በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በምግባራችን ሁሉ ቅዱስ መሆን አለብን

በምግባራችን ሁሉ ቅዱስ መሆን አለብን

“እናንተም ራሳችሁ በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።”1 ጴጥ. 1:15

1, 2. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ምን ዓይነት ምግባር እንዲኖራቸው ይጠበቅባቸዋል? (ለ) ይህ ርዕስ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል?

ሐዋርያው ጴጥሮስ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ ጎላ ተደርጎ የተገለጸውን የቅድስና ባሕርይ በመጥቀስ ክርስቲያኖች በምግባራቸው ቅዱሳን መሆናቸው አስፈላጊ እንደሆነ በይሖዋ መንፈስ መሪነት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 1:14-16ን አንብብ።) “ቅዱስ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ቅቡዓኑም ሆኑ “ሌሎች በጎች” በአንዳንድ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በምግባራቸው ሁሉ ቅዱሳን ለመሆን የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል።—ዮሐ. 10:16

2 በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች መንፈሳዊ ዕንቁዎች መመርመራችን በጣም ይጠቅመናል፤ የተማርነውን ተግባራዊ ማድረጋችን ደግሞ በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን እንድንሆን ይረዳናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ አቋምን ስለ ማላላት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍን በተመለከተ የዘሌዋውያን መጽሐፍ ምን ያስተምረናል? እስራኤላውያን ከሚያቀርቡት መሥዋዕት ምን ትምህርት እናገኛለን?

አቋማችሁን እንዳታላሉ ተጠንቀቁ

3, 4. (ሀ) ክርስቲያኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ልል አቋም ሊኖራቸው የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ከበቀልም ሆነ ቂም ከመያዝ መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?

3 ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን ሕግጋቱንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን መታዘዝ ይኖርብናል፤ ቅድስና የጎደለው አስተሳሰብ ሊኖረን ወይም ትእዛዛቱን በተመለከተ ልል አቋም ልንይዝ አይገባም። በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም እንኳ በሕጉ ውስጥ የሰፈሩት መመሪያዎች፣ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያላቸውን ወይም የሌላቸውን ነገሮች ለማስተዋል ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን  እንዲህ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት [“ቂም አትያዝ፣” NW]፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”—ዘሌ. 19:18

4 ይሖዋ ከበቀልም ሆነ ቂም ከመያዝ እንድንርቅ ይጠብቅብናል። (ሮም 12:19) መለኮታዊ ሕግጋትንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ችላ ብንል ዲያብሎስ ይደሰታል፤ እንዲሁም የይሖዋን ስም ልናስነቅፍ እንችላለን። አንድ ሰው ሆን ብሎ ቢጎዳንም እንኳ ቂም ላለመያዝ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። አምላክ፣ ውድ ሀብት የሆነውን ምሥራቹን የያዘ “የሸክላ ዕቃ” የመሆን ታላቅ መብት ሰጥቶናል። (2 ቆሮ. 4:1, 7) እንደ መርዝ የሆነው ቂም እንደነዚህ ባሉት ዕቃዎች ውስጥ ሊኖር አይገባም!

5. ስለ አሮንና ስለ ልጆቹ ሞት ከሚናገረው ዘገባ ምን እንማራለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

5 ዘሌዋውያን 10:1-11 ላይ የአሮን ቤተሰብ ያጋጠመው ልብ የሚሰብር ክስተት ተመዝግቦ ይገኛል። የአሮን ልጆች የሆኑትን ናዳብንና አብዩድን ይሖዋ በመገናኛው ድንኳን አቅራቢያ ሲቀስፋቸው ቤተሰባቸው በጣም አዝኖ መሆን አለበት። አሮንና ቤተሰቡ ለሟቾቹ እንዳያለቅሱ የተሰጣቸውን መመሪያ መታዘዝ እምነታቸውን የሚፈትን ነገር ነበር። አንተስ ከተወገዱ የቤተሰብህ አባላት ወይም ሌሎች ሰዎች ጋር ባለመቀራረብ ቅድስናህን እየጠበቅክ ነው?—1 ቆሮንቶስ 5:11ን አንብብ።

6, 7. (ሀ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚካሄድ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘትን በተመለከተ ውሳኔ ለማድረግ የትኞቹን ነጥቦች በቁም ነገር ልናስብባቸው ይገባል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚካሄድ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ያለንን አቋም የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ዘመዶቻችን ማስረዳት የምንችለው እንዴት ነው?

6 አሮንና ቤተሰቡ ያጋጠማቸው ዓይነት ከባድ ፈተና ላይደርስብን ይችላል። ይሁንና የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ዘመዳችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያካሂደው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንድንገኝ ቢጋብዘንና በዝግጅቱ ላይ አንድ ሥራ ቢሰጠንስ? እዚያ እንዳንገኝ የሚከለክል ቀጥተኛ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ የለም፤ ይሁንና በዚህ ረገድ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ? *

7 የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ዘመዶቻችን ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በይሖዋ ፊት ቅዱስ ለመሆን ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሲመለከቱ ግራ ሊጋቡ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 4:3, 4) እርግጥ ነው፣ እነሱን ቅር የሚያሰኝ ነገር ላለማድረግ እንጠነቀቃለን፤ ያም ቢሆን ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሆኖም በግልጽ አቋማችንን ማሳወቁ የተሻለ ነው። ምናልባትም ዝግጅቱ ከመድረሱ ቀደም ብለን ብናነጋግራቸው ተገቢ ይሆናል። በሠርጉ ላይ ሥራ ስለሰጡን መደሰታችንን ልንገልጽላቸውና ልናመሰግናቸው እንችላለን። ከዚያም በዝግጅቱ ላይ ተገኝተን እዚያ በሚካሄዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አለመካፈላችን የደስታቸውን ቀን ሊያበላሽባቸው ብሎም እነሱንም ሆነ ተጋባዦቹን ሊያሳፍራቸው እንደሚችል መግለጽ እንችል ይሆናል። ከእምነታችን ጋር በተያያዘ አቋማችንን እንዳናላላ ልንጠነቀቅበት የሚገባ አንዱ ሁኔታ ይህ ነው።

የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፉ

8. የዘሌዋውያን መጽሐፍ የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

8 የዘሌዋውያን መጽሐፍ የይሖዋን ሉዓላዊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በዘሌዋውያን ላይ የሚገኙትን ሕግጋት የሰጠው ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፉ ውስጥ ከ30 ጊዜ በላይ ተገልጿል። ሙሴም ይህን በመገንዘቡ ይሖዋ ያዘዘውን አድርጓል። (ዘሌ. 8:4, 5) እኛም በተመሳሳይ ሉዓላዊው ገዢያችን ይሖዋ እንድናደርግ የሚፈልገውን ነገር ምንጊዜም መፈጸም ይኖርብናል። በዚህ ረገድ የአምላክ ድርጅት ይረዳናል። ይሁንና ኢየሱስ ምድረ በዳ ሳለ እንዳጋጠመው ሁሉ እኛም ብቻችንን ስንሆን የእምነት ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። (ሉቃስ 4:1-13) በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ትኩረት የምናደርግና በእሱ የምንታመን ከሆነ ማንም ሰው አቋማችንን እንድናላላ ሊያደርገን አይችልም፤ እንዲሁም የሰው ፍርሃት ወጥመድ አይሆንብንም።—ምሳሌ 29:25

9. የአምላክ አገልጋዮች በሁሉም ሕዝቦች የሚጠሉት ለምንድን ነው?

9 የክርስቶስ ተከታዮችና የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ሕዝቦች ስደት ያደርሱብናል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ አንጻር ይህ የሚጠበቅ  ነው፤ “በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል እንዲሁም በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴ. 24:9) ሰዎች ለእኛ እንዲህ ዓይነት ጥላቻ ቢኖራቸውም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ እንጸናለን፤ እንዲሁም ምንጊዜም በይሖዋ ዘንድ ቅዱስ ለመሆን እንጥራለን። ሐቀኞች፣ ንጹሕ አኗኗር ያለንና ሕግ አክባሪ ዜጎች ሆነን ሳለን ሰዎች ይህን ያህል የሚጠሉን ለምንድን ነው? (ሮም 13:1-7) ይሖዋ አምላክን እንደ ሉዓላዊ ጌታችን አድርገን ስለተቀበልን ነው! ቅዱስ አገልግሎት የምናቀርበው ‘ለእሱ ብቻ’ ከመሆኑም ሌላ ጽድቅ የሰፈነባቸውን ሕግጋቱንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በመጠበቅ ረገድ አቋማችንን ፈጽሞ አናላላም።—ማቴ. 4:10

10. አንድ ወንድም የገለልተኝነት አቋሙን ባላላበት ወቅት ምን አጋጠመው?

10 በተጨማሪም ‘የዓለም ክፍል አይደለንም።’ በመሆኑም በዓለም ላይ በሚካሄዱ ጦርነቶችና በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ረገድ ገለልተኛ አቋም አለን። (ዮሐንስ 15:18-21ን እና ኢሳይያስ 2:4ን አንብብ።) ሆኖም ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች የገለልተኝነት አቋማቸውን አላልተዋል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ንስሐ በመግባት መሐሪ ከሆነው የሰማዩ አባታችን ጋር ያላቸውን ዝምድና አድሰዋል። (መዝ. 51:17) እርግጥ አንዳንዶች ንስሐ አልገቡም። ለአብነት ያህል፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሃንጋሪ ፍትሕ በጎደለው መንገድ ታስረው የነበሩ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በታች የሆኑ 160 ወንድሞቻችን ያጋጠማቸውን እንመልከት። የአገሪቱ ባለሥልጣናት እነዚህን ወንድሞች በመላው ሃንጋሪ ከሚገኙ ወኅኒ ቤቶች አውጥተው በአንድ ከተማ ውስጥ ሰበሰቧቸው። በዚያም በወታደራዊ አገልግሎት እንዲካፈሉ አዘዟቸው። አብዛኞቹ ወንድሞች የታማኝነት አቋማቸውን በመጠበቅ ጸኑ፤ ከመካከላቸው ዘጠኙ ግን ወታደራዊ ቃለ መሐላ በመፈጸም የደንብ ልብስ ለበሱ። ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ አቋማቸውን ካላሉት ወንድሞች መካከል አንዱ ታማኝነታቸውን የጠበቁትን የይሖዋ ምሥክሮች እንዲረሽን ተመደበ። ከሚረሸኑት መካከል ደግሞ የሥጋ ወንድሙ ይገኝበት ነበር! በኋላ ላይ ግን እነዚህ ወንድሞች ሳይረሸኑ ቀሩ።

ለይሖዋ ምርጣችሁን ስጡ

11, 12. ይሖዋ በጥንቷ እስራኤል ከመሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ የሰጠው መመሪያ በዛሬው ጊዜ ለምንኖር ክርስቲያኖች ምን ትምህርት ይዟል?

11 በሙሴ ሕግ ውስጥ እስራኤላውያን እንዲያቀርቡ የታዘዟቸው መሥዋዕቶች ነበሩ። (ዘሌ. 9:1-4, 15-21) እነዚህ መሥዋዕቶች ፍጹም ለሆነው የኢየሱስ መሥዋዕት ጥላ በመሆናቸው እንከን የሌለባቸው ሊሆኑ ይገባ ነበር። በተጨማሪም እያንዳንዱን መሥዋዕት እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው ለሕዝቡ ዝርዝር መመሪያ ተሰጥቶ ነበር። ለምሳሌ አንዲት ሴት፣ ልጅ ስትወልድ ምን ማድረግ እንደነበረባት እንመልከት። ዘሌዋውያን 12:6 እንዲህ ይላል፦ “ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ልጅዋን ወልዳ የመንጻትዋ ጊዜ ሲፈጸም፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የአንድ ዓመት ጠቦት፣ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ የዋኖስ ጫጩት ወይም አንድ ርግብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዳ ካህኑ ዘንድ ታቅርብ።” አምላክ መሥዋዕቱ እንዴት መቅረብ እንዳለበት መመሪያ ቢሰጥም አፍቃሪና ምክንያታዊ እንደሆነ ሕጉ በግልጽ ያሳይ ነበር። እናትየው፣ ጠቦት ለማቅረብ አቅሟ ካልፈቀደ ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ማቅረብ ትችል ነበር። (ዘሌ. 12:8) ይህች ሴት ድሃ ብትሆንም፣ የበለጠ ወጪ የሚያስወጣ መሥዋዕት ካቀረበው ሰው ባልተናነሰ ይሖዋ ይወዳታል፤ እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከታታል። ታዲያ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ “የምስጋና መሥዋዕት” እንዲያቀርቡ የእምነት ባልንጀሮቹን አበረታቷቸዋል። (ዕብ. 13:15) ከንፈሮቻችን የይሖዋን ቅዱስ ስም በይፋ ማወጅ አለባቸው። መስማት የተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች በምልክት ቋንቋ ይሖዋን ያመሰግናሉ። ከቤት መውጣት የማይችሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በደብዳቤና በስልክ በመመሥከር እንዲሁም ለሚጠይቋቸው ሰዎች በመስበክ አምላክን ያመሰግናሉ። ለይሖዋ የምስጋና መሥዋዕት የምናቀርበው ይኸውም ስሙን በማሳወቅ እሱን የምናወድሰው እንዲሁም ምሥራቹን የምናውጀው ጤንነታችንና አቅማችን በፈቀደው መጠን ሊሆን  ይገባል። ለእሱ ምርጣችንን መስጠት አለብን።—ሮም 12:1፤ 2 ጢሞ. 2:15

13. የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ሪፖርት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

13 የምስጋና መሥዋዕት አምላክን ስለምንወደው ለእሱ በፈቃደኝነት የምንሰጠው ስጦታ ነው። (ማቴ. 22:37, 38) ያም ቢሆን የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ሪፖርት እንድናደርግ እንጠየቃለን። ታዲያ ለዚህ ዝግጅት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? በየወሩ የምናቀርበው ሪፖርት ለአምላክ ያደርን ከመሆናችን ጋር የተያያዘ ነው። (2 ጴጥ. 1:7) እርግጥ ነው፣ ማንኛችንም ብንሆን ብዙ ሰዓት ሪፖርት ለማድረግ ስንል ብቻ በአገልግሎት ረጅም ሰዓት ማሳለፍ እንዳለብን ሊሰማን አይገባም። እንዲያውም በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ያሉ ወይም የአቅም ገደብ ያለባቸው የመንግሥቱ አስፋፊዎች አንድ ሰዓት ባይሞላም እንኳ እስከ 15 ደቂቃ የሚደርስ ሰዓት ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ። ይሖዋ፣ ሪፖርቱ የአስፋፊው ምርጥ መሥዋዕት እንደሆነ ስለሚያውቅ እነዚህን ጥቂት ደቂቃዎች ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ አስፋፊው ለእሱ ያለውን ፍቅርና የይሖዋ ምሥክር ሆኖ የማገልገል የላቀ መብቱን እንደሚያደንቅ የሚገልጽበት መንገድ እንደሆነ ይሰማዋል። ብዙ ወጪ የሚያስወጡ መሥዋዕቶችን ለማቅረብ ሁኔታቸው ያልፈቀደላቸው እስራኤላውያን ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የአቅም ገደብ ያለባቸው የይሖዋ ውድ አገልጋዮች አገልግሎታቸውን ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ። በግለሰብ ደረጃ የምንመልሰው ሪፖርት ተደምሮ ዓለም አቀፉ ሪፖርት ላይ ይካተታል፤ ይህም የይሖዋ ድርጅት የስብከት እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ እቅድ እንዲያወጣ ይረዳዋል። ታዲያ የስብከቱን እንቅስቃሴያችንን ሪፖርት ማድረግ ያን ያህል ከባድ ነው?

የጥናት ልማዳችንና የምስጋና መሥዋዕታችን

14. የጥናት ልማዳችንን መመርመር ያለብን ለምን እንደሆነ አብራራ።

14 በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኘው መንፈሳዊ ሀብት መካከል የተወሰኑትን ከመረመርን በኋላ ‘ይህ መጽሐፍ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ እንዲካተት የተደረገው ለምን እንደሆነ አሁን ይበልጥ ገባኝ’ ብለህ ታስብ ይሆናል። (2 ጢሞ. 3:16) ይሖዋ ቅዱስ እንድንሆን ስለሚጠብቅብን ብቻ ሳይሆን እሱን ለማስደሰት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባን ስለተገነዘብክ ጭምር ቅዱስ ለመሆን ከበፊቱ የበለጠ ጥረት ለማድረግ ትወስን ይሆናል። ምናልባትም በእነዚህ ሁለት የጥናት ርዕሶች ላይ ከዘሌዋውያን መጽሐፍ ያገኘኸው ትምህርት ቅዱሳን መጻሕፍትን በአጠቃላይ በጥልቀት እንድትመረምር አነሳስቶህ ይሆናል። (ምሳሌ 2:1-5ን አንብብ።) እንግዲያው የጥናት ልማድህን በጸሎት አስብበት። የምታቀርበው የምስጋና መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ታዲያ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ወይም በትርፍ ጊዜህ የምታከናውናቸው ነገሮች ትኩረትህን እየከፋፈሉትና ለመንፈሳዊ እድገትህ እንቅፋት እየሆኑብህ ነው? ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ በጠቀሳቸው አንዳንድ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰልህ በጣም ይጠቅምሃል።

በሕይወትህ ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ለቤተሰብ አምልኮ ቅድሚያ ትሰጣለህ? (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

15, 16. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ቀጥተኛ ምክር የሰጣቸው ለምንድን ነው?

15 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ግልጽ ምክር ሰጥቷል። (ዕብራውያን 5:7, 11-14ን አንብብ።) ሐዋርያው ዙሪያ ጥምጥም አልሄደም! ከዚህ ይልቅ ‘ጆሯቸው እንደደነዘዘ’ በቀጥታ ነግሯቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ያለ ኃይለኛና ቀጥተኛ አነጋገር የተጠቀመው ለምንድን  ነው? በመንፈሳዊ ወተት ብቻ ለመኖር እየሞከሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች የይሖዋ ዓይነት ፍቅርና አሳቢነት ስለነበረው ነው። የክርስትናን መሠረተ ትምህርት መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁንና እድገት አድርጎ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ “ጠንካራ ምግብ” መመገብ የግድ አስፈላጊ ነው።

16 ዕብራውያን ክርስቲያኖች እድገት አድርገው ሌሎችን ማስተማር የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረስ ሲኖርባቸው እነሱ ራሳቸው የሚያስተምራቸው ሰው ያስፈልጋቸው ነበር። ለምን? “ጠንካራ ምግብ” ስለማይመገቡ ነው። አንተም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ለጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ትክክለኛ አመለካከት አለኝ? እንዲህ ያለውን ምግብ በጉጉት እየተመገብኩ ነው? ወይስ ከመጸለይና ጥልቅ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከማድረግ ወደኋላ እላለሁ? ከሆነ ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የጥናት ልማዴ ይሆን?’ ለሰዎች በመስበክ ብቻ ሳንወሰን እነሱን ማስተማርና ደቀ መዛሙርት ማድረግ ይኖርብናል።—ማቴ. 28:19, 20

17, 18. (ሀ) አዘውትረን ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስለ መገኘት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

17 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለብዙዎቻችን ቀላል ላይሆን ይችላል። እርግጥ ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ቃሉን እንዲያጠኑ ለማድረግ አይሞክርም። ይሁንና ለአምላክ ራሳችንን የወሰንነው ከበርካታ ዓመታት በፊትም ይሁን በቅርብ ጊዜ፣ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችንን መቀጠል ይኖርብናል። ቅዱስ ሆነን መኖር ከፈለግን እንዲህ ማድረጋችን የግድ ነው።

18 ቅዱስ ለመሆን የአምላክን ቃል በጥልቀት መመርመርና እሱ የሚጠብቅብንን መፈጸም ይኖርብናል። “ያልተፈቀደውን እሳት” በማቅረባቸው የተቀሰፉትን ናዳብንና አብዩድን እንመልከት፤ እነዚህ የአሮን ልጆች ይህን ያደረጉት በአልኮል መጠጥ ተገፋፍተው ሳይሆን አይቀርም። (ዘሌ. 10:1, 2) ናዳብና አብዩድ ከሞቱ በኋላ አምላክ ለአሮን ምን እንዳለው አስተውለሃል? (ዘሌዋውያን 10:8-11ን አንብብ።) ይህ ታሪክ ወደ ክርስቲያን ስብሰባዎች ከመሄዳችን በፊት ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ መቅመስ እንደሌለብን የሚያሳይ ነው? እስቲ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች ልብ በል፦ እኛ በሙሴ ሕግ ሥር አይደለንም። (ሮም 10:4) በአንዳንድ አገሮች የእምነት ባልንጀሮቻችን ወደ ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ምግብ ሲመገቡ የአልኮል መጠጦችን በልኩ መውሰዳቸው የተለመደ ነው። በፋሲካ በዓል ላይ ወይን ጠጅ የያዙ አራት ጽዋዎች ይቀርቡ ነበር። ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ሐዋርያቱ ደሙን የሚወክለውን ወይን ጠጅ እንዲጠጡ አድርጓል። (ማቴ. 26:27) መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። (1 ቆሮ. 6:10፤ 1 ጢሞ. 3:8) በርካታ ክርስቲያኖች በማንኛውም ዓይነት ቅዱስ አገልግሎት ከመካፈላቸው በፊት የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ሕሊናቸው ስለማይፈቅድላቸው በዚህ ጊዜ ጨርሶ መጠጥ አይቀምሱም። ይሁንና ሁኔታዎች ከአገር አገር ይለያያሉ፤ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ክርስቲያኖች ‘የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን በመለየት’ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ቅዱስ ሆነው መመላለሳቸው ነው።

19. (ሀ) የቤተሰብ አምልኮና የግል ጥናት ስናደርግ ምን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል? (ለ) ቅድስናህን በመጠበቅ ረገድ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

19 የአምላክን ቃል በጥልቀት ካጠናን በርካታ መንፈሳዊ ዕንቁዎችን ማግኘት እንችላለን። በቤተሰብ አምልኳችሁና በግል ጥናታችሁ ወቅት በእጃችሁ ያሉ የተለያዩ የምርምር መሣሪያዎችን ተጠቀሙ። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ያላችሁን እውቀት አሳድጉ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ ቅረቡ። (ያዕ. 4:8) መዝሙራዊው እንዳለው ሁሉ እናንተም “ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት” በማለት ጸልዩ። (መዝ. 119:18) የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠበቅ ረገድ ፈጽሞ አቋማችሁን አታላሉ። “ቅዱስ አምላክ” የሆነውን የይሖዋን ላቅ ያሉ ሕግጋት በፈቃደኝነት ታዘዙ፤ “የአምላክን ምሥራች በማወጁ . . . ቅዱስ ሥራ” በቅንዓት ተካፈሉ። (1 ጴጥ. 1:15፤ ሮም 15:16) በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት ቅድስናችሁን ጠብቃችሁ ተመላለሱ። እንግዲያው ሁላችንም በምግባራችን ቅዱስ በመሆን የቅዱሱን አምላክ የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደግፍ።