖር በተሳሳተ አስተሳሰብ፣ በዓለም ፍልስፍና እንዲሁም ለቁሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በሚሰጡ ሰዎች ተከብበናል። (ቆላስይስ 2:20-23ን አንብብ።) የኢየሱስን አርዓያ የምንከተል እንደመሆናችን መጠን በመንፈሳዊነታችን ላይ የሚሰነዘሩ እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን ለመከላከል ንቁ መሆን አለብን።

5. ስለ ቁሳዊ ነገሮች ያለንን አመለካከት መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?

5 ዓለም ስለ ቁሳዊ ነገሮች ያለው አመለካከት በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሮ ይሆን? በአብዛኛው፣ የምናስበውና የምናደርገው ነገር ምን እንደምንወድ በግልጽ ያሳያል። ኢየሱስ “ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናል” ብሏል። (ማቴ. 6:21) ልባችን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ አልፎ አልፎ ራሳችንን መመርመራችን ጠቃሚ ነው። እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ከገንዘብ ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ምን ያህል አስባለሁ? የተሻሉ ስለሚባሉ የሥራ ወይም የንግድ አጋጣሚዎች አሊያም ይበልጥ የተደላደለ ሕይወት ስለ መምራት በመጨነቅ ብዙ ጊዜ አጠፋለሁ? ወይስ ዓይኔ ምንጊዜም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ጥረት አደርጋለሁ?’ (ማቴ. 6:22) ‘በምድር ሀብት በማከማቸት’ ላይ ዋነኛ ትኩረታቸውን የሚያደርጉ ሰዎች ከመንፈሳዊነታቸው ጋር በተያያዘ ከባድ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ኢየሱስ ጠቁሟል።—ማቴ. 6:19, 20, 24

6. ከሥጋዊ ፍላጎታችን ጋር የምናደርገውን ትግል ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

6 ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ሥጋዊ ፍላጎታችንን በሚያረኩ ነገሮች ላይ እንድናተኩር የሚገፋፋ ዝንባሌ አለን። (ሮም 7:21-25ን አንብብ።) የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ ባይሠራ ኖሮ ‘በጨለማ ሥራ’ እንሸነፍ ነበር። የጨለማ ሥራ የሚለው አገላለጽ ‘መረን የለቀቀ ፈንጠዝያንና ስካርን፣ ልቅ የሆነ የፆታ ግንኙነትንና ብልግናን’ ይጨምራል። (ሮም 13:12, 13) “በምድር ባሉት ነገሮች” ማለትም ለሥጋችን አጓጊ በሆኑ ነገሮች ላለመሸነፍ የምናደርገውን ውጊያ በድል መወጣት እንድንችል አእምሯችን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ደግሞ ጥረት ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰውነቴን እየጎሰምኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 9:27) በሕይወት ሩጫ መቀጠል ከፈለግን በዚህ ረገድ ዘና ማለት እንደሌለብን ግልጽ ነው! በጥንት ዘመን የኖሩ ሁለት ታማኝ  ሰዎች “አምላክን በሚገባ ደስ [ለማሰኘት]” ምን እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት።—ዕብ. 11:6

አብርሃም ‘ይሖዋን አመነ’

7, 8. (ሀ) አብርሃምና ሣራ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ገጥመዋቸው ነበር? (ለ) አብርሃም አእምሮው በምን ላይ እንዲያተኩር አድርጓል?

7 አብርሃም ቤተሰቡን ይዞ ወደ ከነዓን ምድር እንዲሄድ ይሖዋ ሲነግረው በፈቃደኝነት ይህን አድርጓል። አብርሃም እምነት ስላሳየና ስለታዘዘ ይሖዋ “ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ” በማለት ቃል ኪዳን ገባለት። (ዘፍ. 12:2) ይሁንና ዓመታት ካለፉም በኋላ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ልጅ አልነበራቸውም። ታዲያ ይሖዋ ለአብርሃም የገባለትን ቃል ረስቶት ይሆን? በዚያ ላይ ደግሞ ከነዓን ውስጥ ሕይወት ቀላል አልነበረም። አብርሃምና ቤተሰቡ፣ ዘመዶቻቸውንና ቤታቸውን ትተው በሜሶጶጣሚያ ከምትገኘው ዑር የተባለች የበለጸገች ከተማ ወጥተዋል። ከነዓን ለመድረስ ከ1,600 ኪሎ ሜትር በላይ የተጓዙ ሲሆን በዚያም የሚኖሩት በድንኳን ውስጥ ነበር፤ እንዲሁም በከነዓን ሲኖሩ ከባድ ረሃብና ዘራፊዎች አጋጥመዋቸው ነበር። (ዘፍ. 12:5, 10፤ 13:18፤ 14:10-16) ያም ሆኖ በዑር ወደነበረው የተመቻቸ ቤታቸው ለመመለስ ጨርሶ አላሰቡም!—ዕብራውያን 11:8-12, 15ን አንብብ።

8 አብርሃም “በምድር ባሉት ነገሮች ላይ” ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በይሖዋ ‘አምኗል።’ (ዘፍ. 15:6) አእምሮው ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጓል፤ በሌላ አባባል ትኩረቱ ያረፈው አምላክ በገባው ቃል ላይ ነበር። እንዲህ ዓይነት እምነት በማሳየቱም ተክሷል፤ ሉዓላዊ የሆነው አምላክ ለአብርሃም ተገልጦ እንደሚከተለው ብሎታል፦ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቍጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቍጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል።” (ዘፍ. 15:5) ይህ የአብርሃምን እምነት ምንኛ አጠናክሮት ይሆን! አብርሃም በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ባየ ቁጥር ይሖዋ ዘሩን እንደሚያበዛለት የገባለትን ቃል ማስታወሱ አይቀርም። ደግሞም አምላክ፣ ቃል በገባው መሠረት እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለአብርሃም ወራሽ ሰጠው።—ዘፍ. 21:1, 2

9. የአብርሃምን ምሳሌ መከተላችን በአምላክ አገልግሎት እንድንጠመድ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

9 እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም አምላክ የገባው ቃል የሚፈጸምበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ነው። (2 ጴጥ. 3:13) አእምሯችን በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ካላደረግን እነዚህ ተስፋዎች የሚፈጸሙበት ጊዜ እንደዘገየ ሊሰማንና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚኖረንን ተሳትፎ ልንቀንስ እንችላለን። ለምሳሌ፣ አቅኚ ለመሆን ወይም በሌላ መንገድ አገልግሎትህን ለማስፋት ስትል ከዚህ ቀደም መሥዋዕትነት ከፍለሃል? ከሆነ እንዲህ ማድረግህ የሚደነቅ ነው። ታዲያ አሁንስ? አብርሃም አእምሮው ‘እውነተኛ መሠረት ባላት ከተማ’ ላይ እንዲያተኩር እንዳደረገ አስታውስ። (ዕብ. 11:10) ቅዱሳን መጻሕፍት “በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለው አሳየ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” ይላሉ።—ሮም 4:3

ሙሴ “የማይታየውን” አይቷል

10. ሙሴ ወጣት እያለ ምን ዓይነት ሕይወት ነበረው?

10 አእምሮው ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ያደረገው ሌላው ሰው ደግሞ ሙሴ ነው። ወጣት ሳለ “የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ” ተምሮ ነበር። የቀሰመው ትምህርት እንደ ተራ የሚታይ አልነበረም። በወቅቱ ግብፅ የዓለም ታላቅ ኃይል ነበረች፤ ሙሴ ደግሞ የሚኖረው በፈርዖን ቤት ነበር። ሙሴ ካገኘው ከፍተኛ ትምህርት አንጻር “በንግግሩና በተግባሩ ብርቱ” መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። (ሥራ 7:22) ሊያገኛቸው ይችል የነበሩትን አጋጣሚዎች እስቲ ለማሰብ ሞክር! ሙሴ ግን ያተኮረው ከዚያ በላቁ ነገሮች ይኸውም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ነበር።

11, 12. ሙሴ ከፍ አድርጎ የተመለከተው የትኛውን ትምህርት ነው? ይህን እንዴት እናውቃለን?

11 ሙሴ ትንሽ ልጅ እያለ እናቱ ዮካብድ፣ የዕብራውያን አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ እንዳስተማረችው ጥርጥር የለውም። ሙሴ ስለ ይሖዋ ያገኘውን እውቀት ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል፤ እንዲሁም ሊያገኝ ከሚችለው ከማንኛውም ሀብት የላቀ እንደሆነ ተገንዝቧል። በመሆኑም በፈርዖን ቤት በመኖሩ የሚያገኛቸውን መብቶችና አጋጣሚዎች ለመተው ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብራውያን 11:24-27ን አንብብ።) በእርግጥም ሙሴ ያገኘው  መንፈሳዊ ትምህርትና በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት አእምሮው በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል።

12 ሙሴ በዘመኑ ከነበረው ሁሉ የላቀውን ሰብዓዊ ትምህርት አግኝቶ ነበር፤ ሆኖም ይህን ሥልጠና የተጠቀመበት በግብፅ ትልቅ ቦታ ለማግኘት፣ ስሙን ለማስጠራት ወይም ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ነው? በፍጹም። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ “የፈርዖን ሴት ልጅ፣ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እምቢ አለ፤ በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን መረጠ” ሊባልለት አይችልም ነበር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሙሴ ያገኘውን መንፈሳዊ ትምህርት የይሖዋን ዓላማ ለማራመድ ተጠቅሞበታል።

13, 14. (ሀ) ሙሴ፣ ይሖዋ ለሚሰጠው ኃላፊነት ዝግጁ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? (ለ) እንደ ሙሴ ሁሉ እኛም ምን ማድረግ ሊኖርብን ይችላል?

13 ሙሴ ለይሖዋና ለሕዝቡ ጥልቅ ፍቅር ነበረው። ሙሴ 40 ዓመት ሲሆነው የአምላክን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ነፃ ማውጣት እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። (ሥራ 7:23-25) ይሁንና ይህን ኃላፊነት ከይሖዋ ከመቀበሉ በፊት ማድረግ የሚገባው ነገር ነበር። እንደ ትሕትና፣ ትዕግሥት፣ ገርነትና ራስን መግዛት ያሉትን ባሕርያት ማዳበር ነበረበት። (ምሳሌ 15:33) ሙሴ ከፊቱ የሚጠብቁትን አስቸጋሪና ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት እንዲዘጋጅ የሚረዳውን ሥልጠና ማግኘት ያስፈልገው ነበር። እረኛ ሆኖ ያሳለፋቸው ጥቂት አሥርተ ዓመታት አምላክ የሚፈልጋቸውን እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር ረድተውታል።

14 ታዲያ ሙሴ እረኛ ሆኖ ካገኘው ተግባራዊ የሆነ ሥልጠና ጥቅም አግኝቷል? አዎን! የአምላክ ቃል እንደሚለው “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” ሆኗል። (ዘኁ. 12:3) ሙሴ ትሕትና ያዳበረ ሲሆን ይህም የተለያዩ ሰዎችንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በትዕግሥት ለመያዝ ረድቶታል። (ዘፀ. 18:26) እኛም በተመሳሳይ “ታላቁን መከራ” አልፈን ጽድቅ ወደሰፈነበት የአምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት የሚረዱንን መንፈሳዊ ባሕርያት ማዳበር ያስፈልገን ይሆናል። (ራእይ 7:14) ቁጡና በቀላሉ የሚጎዱ እንደሆኑ የሚሰማንን ሰዎች ጨምሮ ከሌሎች ጋር ተስማምተን መኖር እንችላለን? ሐዋርያው ጴጥሮስ ለእምነት ባልንጀሮቹ የሰጠውን “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” የሚለውን ምክር ልብ ማለታችን ጠቃሚ ነው።—1 ጴጥ. 2:17

አእምሯችን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ

15, 16. (ሀ) አእምሯችን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች መልካም ምግባር ይዘው መኖር ያለባቸው ለምንድን ነው?

15 የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) በመሆኑም በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር አእምሯችን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል። (1 ተሰ. 5:6-9) በሕይወታችን ውስጥ ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት።

16 ምግባራችን፦ ጴጥሮስ መልካም ምግባር ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እነሱ ራሳቸው በዓይናቸው ባዩት መልካም ሥራችሁ የተነሳ አምላክን እንዲያከብሩ በአሕዛብ መካከል መልካም ምግባር ይዛችሁ ኑሩ።” (1 ጴጥ. 2:12) በቤታችንም ሆነ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ስንሆን አሊያም ስንዝናና ወይም ስናገለግል በመልካም ምግባራችን ለይሖዋ ክብር ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ስህተት እንሠራለን። (ሮም 3:23) ሆኖም “መልካሙን የእምነት ተጋድሎ” መጋደላችንን ከቀጠልን ከአለፍጽምናችን ጋር የምናደርገውን ትግል በድል መወጣት እንችላለን።—1 ጢሞ. 6:12

17. ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረውን አስተሳሰብ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

17 አስተሳሰባችን፦ ትክክለኛ አስተሳሰብ ማዳበር መልካም ምግባር ይዞ ከመኖር ጋር የተሳሰረ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር” ብሏል። (ፊልጵ. 2:5) ኢየሱስ ምን ዓይነት አስተሳሰብ  ያለው ሰው ነበር? ትሑት ሰው ነበር። ትሕትና በአገልግሎት ላይ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት እንዲያደርግ አነሳስቶታል። በአእምሮው ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነበር። (ማር. 1:38፤ 13:10) ኢየሱስ የአምላክን ቃል እንደ ከፍተኛው ባለሥልጣን አድርጎ ተመልክቶታል። (ዮሐ. 7:16፤ 8:28) ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ያጠና ነበር፤ በመሆኑም ከአምላክ ቃል ጠቅሶ መናገር፣ ለቃሉ ጥብቅና መቆም እንዲሁም ቃሉን ማብራራት ችሏል። እኛም ትሕትናን በማዳበር፣ በአገልግሎታችን ቀናተኛ በመሆንና መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት የክርስቶስን ዓይነት አስተሳሰብ ይበልጥ ማዳበር እንችላለን።

በኢየሱስ አእምሮ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ነገር የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነበር (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

18. የይሖዋን ሥራ በየትኛው አስፈላጊ መንገድ መገደፍ እንችላለን?

18 ጥረታችን፦ የይሖዋ ዓላማ “በሰማይና በምድር . . . ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው።” (ፊልጵ. 2:9-11) ኢየሱስ የላቀ ቦታ ቢሰጠውም ለአባቱ ፈቃድ በትሕትና ይገዛል፤ እኛም የእሱን ምሳሌ ልንከተል ይገባል። (1 ቆሮ. 15:28) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እንድንሠራው የተሰጠንን ሥራ ይኸውም ‘ብሔራትን ደቀ መዛሙርት’ የማድረጉን ሥራ በሙሉ ልባችን ለመደገፍ በመጣር ነው። (ማቴ. 28:19) በተጨማሪም ‘ለሁሉም ሰዎች’ ይኸውም ለባልንጀራችንም ሆነ ለወንድሞቻችን “መልካም ነገር እናድርግ።”—ገላ. 6:10

19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

19 አእምሯችን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ይሖዋ ለሚሰጠን ማሳሰቢያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! አእምሯችን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር “ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት [መሮጥ]” ይኖርብናል። (ዕብ. 12:1) እንግዲያው ሁላችንም ‘ለይሖዋ እንደምናደርገው በማሰብ በሙሉ ነፍሳችን’ እንሥራ፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በሰማይ ያለው አባታችን ጥረታችንን ይባርክልናል።—ቆላ. 3:23, 24