በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢየሱስ ትንሣኤ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

የኢየሱስ ትንሣኤ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

‘ኢየሱስ ተነስቷል።’ማቴ. 28:6

1, 2. (ሀ) አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ምን ጥያቄ አንስተው ነበር? ጴጥሮስስ ምን ምላሽ ሰጠ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ ድፍረት እንዲያሳይ የረዳው ምንድን ነው?

ኢየሱስ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኃይለኛ በሆኑና በጥላቻ በተሞሉ ሰዎች ፊት ቀረበ። እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ሲሆኑ ኢየሱስ እንዲገደል ሁኔታዎችን ያቀነባበሩትም እነሱ ናቸው። ሰዎቹ ጴጥሮስን በጥያቄ አፋጠጡት። ጴጥሮስ፣ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ሽባ የሆነን ሰው በመፈወሱ ይህን ያደረገው በምን ሥልጣን ወይም በማን ስም እንደሆነ የሃይማኖት መሪዎቹ ጠየቁት። ሐዋርያው በድፍረት እንዲህ የሚል መልስ ሰጣቸው፦ “ይህ ሰው . . . ጤናማ ሆኖ እዚህ ፊታችሁ የቆመው፣ እናንተ በሰቀላችሁት ሆኖም አምላክ ከሞት ባስነሳው በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም [ነው]።”—ሥራ 4:5-10

2 ከዚህ በፊት ጴጥሮስ በፍርሃት ስለራደ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ክዶት ነበር። (ማር. 14:66-72) ታዲያ አሁን በሃይማኖት መሪዎቹ ፊት ሲቀርብ በድፍረት እንዲናገር የረዳው ምንድን ነው? በዚህ ረገድ መንፈስ ቅዱስ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ጥያቄ የለውም፤ ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኛ መሆኑ በድፍረት እንዲናገር ረድቶታል። ይሁንና ሐዋርያው፣ ኢየሱስ ሕያው መሆኑን እርግጠኛ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? እኛስ እንዲህ ዓይነት እምነት እንዲኖረን የሚያደርገው ምንድን ነው?

3, 4. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት ከመወለዳቸው በፊት የትኞቹ ትንሣኤዎች ተከናውነው ነበር? (ለ) ኢየሱስ እነማንን ከሞት አስነስቷል?

 3 የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ ማግኘታቸው ለኢየሱስ ሐዋርያት አዲስ ነገር አልነበረም፤ እነሱ ከመወለዳቸው በፊት እንኳ ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ነበሩ። አምላክ ለነቢዩ ኤልያስና ለነቢዩ ኤልሳዕ የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ኃይል እንደሰጣቸው ያውቃሉ። (1 ነገ. 17:17-24፤ 2 ነገ. 4:32-37) እንዲያውም በአንድ ወቅት የአንድ ሰው ሬሳ የኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ወድቆ የነቢዩን አፅም በመንካቱ ግለሰቡ ከሞት ተነስቷል። (2 ነገ. 13:20, 21) እኛ የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን እንደምናምን ሁሉ የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም እነዚህ ዘገባዎች እውነት እንደሆኑ ያምኑ ነበር።

4 ኢየሱስ ከሞት ያስነሳቸውን ሰዎች ዘገባ ስናነብ የሁላችንም ልብ እንደሚነካ የታወቀ ነው። ኢየሱስ የመበለቷን ብቸኛ ልጅ ከሞት ሲያስነሳ እናቱ በጣም ተደስታ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 7:11-15) በሌላ ወቅት ደግሞ አንዲት የ12 ዓመት ልጅ ከሞት አስነስቷል። በሐዘን ተደቁሰው የነበሩት የልጅቷ ወላጆች ልጃቸው ስትነሳ የተሰማቸውን የደስታና የአድናቆት ስሜት መገመት አያዳግትም! (ሉቃስ 8:49-56) አልዓዛር ሕያውና ጤነኛ ሆኖ ከመቃብር ሲወጣ የተመለከቱ ሰዎች ምንኛ ተደንቀው ይሆን!—ዮሐ. 11:38-44

የኢየሱስን ትንሣኤ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

5. የኢየሱስ ትንሣኤ ከዚያ ቀደም ከተከናወኑት ትንሣኤዎች የሚለየው እንዴት ነው?

5 የኢየሱስ ትንሣኤ ከዚያ በፊት ከተከናወኑት ትንሣኤዎች የተለየ እንደሆነ ሐዋርያት ያውቁ ነበር። ከዚያ ቀደም ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች የተነሱት ሥጋዊ አካላቸውን ይዘው ሲሆን ከጊዜ በኋላም እንደገና ሞተዋል። ኢየሱስ የተነሳው ግን ሊበሰብስ የማይችል መንፈሳዊ አካል ይዞ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 13:34ን አንብብ።) ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “በሥጋ እያለ ተገደለ፤ ሆኖም መንፈስ ሆኖ ሕያው እንዲሆን ተደረገ” በማለት ጽፏል። ኢየሱስ “ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል፤ እንዲሁም መላእክት፣ ሥልጣናትና ኃይላት እንዲገዙለት ተደርጓል።” (1 ጴጥ. 3:18-22) ቀደም ሲል የተከናወኑት ትንሣኤዎች በጣም አስደናቂና በተአምር የተፈጸሙ ቢሆኑም አንዳቸውም ቢሆኑ ከሁሉ የላቀ ተአምር ከሆነው ከኢየሱስ ትንሣኤ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም።

6. የኢየሱስ ትንሣኤ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል?

6 የኢየሱስ ትንሣኤ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። ጠላቶቹ እንዳሰቡት ኢየሱስ ሞቶ አልቀረም። ከዚህ ይልቅ ማንም ሰው ጉዳት ሊያደርስበት የማይችል ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ ተነስቷል። ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ የአምላክ ልጅ መሆኑን አረጋግጧል፤ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሐቅ መገንዘባቸው ደግሞ ከጥልቅ ሐዘን ወጥተው በደስታ እንዲፈነድቁ አድርጓቸዋል። ከዚህም በላይ ፍርሃታቸው ተወግዶ ድፍረት አግኝተዋል። የኢየሱስ ትንሣኤ ከአምላክ ዓላማ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱ እስከ ምድር ዳር ድረስ በድፍረት እያወጁ ካሉት ምሥራች ጋር በተያያዘ ቁልፍ ሚና ነበረው።

7. ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ ነው? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

7 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ ታላቅ ሰው ብቻ እንዳልነበር በሚገባ እናውቃለን። ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ሕያው ከመሆኑም ሌላ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በበላይነት እየመራ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በመግዛት ላይ ያለ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በቅርቡ ከምድር ላይ ክፋትን በማስወገድ ምድርን ወደ ገነትነት ለውጦ ሰዎች በዚያ ለዘላለም እንዲኖሩ ያደርጋል። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ ይህ ሁሉ መሆን አይችልም። ታዲያ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን እንድናምን የሚያደርጉ ምን ምክንያቶች አሉ? ደግሞስ የእሱ ትንሣኤ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

ይሖዋ በሞት ላይ ያለውን ኃይል አሳየ

8, 9. (ሀ) የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስ መቃብር ላይ ጠባቂዎች እንዲቆሙ የጠየቁት ለምንድን ነው? (ለ) ወደ መቃብሩ የመጡት ሴቶች ምን አጋጠማቸው?

8 ኢየሱስ ከተገደለ በኋላ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን  ወደ ጲላጦስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ክቡር ሆይ፣ ያ አስመሳይ በሕይወት ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሳለሁ’ ብሎ የተናገረው ትዝ አለን። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው እንዳይሰርቁትና ለሕዝቡ ‘ከሞት ተነስቷል!’ እንዳይሉ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ መቃብሩ እንዲጠበቅ ትእዛዝ ስጥልን፤ አለዚያ ይህ የኋለኛው ማታለያ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል።” ጲላጦስም “ጠባቂዎች አሏችሁ። ስለዚህ ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ” አላቸው። እነሱም ያደረጉት ይህንኑ ነበር።—ማቴ. 27:62-66

9 የኢየሱስ አስከሬን ያረፈው ከዓለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ ሲሆን ደጃፉ በትልቅ ድንጋይ ተዘግቶ ነበር። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ምኞት ኢየሱስ በድን ሆኖ እዚያው መቃብር ውስጥ እንዲቀር ነበር። የይሖዋ ዓላማ ግን ከዚህ ጨርሶ የተለየ ነው። በሦስተኛው ቀን መግደላዊት ማርያምና ሌላዋ ማርያም ወደ መቃብሩ ሲመጡ ድንጋዩ ተንከባሎና አንድ መልአክ በላዩ ተቀምጦ አገኙ። መልአኩም መቃብሩ ባዶ መሆኑን ራሳቸው እንዲመለከቱ ለሴቶቹ የነገራቸውን ከመሆኑም ሌላ “ስለተነሳ እዚህ የለም” አላቸው። (ማቴ. 28:1-6) አዎ፣ ኢየሱስ ሕያው ሆኗል!

10. ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አቅርቧል?

10 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በነበሩት 40 ቀናት የተከናወኑት ነገሮች ከሞት መነሳቱን በሚገባ አረጋግጠዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ማስረጃውን ጠቅለል አድርጎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው እንዲህ ብሏል፦ “እኔም የተቀበልኩትን ከሁሉ በላይ የሆነውን ነገር ለእናንተ አስተላልፌያለሁ፤ ይኸውም ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረም፤ ደግሞም ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት በሦስተኛው ቀን ተነሳ፤ ለኬፋም ታየ፤ ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ ታየ። በኋላ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወንድሞች የታየ ሲሆን አብዛኞቹ እስካሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን በሞት አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ፤ በመጨረሻ ደግሞ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ተገለጠልኝ።”—1 ቆሮ. 15:3-8

ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል እንድንል የሚያስችሉ ምክንያቶች

11. የኢየሱስ ትንሣኤ የተከናወነበት መንገድ “ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት” የሆነው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል የምንልበት አንዱ ምክንያት ትንሣኤው የተከናወነው “ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት” መሆኑ ነው። የአምላክ ቃል ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳ አስቀድሞ ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ‘ቅዱሱን’ መቃብር ውስጥ እንደማይተወው ዳዊት ጽፏል። (መዝሙር 16:10ን አንብብ።) በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህ ትንቢት በኢየሱስ ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ክርስቶስን በሔዲስ እንደማይተወውና ሥጋውም እንደማይበሰብስ [ዳዊት] አስቀድሞ ተረድቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ።”—ሥራ 2:23-27, 31

12. ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የተመለከቱት እነማን ናቸው?

12 ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል የምንልበት ሁለተኛው ምክንያት ትንሣኤውን የተመለከቱ በርካታ የዓይን ምሥክሮች መኖራቸው ነው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በነበሩት 40 ቀናት፣ መቃብሩ አካባቢ ባለው የአትክልት ስፍራ፣ ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦላቸዋል። (ሉቃስ 24:13-15) በእነዚህ አጋጣሚዎች ጴጥሮስን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦችን እንዲሁም አንድ ላይ የነበሩ ሰዎችን አነጋግሯል። ከሞት ከተነሳ በኋላ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎችም የተገለጠበት ጊዜ አለ! በእርግጥም በርካታ እማኞች የሰጡትን ምሥክርነት ማስተባበል አይቻልም።

13. ደቀ መዛሙርቱ ያሳዩት ቅንዓት ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን በተመለከተ እርግጠኞች እንደነበሩ የሚያሳየው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል የምንልበት ሦስተኛው ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ ስለ ትንሣኤው ለመመሥከር ያሳዩት ቅንዓት ነው። ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ትንሣኤ በቅንዓት ማወጃቸው ለስደትና ለሥቃይ አልፎ ተርፎም ለሞት አጋልጧቸዋል። ኢየሱስ ከሞት ባይነሳና ትንሣኤው ሌሎችን ለማታለል የተፈጠረ ወሬ ቢሆን ኖሮ ጴጥሮስ፣  ኢየሱስን በሚጠሉትና ሞቱን ባቀነባበሩት የሃይማኖት መሪዎች ፊት ስለ ትንሣኤው በመመሥከር ሕይወቱን አደጋ ላይ ይጥል ነበር? ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ስለ ትንሣኤው የተናገሩት ኢየሱስ እንደተነሳ እንዲሁም አምላክ እንዲከናወን የሚፈልገውን ሥራ እየመራ እንደሆነ እርግጠኞች ስለነበሩ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ፣ ተከታዮቹ እነሱም ቢሞቱ ትንሣኤ እንደሚያገኙ እርግጠኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ እስጢፋኖስ ሲሞት የትንሣኤ ተስፋ እንዳለው እርግጠኛ ነበር።—ሥራ 7:55-60

14. ኢየሱስ ሕያው እንደሆነ የምታምነው ለምንድን ነው?

14 ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል የምንልበት አራተኛው ምክንያት አሁን ንጉሥ ሆኖ እየገዛ እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ሆኖ እየሠራ እንዳለ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መኖራቸው ነው። እውነተኛ ክርስትና እየተስፋፋ ያለው በዚህ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ ክርስትና ይስፋፋ ነበር? እንዲያውም ኢየሱስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ ስለ እሱ አንዳች ነገር አንሰማም ነበር። ኢየሱስ ሕያው እንደሆነ እንዲሁም ምሥራቹን እስከ ምድር ዳር ድረስ የመስበኩን ሥራ ስናከናውን እየመራን እንዳለ የሚያረጋግጡ ጠንካራ ማስረጃዎች አሉ።

የኢየሱስ ትንሣኤ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

15. የኢየሱስ ትንሣኤ ምሥራቹን ለመስበክ ድፍረት የሚሰጠን እንዴት ነው?

15 የኢየሱስ ትንሣኤ ምሥራቹን ለመስበክ ድፍረት ይሰጠናል። ላለፉት 2,000 ዓመታት የአምላክ ጠላቶች ምሥራቹን ለማስቆም ሲሉ ያልተጠቀሙበት መሣሪያ የለም፤ ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል ክህደት፣ ፌዝ፣ ዓመፅ፣ እገዳ እንዲሁም ማሠቃየት አልፎ ተርፎም መግደል ይገኙበታል። ያም ሆኖ ማንኛውም ነገር ይኸውም ‘በእኛ ላይ እንዲደገን የተበጀ’ ምንም ዓይነት መሣሪያ ምሥራቹን የመስበኩን እና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ሊያስቆመው አልቻለም። (ኢሳ. 54:17) የሰይጣንን ግብረ አበሮች ወይም አገልጋዮች አንፈራም። ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ከእኛ ጋር ሆኖ እየረዳን ነው። (ማቴ. 28:20) ጠላቶቻችን እኛን ዝም ለማሰኘት ምንም ያህል ቢጥሩ ፈጽሞ ስለማይሳካላቸው ደፋር ለመሆን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን!

የኢየሱስ ትንሣኤ ለመስበክ ድፍረት ይሰጠናል (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

16, 17. (ሀ) የኢየሱስ ትንሣኤ፣ እሱ ያስተማረው ትምህርት ሁሉ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው? (ለ) በዮሐንስ 11:25 መሠረት ኢየሱስ ምን እንዲያደርግ አምላክ ኃይል ሰጥቶታል?

16 የኢየሱስ ትንሣኤ፣ እሱ ያስተማረው ትምህርት ሁሉ ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጣል። ክርስቶስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ የክርስትና እምነትም ሆነ የስብከቱ ሥራ ከንቱ ሆኖ እንደሚቀር ጳውሎስ ተናግሯል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ክርስቶስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ . . . ክርስቲያኖች በአንድ ታላቅ ውሸት የተጭበረበሩ ምስኪኖች ይሆኑ ነበር።” ኢየሱስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ የወንጌል ዘገባዎች አንድ ጥሩና ጥበበኛ የሆነ ሰው በጠላቶቹ ስለመገደሉ የሚያወሱ አሳዛኝ ተረቶች ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም ነበር። ይሁንና ክርስቶስ ከሞት ተነስቷል፤ ይህም ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተናገረውን ጨምሮ ያስተማራቸው ነገሮች ሁሉ እውነት መሆናቸውን ያረጋግጣል።—1 ቆሮንቶስ 15:14, 15, 20ን አንብብ።

17 ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል” ብሏል። (ዮሐ. 11:25) ትልቅ ትርጉም የያዘው ይህ ሐሳብ መፈጸሙ አይቀርም። ኢየሱስ መንፈሳዊ አካል ለብሰው በሰማይ የሚኖሩትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙትን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችንም ከሞት እንዲያስነሳ ይሖዋ ኃይል ሰጥቶታል። የኃጢአት ሥርየት የሚያስገኘው የኢየሱስ መሥዋዕትም ሆነ ትንሣኤው ሞት እንደሚወገድ ዋስትና ናቸው። ታዲያ ይህን ማወቅህ የሚያጋጥምህን መከራ ሁሉ ሌላው ቀርቶ ሞትንም እንኳ በድፍረት ለመጋፈጥ ብርታት አይሰጥህም?

18. የኢየሱስ ትንሣኤ ምን ዋስትና ይሰጠናል?

18 የኢየሱስ ትንሣኤ፣ የምድር ነዋሪዎች ፍርድ የሚሰጣቸው ፍቅር በሚንጸባረቅባቸው የይሖዋ መሥፈርቶች መሠረት እንደሆነ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ጳውሎስ በጥንቷ አቴና ለነበሩት ሰዎች ሲናገር  እንዲህ ብሏል፦ “[አምላክ] በሾመው ሰው አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን . . . እሱንም ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።” (ሥራ 17:31) አምላክ የሾመው ፈራጅ ኢየሱስ ሲሆን እሱም ፍትሐዊ በሆነና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እንደሚፈርድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 11:2-4ን አንብብ።

19. ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ ማመናችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

19 በኢየሱስ ትንሣኤ ማመናችን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያነሳሳናል። ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት ባያደርግና ከዚያም ትንሣኤ ባያገኝ ኖሮ የኃጢአትና የሞት ባሪያ ሆነን እንቀር ነበር። (ሮም 5:12፤ 6:23) ኢየሱስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ እኛም ተስፋ ስለማይኖረን “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” ከሚሉት መካከል ብንሆን አያስገርምም። (1 ቆሮ. 15:32) አሁን ግን ተድላ በማሳደድ ላይ አናተኩርም። ከዚህ ይልቅ የትንሣኤን ተስፋ ከፍ አድርገን እንመለከታለን፤ በመሆኑም ይሖዋ የሚሰጠንን ማንኛውንም መመሪያ ለመታዘዝ የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለን።

20. የኢየሱስ ትንሣኤ የአምላክን ታላቅነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

20 የክርስቶስ ትንሣኤ፣ ‘ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ’ የሆነውን የይሖዋን ታላቅነት የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ነው። (ዕብ. 11:6) ይሖዋ ኢየሱስን ለማስነሳትና በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት ለመስጠት ምን ያህል ኃይልና ጥበብ እንደተጠቀመ እስቲ አስበው! በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ ኢየሱስን በማስነሳቱ፣ የገባውን ቃል ሁሉ መፈጸም እንደሚችል አረጋግጧል። ይህም ከአጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጉዳይ መልስ በመስጠት ረገድ የጎላ ሚና የሚጫወት ልዩ ‘ዘር’ እንደሚኖር አምላክ የተናገረውን ትንቢትም ይጨምራል። ይህ ትንቢት እንዲፈጸም ኢየሱስ መሞትና ትንሣኤ ማግኘት ነበረበት።—ዘፍ. 3:15

21. የትንሣኤ ተስፋ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

21 እንግዲያው አስተማማኝ የሆነ የትንሣኤ ተስፋ ስላለን ይሖዋን ልናመሰግነው አይገባም? ቅዱሳን መጻሕፍት የሚከተለውን ማረጋገጫ ይሰጣሉ፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” ይህ አስደናቂ ተስፋ የተሰጠው ለታማኙ ሐዋርያ ለዮሐንስ ሲሆን “እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸውና እውነት ስለሆኑ ጻፍ” ተብሎ ነበር። ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት የተሰጠውን ይህን ራእይ የተቀበለው ከማን ነበር? ትንሣኤ ካገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ራእይ 1:1፤ 21:3-5