በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቅዱስ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

ቅዱስ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

“ቅዱሳን ሁኑ።”ዘሌ. 11:45

1. የዘሌዋውያን መጽሐፍ የሚረዳን በምን መንገድ ነው?

ቅድስና ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሁሉ ይልቅ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ በብዛት ተጠቅሷል። ይሖዋ፣ እውነተኛ አምላኪዎቹ በሙሉ ይህን ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ስለሚጠብቅባቸው የዘሌዋውያንን መጽሐፍ በሚገባ መረዳታችንና ለመጽሐፉ ያለንን አድናቆት ማሳደጋችን ቅድስናችንን ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል።

2. የዘሌዋውያን መጽሐፍ አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

2 በነቢዩ ሙሴ የተጻፈው የዘሌዋውያን መጽሐፍ ለማስተማር ከሚጠቅሙት ‘ቅዱሳን መጻሕፍት’ አንዱ ነው። (2 ጢሞ. 3:16) የይሖዋ ስም በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ በአማካይ አሥር ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። የዘሌዋውያንን መጽሐፍ አጠቃላይ መልእክት መረዳታችን መለኮታዊውን ስም የሚያስነቅፍ ምንም ነገር እንዳናደርግ ይረዳናል። (ዘሌ. 22:32) ‘እኔ ይሖዋ ነኝ’ የሚለው አገላለጽ በመጽሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚገኝ መሆኑ አምላክን መታዘዝ እንዳለብን ያስታውሰናል። በቅዱስ አምልኮ እንድንካፈል በሚረዳንና የአምላክ ስጦታ በሆነው በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የምናገኛቸውን እንደ ዕንቁ የሆኑ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

የአምላክ ሕዝቦች ቅዱስ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል

3, 4. የአሮንና የልጆቹ መታጠብ ምን ያመለክታል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

3 ዘሌዋውያን 8:5, 6ን አንብብ። አሮን የእስራኤል ሊቀ ካህን፣  ልጆቹ ደግሞ ብሔሩን የሚወክሉ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ይሖዋ መርጧቸው ነበር። አሮን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ ልጆቹ ደግሞ የኢየሱስን ቅቡዓን ተከታዮች ይወክላሉ። ታዲያ አሮን መታጠቡ ኢየሱስ መንጻት እንደሚያስፈልገው ያሳያል? በፍጹም፣ ኢየሱስ ኃጢአትም ሆነ “እንከን” የሌለበት በመሆኑ መንጻት አያስፈልገውም። (ዕብ. 7:26፤ 9:14) ሆኖም አሮን ከታጠበ በኋላ የነበረበት ሁኔታ ኢየሱስ ንጹሕና ጻድቅ መሆኑን ያመለክታል። የአሮን ልጆች መታጠባቸውስ ምን ያመለክታል?

4 የአሮን ልጆች መታጠባቸው በሰማይ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ የተመረጡት ሰዎች እንደሚነጹ የሚያሳይ ጥላ ነው። ታዲያ የቅቡዓኑ ጥምቀት ከአሮን ልጆች መንጻት ጋር የተያያዘ ነው? አይደለም፣ ምክንያቱም ጥምቀት ከኃጢአት አያነጻም፤ ከዚህ ይልቅ ጥምቀት የሚያመለክተው አንድ ግለሰብ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ አምላክ መወሰኑን ነው። ቅቡዓኑ የሚታጠቡት “በቃሉ አማካኝነት” ሲሆን ይህ ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ የክርስቶስን ትምህርት በሙሉ ልብ ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቅባቸዋል። (ኤፌ. 5:25-27) እንዲህ ካደረጉ ቅዱስ መሆንና መንጻት ይችላሉ። ስለ ‘ሌሎች በጎችስ’ ምን ማለት ይቻላል?—ዮሐ. 10:16

5. ሌሎች በጎች በአምላክ ቃል አማካኝነት ይነጻሉ የምንለው ለምንድን ነው?

5 የአሮን ልጆች የኢየሱስ ሌሎች በጎች የሆኑትን ‘እጅግ ብዙ ሕዝብ’ አያመለክቱም። (ራእይ 7:9) ታዲያ እነዚህ የተጠመቁ ሰዎችም ቅዱስና ንጹሕ የሆኑት በአምላክ ቃል አማካኝነት ነው? እንዴታ! ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች፣ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ምን ያህል ዋጋና ኃይል እንዳለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማንበብ እምነት ያዳብራሉ፤ ይህም “ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት” እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል። (ራእይ 7:13-15) የቅቡዓኑም ሆነ የሌሎች በጎች መንጻት ቀጣይ ሂደት ነው፤ ይህ ደግሞ ‘መልካም ምግባር ይዘው እንዲኖሩ’ ይረዳቸዋል። (1 ጴጥ. 2:12) ይሖዋ፣ እረኛቸውን ኢየሱስን በሚሰሙትና በታማኝነት በሚከተሉት ቅቡዓንም ሆነ ሌሎች በጎች ንጽሕና ብሎም በመካከላቸው ባለው አንድነት ይደሰታል!

6. በምን ረገድ ራሳችንን መመርመራችን ጠቃሚ ነው?

6 የእስራኤል ካህናት አካላዊ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ የሚያዝዘው ሕግ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም አለው። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የአምልኮ ቦታችን ንጹሕ እንደሆነ እንዲሁም እኛ ራሳችን ንጹሕና ሥርዓታማ አለባበስ እንዳለን ያስተውላሉ። በተጨማሪም የካህናቱ ንጽሕና፣ ላቅ ወዳለው የይሖዋ አምልኮ ተራራ የሚወጣ ማንኛውም ሰው “ንጹሕ ልብ” ሊኖረው እንደሚገባ ያስገነዝበናል። (መዝሙር 24:3, 4በNW አንብብ፤ * ኢሳ. 2:2, 3) ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ስናቀርብ አእምሯችን፣ ልባችንና አካላችን ንጹሕ ሊሆን ይገባል። ይህ ደግሞ በየጊዜው ራሳችንን መመርመርን ይጠይቃል፤ አንዳንዶች እንዲህ ያለ ምርመራ ካደረጉ በኋላ ቅዱስ ለመሆን ሲሉ ጉልህ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸው ይሆናል። (2 ቆሮ. 13:5) ለምሳሌ ያህል፣ ፖርኖግራፊ ሆን ብሎ የሚመለከት አንድ ክርስቲያን ‘ቅዱስ ሆኜ እየኖርኩ ነው?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ ተገቢ ነው። ከዚህም ሌላ ይህን ርኩስ ልማድ ለማሸነፍ እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል።—ያዕ. 5:14

ታዛዥነት በማሳየት ቅዱሳን ሁኑ

7. ዘሌዋውያን 8:22-24 ላይ ካለው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?

7 በእስራኤል የክህነት ሥርዓት ሲቋቋም የአውራ በግ ደም በአሮንና በልጆቹ ቀኝ ጆሮ እንዲሁም የቀኝ እጅና የቀኝ እግር አውራ ጣት ላይ ይደረግ ነበር። (ዘሌዋውያን 8:22-24ን አንብብ።) ደሙ በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉ ካህናቱ ኃላፊነታቸውን በታዛዥነት ለመወጣት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ያመለክታል። በተመሳሳይም ሊቀ ካህኑ ኢየሱስ፣ ለቅቡዓኑና  ለሌሎች በጎች ፍጹም ምሳሌ ትቷል። የአምላክን መመሪያ ለመስማት ጆሮውን አቅንቶ ነበር። የኢየሱስ እጆች የይሖዋን ፈቃድ ይፈጽሙ ነበር፤ እግሮቹም ከቅዱስ ጎዳና ስተው አያውቁም።—ዮሐ. 4:31-34

8. ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ምን ሊያደርጉ ይገባል?

8 ቅቡዓን ክርስቲያኖችና የኢየሱስ ሌሎች በጎች የሊቀ ካህናቸውን ምሳሌ በመከተል ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በአምላክ ቃል ላይ የሚገኙትን መመሪያዎች መታዘዝ አለባቸው፤ ይህም መንፈሱን ከማሳዘን ይጠብቃቸዋል። (ኤፌ. 4:30) ‘ለእግራቸው ቀና መንገድ ማበጀት’ ይኖርባቸዋል።—ዕብ. 12:13

9. ከበላይ አካል አባላት ጋር በቅርበት የሠሩ ሦስት ወንድሞች ምን ሐሳብ ሰጥተዋል? የተናገሩት ሐሳብ ቅዱስ ሆነህ ለመመላለስ የሚረዳህ እንዴት ነው?

9 ከበላይ አካል አባላት ጋር ለአሥርተ ዓመታት በቅርበት ሲሠሩ የቆዩ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሦስት ወንድሞች ስሜታቸውን እንዴት እንደገለጹ እንመልከት። አንደኛው ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከእነዚህ ወንድሞች ጋር መሥራት ልዩ መብት እንደሆነ አይካድም፤ ያም ቢሆን ከእነሱ ጋር ተቀራርቤ መሥራቴ እነዚህ ወንድሞች በመንፈስ ቢቀቡም ፍጹማን አለመሆናቸውን እንዳስተውል አድርጎኛል። ሆኖም ባለፉት ዓመታት ካወጣኋቸው ግቦች አንዱ አመራር ለሚሰጡት ለእነዚህ ወንድሞች ምንጊዜም መታዘዝ ነው።” ሁለተኛው ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “‘ለክርስቶስ ስለመታዘዝ’ የሚገልጹ እንደ 2 ቆሮንቶስ 10:5 ያሉ ጥቅሶች አመራር ለሚሰጡ ወንድሞች ታዛዥ እንድሆንና ከእነሱ ጋር ተባብሬ እንድሠራ ረድተውኛል። የምታዘዘው ከልቤ ነው።” ሦስተኛው ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የሚወደውን መውደድና የሚጠላውን መጥላት እንዲሁም ሁልጊዜ የእሱን መመሪያ መሻትና ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ሲባል ድርጅቱን ብሎም በምድር ላይ ዓላማውን ለመፈጸም የሚጠቀምባቸውን ሰዎች መታዘዝ ማለት ነው።” ይህ ወንድም፣ በ1925 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣው “የብሔሩ መወለድ” በሚለው ርዕስ ላይ የቀረቡትን ነጥቦች አንዳንዶች መቀበል ቢከብዳቸውም እንኳ ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ናታን ኖር ግን ትምህርቱን በቀላሉ እንደተቀበለው ያስታውሳል። የወንድም ኖር ታዛዥነት በጣም አስደንቆት ነበር። አንተም ከላይ የተጠቀሱት ወንድሞች በተናገሩት ሐሳብ ላይ ማሰላሰልህ ታዛዥነት በማሳየት ቅዱስ እንድትሆን ይረዳሃል።

አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ በመታዘዝ ቅዱስ መሆን

10. አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ መታዘዛችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

10 ዘሌዋውያን 17:10, 14ን አንብብ። እስራኤላውያን “የማንኛውንም ፍጡር ደም” እንዳይበሉ ይሖዋ አዟቸው ነበር። ክርስቲያኖችም ቢሆኑ የእንስሳም ሆነ የሰው ደም ከመጠቀም መራቅ ይኖርባቸዋል። (ሥራ 15:28, 29) አምላክ ፊቱን እንደሚያከብድብንና ከጉባኤው እንደሚያስወግደን ማሰቡ እንኳ ያስፈራናል። ይሖዋን ስለምንወደው እሱን መታዘዝ እንፈልጋለን። ሕይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ቢያጋጥመንም እንኳ ይሖዋን የማያውቁና የእሱን ሕጎች መታዘዝ የማይፈልጉ ሰዎች በሚያሳድሩብን ተጽዕኖ ላለመሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ከደም በመራቃችን ሌሎች ሊያፌዙብን እንደሚችሉ ብናውቅም አምላክን ለመታዘዝ መርጠናል። (ይሁዳ 17, 18) ታዲያ ደምን እንዳንበላ ወይም እንዳንወስድ ‘ለመጠንቀቅ’ ያደረግነውን ውሳኔ የሚያጠናክርልን ምን ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ነው?—ዘዳ. 12:23

11. በዓመታዊው የስርየት ቀን የሚከናወነው ነገር ምንም ትርጉም የሌለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

11 በጥንቷ እስራኤል ሊቀ ካህኑ በዓመታዊው የስርየት ቀን የእንስሳትን ደም መጠቀሙ አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ለመረዳት ያስችለናል። ደም ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ለልዩ ዓላማ ይኸውም የይሖዋን ይቅርታ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ኃጢአታቸው እንዲሰረይ ለማድረግ ነው። የወይፈን እና የፍየል ደም የቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ አካባቢ እንዲሁም ከመክደኛው  ፊት ይረጭ ነበር። (ዘሌ. 16:14, 15, 19) ይህም ይሖዋ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር እንዲልላቸው በር ይከፍታል። በተጨማሪም አንድ ሰው እንስሳ ቢያርድ ሥጋውን ከመብላቱ በፊት ደሙን አፍስሶ አፈር ሊያለብሰው እንደሚገባ ይሖዋ አዝዞ ነበር፤ ምክንያቱም “የፍጡር ሁሉ ሕይወት ደሙ ነው።” (ዘሌ. 17:11-14) ይህ ሁሉ ምንም ትርጉም የሌለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነበር? አይደለም፤ ደም በስርየት ቀን ጥቅም ላይ እንዲውልና እንስሳት ሲታረዱ ደማቸው መሬት ላይ እንዲፈስ የተሰጠው ትእዛዝ ቀደም ሲል ይሖዋ ለኖኅና ለዘሮቹ ደምን አስመልክቶ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር ይስማማል። (ዘፍ. 9:3-6) ይሖዋ አምላክ ደም መብላትን ከልክሏል። ታዲያ ይህ ለክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው?

12. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ደምን የኃጢአት ይቅርታ ከማግኘት ጋር ያያያዘው እንዴት ነው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ ደም ስላለው የማንጻት ኃይል ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ “በሕጉ መሠረት ሁሉም ነገር ለማለት ይቻላል፣ በደም ይነጻል፤ ደም ካልፈሰሰ በስተቀር ይቅርታ አይደረግም” ብሏል። (ዕብ. 9:22) በተጨማሪም ጳውሎስ የእንስሳት መሥዋዕት የተወሰነ ጥቅም ቢኖረውም ዓላማው እስራኤላውያን ኃጢአተኞች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ማድረግ እንደሆነ ገልጿል፤ በተጨማሪም ኃጢአታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ የላቀ ነገር እንደሚያስፈልጋቸው ያስታውሳቸው ነበር። በእርግጥም ሕጉ “ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ የእነዚህ ነገሮች እውነተኛው አካል አይደለም።” (ዕብ. 10:1-4) ታዲያ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

13. ኢየሱስ የደሙን ዋጋ ለይሖዋ በማቅረቡ ምን ይሰማሃል?

13 ኤፌሶን 1:7ን አንብብ። ‘ለእኛ ሲል ራሱን አሳልፎ የሰጠው’ የኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት እሱንና አባቱን ለሚወዱ ሁሉ ትልቅ ትርጉም አለው። (ገላ. 2:20) ያም ቢሆን ከኃጢአት ነፃ ያወጣንና ስርየት እንድናገኝ ያስቻለን፣ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ያከናወነው ነገር ነው። ኢየሱስ በሙሴ ሕግ ውስጥ በስርየት ቀን ይከናወን የነበረውን ነገር ፈጽሟል። በዚህ ቀን ሊቀ ካህኑ መሥዋዕት ከተደረጉት እንስሳት ደም የተወሰነውን ወደ ማደሪያው ድንኳን፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ  ወደ ሰለሞን ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ይዞ በመግባት በአምላክ ፊት ያቀርበው ነበር። (ዘሌ. 16:11-15) በተመሳሳይም ኢየሱስ የደሙን ዋጋ ይዞ ወደ ሰማይ በመሄድ በይሖዋ ፊት አቅርቦታል። (ዕብ. 9:6, 7, 11-14, 24-28) በኢየሱስ ደም በማመናችን የኃጢአት ይቅርታና ንጹሕ ሕሊና አግኝተናል፤ ለዚህ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

14, 15. ይሖዋ ደምን አስመልክቶ የሰጠውን ሕግ መረዳታችንና መታዘዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ “የማንኛውንም ፍጡር ደም” እንዳንበላ ያዘዘን ለምን እንደሆን አሁን ይበልጥ ግልጽ ሆነልህ? (ዘሌ. 17:10, 14) አምላክ ደምን ቅዱስ አድርጎ የሚመለከተው ለምን እንደሆነስ ተገነዘብክ? በአምላክ ፊት ደም ማለት ሕይወት ነው። (ዘፍ. 9:4) አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት መቀበልና ከደም እንድንርቅ የሰጠውን ትእዛዝ ማክበር እንዳለብን ይሰማሃል? ሁላችንም ከአምላክ ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖረን የሚችለው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ካሳደርንና ፈጣሪያችን ለደም ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ከተገነዘብን ብቻ ነው።—ቆላ. 1:19, 20

15 ማንኛችንም ብንሆን ከደም ጋር በተያያዘ ባለን አቋም ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ድንገተኛ ሁኔታ ያጋጥመን ይሆናል። አሊያም ደግሞ አንድ የቤተሰባችን አባል ወይም ጓደኛችን ደም ከመውሰድ ጋር የተያያዘ ፈተና ሊደቀንበት ይችላል። እንዲህ ያለ ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥም የደም ክፍልፋዮችንና አንዳንድ ሕክምናዎችን በተመለከተም ውሳኔ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። በመሆኑም አስቀድሞ ምርምር በማድረግ እንዲህ ላለው ድንገተኛ ሁኔታ መዘጋጀቱ በጣም አስፈላጊ ነው። አስቀድመን መዘጋጀታችንና መጸለያችን በአቋማችን እንድንጸና እንዲሁም በፈተናው እንዳንወድቅ ይረዳናል። የአምላክ ቃል የሚያወግዘውን ነገር በማድረግ የይሖዋን ልብ ማሳዘን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። በርካታ የሕክምና ባለሙያዎችና ደምን ለታካሚዎች መስጠትን የሚደግፉ ሌሎች ግለሰቦች ደም የሕመምተኞችን ሕይወት እንደሚያድን ስለሚያስቡ ሰዎች ደም እንዲለግሱ ያበረታታሉ። ይሁንና ቅዱስ የሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች ደም እንዴት ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት የመወሰን መብት ያለው ፈጣሪ እንደሆነ ይገነዘባሉ። እሱ “የማንኛውንም ፍጡር ደም” ቅዱስ አድርጎ ይመለከተዋል። እንግዲያው ይሖዋ ደምን አስመልክቶ የሰጠውን ሕግ ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ከዚህም ሌላ የኢየሱስ ደም ሕይወትን የማዳን ኃይል እንዳለው በመገንዘብ ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው በቅዱስ ምግባራችን እናሳይ፤ ምክንያቱም የኃጢአት ይቅርታና የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘው የኢየሱስ ደም ብቻ ነው።—ዮሐ. 3:16

ይሖዋ ደምን አስመልክቶ የሰጠውን ሕግ ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? (አንቀጽ 14, 15ን ተመልከት)

ይሖዋ ቅዱስ እንድንሆን የሚጠብቅብን ለምንድን ነው?

16. የይሖዋ ሕዝቦች ቅዱስ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

16 አምላክ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው “አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሏቸው ነበር። (ዘሌ. 11:45) ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ እስራኤላውያንም ቅዱስ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸው ነበር። እኛም የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ቅዱስ መሆን አለብን። የዘሌዋውያን መጽሐፍ ይህን በግልጽ ያሳያል።

17. ይህን ርዕስ ካጠናን በኋላ ስለ ዘሌዋውያን መጽሐፍ ምን ይሰማሃል?

17 የዘሌዋውያንን መጽሐፍ የተወሰኑ ክፍሎች መመርመራችን እንደጠቀመን ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ርዕስ፣ በመንፈስ መሪነት ለተጻፈው የዘሌዋውያን መጽሐፍ ያለህን አድናቆት ከፍ እንዳደረገው እርግጠኞች ነን። በዚህ መጽሐፍ ላይ በሚገኙት በዋጋ የማይተመኑ ትምህርቶች ላይ ማሰላሰላችን ቅዱስ መሆን ያለብን ለምን እንደሆነ ይበልጥ እንድትገነዘብ እንደረዳህ ጥያቄ የለውም። ይሁንና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ምን ሌሎች መንፈሳዊ ዕንቁዎች ይዟል? ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ከማቅረብ ጋር በተያያዘ ከዚህ መጽሐፍ ምን ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን? እነዚህ ነጥቦች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።

^ አን.6 መዝሙር 24:3, 4 (NW)፦ “ወደ ይሖዋ ተራራ መውጣት የሚችል ማን ነው? በቅዱስ ስፍራውስ ሊቆም የሚችል ማን ነው? ከክፋት የጸዱ እጆችና ንጹሕ ልብ ያለው፣ በእኔ ሕይወት በሐሰት ያልማለ፣ በማታለልም መሐላ ያልፈጸመ።”